ግርማ መንግሥቴ
የሰው ልጅ ሰው ሆኖ ከተፈጠረባት ከዛች ጊዜ ጀምሮ ከየት ጀምሮ የት ደረሰ፤ ምን ምን ተግባራትን አከናውኖ በየትኛው ውጤታማ፤ በየትኛውስ ክስረት ደረሰበት፤ ምን ምን አይነት ዘመናትንስ ተሻገረ፣ ተሸጋገረስ? ብሎ ለጠየቀ መልሱ ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ቢያንስ ቢያንስ የሰው ልጅ ፍሬ ለቅሞ ይመገብ ከነበረበት ከዚያ ሩቅ ጊዜ ጀምሮ ያለፈባቸውን ዘመናትና የፈፀማቸውን ተግባራት አይደለም ባንድ ገፅ ሰማይን የሚያክል ወረቀት ቢፈቀድ እንኳን ሂደቱን ለመግለፅ የሚቻል አይመስልም። የሆነ ሆኖ ግን እዚህ ዛሬ ላይ ደርሶ የዘመናዊቷ አለማችን ባለቤት ሆኗልና ስለዚሁ ዘመናዊነትና እሱ ያመጣቸውን ትሩፋቶች አስመልክተን አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተን እንነጋገር።
የአሁኑ ዘመን በተለይም ከ17 እና 18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ ደረሰባቸው ከሚባሉት ደረጃዎች አንዱና ምናልባትም ዋናው ዘመናዊ (እና፣ ዲሞክራሲያዊ) መንግስት መመስረቱና በእሱም መተዳደሩ ሲሆን፤ በተለይም ይህንኑ ሥነ-መንግሥትዊ አወቃቀርና መዋቅር ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የዘየዳቸው ዘመናዊ አሰራሮች ናቸው።
ከእነዚህ አሰራሮችና ብልሀቶች መካከል ቀዳሚው የመንግሥት ብልፅግና እንዳይከሰት፣ አምባገነን ስርአት እንዳይፈጠር፣ ሙስና እንዳይንሰራፋ፣ የጨቋኝና ተጨቋኝ መደብ እንዳይፈጠር ወዘተ በማሰብ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እንዲሉ የመንግስት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር ነው።
በተለይም የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ እየዳበረ መምጣትና እንደ ሥርዓትና የሕዝብ አስተዳደርነት መወሰድን ተከትሎ በመጣው የውክልና ዲሞክራሲን ተከትሎ የመጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊነት መነሻው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተወካይ እንዲኖረውና የሀሳብ ፍጭትን በመፍጠር የተሻለውን ለመውሰድ እንዲቻል በማሰብ ነበር።
የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር አቢይ ዓላማው እንዲህ አሁን እንደሚስተዋለው ቅጥና ቅርፅ ያጣ፤ ስግብግብነት አናቱ ላይ የነገሰ፤ ግለኝነትና ጥቅመኝነት እግር ከወርች ያሰረው ወዘተ ሆኖ መገኘት ሳይሆን የተሻለና በሕዝብ ለሕዝብ የሆነ መንግሥት ይመሰረትና አገርና ሕዝብ ይበለፅግ ዘንድ የራሱን ሚና መጫወት፤ የሕግ የበላይነት ይሰፍን ዘንድ መንግሥትን “የመቆጣጠር” ሚናን መጫወት ነበር። ዛሬ ግን ፓርቲ መመስረት አንዱ ለራስ የስራ እድል መፍጠርና እስኪበቃ ድረስ ገንዘብ ማጋበስ መቻያ ቀላል መንገድ ሆኖ ይገኛል። ይህም እዚህ ወይም እዛ የሚታይ ተብሎ በቦታና ጊዜ የሚወሰን ሳይሆን ሁሉም ጋር በሁሉም ቦታና ግዜ የሚታይ እኩይ ተግባር ከሆነ ቆይቷል። ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀላሉ ብቅ ብቅ እንዲሉ እድል የሰጠውን ያህል በቀላሉ እንዲከስሙም ምቹ ሁኔታን አመቿችቷል።
ጆን ጄ. ኮልማን የተባሉ የፖለቲካ ተንታኝ “The Rise and Fall of American Political Parties: American Parties in the Fiscal State” ጽሑፋቸው ላይ እንዳብራሩት በአሜሪካ የፖለቲካ ህይወትና እድገት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦታ መለዋወጥ ቁልፉን ሚና ሲጫወት ኖሯል። በ1980ዎቹና 90ዎቹ ምሁራን በፖለቲካ እድገትና ሂደት ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አይነት ገንቢ ሚና እንዳላቸው ለይተው ለማወቅ ምሁራን በከፍተኛ ጥናትና ምርምር ስራ ላይ የተጠመዱበት ጊዜ ነበር። በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ “የእነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ አቋም ምን ይመስላል?” የሚለው ሰፊ ቦታን ይዞ እንደነበር ኮልማን ይናገራሉ። ጥናትና ምርምሮቹም እነዚህ ፓርቲዎች እየዘቀጡ፣ እየተናዱና እየከሰሙ መምጣታቸውን ያመለከቱ ሲሆን የመክሰማቸውንም ምክንያቶች ጠንካራና ሕዝባዊ ተቋማት እየተፍረከረኩ መምጣት፣ የፓርቲ ዲሲፕሊን መጣስ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ መበላሸት፣ ተራማጅ አስተሳሰብ የያዘ የፖለቲካ ፓርቲና አመራር መፈጠርና ወደ ላይኛው የመንግሥት እርከን መምጣት፣ የሕዝቡ ለውጥ መፈለግ ወዘተ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚሁ ችግሮች ስር እየሰደዱ ሄደውም ብዙዎቹ ነባር የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሳይቀር እንደገፈተሯቸውና ጠልፈው እንደጣሏቸው ያስረዳሉ። የከሰሙትም ሆኑ ያልከሰሙት እነዚህን ችግሮቻቸውን ከፈቱ ከነህልውናቸው ሊቆዩ እንደሚችሉም አስምረውበታል።
በአሜሪካ ሕገ-መንግስት ውስጥ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚናገር አንድም ቃል የለም። ይሁን እንጂ የአሜሪካ መስራች አባቶች መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣና ተጠሪነቱም ለሕዝብ መሆኑን አምኖ ይሰራ ዘንድ፣ አማራጭ ሀሳቦችን እንዲያመነጩና ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጉ ዘንድ፤ እንዲሁም ለመንግስት እንደ አንድ ልጓም ሆነው ያገለግላሉ የሚል እምነት ስለነበራቸው እድሉን በማመቻቸት ለዚህ አብቅተዋቸዋል የሚሉን ደግሞ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ጆሴፍ ፖስቴል ሲሆኑ በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ የፓርቲዎች መውደቅና መነሳት ሲፈራረቁ የኖሩ ክስተቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።
ታላላቅና ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለፓርቲያቸው የሥነምግባርም ሆነ አጠቃላይ ሕግ ይገዛሉ እንጂ እራሳቸውን (አባላቱን ማለታቸው ነው) ከሕጉ በላይ አያደርጉም። የፓርቲውንም ሀብት የራሳቸው በማድረግ አይመዘብሩም የሚሉት ጆሴፍ ፖስቴል ስልጡን የፖለቲካ ፓርቲ በሕግ የበላይነት ያምናል፣ ብቃት ያለው አመራር ይሰጣል፣ በራሱ የመወሰን አቅም አለው፣ ጠንካራ አገር እንዲመሰረት ይፈልጋል፤ ለዚህም አጥብቆ ይሰራል ሲሉም ያስረዳሉ። በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥትም በተለያዩና አገርን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ያግዛል፤ አማራጭ ሀሳቦችን በማፍለቅ የፖሊሲ አማራጮችን ያቀርባል በማለት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ተግባርና ኃላፊነት ይገልፃሉ። ይህን የማያደርጉና በመርህ የማይመሩ ከሆነ መጨረሻቸው እንጦሮጦስ መውረድ፤ ወይም በትሁት ቋንቋ መክሰም ነው።
“The Federalist Era” (1789-1801) ተብሎ የሚታወቀው ዘመን (የአሜሪካ ሕገመንግሥት በ1787 ተፅፎ፣ በ1788 ፀድቆ፣ በ1789 ነው ስራ ላይ የዋለው) “ፌዴራሊስት ፓርቲ” የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ ሲንቀሳቀስበት የነበረበት ዘመን ሲሆን በወቅቱም በከፍተኛ ደረጃ ተፅእኖ ፈጣሪ የነበረ ፓርቲ መሆኑ ተመዝግቦ ይገኛል። “Whig Party”ም ከስሟል።
በ1949 በአውስትራሊያ በሶስት አንጋፋ ፓርቲዎች ላይ ሕዝቡ የወሰደው (በድምፅ የመቅጣት) እርምጃ በዓለም የፖለቲካ ፓርቲዎች አወዳደቅን በተመለከተ በምሳሌነት በስፋት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው። የደቡብ አፍሪካው ሲኤንኤን የገባበትን ቅርቃርና ሌሎችንም በዚሁ መንገድ ማሰብ ያስፈልጋል። ወደ አገራችን እንምጣ።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ በአገራችን እድሜው ረጅም አይደለም። ቅርብ ነው። ይሁን እንጂ ታሪኩን ስንፈትሸው ከጅምሩ ጀምሮ ሳያምርበት እዚህ የደረሰ ነው።
ይህ በአገራችን የሚታየውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግብታዊ አነሳስና ያልተጠበቀ አወዳደቅ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ (አማፂ አልተባለም) የሚለው እራሱ ብቅ ካለበት 1950ና 60ዎቹ ጀምሮ በአገሪቱ የሚታየው የፓርቲዎች ትርምስ ነበር። ደርግ ስልጣን ሲይዝ ዙሪያውንም ይሁኑ አብረውት ባይታወቅም አምስት ያህል ዋና ዋና ፓርቲዎች (ሰደድ፣ ወዝሊግ፣ ኢጫት፣ ኢህአፓ እና መኢሶን) ነበሩ። ማንም ማንንም ሳያስተርፍ ተጨራረሱ።
ደርግ በኢህአዴግ መንበሩን ከተነጠቀ ወዲህም እስከ 111 የደረሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀፍቅፈው ነበር። አፍታም ሳይቆዩ በጣት የሚቆጠሩት ሲቀሩ ሌሎቹ የሉም። ኢህአዴግ በራሱ ውስጥ ለውጥ ከመጣበትና ጠ/ሚ አቢይ መንበረ ስልጣኑን ከወረሱ ወዲህ በፈጠሩት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተነሳሽነት እስከ 140 የሚደርሱ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ የሚለው አይመጥናቸውም የሚሉ አሉ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመቀፍቀፍም በላይ ተቀፈቀፉ። የሰፋው የዲሞክራሲ ምህዳር ኢትዮጵያ ምድር ቁና ትሆን ዘንድ እድሉን ሰጠ፤ መግባባት ጠፋ፤ የሕግ የበላይነት ይሉ ነገር ከነሽታውም አልታይ፣ አልሰማ፣ አልዳሰስ አለና “ሁለት መንግሥት ነው ያለው” እስኪባል ድረስ ተዘለቀና አገርና ሕዝብን ግራ አጋባ። በዚሁ ምክንያትም የንፁሀን ደም መፍሰስ የተለመደ የእለት ተእለት ተግባር ሆነ። (ዝርዝሩ ብዙ ነው።)
ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎሽ ምክንያቶቹ እንደየተቀናቃኞቹ ሊለያዩና እጅግም ሊበዙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የደከሙት ግን የሚሉት አላቸው።
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እይታ ፖለቲካ የገባውም ሆነ ፖለቲከኛ ገና አልተፈጠረም፤ አሁን ያለው በስልጣን ጥም የናወዘና ያንን ጥሙን ለማርካት ሲል የሚሯሯጥ አካል ነው ያለው። ሁሉም የራሱን ጥቅም ነው እየፈለገ ያለው።
ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በበኩላቸው እዚህ አገር ያለው ችግር መንግስት በመጣ ቁጥር የሚወስደው ስር ነቀል እርምጃ ነው። ይህችን አገር ለዚህ ሁሉ ፍዳ ያበቃት ይህ ስር-ነቀላዊነት ርእዮተ አለም ነው።
እንደ ግዮን ፈንታሁን (የ”ፍትሕ” መጽሔት አምደኛ) አተያይ ደግሞ እኛ አገር ስር የሰደደውና እያተራመሰን፣ እያጨራረሰን፣ እያባላንና ለዚህ ሁሉ ውድቀት እየዳረገን ያለው ለሕግ-ተቃርኖ (ዲያሌክቲክስ) አለመገዛታችን፤ በእሱም አለማመናችንና መቀበል አለመቻላችን ነው። እንደ ግዮን ከሆነ ሕገ-ተቃርኖ ማለትም የተገዳዳሪ ሀሳብ መኖር ለእድገት ቁልፉ ጉዳይ ሲሆን ለማንኛውም ማህበራዊ ለውጥም እርሾ ነው። በመሆኑም ይህንን አምኖ መቀበልና ተቃራኒ ሀሳብን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ እንደዚሁ እየተጨራረሱ መኖር ነው የሚሆነው። (ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀብታሙ አለባቸውን “ታላቁ ተቃርኖ”ንም መመልከት ይቻላል።)
እነዚህና ሌሎች ጥናቶችን መሰረት ያደረጉ አስተያየቶች የሚነግሩን አቢይ ጉዳይ ቢኖር በእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበት ደረጃ ገና እንጭጭ የሚባል መሆኑን ነው። ብስለት የለም፣ አስተዋይነት የለም፤ የጠራ ርእዮት የለም፣ አማራጭ ፖሊሲ የለም፣ ግልፅ የሆነ መዋቅር እንኳን ስለመኖሩ የሚታወቅ አንድም ነገር የለም። ይህ ብቻም አይደለም፤ በአብዛኞቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ አንዳችም አገራዊ አጀንዳም ሆነ ሕዝባዊ አተያይ የለም፤ ያለው ዘርን መሰረት ያደረገ አተያይ፣ ጎጥን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴና ንቅናቄ (ለዛውም ከተባለ)ና የእውር ድንብር አካሄድ ነው። ሽፋኑ ዲሞክራሲ ሲገላለጥ ግን የዘር አኩፋዳ ነው የሚገኘው።
ፕሮፌሰር መስፍን በመጨረሻው (ከመሞታቸው ወራት በፊት ለንባብ የበቃው) “ትናንትም እንደዛሬ?” መጽሐፋቸው ላይ በዝርዝር እንዳስቀመጡት በአንድ ብሔረሰብ ስም ከ18 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተው ለዛ ብሄረሰብ “እየታገሉ” ነው። ይህ ነው እንግዲህ እርስ በእርስ እንኳን መግባባት በማይቻልበት ደረጃ ነው የኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታና ይዞታ። ልክ ለመመስረታቸው በቂ ምክንያት እንደሌላቸው ሁሉ፤ ከመንጫጫት ያለፈ፣ የሕዝብን ልብ ሊማርክና ወደ እነሱ ሊያመጣ የሚችል፣ ለመፍረስ መክሰማቸውም በቂ ያለመፍረስና ያለመክሰም መከራከሪያ እንኳን ማቅረብ የሚችሉበት አቅም፣ እውቀትም ሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና የላቸውም። ያሉበትም ሆነ እየኖሩት ያሉት የፖለቲካ ህይወት በፈረንጂኛው “Into the Abyss” ሁሌም ወደ እንጦሮጦስ ጉዞ ማድረግ ነው፤ ወደ መክሰም።
“ከጥንት ጀምሮ . . .” እንደተባለው ስናየው የኖርነው ይህንኑና ይህንኑ ብቻ ነው። (እዚህ ላይ ስለፖለቲካ ምህዳር ምናምን ማንሳት አስፈላጊ አይደለም። እየተነጋገርን ያለነው ስለ ሁሉም ነውና።) ይህ አይነቱ መሪር ችግር ቢገጥማቸው ይመስላል ፒይሮ ኢግናዚ “The Crisis of Parties and the Rise of New Political Parties”ን ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውና የፓርቲዎችን የለውጥ ጠይነትና የአዳዲስ አስተሳሰቦችን አይቀሬነት ለማሳየት የደከሙት። “እያራገፉ መሄድ” ይሏል እንዲህ ነው። ምክንያቱም “እኔ ከሌለሁ አገር ትፈርሳለች” የሚሉ ወገኖች፤ “እናንተ ባትኖሩም ሌሎች አዳዲሶች ይመጣሉ፤ አገርም አትፈርስም” የምንለውን የሕዝብ አስተያየት የሚደግፍ ስራ ነው ይህ ፒይሮ ኢግናዚ ስራ።
በአሜሪካ ሁለቱ ማለትም ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና ሪፐብሊካን ፓርቲ በበላይነት አገሪቱን እየተፈራረቁ ይምሩ እንጂ በአገሪቱ እጩዎቻቸውን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ብቻ የሚያሳትፉ ስድስት ያህል ፓርቲዎች (ሪፎርም ፓርቲ፣ ላይብሬሽን ፓርቲ፣ ሶሻሊስት ፓርቲ፣ ናቹራል ሎው ፓርቲ፣ ኮንስቲቲውሽን ፓርቲ እና ግሪን ፓርቲ) አሉ። ይኑሩ እንጂ በአገርና ሕዝብ ጉዳይ ላይ ቀልድ የለምና ኮሽ ሲሉ አይሰማም። እዚህ ግን በስመ ዲሞክራሲ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጫረስ እቅድ ወጥቶና በጀት ተይዞ ከዚህ መለስ ባልተባለ መልኩ ይሰራል። ይህ ደግሞ ፓርቲዎቹን ወደ መውደቅና መክሰም እንጂ ወደ ሌላ ሊወስዳቸው ከቶም አችልም።
ከላይ እንዳየናቸውና ሌሎች በርካታ ጥናቶች እንደሚያስገነዝቡት የእንደዚህ አይነት ፖለቲካ ፓርቲዎች መጨረሻቸው አይቀሬው ውደቀት፤ ከዛም ክስመት ነው። በተለይ ለአንደ አገር ጥንካሬና ለጠንካራ አገረ መንግሥት ምስረታ እማይተጋ ከሆነ፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ቀልቡን ካሳረፈ የሕዝብ ልብ ውስጥ መግባት አይቻለውምና ያ ፓርቲ ያለ ጥርጥር ከሳሚ ነው።
ሌላው ለፓርቲዎች ውድቀትና ክስመት ተአማኒነትን (ትረስት) ማጣት ነው። አንድ ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ፤ ወይም በፓርቲነት ብቅ ሲል ለሕዝብ ቃል የሚገባው ነገር ይኖራል። ያንንም አምኖ ሕዝብ አመኔታ ይጥልበታል። ያንን የተጣለበትን እምነት ካጎደለ ያ ፓርቲ መጨረሻው በሕዝብ ተገፍትሮ መውደቅ፤ ክስመት እንጂ ሌላ አይደለም።
የምርምር ስራዎች እንደሚያስገነዝቡት የፓርቲዎች ውድቀት የአመራር ውድቀት ነው፤ የፓርቲዎች ውድቀት የአባላቱ ውድቀት ነው፤ የፓርቲዎች ውድቀት የጠራ መስመር አለመኖርና ብዥታ መፈጠር ነው፤ የርእዮት ማጣትና የአማራጭ ሀሳብ ማፍለቅ ያለመቻል ድርቀት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድቀት ለውጥን ካለመቀበልና ፍቃደኛ ካለመሆን ብቻ ሳይሆን ባሉበትም ተቸክሎ መቅረት ነው።
የፓርቲዎች ውድቀትና እሱን ተከትሎ ለሚመጣው ክስመት አንዱ መንስኤ ለውጥን ከመጥላትና ከማደናቀፍ ይጀምራል። ለውጥ ጠልነት ደግሞ በየትኛውም አተያይ ከጊዜ ጋር መሄድ ያለመቻል ውጤት ነውና መጨረሻው ክስመት ነው።
ሙስና ሥርዓታዊ በሆነበት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰራር ውስጥ ይቆይ እንደሆን እንጂ ክስመት አይቀሬ ነው። ይህም ከእኛው አገር ፓርቲዎች ጀምሮ እየታየ ነውና የሚገርም አይደለም። የቼክ ሪፐብሊክን፣ ስሎቫኪያን እና የሀንጋሪን የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የተካሄዱ ምርጫዎችን፤ እንዲሁም የፓርቲዎቹን እጣ ፈንታ ከመረመረው ከ”Where do parties go when they die? The fate of failed parties in the Czech Republic, Slovakia, and Hungary 1992–2013″ ማጠቃለያ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።
በእንግሊዙ “UKEssays” ከተዘጋጀውና በ2352 ቃላት ተመጥኖ ከቀረበው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አመጣጥ፣ እድገትና ምክንያት ውድቀትና ክስመትን ከተመለከተው ጥናት መገንዘብ እንደተቻለው ከሆነ የአሁኖቹን ከድሮዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስናወዳድር ወደድንም ጠላን የአሁኖቹ ለአገርና ማህበረሰብ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦዋቸው አንፃር ሲመዘኑ ወድቀዋል፤ ሥራቸው ሁሉ ወደ ንግዱ ዓለም ያደላ፤ የግል ጥቅም ላይ ያተኮረና አገርና ሕዝብን የዘነጋ ነው። በዚህ ከቀጠሉ ክስመት እጣ ፈንታቸው ይሆናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013