ተገኝ ብሩ
አደባባዩ በባንዲራ ደምቆ፣ መንገዱ ባህላዊ አልባሳት በተጎናፀፉ ምዕመናን ተውቦ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘማሪያን ውብ ዜማና ሽብሻቦ ታጅቦ በተለየ ድባብ የሚከበር ነው ጥምቀት። እድለኛ ነህ! በዚህች ውብ አገር ተገኝተሀል። ተፈጥሮ በራሱ በኳላት፤ አመቱ ሙሉ ፀሐይ በማይጠልቅባት አገር መገኘትህን ውደድ።
በተዋበ ባህል ውስጥ ማደግህ፤ በልዩነት ውስጥ በተፈጠረ ህብረ ቀለም ባጌጠ በመተሳሰብ በፀና አንድነት ውስጥ መኖርህን አድንቅ። ሕዝቧ በዕምነት ፀንቶ የሚኖርባት በበጎነት ተዋዶ በሚያድርባት በፍቅር አንድ ላይ በሚኖሩባት ምድር ላይ መወለድህ የእውነትም ባለዕድል ነህ።
በዚህ ውብ በዓል ለፍቅር ይፀነሳል፤ መውደድ ይገመዳል። ለፍቅር ማሰሮ፤ ለመውደድ ቋጠሮ ይሆን ዘንድ ሎሚ ይወረወራል። እኔም ለክብረ በዓሉ ይጠቅማል፤ ለወቅቱ ይሆናል የምለውን መልዕክት መወርወር ፈለኩ። ብዙ እንድንቆይ የሚረዳን ደጋግመን ጥምቀት ላይ መድረስ እንድንችል ይሄንን እናድርግ። የወቅቱን ፈተና ለማለፍ፤ የጊዜውን ጋሬጣ ለመሻገር ጥምቀትን በድምቀት ማክበር ጥንቃቄንም ስንቅ ማድረግ ግድ ይላል።
ዛሬ ጥምቀት ነውና በባህላዊ ልብስ ያጌጠ ለእምነቱ ያደረ ደግ ሕዝብ በየአደባባዩ ወጥቶ በአንድነት ለአምላኩ ሲዘምር ታያለህ። ወገንህ እርስ በርስ ፍቅርን ሲጋራ አንዱ ለአንዱ ሲቆም ትመለከታለህ።ወገንህ በሕብረት ሲጓዝ ወዳጆችህ ተሰባስበው ሲጨፍሩ ይገጥምሀል። ይህን ግን አስታውሳቸው። ወቅቱን እንዳይረሱ ንገራቸው።
ይህ ድምቀት እንዲቀጥል ተጠንቀቁ ሁሌም እንድናከብረው በሀገራችን እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል አስቡ በላቸው።
ጥምቀት ደምቆ መከበር ይገባዋል። አንተም ከበዓሉ ድምቀት ፈርጦች አንዱ ነህና ባህልህን የሚገልፅ አንተነትህን የሚያጎላ ባህላዊ ልብስህን ተጎናፅፈህ ውጣ፤ከወዳጆችህ ጋር ተገናኝ ። ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚፈቅደውን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እየፈፀምክ ዋል።
ሀገርህ የተቸረችውን አምላካዊ ፀጋዋን እያደነቅህ፤ የተፈቀደልህን እየከወንክ ከዘመኑ ክፉ ራስህን ጠብቅ። ከወቅቱ መቅሰፍት ራስህን አለፍ ሲልም ወገንህን ተከላከል። ሀይማኖቱ የሚያዘውን እየፈፀምክ አንተን ወደ ቀጣይ ዘመን እንዳትሻገር ሳንካ ከሚሆንብህ ደዌ ራሰህን ጠብቅ ። ነገ ከሌለህ ይሄ ድምቀት አይኖርም፤ ያላንተ አገርህ አትቀጥልምና ጥንቁቅ ሁን።
በዓሉን ስናከብር በምንወስደው የጥንቃቄ እርምጃ ብዙ ወገን ይተርፋል። መዘናጋታችን ደግሞ የሚያሳጣን ብዙዎችን ነው።ዛሬ አለም ስጋት ውስጥ ወድቃ የሰው ልጆች ግራ ተጋብተው የተጋረጠባቸው ወረርሽኝ ፋታ ነስቷቸው ይገኛል። እኛ እድል ሆኖ የተፈራውን ያህል ባይደቁሰንም ቀድሞ ያሰብነው ያህል በስፋት ባያናጋንም ያደረሰብን ጉዳት ግን ቀላል የሚባል አይደለም። በወረርሽኙ የሞቱ ዜጎቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም ፤በበሽታው ምክንያት በእግሩ ያልቆመው ኢኮኖሚያችን መንገዳገዱን ተመልክተናል። ኪሳችንን አሳስቶታል።
ወጣቶች ይህን ዘንግተዋል ፤በየቦታው የሚታየው መዘናጋት ነገ የሚስከፍለውን ታላቅ ዋጋ ዛሬ ቆም ተብሎ ካልታሰበ ያስፈራል። ወረርሽኙ ብሶበት ባህሪውን ቀይሮ ዓለም ላይ እንደገና እየተቀሰቀሰ ጉዳት እያዳረሰ ባለበት በዚህ ወቅት እኛ ይበልጥ እየተዳፈርነው ይበልጥ እየረሳነው ስለመሆኑ ተግባርና እንቅስቃሴያችን ማሳያ ነው።
መነሻ እንጂ መድረሻው በማይታወቅ ወረርሽኝ እስከ አሁን በመላው ዓለም በበሽታው 95 ሚሊዮን ሰዎች ተይዘዋል።ከሁለት ሚሊዮን ሰላሳ ሺ በላይ ሰዎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በሀገራችንም በበሽታው እስከ አሁን ሁለት ሺ ሰላሳ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።በአጠቃላይ 131 ሺ 195 ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፣በአሁኑ ወቅትም 13 ሺ016 ሰዎች ቫይረሱ አለባቸው። በአሁኑ ወቅት የጽኑ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።ይህም የመከላከልን አስፈላጊነት ያስገነዝባል።መንግስት በሽታውን መከላከል የሚያስችል አዲስ መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ፅኑ የሆነ እምነት በውስጣችን አለ። ባምላክ ማመናችን መልካም በሱ መመካታችን የሚደነቅ ነው። ነገር ግን እሱ በሰጠን አዕምሮ እሱ በሰጠን ጥበብ ራሳችንን መጠበቅ ደግሞ ግዴታችን ነው። እምነታችን በልባችን መጠንቀቁ ደግሞ በአካላችን እንተግብር። ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ስንፈፅም አምላካዊ ትዕዛዛትን ስነከውን ራሳችንን እና ወገናችንን ከበሽታው በመከላከል ወደፊት የሚመጡ የብዙ ዓመታትና ጊዜያት ለመድረስ እንድንችል በሚያደርግ መልኩ መሆን ይገባዋል።
ዛሬ ተውቦ የታየው ነገ እናዳይጎድል፤ ዛሬ ደምቆ የዋለው ክብረ በዓል ከሳምንታት በሁዋላ እንዳይደበዝዝ በጤና ነገር ሁላችንም መገኘት ይገባናል። እንደዛሬው ብዙ ሆነን እናት አባቶች ሲመርቁ እህት ወንድሞች ሰርተው አገራቸውን ሲለውጡ ማየት ይገባናል። ለዚያ ደግሞ ዛሬ መጠንቀቅ ዛሬ ልብ መግዛት ግድ ይላል። ሁላችን ጋር የሌለው መሰረታዊ ግንዛቤ ማድረስ የሁላችን ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፤ የዘነጋን ማስታወስ የረሳን ማሳሰብ እንደ ዜጋ የሁላችንም ተግባር መሆን ይገባዋል።
ጥምቀት ለኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ተውበው የሚታዩበት መስክ፤ በመቻቻል የሚዋቡበት መድረክም ነው። ሁሉም በባህሉ አልባሳት ተውቦ ማህበረሰቡ ያወረሰውን ፍቅር ተካፍሎ በመተሳሰብ የሚውልበት ባህል የሚወራረስበት እንደመሆኑ ጥምቀት ላይ ሁሉም ያለውን ይዞ አደባባይ ይቀርባል። ይህን አጋጣሚ መጠቀም ይገባል። አንደኛችን የሌሎችን ባህል አይተን ማድነቁ በባህላዊ ሁነቱ ተሳትፎ በጭፈራና በልምዱ ተደስቶ ቀኑን ማሳለፉ በዚሁ ክብረ በዓል የምንጎናፀፈው ልዩ በረከት ነው።
በዓሉ የተዋበ እንዲሆን የሁላችን ጥረት ይጠይቃል። ዛሬ የምንውለው የደመቀ በዓል ነገን ሳይነጥቀን ሰላማዊ በሆነና ጥንቃቄ በተሞላበት መልክ ማሳለፍ ይገባል። በመሆኑም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር የወጡ መመሪያዎችን ሁሉ መተግበር ይጠበቅብናል። ርቀተን መጠበቅ፣የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በአግባቡ መጠቀም ፣እጅን በውሃ ካልተቻለም በሳኒታይዘርና በመሳሰሉት ማጽዳት የዚህ በዓል ወቅት ኃላፊነታችን ይሁን።
ራሳችን መጠበቃችን እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ከማሳሰብ መቆጠብ የለብንም።ኮሮና ማህበራዊ ችግር እንደመሆኑ በአንድ ሰው መጠንቀቅ ብቻ ልንከላከለው አንችልም።የሁሉንም ወገን ጥንቃቄ ይፈልጋል።ይህንንም እናድርግ።አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013