ከገብረክርስቶስ አፍታ
ከወርሃ-መጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ ይበልጡንም ከትህነግ ወደ መቃብር መውረድ ማግስት ያለው ይህ ወቅት የአገራችንን መጻኢ እድል የሚወስን ምዕራፍ ሆኗል።
የሺህ ዘመናት የንግስና ሥርወ-መንግስትን የገረሰሰው የ1960ዎቹ አብዮት የያኔው የኢትዮጵያ ዕድል ነበር። ግና ያለፍሬ ጨነገፈ። የ1983ቱም አጋጣሚ ከነችግሮቹ የአገራችንን የጉዞ ትልም ያበሰረ ቢሆንም ቅሉ ከመክሸፍ አልዳነም።
የ1997ቱ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታችንን ያጭራል። ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዴሞክራሲና የፍትሐዊ ሥርዓት ቋጠሮ የተወጠነበት ነበር። ይሁንና እንደቀደሙቱ ወርቃማ ዕድሎች መጨንገፍ ሆኗል ፍጻሜው።
አሁን ሌላ ዕድል መጥቷል። ይህ ዕድል ከቀደሙቱ በተለይም ከ1983ቱ እና 1997ቱ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ አንጸባራቂ አጋጣሚ ነው።
ቀዳሚዎቹ ዕድሎች ትህነግ ይሉት የሸፍጥና የዘረኝነት ደራሲ ራሱ ጽፎ ራሱ የተወናቸው ነበሩ። የአሁኑ አጋጣሚ ግን በዋናነት ሴረኛውን ወያኔን ወደ ገሃነም የከተተ በመሆኑ ከሁሉም በጣሙን ይለያል። የተሻለ የተስፋ ነጸብራቅም ይታይበታል።
እናም አሁን የተገኘው ዕድል እንዳይጨነግፍና ተስፋውም እውን እንዲሆን ማህበረሰቡም ሆነ መንግስት እንዲሁም ሌሎች ተቋማትና አደረጃጀቶች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
በዚሁ መነሻ በገዥው ፓርቲ እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሥር እየሰደደ በመጣውና በአምሳለ-ትህነግ በተቀረጸው የዘረኝነትና የተደራጀ ዝርፊያ ላይ በሌላ ጊዜ የብዕራችንን ሾተል የምንመዝበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለዛሬ የብዙ ችግሮቻችን ቁልፍ የሆነውን የሕግ የበላይነትን በተመለከተ መጠነኛ የሀሳብ ቋጠሮ እናካፍላችሁ።
ስለ ሕግ መቼም ሕግ የሚለው ቃል እንግዳችን አይደለም፤ በየዕለቱ አብዝተን ስንናገረው እና ስንሰማው የምንውል እንጂ። “ሕግ ይከበር! የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ!” የሚሉት ጉዳዮች የሁሉም ነገራችን ማጣፈጫዎች ሆነዋል።
አንድ ሰው ሕግ ይከበር፤ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ በሚል ጥያቄ ሲጠይቅ ወይም ሲደሰኩር በጥቂቱም ቢሆን ሕግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረድቶ ሊሆን ይገባዋል።
በየትኛውም የዓለም ጥግ የሚኖሩ የሰው ዘሮች ባህላዊም ሆነ ዘመኑን የዋጀ የሕግ ስርዓትን ዘርግተው ይኖራሉ። በሕግ ማደርና ከሕግ ጋር አብሮ መኖር ከሰው ልጅ ሥነ-ተፈጥሮ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
እርግጥ ነው እንስሳትም በተፈጥሯቸው ሕገ-አራዊት በሚባለው ደመ-ነፍሳዊ ስርዓታቸው ይንቀሳቀሳሉ፣ ያድናሉ፣ ይኖራሉ፣ “ጦርነት ይገጥማሉ” ወዘተ። የሰው ልጅ ደግሞ ከእንስሳት ፍጹም በተለየ መልኩ አገር መስርቶ፣ መንግስት አቁሞ በዘመናት ቅብብሎሽ ሲወርድ ሲዋረድ ባዳበረው የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ ሕግ አልያም የሐይማኖትም ሆነ የሞራል ሕግ ሲመራ ኖሯል፤ ይኖራልም።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ዜጎችም ሆኑ የመንግሥት አካላት ተስማምተውም ሆነ ሳይስማሙ አጽድቀው በሥራ ላይ ያኖሯቸውን ሕጎች ሊያከብሩ፣ሊያስከብሩና ሊጠብቋቸው ያስፈልጋል። ሕጎቹን ሲቀይሯቸውም ሆነ ሲሽሯቸው ባለማክበርና በመጣስ ሳይሆን በሕግ አግባብ መሆን ይኖርበታል።
እርግጥ ነው ሕግን ማክበርና ለሕግ የበላይነት መገዛት ከንቃተ-ሕግም በላይ ነው። የሕግ ግንዛቤ መጎልበት ብቻውን መሰረታዊ ጉዳይ አይደለም። ለሰው ልጅ የሕግ ሁሉ ማፍለቂያው ሕሊናው ነው። ዳኝነት በሕሊና ነው። መፋረጃውም መፍረጃውም፣ ሕጉም የህሊና ሚዛን ነው።
ሕግን ማክበር በሕሊና ውስጥ የሚዳብር ራስን የመግዛት ረቂቅ መገለጫ ነው። ራስን መግዛት ደግሞ በምድር ካሉ ስልጣኖች ሁሉ ይልቃል። ለሰው ከራሱ በላይ ሕግ፣ ከራሱ በላይ ፍርድ ቤት፣ ከራሱ በላይ ዳኛ፣ ከራሱ በላይ አስተማሪ የለውም።
ያም ሆኖ በተፈጥሮ የተጎናጸፍነውን ይህንን የሕሊና ጸጋ በአግባቡ እንድንጠቀም በየጊዜው ግንዛቤን ማሳደግ፣ ለሕግ ያለንን የንቃት አድማስ ማስፋት አስፈላጊ ነው።
የሕግን ትርጓሜ በተመለከተ እንደብዙ ሌሎች ጉዳዮቻችን ዓለምን በሙሉ የሚያስማማ አንድምታ እስካሁን አልተገኘም። ይሁንና በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ በሕግ ዙሪያ ሃሳብ አፍልቀው የማህበረሰብን አስተሳሰብ የሚቀርጹ በርካታ ልሂቃን የሚስማሙባቸው ትርጓሜዎች አሉ።
በመሆኑም ሕግ የግለሰቦችን ወይም የማህበረሰብን ባህርይ ለመቅረጽ የሚሰናዳ ወይም የሚዘረጋ ስርዓት መሆኑ ብዙሃንን ያስማማ አንድምታ ነው። በሌላ በኩል ሕግ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ሊኖራቸው የሚገባ መብትና ግዴታን ደንግጎ ያስቀምጣል።
ከሁሉም በላይ ሕግ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ወይም የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ለመኖር በመሰረቱት ሥርዓት ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባ ወይም ሊከተሉት፣ ሊያደርጉት፣ ሊላበሱት የሚገባ ዝቅተኛው የባህርይ ደረጃ ነው።
አሁን በምንኖርበት ዘመን እሳቤ ሕግ ሲባል ወደ ሕሊናችን ቀድሞ የሚመጣው መንግስት በሕግ አውጭው አጽድቆ የሚሰጠን ድንጋጌ (አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ) ነው።
ይሁንና ቀደም ባሉት ዘመናት የሰው ልጅ ይመራባቸው የነበሩት ዓይነተኛ ሕግጋት የባህል፣ የሞራልና የሐይማኖት (የእምነት) መመሪያዎች ነበሩ። በእነዚያ ሩቅ ዘመናት እነዚህ መመሪያዎች የሰውን መስተጋብር ለመምራት በተፈጥሮ በራሱ የተቀመጡለት ሕግጋት ተደርገው በጽኑ ይታመኑ ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን በጊዜ ሂደት የሰው ልጅ ቀስ በቀስ ከተፈጥሮ ሕግጋት በተጨማሪ ራሱ በሚያወጣቸው ሰው ሰራሽ ሕጎች ወደመመራት ተሸጋገረ። ዛሬ ላይም የግልና የጋራ የሆኑ ባህርያትን በመቅረጽና በመምራት ረገድ ሰው ሰራሽ ሕግ ቀዳሚውን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ሰው ሰራሽ ሕግን ማህበረሰብ ራሱ ሊቀርጽና ሊያዳብረው ይችላል። በመንግስትም በሕግ አውጭው አካል አማካኝነት ሕግ ያወጣል። ግለሰቦችም በአንድ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ዙሪያ ሕግን ለራሳቸው ያወጣሉ፤ ይህም ውል ይባላል። ይህ ውል ደግሞ በተዋዋዮቹ መካከል ሕግ ሆኖ ይገዛቸዋል።
በአጠቃላይ ሕግ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ የአንድን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ፣ የታሪክና የማህበራዊ አቋሞችን የሚቀርጽ ሁነኛ መሳሪያ ነው ለማለት ይቻላል።
በዚህ የአንድምታ መነጽርነት ታዲያ ሁላችንም እንደግለሰብም ሆነ እንደማህበረሰብ ዝቅተኛውን የባህርይ ደረጃ አሟልተናል ወይ የሚለው ጥያቄ በሕሊናችን ጓዳ ሊያቃጭል ይገባል።
ካሟላን አሁን በአገራችን የሚፈጠሩት እና ምናልባትም በሌሎች የዓለም ጥጎች ያልታዩ ዘግናኝ እልቂቶች ለምን ይከሰታሉ? ካላሟላንስ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል።
መንግስትም እንዲሁ ነው – መንግስት ያስፈለገበትን ትንሹን መስፈርት ማለትም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ለምን ተሳነኝ ማለት ይገባዋል።
ሕግ ለምን?
በታሪክ ሰረገላ ተሳፍረን፤ በልሂቃን የአብርሆት መነጽር እየተመራን የጥንቱን ዘመን፣ የጋርዮሹን ስርዓተ-ማህበር ለአፍታ እንቃኝ።
የያኔውን የሰው ልጅ ኑሮና የሕግን ሁኔታ ማየታችን “ሕግ ለምን?” የሚለውን በቅጡ እንድንረዳ ያስችለናል። ይበልጡኑም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለውን ሁኔታና በዘመኑ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሕግን አክብሮ የማስከበር ደረጃችንን እንዲሁም እየተጓዝን ያለንበትን መንገድና ፍጻሜውን በደንብ እንድንገነዘበው ያደርገናል።
ቶማስ ሆብስ የተባለው የሕግና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ በደረሰበት የጥናቱ ድምዳሜና ኋላም የእርሱን ፈለግ የተከተሉት ሌሎች ምሁራን እንዳረጋገጡት በጥንት ዘመን የሰው ልጅ በሕግ የማይመራ ነበር። ውሎና አዳሩ ግጭትና ጦርነት ነበር።
የሕይወትና የአካል ደህንነት፤ የንብረትም ዋስትና አልነበረም። አገር መስርቶ፣ መንግስት አቁሞ፣ የሕግ ስርዓትን ሰርቶ መኖር የሚባል ነገር የለም ያኔ። ግጭት፣ መገዳደል እና ዝርፊያ የዕለት ተዕለት መገለጫዎች ነበሩ።
በዚህም የተነሳ አሰቃቂ ግድያዎች፣ ዘግናኝ የአካል ጉዳቶችና አስከፊ የተፈጥሮ ውድመቶች ተከስተዋል። የሰው ልጅ ሕሊና ከግጭትና ከጦርነት አልፎ እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ኪነ ጥበብና ስነ ጥበብን ለማሰብ የተሳነው ነበር።
ማምረት፣ ማደግ መመንደግና መበልጸግም አልተቻለውም። መብትና ግዴታ፣ ፍትህና ርትዕ፣ እውነትና ሃቅ፣ ሕግና መንግስትም አልነበሩም።
በጊዜ ሂደት ታዲያ ያ የጥንት ሰው ከመካከሉ አንዱን ወይም የተወሰኑትን መርጦ በእነሱ መመራት እንዳለበት አሰበ። አስቦም አልቀረ በመረጠው አካል መመራት ጀመረ።
ልሂቃኑ “ማህበራዊ ውል/Socilal Contract” በሚል በሰየሙት በዚህ ሂደት የመሪውና የተመሪው መብትና ግዴታ፤ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመደንገጋቸው በሕግ የመመራት ዝንባሌ ማቆጥቆጥ ጀመረ። ቀስ በቀስም የሰው ልጅ በሕግ በመመራትና ለሕግ የበላይነት በመገዛት ዛሬ የደረሰበት ስልጡን ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሰው በሕግ መመራት በመጀመሩ በንጽጽር ከትላንት የተሻለ ዛሬ ኖሮታል።
ሕግ ከሌለ መሰልጠን፣ ማደግና መበልጸግ አይታሰብም። ሕግ በሌለበትና ኖሮም በማይከበርበት ማህበረሰብ ውስጥ ስርዓት አልበኝነት፣ ግድያና ዘረፋ፤ መገፋፋትና መጠፋፋት የዕለት ተዕለት ክስተቶች ይሆናሉ። ሕግ በማይከበርበት አገር ውስጥ ሰው ከእንስሳት ብዙም በማይለይበት የህይወት አዙሪት ውስጥ ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ጎረቤት ሶማሊያንና በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቅንጡ ሕይወት ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የሊቢያና የሶርያ ዜጎች አሁናዊ ሰቆቃን መመልከት ይበቃል።
በአንጻሩ የሕግ የበላይነት ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ሰላም ይሰፍናል። ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች ይከበራሉ። የሕይወትና የአካል ደህንነት ይከበራል። ንብረት ይጠበቃል። መገፋፋትና መጠፋፋት አይኖርም። ውሎች በአግባቡ ይፈጸማሉ።
ጉልበተኛና ደካማ አይኖርም። አሰሪዎችና ሰራተኞች በየፊናቸው መብታቸው ተከብሮ የኢንዱስትሪ ሰላም ይሰፍናል። ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ይሆናሉ። ማህበራዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት ይኖራል። ዴሞክራሲ ያብባል።
ፖለቲካና ስልጣን የሕዝብ ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይሆንም። ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፤ ምርትና ምርታማነት ይጨምራል። በፍጻሜውም ዜጎች በደስታና በብልጽግና ይኖራሉ።
በእውነት የአባት የእናቶቻችን ልጆች ነንን?
ሕግ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። እስከ አምስት ሺህ ዘመን የሚዘልቅ የአገርነት፣ የመንግስትና የሕግ ልምምድ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ኢትዮጵያውያን።
የኢትዮጵያውያን የመንግስት ታሪክና የሕግ አክባሪነት እንዲሁም የጨዋነትና የግብረ ገብነት ተምሳሌትነት በጥንታውያኑ የግሪክ የታሪክ የቀለም ቀንዶች ሳይቀር ተመስክሯል። ኢትዮጵያውያን “በሕግ አምላክ” የሚሉ ሕዝቦች ናቸው።
መርከብ ገንብተው፣ ሳንቲም ቀርጸው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሲገበያዩ የነበሩ፤ ያኔ ተቆናጠው የነበረውን የስልጣኔ እርካብ ለትውልድ ቁጭትም ኩራትም እንዲሆን አሻራ ትተው ያለፉ ቀደምት ስልጡን ሕዝቦች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ዓለምን በብዙ መልኩ የቀረጹና በተለምዶ “ታላላቅ” የሚባሉትን እምነቶች ገና ከማለዳው ጀምሮ ተቀብለው የዘለቁ ጽኑ ሕዝቦች ናቸው።
“የሕግ ምንጭ ፈጣሪ ነው፤ ፈጣሪ ሕግ ሰርቶ ትዕዛዝ ጨምሮ ለሰው ልጆች አስተላለፈው፤ የሰው ልጆችም ከፈጣሪ ቀጥሎ በላያቸው ላይ በሚሾሙት መሪያቸው በሚወጣላቸው ሕግ መመራት ጀመሩ፤ ስለሆነም ሕግና የሰው ልጅ ጥብቅ አብሮነት አላቸው” የሚል አስተምህሮ ያሰፈኑ ሕዝቦች ናቸው።
ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊት አገር ናትና ከ80 የሚልቁ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ያዳበሩት የባህልና የልማድ ሕጎችም ባለቤት ናቸው ሕዝቦቿ።
በየዘመኑ የተነሱ መሪዎች ሕዝቡን ሲያስተዳድሩባቸው የነበሩና ለብዙ መቶ ዓመታት የዘለቁ ፈውሰ መንፈሳዊ፣ ስርዓተ መንግስት እና ፍትሐ ነገስትን የመሳሰሉ የተጻፉ ሕጎችም ነበሩ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የሕግ ስርዓቱን ለማዘመንና ከተረኞቹ ስልጡኖች ጎራ ለመሰለፍ በሚል የተለያዩ ጥራዝ ሕጎች (ኮዶች) ወጥተዋል። አስገራሚው ነገር ደግሞ እነዚህ ሕጎች ዛሬም ድረስ በሥራ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው። ሕገ-መንግሥት በማውጣትም ከአፍሪካ ቀደምት አገር ናት።
እንዲህ ያለ የሺህ ዘመናት ዕድሜ ያስቆጠረ የሕግና የመንግስት ታሪክ ያላት አገር ሕዝቦች ታዲያ በየዘመኑ በፈጠሯቸው ችግሮች የኋሊት መጓዛቸው አልቀረም። በአንድ ወቅት የምድሪቱ የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ የነበሩ ሕዝቦች የኋላ ኋላ የድህነት ምሳሌ ሆኑ።
አገሪቱም እንደጠፋ በግ በዓለም መድረክ ተዘነጋች። መገፋፋት፣ በፖለቲካና በኃይማኖት ልዩነት መነሾ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት እጣ ፋንታዋ ሆነ። በእንቅርት ላይ እንዲሉ በየጊዜው የሚከሰት ድርቅ የወለደው ረሃብ ሕዝቦቿን አረገፈ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አገሪቱና ሕዝቦቿ ቀድሞ ወደነበሩበት ልዕልና ለመመለስ የሚያስችላቸውን ጭላንጭል አይተዋል። አንጻራዊ መረጋጋት፣ ሰላም፣ በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነትን በልዩነት ውስጥ ለመፍጠር በጎ መሰረቶች ተጥለዋል።
ይሁንና የታየው የተስፋ ወጋገን በጭጋግ እንዳይሸፈን ሁሉም ሊጠነቀቅ ይገባል። የሕግ አለመከበር አደጋ እንዳይሆን ያሰጋል። የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ቡድኖችና ሕዝቦችም ጭምር በሕግ ጥላ ስር ከመተዳደር ይልቅ በማፈንገጥ የሕግ የበላይነትን አደጋ ላይ ሲጥሉት ይስተዋላል።
ከ2010ሩ ለውጥ ጀምሮ ያስተናገድናቸው አያሌ መገፋፋቶች፣ መፈናቀሎች፣ መጠፋፋቶች፣ አለመደማመጦች እንዲሁም የሁሉም ተናጋሪ መሆንና በብሔር ተቧድኖ ጎራ የመለየት ስንክሳሮቻችን ጥቂትም ቢሆን ጋብ ያሉ ይመስላሉ።
በዙሪያው ተቧድነው የተሰባሰቡለትን አንድን ሰው ወይም ቡድን ያለልክ ጀግና አድርጎ ከሰማይ ጥግ መስቀል፤ ሌላኛውን ደግሞ ጭራቅ አድርጎ በመሳል ከእንጦርጦስም በታች አውርዶ በጥልቅ አዘቅት ውስጥ መክተት ብዙዎቻችንን ተጠናውቶን ሰነባብቷል።
ራስን ብቻ አዋቂ አድርጎ ሌላውን ባላዋቂነት አኮስሶ ማየት ነግሷል። ምክንያታዊነትና ቅንነት ከብዙዎች የሕሊና ሰሌዳ ተፍቀዋል። አብዛኛውን ዜጋ በተለይም ከተሜውን ወሬ ፈትቶት ነው የከረመው።
መሪዎቻችን በየዕለቱ ዋነኛ ስራቸው ምጣኔ ኃብታችን፣ ማህበራዊ ብልጽግናችን፣ ዓለም አቀፍ መስተጋብራችን ወዘተ ሊሆን ሲገባ ነጋ መሸ ፖለቲካ ሲከኩ ሲሰልቁ እንዲውሉ ተገደዋል።
አሁን ካለንበት ወሳኝ ምዕራፍ በተለይም ከምርጫው መቃረብ አንጻር ሁሉም በማስተዋል ሊጓዝ ያስፈልጋል። አገራዊ የጋራ ሃሳብ መገንባት አለብን።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ቆም ብሎ ሊያስተውል ይገባዋል። ለሚናገረውና ለሚያደርገው እንዲሁም ለሚወስነው ሁሉ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት። ለሕሊና ሚዛን፣ ለሞራል ዳኝነት ምርኮኞች መሆን ያስፈልገናል። ይህ የስልጡንነት መለኪያ ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትን አንድ ብለን ቆጥረን ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ብቻ በአገሪቱ የፌደራል ፓርላማ ብቻ ከአንድ ሺ 200 በላይ አዋጆች ወጥተዋል። በየክልል ሕግ አውጭ አካላት የወጡ አዋጆችን ክልሎች ይቁጠሯቸው።
አዋጆቹን ለማስፈጸም በሚል የወጡት ደንብና መመሪያዎችማ ለቁጥር ያዳግታሉ። ያም ሆኖ እነዚህ ሁሉ ሕጎች እንደታሰቡት በልዩ ልዩ ጉዳዮች የሕዝብን ባህርይ ቀርጸው ከሕግ አክባሪዎችና የሕግ የበላይነት ከነገሰባቸው ስልጡን ሕዝቦች ተርታ ሊያሰልፉን አቅም አላገኙም።
ሕግን ማክበር የመጀመሪያው ግዴታ ነው። በዚህም ወደ ሞራል ልዕልና መጓዝ ያስፈልጋል። የሕሊና ሰው መሆን የግድ ነው። ሕሊናውን የሚያደምጥ ሰው ግብታዊ አይደለም። ከሕግ አስቀድሞ ለሕሊና መገዛት ያስፈልጋል።
በሕሊና መገዛት ክፉ ሃሳብ በአእምሮ እንዳይፈልቅ ያደርጋል። ቢፈልቅ እንኳን ሕሊና ከሕግ በላይና ከሕግ አስቀድሞ ክፉ አሳቢውን ሰው ይቀጣዋል። ምክንያቱም ሕሊና ክፉ ድርጊትን ብቻ ሳይሆን እኩይ ሃሳብንም ያወግዛልና።
ስለሆነም በምክንያታዊ ሕሊና መጓዝ ይጠበቅብናል። ሃሳብ አፍላቂዎች፣ ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ዜጎች በአጠቃላይ ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች ሕግን ማክበርና ለሕግ የበላይነት መከበር ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።
የህግ የበላይነት የሰፈነባቸው ጠንካራ የመንግሥትና የማህበረሰብ ተቋማትም መገንባት አለባቸው። ይህ ሲሆን ነው ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ታሪክ ሰርቶ ማለፍ የሚቻለው።
በደህና እንሰንብት!