የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል ስናከብር የግድ ሁለት ነገሮችን እናስታውሳለን። የመጀመሪያው በዓሉ የትኅትና በዓል መሆኑን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዓሉ የለውጥ በዓል መሆኑን ነው።
ሁሉን ቻይ፤ ሁሉን አድራጊ፤ ሁሉን ፈጣሪና ሁሉን ወሳኝ የሆነው አምላክ በውኆች መካከል ተገኘ። በዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ ዮሐንስ ዘንድ ወረደ፤ ምንም የሌለው መስሎ ከሰዎች መካከል ተገኘ። ምናልባት በዚያ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ የተገኙት ሰዎች ከእነርሱ እንደ አንዱ ሊቆጥሩት ይችላሉ። በሄኖምና በዮርዳኖስ ማዶ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል የመጣ መስሏቸው ይሆናል። ያ በመካከላቸው ደካማ መስሎ የቆመው ክርስቶስ እልፍ አእላፍ ሠራዊት እንዳለው አያውቁም ይሆናል።
የሚያጠምቀውን ዮሐንስን አስቀድሞ የላከ፤ በዙሪያ ሊጠመቁ የከበቡትን ከአፈር የፈጠረ፤ የሚጠመቁበትን የዮርዳኖስ ወንዝ ያስገኘ መሆኑን አያውቁም። ዓይን ለማየት፣ ጆሮም ለመስማት የምትጓጓለት፤ ክብሩን ቢገልጥ ምድርና ሰማይ በፊቱ ሊቆሙ የማይቻላቸው መሆኑን አያውቁም። ትኁት ሆኖ በመካከላቸው ተገኝቷልና። በትኅትና ውስጥ ያለውን ኃይልና በትዕቢት ውስጥ ያለውን ድካም ዓለም አታውቀውም። በትዕቢት የወደቀውን ዲያብሎስ፣ ክርስቶስ በትኅትና ድል ነሣው። ዲያብሎስም የታለለው ኃይል ከትዕቢት ጋር ያለ መስሎት ነበር። በቤተልሔም በከብቶች በረት መወለድ የትኅትና ሥራ ነው። በዮርዳኖስ ከዮሐንስ ዘንድ ለመጠመቅ ከሰማያት መውረድ የትኅትና ሥራ ነው። ዲያብሎስ ሁለቱንም አላወቃቸውም።
ተዉ ማለት፤ እንታረቅ፣ እንስማማ ማለት፤ እንነጋገር እንወያይ ማለት፤ ጦርነትና ግጭት፣ ጠብና ጥላቻ አያስፈልገንም ብሎ መለመን ዐቅም ማጣት አይደለም። ድንበር ለሚጋፉ የሰላምን እጅ መዘርጋት፤ ለሚፎክሩ የፍቅርን ልብ ማሳየት፤ ለሚወርሩ የዲፕሎማሲን መንገድ መምረጥ ዐቅም ከማጣት የሚመጣ አይደለም። የኃያልነት ምልክቱ ትኅትናና ትዕግሥት ስለሆነ እንጂ። የትኅትና ገመድ የመጨረሻዋ ቋጠሮ ብርቱ ክንድ ናት። ከተሠነዘረች ሳታደቅቅ አትመለስም።
የጥምቀት ሥራ በልደት፣ የሆሳዕና ሥራ በጥምቀት፣ የስቅለት ሥራ በሆሳዕና፣ የትንሣኤም ሥራ በስቅለት ቀን አይሠራም። ክርስቶስ ያስተማረን ይሄንን ነው። ሁሉን በጊዜው መሥራትን። ሁሉም ሥራ የሚሠራበት ትክክለኛ ጊዜ አለው። ያ ቀን ሲደርስ ማንም ወደኋላ አይመልሰውም። ያ ቀን ሲደርስ ማንም ሽንፈቱን አይቋቋምም። ያ ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርሳል፤ ያ ቀን ሲደርስ ተራራው ይናዳል፣ እሳቱም ይበርዳል።
የጥምቀት በዓል የለውጥ በዓል ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ዓለም በንፍር ውኃ ጠፍታለች። የሰው ልጅ ራሱ የተፈጠረበት፣ ለሰው ልጅ ኑሮ ተብሎ የተፈጠረው፤ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የዓለምን አንድ ሦስተኛ የያዘው ውኃ የሰውን ልጅ አጥፍቶታል። ኖኅና ስምንት ቤተሰቡ፣ ከእንስሳቱ ጋር ሲቀሩ ዓለም በጥፋት ውኃ ጠፍታ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ለጥፋት የዋለውን ውኃ ለድኅነት፤ ለመቅሰፍት የዋለውን ውኃ ለበረከት ለውጦታል። የውኃውን ተፈጥሮ ሳይሆን የውኃውን አገልግሎት፣ የውኃውን ታሪክ ነበር የለወጠው።
ከዚህ ትልቅ ትምህርት መውሰድ አለብን። በሀገራችን ለጥፋትና ለመቅሰፍት የዋሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ሕዝብ ለማፋጀት፤ ሕዝብ ለመከፋፈል፤ ሕዝብ ለማለያየት የዋሉ ብዙ መሣሪያዎች አሉ። አያሌ ሕጎችና አሠራሮች አሉ፤ ተቋማትና ሥርዓቶች አሉ። ውኃን ወደ መቅሰፍት የቀየረው የሰው ልጅ ክፋት ነበረ። እነዚህን ሕጎች፣ አሠራሮችና ተቋማት ወደ ጥፋት መሣሪያነት የቀየራቸው የሰዎች ክፋት ነው። እነዚህ መሣሪያዎች የሕዝብን ደኅንነት፤ የሀገርን አንድነት፤ የዜጎችን ሰብአዊ መብት፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ዕድገት እንዲያመጡ አድርገን መለወጥ አለብን። እሳት ምግብ ለማብሰያም ቤት ለማቃጠያም ይውላል። ወሳኙ ተጠቃሚው ሰው ነው። እሳትን ለጥቅም ለማዋል እሳቱን ወደ ውኃነት መቀየር አያስፈልግም፤ የእሳቱን አጠቃቀም መቀየር እንጂ።
ዓለም ለልማት፤ ለዕድገት፤ ለዴሞክራሲ፤ ለሰላም እና ለብልጽግና የተጠቀመባቸው ሕግጋት፣ ተቋማት፤ አሠራሮች፣ ሞያዎች፣ ሥርዓቶች፣ በሀገራችንም ከሞላ ጎደል አሉ። የምንፈልገውን ሰላም፣ ብልጽግናና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግን አላመጡልንም። የለውጥ ሥራችንን በሚገባ አልሠራንም ማለት ነው። ለውጥ እያንዳንዱን የመቅሰፍት ዱካ እየተከተሉ መለወጥን ይጠይቃል። ክርስቶስ ሥራውንም ከዓይን ቅጽበት ባነሰ ጊዜ መፈጸም ይችል ነበር። የሰውን ልጅ ድኅነት ለማረጋገጥ ግን 33 ዓመት ከ3 ወራት በምድር ላይ ኖሯል።
ከልደት እስከ ዕርገት የተሠራው ሥራ 34 ዓመታትን ወስዷል። ይህም ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ነው። እያንዳንዱን የሰውን ልጅ የመቅሰፍት ዱካ እየተከተለ መርገሙን ወደ በረከት፤ መቅሰፍቱን ወደ ምሕረት፤ ጥፋቱን ወደ ድኅነት፤ ሞቱን ወደ ሕይወት ለውጦታል። በሀገራችን ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በየቦታው የተዘራው፣ የተቀበረውና የበተነው መቅሰፍት ብዙ ነው። ጠላት የዕዳ ደብዳቤያችንን በየቦታው ቀብሮታል።
ዛሬ ምናየው የወገኖቻችን ስቃይ፤ ግፍ፤ መከራና ስደት የዚያ የዕዳ ደብዳቤ ውጤት ነው። በንጹሐን ላይ እየወረደ ያለው ውርጅብኝ የዚያ ዕዳ ደብዳቤ ውጤት ነው። ከግራ ከቀኝ የምንሰማው ፉከራ ሁሉ የዕዳ ደብዳቤው ዕዳ ነው። እኛ ማድረግ ያለብን የመቅሰፍቱን ዱካ ተከትለን የዕዳ ደብዳቤውን መደምሰስ ነው። ጊዜ ይወስድ ይሆናል። ትዕግሥት ይጠይቅ ይሆናል፤ ደካማ አስመስሎ ያሳይ ይሆናል፤ ዐቅመ ቢስ ያስመስል ይሆናል፤ ወደ ታች መውረድ ይጠይቅ ይሆናል፤ ግን እያንዳንዱን መርገም ወደ በረከት፤ እያንዳንዱን መቅሰፍት ወደ ምሕረት፤ እያንዳንዱን ጥፋት ወደ ድኅነት፤ እያንዳንዱንም ሞት ወደ ሕይወት መቀየራችን አይቀርም። የኢትዮጵያ አምላክ ከእኛ ጋር ነውና።
ጠላት በሕዝቡ ውስጥ የቀበረው፣ የዘራውና የበተነው ብዙ መቅሰፍት አለ። አንዳንዱን መዋቅራዊ አድርጎታል፤ አንዳንዱን የሕግ ቅርጽ ሰጥቶታል፤ ለአንዳንዱ ሥርዓት ሠርቶለታል፤ ሌላውን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አካትቶታል፤ ለአንዳንዱ በዓል ሰይሞለታል፤ ለሌላው ሚዲያ አዘጋጅቶለታል። ለአንዳንዱ ተቋም አቁሞለታል። አንዳንዱ የሕዝቡ ትርክት ሆኗል፤ ሌላው በዘፈን ውስጥ ገብቷል፣ ሌላውም የፓርቲ ፕሮግራም ሆኗል። ይሄን ሁሉ ዱካ በዱካ እየተከተልን የዕዳ ደብዳቤውን መደምሰስ ይጠበቅብናል።
ለውጡ ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል። እውነታው ግን አይቀሬ መሆኑ ነው። የክርስቶስ ሲወለድ መጠመቁ አይቀሬ መሆኑን አሳይቷል። መጠመቁ ደግሞ ማስተማሩ አይቀሬ መሆኑን አመልክቷል። ማስተማሩ መሰቀሉን፤ መሰቀሉም መነሣቱን፤ መነሣቱም ማረጉን፣ ማረጉ ዳግም መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን አስረግጧል። ሁሉንም በየምዕራፉ ለማስቆም የሞከሩ ነበሩ። አልተሳካላቸውም። ሁሉም በጊዜውና በሰዓቱ ተፈጽሟል። የኢትዮጵያ ትንሣኤም ሂደቱ ይሄው ነው። የጀመርነው የለውጥ ሥራ አንዱ ለሌላው መሠረት እየሆነ፤ አንዱ የሌላውን መምጣት እያበሠረ፤ አንዱ የሌላውን አይቀሬነት እየተናገረ ይቀጥላል። በየደረጃው በአጭር ሊያስቀሩት የሚሞክሩ ይኖራሉ። ትርፉ ድካም ነው። የኢትዮጵያ መለወጥ እንደሆን አይቀሬ ነው። ዱካ በዱካ የዕዳ ደብዳቤዋ እየተደመሰሰ፣ መርገሙ ወደ በረከት፤ መቅሰፍቱ ወደ ምሕረት፤ ጥፋቱ ወደ ድኅነት፤ ሞቱ ወደ ሕይወት መለወጡ አይቀሬ ነው።
ክርስቶስ ከውልደቱ እስከ ጥምቀትና ስቅለቱ፣ ትንሳኤና እርገቱ ያለው ሒደት ተስፋውን ሲጠባበቁ ለነበሩ ሁሉ፥ የሰው ልጆች የዘመናት ፍዳ የሚያበቃበት ጊዜ እየቀረበ መምጣቱን ጠቋሚ ነበር። በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ክርስቶስ የፈጸማቸው ተግባራት፥ የአዳምን ዘር የመዳን ተስፋ ያለመለሙና ጠላት ዲያቢሎስን ያሸነፉለት በመሆናቸው ለሰዎች ልጆች ሁሉ ትልቅ ብስራት ናቸው። ታላቅ ደስታም አስገኝተውለታል፡፡
ኢትዮጵያችን የዘመናት ፈታኞቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸነፉና ብሩህ ተስፋዋ እየበዛላት በመሆኑ ሁላችንም እንደሰታለን። ለዚያ ደስታ ስለታጨን በእርግጥም ሀሴት ማድረግ ይገባናል። ነገር ግን ለታላቅ ደስታ የታጨ ሁሉ እስከመጨረሻው በጽናት ይጓዛል፤ ድልን ይጎናጸፋል ማለት አይደለም። በክርስቶስ የማዳን መንገድ የአዳም ዘር በሞላ ለደስታ ቢታጭም እንደ ይሁዳ ያሉት በመንገዱ ተሸንፈው ስለወደቁ የድሉ ባለቤት አልሆኑም። ስለዚህ የተስፋ መንገዳችን በስኬት እንዲቋጭ ዛሬም ሆነ ነገ ፈተናውን በድል መወጣት ይኖርብናል። በየመንገዳችን የሚገጥሙን ፈተናዎች ወደ ተስፋ መሻገሪያ በሮቻችን ናቸው፡፡ ጥምቀቱና ስቅለቱ ለክርስቲያናዊው የቅድስና ጉዞ የመዳን በሮች እንደሆኑት ሁሉ እንደ ሀገር ለምናደርገው የዲሞክራሲ ጉዞ ከፊታችን የሚጠብቀን ምርጫ በድል ከተወጣነው አንዱ የተስፋ በራችን መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ ሁላችንም ጥሩ ዝግጅት አድርገንና መንፈሳችንን አጽንተን በድል ልንሻገረው ይገባል።
ሌላው በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ቅንነትን ተላብሰን፤ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የተጎዱ ወገኖቻችንን በቸርነት ዓይናችን እያየን፣ የተቸገሩትን በድጋፍ እጃችን እየጎበኘን፤ ለመልካም ለውጥ ሳንሰንፍ፣ ከብልጽግና ጉዟችን ሳንደናቀፍ፣ የወቅቱን የኮቪድ-19 ስርጭት ችላ ሳንል ልናከብረው ይገባል። በአውሮፓና የአሜሪካ ሀገራት የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት መጀመራቸው ይታወቃል። እኛ ክትባቱን እስክንጀምር ለጊዜው ያለን አማራጭ መከላከል ብቻ ነው። በእስከ ዛሬው የጥንቃቄ ዘዴዎቻችን አማካኝነት ራሳችንን ከወረርሽኙ እየጠበቅን፥ በፊታችን የሚፈነጥቀውን የተስፋ ጮራ አብረን ለማየት ያብቃን እላለሁ፡፡
በድጋሚ፣ መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 10፣ 2013 ዓ.ም