ኢያሱ መሰለ
ኢትዮጵያ እንዳሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት አይነት የብርሃንና ጨለማን ትንቅንቅ አላስተናገደችም ብል አላጋነንኩም። የፈነጠቀልንን ብርሃን እያጣጣምን ከርቀት በሚታየን ተስፋ ፈካ ማለት ስንጀምር የጨለማ ሃይሎች በሚፈጽሙት እኩይ ሴራ የሀገራችን ሰማይ ይጠቁራል። እርሱን አልፈን እንደገና ብርሃን ጭል ጭል ማለት ሲጀምር አሁንም ሌላ የሐዘን ድባብ ይፈጥሩልናል። በብርሃንንና ጨለማ ምልልስ እዚህ ደርሰናል። አሁን ብርሃን ለረዥም ሰዓት ከእኛ ጋር የሚቆይበት፤ ተስፋችንና ህልማችን እውን የሚሆንበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል።
ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የፖለቲካ ምህዳሩ በመስፋቱ ምክንያት ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ነጻነት አግኝተዋል። አንዳንዶች ያገኙትን እድል በሰላማዊ መንገድ ሲጠቀሙበት ሌሎች ደግሞ የላላውን ልጓም አውልቀው እንዳስፈለጋቸው ሲፈነጩ ታይቷል። በዚህም እዚያና እዚህ በሚፈጥሯቸው ግጭቶች ምክንያት የኢትዮጵያን ሰላም አውከዋል፤ የህዝቦችን የመኖር ህልውና እና መተማመን አደጋ ላይ ጥለዋል፤ ዜጎችን ወጥቶ የመግባት፤ ሰርቶ የመብላት ዋስትና አሳጥተዋል።
ሀገር አማን ብለው በሰላም የሚኖሩ ሰዎች ድንገተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ከመንደራቸው ተፈናቅለዋል፤ ቤት ንብረታቸው ወድሟል፤ አንዳንዶችም ያለምንም ምክንያት በግፍ ተገድለዋል። ኢንቨስትመንቶች ተስተጓጉለዋል ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ተግባር ማከናወኛ ተቋም መሆናቸው ቀርቶ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሆነዋል። በአጠቃላይ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመት ከአጋማሽ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ አሰቃቂና አሳዛኝ ክስተቶች ተስተውለዋል። ከነዚህ ሁሉ ጥፋቶች ጀርባ ያለው ማን ነው? ለምን እንዲህ አይነት የሀገር ክህደት መፈጸም አስፈለገ? ከተባለ መልሱ ግልጽ ነው። ለምን ኢትዮጵያ ከእኛ ውጭ ትመራለች፤ ለምን መንግስት ጉዳችንን ለህዝብ አጋለጥብን፤ ለምን የዘረፋ እና የስርቆት በሮች ይዘጉብናል የሚሉና ሌሎችም የጥቅም ጉዳዮች ናቸው።
የጁንታው አባላት ስልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ ኢትዮጵያን የማተረማመስና የመበታተን ሀሳባቸውን በየአደባባዩ ገልጸዋል። ለአብነት የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል በአንድ ወቅት ንግግራቸው ‹‹ወይ እንበታተናለን ወይ እንከባበራለን ማለታቸው አይረሳም፤ አቶ ስዩም መስፍን ‹‹ ኤርትራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትም በሌሎች አካላት ጉዳይ ጣልቃ የማይገቡበት ምክንያት የለም›› ስለዚህ ቤኒሻንጉል ወይም ኦሮሚያ ክልል ሊተራመስ እንደሚችል ነግረውናል። እነ ጌታቸው ረዳና ሴኮ ቱሬን የመሳሰሉትም ተመሳሳይ ሀሳቦችን ሲያንጸባርቁ ሰምተናል።
ሳያስበው ስልጣኑን ያጣው የጁንታው ቡድን ሀገር የማፈራረስ አላማውን ለማሳካት ሲል ቀደም ሲል በአሸባሪነት ሲፈርጃቸው ከነበሩ ቡድኖች ጋር ጋብቻ መስርቶ ብዙ ጥፋቶችን በእጅ አዙር ሲያስፈጽም እንደነበር ስንቶቻችን ታዝበን ይሆን? ከኤርትራ የገቡት የኦነግ አባላት መቀሌ ላይ ምሳ በተጋበዙበት ወቅት ስብዓት ነጋ የኦነግን ባንዲራ ይዘው ሲያውለበለቡ ስናያቸው አንድ ነገር መገመታችን አይቀርም።
ስብዓት ነጋ ኦነግን በአሸባሪነት ፈርጀው ከሀገር ካስወጡት ጉምቱ የህወሓት ባለስልጣናት አንዱ ናቸው። በህወሓት ሰዎች የስልጣን ዘመን እንኳንስ ኦነግ ተሁኖ ይቅርና የኦነግን ባንዲራ ይዞ የተገኘ ሰው እጣ ክፍሉ ምን ሊሆን እንደሚችል የምናውቀው ነው። ጁንታው ዛሬ ኦነግ ሸኔን የስልጣን መወጣጫው ለማድረግ ተወዳጀው እንጂ በለስ ቀንቶት ወደ ስልጣን ቢመጣ በመጀመሪያ በጠላትነት ፈርጆ ከሀገር የሚያጠፋው እርሱኑ ነው ፤ ይህን ከቀደመ ባህሪው መረዳት አይከብድም።
ጁንታው ከጽንፈኞች ጋር ሆኖ በእጅ አዙር አንዳንዴም በቀጥታ የሀገሪቱን ሰላም የማወክና ህዝቦች ተረጋግተው እንዳይኖሩ የማድረግ ስራዎችን እንደሚሰራ በግልጽ እየታወቀ በትዕግስት ታልፏል። በአገዛዝ ዘመኑ በፈጸማቸው ኢሰብአዊ ወንጀሎችና ምዝበራዎች ሳይጠየቅ አርፎ እንዲቀመጥ እድል ቢሰጠውም መጠቀም አልፈለገም። የሰላም አምበሳደር እናቶችን፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን የሰላም ጥሪና ምልጃም አልተቀበለም። ይልቁንም ለሰላም ሲባል የሚደረገውን ትእግስትና ምልጃ እንደፍርሃት ቆጥሮ ለያዥ ለገላጋይ ሲያስቸግር ከረመ።
ጭራሽ አይናቸውን በጨው ያጠቡ የጁንታው ከፍተኛ አመራሮች በድምጸ ወያኔ እና በዲ ደብሊው የተሌቪዥኖች እየቀረቡ ዛቻና ማስፈራራታቸውን ቀጠሉ። ከፌደራል መንግስት እውቅና ውጭ በራሳቸው ፕሮግራም ምርጫ እስከማድረግም ደረሱ። ይህ ሁሉ ሲሆን መንግስት የሰላም አማራጮችን አሟጦ ከመጠቀም ውጭ ምንም አይነት የሃይል እርምጃ ለመጠቀም አለመፈለጉን ሁላችንም የታዘብነው ነው።
የመንግስት ሆደ ሰፊነትና ከልክ ያለፈ ትእግስት ሀገር ወዳድ ዜጎችን ያስቆጣ እንደነበርም እናስታውሳለን። አንዳንዶችም በመንግስት ላይ አመኔታ እስከማጣት ደርሰው፤ መንግስት ህግ የማስከበር አቅም የለውም የሚል ትችት ሲሰነዝሩ ተሰምቷል።
የመጨረሻው ሰዓት ደረሰ።
‹‹አይጥ ለሞቷ የድመትን አፍንጫ ታሸታለች›› እንዲሉ የለመዱት የጁንታው የጥፋት እጆች በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ቃጡ። የኢትዮጵያን ክብር ያዋረደ፣ ህዝቦችን እጅግ ያስቆጣና የመንግስትንም ትእግስት ያሟጠጠ የድፍረት ተግባር ፈጸሙ። ጁንታው በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት እንደ ትልቅ ጀብድ ቆጥሮ በሚዲያ እስከ ማቅራራት ደረሰ፤ እዚህ ጋር ሴኩቱሬ ጌታቸው በዲ ደብሊው ቴሌቪዥን ቀርቦ ያሰማውን ንግግር ቀንጨብ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል።
‹‹መንግስት በምእራብ ትግራይ ሃይል ማሰባሰብ ሲጀምር የትግራይ መንግስት ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ። በመጀመሪያ የሰሜን እዝ ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ጎን እንዲቆም የማድረግ ጥረት ተደረገ። ለዚህም ብዙ የማግባባት ስራ ተሰራ። በርከት ያሉ የጦር መሪዎች የትግራይ ህዝብ ፍትሃዊ የሆኑ ጥያቄዎች ያሉት ስለሆነ አንወጋውም አሉ። በጉዳዩ ላይ የሚያንገራግሩና የተቃወሙም ነበሩ። እጃችንን አናነሳም ካሉት የእዙ ሰራዊት ጋር በመተባባር ለመተባባር ፈቃደኛ ያልሆኑትን በሃይል ተልእኳቸውን እንዳይወጡ በማድረግ በ45 ደቂቃዎች ውስጥ እዙን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተችሏል።
ፈጣን የሆነ መብረቃዊ ጥቃት በማድረስ የወራሪውን ሃይል በማተራመስ ራሳችንን ከጥቃት አድነናል። የሰሜን እዝን እንቅስቃሴ በመግታት በሰላም የሚገቡት በሰላም እንዲገቡ በማድረግ በሀገሪቱ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የጦር መሳሪያና የተኩስ አቅም የትግራይ ህዝብ አቅም እንዲሆን በማድረግ አጠናቀናል። በዚህ ሁኔታ አሁን ትግራይ ውስጥ በአብይ አህመድ የሚታዘዝ ሰሜን እዝ የሚባል ሃይል የለም ›› ነበር ያሉት።
ሴኩቱሬ ይህን ይበል እንጂ የሰሜን እዝ ሰራዊት በጥቅም የተደለሉ የጁንታው ተላላኪ ከሆኑ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች በስተቀር የእኩይ ተግባራቸው ተባባሪ የሆኑ ሌሎች አባላት አልነበሩም። እንደውም በሰሜን እዝ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችም ቢሆኑ በሙሉ የጁንታዊ ተባባሪዎች ነበሩ ማለት አያስደፍርም።
እዚህ ጋር በቦታው ከነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አንደበት የሰማሁትን አንድ ታሪክ ላንሳ። የትግራይ ተወላጅ የሆነ የመካናይዝድ ክፍል አባል ነው። ክህደት የፈጸሙት የሰራዊቱ አባላት አብሯቸው በመሆን ሰራዊቱ ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ሊያግባቡት ሞከሩ፤ እርሱ ግን እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ አገልጋይ እንጂ የአንድ ፓርቲ ቅጥረኛ አይደለሁም በማለት ነበር ዘሎ ወደ ታንኩ ውስጥ የገባው። ውጊያው እንደተጀመረም ጥቃት ከሚፈጸምባቸው የሰራዊቱ አባላት ጎን ተሰልፎ ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ጠዋት ድረስ ሲዋጋ አድሮ መሰዋቱን እና ሌሎችም መሰል ታሪክ ያላቸው የትግራይ ተወላጆች እንዳሉ ሰምቻለሁ።
የጁንታው አባላት ሰራዊቱን ከጀርባው ካስወጉትና ትጥቁን ከዘረፉት በኋላ ከትግራይ ህዝብ ጎን ቆሟል በማለት ተዘባብተዋል።
በእብሪት የተወጠረው ይህ ቡድን ከሰላም ይልቅ ጦርነትን የመጨረሻ ምርጫው አድርጎ በማይወጣው ውጊያ ውስጥ መግባቱ ኢትዮጵያን በመበታተንና በሮቿን በመከፋፈት ለውጭ ወራሪዎች ለማጋለጥ ካልሆነ በስተቀር በመከላከያ ሰራዊት ላይ የበላይነትን አግኝቼ መንበረ ስልጣን አገኛለሁ ብሎ አይደለም።
ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን አደጋ እንመልከት፤ ቀደም ሲል በአቶ ሴኩቱሬ ንግግር እንደተገለጸው ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ አቅም የሚገኘው በሰሜን እዝ ሰራዊት እጅ ነው፤ ይህ የጦር መሳሪያ ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ለመታደግ ያስችላል ተብሎ የታመነበትና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ነው። የውጭ ወራሪ ሃይሎች በሀገራችን ላይ እያንዣበቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ጁንታው የመከላከያ ሰራዊቱን አቅም ማዳከሙ ከማን ጋር እየሰራ እንዳለ ያየንበት ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ ህግ የማስከበር ተልእኮ ይዞ ወደ ትግራይ ክልል እንደተንቀሳቀሰ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው መግባታቸው ከጁንታው ጋር መተባበራቸውን የሚያመላክት ነው። ጁንታው ከውጭ ሃይል ጋር ተሻርኮ በዚህ መልክ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ማስደፈሩ የክህደቱን ጥግ የሚያሳይ ነው።
ለትግራይ ህዝብ ቆሜያለሁ የሚለው ይህ ቡድን በህግ ማስከበሩ ሂደት ከመንግስት የሚደርስበትን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው እልሁን የሚወጣው መሰረተ ልማቶችን በማውደም እንደነበር ታይቷል። በከፍተኛ ወጪ የተሰሩ ድልድዮች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ኤርፖርቶችን አውድሟል። ቤተ እምነቶችን የጦር መሳሪያ ማከማቻ፣ ምሽግና መዋጊያ አድርጓቸዋል። በጦርነቱ ላይ ያሰለፋቸው በርካታ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ለተሳሳተ ዓላማ ያሰለፋቸውን ምስኪን የደሃ ልጆችን እሳት ውስጥ ማግዷል።
ጁንታው በስልጣን ዘመኑ ዞር ብሎ ያላየውን የትግራይ ህዝብ ምሽግ አድርጎ ሀገር እያተራመሰ እድሜውን ማስረዘም ቢመኝም ሁኔታዎች አልፈቀዱለትም። የቆፈራቸው ምሽጎችና ዋሻዎች አንቅረው ተፍተውቷል፤ የትግራይ ህዝብ ጀርባው ላይ ተቀምጠው ደሙን የሚመጡትን ነፍሰ በላዎች ለህግ አስከባሪው አሳልፎ እየሰጠ ነው።
ጁንታው የትግራይ ህዝብን ስነልቦና በቅጡ ተረድቶ ቢሆንና፤ ዘመኑ የደረሰባቸውን የጦርነት ቴክኖሎጂዎች ደርሶባቸው ቢሆን ኖሮ ዘው ብሎ ውጊያ አይጀምርም ነበር። ባረጀ አስተሳሰብ እየተመራ፤ በድሮ በሬ ማረስ ዳዳው። መከላከያ ሰራዊትን በመተንኮስ የመንግስትን እሽሩሩና ማባበል በራሱ ጊዜ ወደ ጦርነት የቀየረው ጁንታ እራሱን በራሱ አጠፋ። ‹‹ገዳይ ቢያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል›› ይሉታል ይህ ነው።
አሁን መንግስት ወንጀለኞችን በማደንና በመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ይህ ማለት በአንድ በኩል በጦርነቱ ተሸንፈው በየዋሻው የተደበቁ የጁንታው አባላትን እየያዙ ለህግ የማቅረብ እና ጎን ለጎን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ነው።
ወንጀለኞች ባለቀ የጦርነት ምእራፍ ውስጥ ሆነውም እጃቸውን እንዲሰጡ የሚቀርብላቸውን ጥሪ ከመቀበል ይልቅ መሳሪያ ይዘው ለመዋጋት መሞከራቸው ጀብደኝነታቸውን ሳይሆን ግትርነታቸውን የሚያሳይ ነው። ትናንት የመንግስት ከፍተኛ አመራር ሆነው ሀገር ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ተራ ወንበዴ ሆነው በየዋሻው ሲሽለኮለኩ ማየት ያሳፍራል። ለፖለቲካ ዱስኩራቸው ሲሉ ብቻ ህገ መንግስት ይከበር እያሉ ሲወተውቱ የነበሩ አካላት እራሳቸው አርቅቀው ያጸደቁትን ህግ መንግስት ጥሰው በርካታ ወንጀሎችን ሲሰሩ መመልከት ከትዝብትም በላይ ነው።
ዛሬ ሀገሪቱን እየመራ ያለው አካል ከጦርነት ይልቅ በሀሳብ ልዕልና ያምናል። ለዚህም ነው በርካታ ወንጀሎች ሲሰሩ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በትዕግስት ሲመለከት የነበረው የትዕግስት ፍሬ ጣፋጭ በመሆኑ ነው።
መንግስት ጦርነትን የመጨረሻው አማራጭ አድርጎ እርምጃ መውሰድ ሲጀመር የነበረው እንዳልነበረ ሲሆን አይተናል። የጦርነት ውጤቱ መራራ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል። እንግዲህ ያ ሁሉ የመንግስት ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት እንዲህ አይነት መራራ ውጤት እንዳይኖር ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013