ምርጫ 2013 ሊካሄድ አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን ሆኖ መወሰኑ ይታወቃል። በፀጥታ ችግሮችና በሌሎች ምክንያቶች ሰኔ 14 ቀን ድምጽ መስጠት በማይቻልባቸው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የድምፅ መስጫው ቀን ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫውን ለማስፈፀም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ሰኔ 14 ቀን ድምጽ መስጠት የማይቻልባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሰረት በተጠቀሰው ምክንያት ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የማይካሄድባው አካባቢዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሽ እና ዳለቲ)፣ በኦሮሚያ ክልል (ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ ገሊላ፣ አሊቦ፣ ጊዳሚ እና ኮምቦልቻ)፣ በአማራ ክልል (ማጀቴ/ማኮይ፣ አርጎባ ልዩ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ ላይ አርማጭ እና አንኮበር)፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ሱርማ ልዩ፣ ዲዚ ልዩ፣ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ማጀት መደበኛ፣ ሸኮ ልዩ እና ቴፒ) እንዲሁም በሐረሪ ክልል (ጀጎል ልዩ እና ጀጎል መደበኛ) የተባሉት የምርጫ ክልሎች ናቸው።
በሌላ በኩል ከፀጥታ ችግር ባሻገር በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ በተፈፀሙ ጉድለቶች ምክንያት ከላይ ከተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች በተጨማሪ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ የማይከናወንባቸው ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንዳሉም ቦርዱ ይፋ ባደረገው መረጃ አመልክቷል። ቦርዱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ 54 የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ችግሮች አጋጥመው እንደነበርና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር በማድረግ በአማራጭ መፍትሄዎች ላይ እንደተወያየ ጠቁሞ፤ ከእነዚህ የምርጫ ክልሎች መካከል በፍጥነት ህትመት ሊከናወንባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች በመፈለግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ችግር ያለባቸው የምርጫ ክልሎች ቁጥር 27 ስለመሆናቸው ገልጿል። ስለሆነም በእነዚህ 27 የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ድምጽ የሚሰጠው ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሆነ ቦርዱ አሳውቋል።
በተጨማሪም በሱማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ በ14 ምርጫ ክልሎች ምርመራ ተከናውኖ በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀት ድጋሚ ህትመት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚመለከታቸው የምርጫ ክልሎች መካከል የሚመደቡ በመሆናቸው በክልሉ የሚደረገው ድምጽ አሰጣጥ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።
በሌላ በኩል ‹‹ከቦርዱ እውቅና ውጭ በተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች (በአዲስ አበባ ሁለት፣ በድሬዳዋ ስድስት እንዲሁም በደቡብ ክልል 71) የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ህጋዊ አይደሉም›› ሲል ቦርዱ ወስኗል። በቦርዱ መረጃ መሰረት ከድምጽ መስጫ ወረቀት ጋር በተገናኘ ጉድለት በታየባቸው የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የተመዘገበውን መራጭ ሳይጨምር ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በጠቅላላው 37 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሕዝብ በመራጭነት ተመዝግቧል።
ምርጫ ቦርድ ከድምፅ መስጫ ወረቀት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ ውሳኔ መስጠቱና ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የድምጽ መስጫው ቀን እንዲራዘም ማድረጉ ቀላል ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ይህ ተግባር ከፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ ቅሬታ ብቻ የተወሰነ የአጭር ጊዜ ስራና የመልካም ፈቃድ ስጦታ ሳይሆን የድምፅ መስጫ ወረቀት እና የውጤት ማሳወቂያ ፎርሞች በጥንቃቄ በማመሳከርና የማመሳከሩ ውጤቶች ባሳዩት ጉድለቶች ምክንያት የተወሰነ ጥንቃቄን የሚፈልግ ስራ እንደሆነ መዘንጋት አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በአገሪቱ በተደረጉት ‹‹ምርጫዎች›› መሰል የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ስለመኖራቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ሲታሰብ፤ ይህ የቦርዱ ተግባር በቀላሉ የሚታይ ስራ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ነው።
በዛሬው ትዝብቴ አፅንዖት ሰጥቼ ማብራራት ወደፈለግሁት ጉዳይ ልመለስ … የትዝብቴ አጠቃላይ ጭብጥ በቅድመ ምርጫው ለታዩ ችግሮችን መፍትሄ በመስጠት ድህረ ምርጫውን ጊዜ ሰላማዊ ማድረግ ላይ ያተኩራል። ከላይ የተጠቀሱት የአሰራር ጉድለቶች በምርጫ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉና የሚጠበቁ ቢሆኑም አንዳንዶቹ፣ በተለይ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ የተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች ጉዳይ፣ ግን የሚያስገርሙም የሚስተዛዝቡም ናቸው። የምርጫ ጣቢያዎችን ማደራጀትን ጨምሮ ምርጫውን የማስፈፀም አጠቃላይ ሂደቱን የመምራትና የመቆጣጠር ኃላፊነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ሳለ ‹‹የምርጫ ጣቢያዎችን›› ከአስፈፃሚው/ተቆጣጣሪው እውቅና ውጭ ማቋቋምና ‹‹መራጮችን መመዝገብ›› የለየለት ሕገ ወጥነት ነው። በእርግጥ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረገው መረጃ በታችኛው የመንግሥት እርከን ላይ የሚገኙ ሰራተኞች በስራው ላይ ጣልቃ እየገቡበት እንደሆነ ገልፆ ነበር። እነዚህ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ የተቋቋሙና ‹‹መራጮችን የመዘገቡ የምርጫ ጣቢያዎች›› በማን እንደተቋቋሙ በይፋ ቢገለፅ ጥሩ ነው፤መገለፅም አለበት።
በፀጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ መስጫ ቀን ከሰኔ 14 ወደ ጳጉሜ አንድ ቀን የተዛወረባቸው አካባቢዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከላይ ከተጠቀሱት አካባቢዎች በተጨማሪ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከአገራዊ ምርጫው ጋር እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔም ወደ ጳጉሜ አንድ ቀን ተዛውሯል። እንደምርጫ ቦርድ ማብራሪያ፣ ሕዝበ ውሳኔው በሚከናወንባቸው የምርጫ ክልሎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ድምጽ የማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች አሉ። ይህም የሕዝበ ውሳኔውን ምሉዕነት ስለሚያጎድለውና የሁሉንም መራጮች ምርጫ በትክክል መመዘን ስለማይቻል፣ ሕዝበ ውሳኔው ከሌሎች የምርጫ ክልሎች ጋር ጳጉሜ አንድ ቀን 2013 ዓ.ም እንዲከናወን ተወስኗል። የፀጥታ ችግሮች ያለፉት ጥቂት ዓመታት የአገሪቱ ዋነና ፈተናዎች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የምርጫ ወቅት ደግሞ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል።
የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭትም ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። በምርጫ ወቅቶች የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እጅግ ይበዛል። ሰከን ብሎ ማሰብና ማመዛዘን ካልተቻለ ሐሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ሂደት ላይ እንዲሁም ከምርጫ በኋላ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው። ሐሰተኛ መረጃዎች መራጮች በአጠቃላይ ዜጎች ስለእጩዎች፣ ስለመንግሥትም ሆነ ስለህብረተሰባቸው ትክክለኛ መረጃ እንዳይኖራቸው የማድረግ አደጋን ያስከትላሉ። ከምርጫ በኋላም ለሚፈጠሩ ችግሮችም መንስዔ ይሆናሉ። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች ከሐሰተኛ መረጃዎች ሁሉ ቅድሚያ ይይዛሉ።
ስለሆነም ዜጎች የመረጃዎቹን ምንጮች ታማኝነት መገምገም፣ ምንጮቹ ከዚህ ቀደም ስለነበራቸው ልምድ/ ታሪክ ማጣራት፣ የመረጃዎቹ ዓላማዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰላሰል፣ የታወቀ የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እስከሚሰጥ ድረስ መረጃዎቹን ለሌሎች አለማጋራት እንዲሁም አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች ሐሰተኛ መረጃዎቹ ሊፈጥሩ የሚችሏቸውን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይችሉ እንኳ አደጋዎቹን ለመቀነስ ግን ያስችላሉ። በተጨማሪም ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት በሐሰት መረጃ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል!
በፌስቡክ ሜዳ ላይ የታዘብናቸው የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች አባላት ሽኩቻዎች በእውነተኛ የሃሳብ ግብይት ላይ ተመስርቶ ከሚደረግ ክርክር ያፈነገጡ ናቸው። አሉባልታዎች ስር እየሰደዱ ከሄዱ መራጩ ሕዝብ ትኩረቱን ያልረባ ነገር ላይ አድርጎ ድምፁን ለአገር ለማይጠቅም ነገር ላይ እንዳያውለው ያሰጋል። አሉባልታዎች ሲበዙ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ችላ ተብሎ የጉልበትና የአሻጥር መንገዶች እንዲመረጡ ምክንያት ይሆናል። በሕግ ዕውቅና ያገኘው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በግላጭ እየተደፈጠጠ፣ የጥቂቶች ድምፅ ከመጠን በላይ እየተስተጋባ ችግር ይፈጠራል።
በአጠቃላይ እነዚህ ድርጊቶች መፍትሄ ካልተሰጣቸው ‹‹ … ከምርጫው በኋላ የፀጥታ ችግር ይፈጠራል፤ኢትዮጵያም ትተራመሳለች …›› ብለው አሰፍስፈው ለሚጠብቁ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ ስለሚችሉ አስቸኳይ ምላሽና መፍትሄ ሊያገኙ ይገባል። በአጥፊዎችም ላይ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል። አለበለዚያ ግን የእነዚህኞቹ አካላት ሕገ ወጥ ተግባራት ድህረ ምርጫውን የግጭት ጊዜ ለማድረግ ለሚመኙ ኃይሎች የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ።
ቀደም ሲል በመራጮች ምዝገባ ወቅት በወቅቱ ከክልሎች የሚገኘው የቢሮዎች ትብብር በመዘግየቱ፣ የእጩዎች ምዝገባ ከተጀመረም በኋላ ዝግጁ ያልሆኑ የተወሰኑ ቢሮዎች የነበሩ በመሆኑ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችም ተጨማሪ ቀናት በመጠየቃቸው እና የእጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ፣ ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመኖራቸው፣ አንድ ምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችለውን የመራጭ ቁጥር (1500 ሰው ብቻ) መዝግበው በጨረሱ አካባቢዎች ተጨማሪ ንኡስ የምርጫ ጣቢያዎች በማስፈለጋቸው እንዲሁም በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠሙት የቁሳቁስ ማጓጓዝ ተግዳሮቶች በመገምገምና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ስራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን ሲባል የመራጮች ምዝገባ ከአንድም ለሁለት ጊዜያት ያህል እንዲራዘም መደረጉና በፓርቲዎች ቀርበው የነበሩና ቦርዱም በአሰራሩ ያስተዋላቸው ችግሮች ከሞላ ጎደል ምላሽ ማግኘታቸው ለድህረ ምርጫው ሰላማዊነት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ አይጠረጠርም።
ቀደም ባሉት ሳምንታት ባጋራኋቸው ትዝብቶቼ እንደጠቀስኩት ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ኃላፊነት ያለባቸው ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎቸውም ሆኑ ማኒፌስቶዎቻቸው የሐሳብ ልዩነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፈረሙት የጋራ ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ የተፎካካሪዎቻቸውን ስም ከማጥፋትና ከውንጀላ መታቀብ ይኖርባቸዋል። የምርጫው ውጤት አሳማኝ ሆኖ ቅቡልነት ማግኘት የሚችለው ሒደቱ የተስተካከለ ሲሆን ብቻ ነው። ቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ቀንና ድኅረ ምርጫ ሒደቶቻቸው ከተስተካከሉ ውጤቱም አሳማኝ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች መተማመን ይኖርባቸዋል።
መተማመን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ወገኖች ኃላፊነት አለባቸው። መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ፣ አገር በሕግና በሥርዓት እንድትመራ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። የሕግ የበላይነት እንዲከበር የማድረግ፣ የተቋማትን ነፃነትና ገለልተኛነት የማጠናከር እንዲሁም የሕግ ማዕቀፎችን ከወቅቱ ቁመና ጋር የማመጣጠን ኃላፊነቶች አሉበት።
ለምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሴራ ፖለቲካ ራሳቸውን ነጻ ሊያደርጉ ይገባል። ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ተገዢ ያልሆነ የሴራ ፖለቲካ ትርፉ እርስ በእርስ መፋጀትና አገርን ማፍረስ ነው። በሃሳብ ግብይት በኩል ለሕዝብ ዳኝነት በመቅረብ የአሸናፊነትን መንበር መቀዳጀት የመሰለ ሥልጡን አካሄድ እያለ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹ዓይንህን ለአፈር›› የሚያባብል ኋላቀር ድርጊት ውስጥ መገኘት አሳፋሪ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት የሚቻለው የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ነው። የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ራሳቸውን ከሴራ፣ ከቂም፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነትና ከጉልበተኝነት አባዜ ማላቀቅ ይኖርባቸዋል። ሃሳብን ማዕከል ላደረገ የውይይትና የሰለጠነ ክርክር ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል።
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ የድህረ ምርጫውን ጊዜ እንዳያበላሹት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በድህረ ምርጫው ጊዜ አስተማማኝ ሰላም የሚሰፍነው በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት ሕግን ብቻ ተከትለው ሲፈጸሙ ነው። ስለሆነም የቅድመ ምርጫና የምርጫ ወቅት ተግባራትን ሰላማዊና ሕጋዊ በማድረግ የድህረ ምርጫውን ጊዜ ሰላማዊ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ወሳኝ አገራዊ ኃላፊነት ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013