‹‹ወደቀ›› ሲሉ ‹‹ተሰበረ››

በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው ‹‹በስንቱ›› ሲትኮም ድራማ ላይ ያየሁት አንድ መልዕክት፤ ተማሪ እያለሁ በቤተሰብ፣ በጎረቤትና አካባቢ የታዘብኳቸውን ነገሮች አስታወሰኝ:: ከድራማው ልጀምር::

ገጸ ባህሪው (በስንቱ) ሥራ ለቋል:: ሥራ የለቀቀው አነቃቂ ንግግር ሰምቶ ነው:: መልቀቂያ ሊያስገባ ሲሄድ ግን ሊለቅ ሲያስብ ያልሆነ ነገር ሰርቶ ነበርና ባለቤቱም ከሥራ ሊያሰናብተው ደብዳቤ ጽፎ ነው የጠበቀው:: አጋጣሚ ተገጣጠመ:: ያም ሆነ ይህ ሥራ ለቀቀ::

ከሥራ ተባረረ ተብሎ ተወራ:: አልተባረርኩም ራሴው ነኝ የለቀቅኩ ቢልም የሚሰማው ጠፋ:: ሰዎች ከባለቤቱ መረጃ ይልቅ በስሚ ስሚ የሰሙትን አሉባልታ ነው ማስተጋባት የፈለጉት:: ራሴው ነኝ የለቀኩት ብሎ የነገራቸው ሁሉ ተባረረ እያሉ ከንፈር ይመጣሉ፤ እሱ ተባረርኩ ብሎ ሳያዝን በግድ ከላዘንልህ አሉት::

ይሄ ብቻ አይደለም:: አበደ ብለው ማስወራትም ጀመሩ:: በገመድ አልባ(ዋየርለስ) የጆሮ ማዳመጫ ስልክ ሲያወራ ‹‹እዩት አብዶ ብቻውን ሲያወራ›› ተባባሉ:: እንደማንኛውም ሰው ጤነኛ መልስ እየመለሰ ዳሩ ግን በአዕምሮ መቃወስ የሚመልስ ነው የሚመስላቸው::

ድራማው ላይ ይህን ክፍል ሳይ ከአሥራ ምናምን ዓመታት በፊት ተማሪ እያለሁ በቤተሰብና አካባቢያችን የታዘብኳቸው ነገሮች ትዝ አሉኝ:: ከዚህ የምናብ ፈጠራ ከሆነ ድራማ ጋር በቀጥታ የሚመሳሰል እውነተኛ ክስተት ነበር:: ነገሩ እንዲህ ነው::

አንዲት አክስቴ መነኮሰች:: በአካባቢው ልማድ ሲመነኩሱ ሰይጣን ይፈታተናቸዋል ተብሎ ይታመናል:: ሲመነኩሱ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አቃቤ ነው የሚሆኑት:: አቃቤ ማለት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ነው:: አገልግሎቱን የሚሰጡ ብቻቸውን ነው:: በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ ሰይጣን ያገኛቸዋል ተብሎ የሚፈራው:: ይህቺ አክስቴም ተይ ብትባልም እምቢ ብላ መንኩሳ ገባች:: ገብታም ያንኑ የተለመደውን አገልግሎት መስጠት ጀመረች:: ሰይጣኑ አግኝቶ ያሳብዳታል የሚለው ስጋት መናፈስ ጀመረ::

ይሄ ነገር በልቦናቸው ውስጥ ስላለ ከዚያ በኋላ በበፊቱ አይናቸው አይደለም የሚረዷት:: ትክክለኛ ነገር ተናግራ ሁሉ እንደተሳሳተች አድርገው ነው የሚያወሩት:: ልክ እንደበፊቱ እያወራች ሳለ ከንፈራቸውን እየመጠጡ ‹‹በጤናዋ እኮ አይደለም!›› ይላሉ:: አልፎ አልፎ እኛ ቤት ትመጣለች፤ በተደጋጋሚ የምታዘበው ያንኑ የተዛባ አረዳዳቸውን ነው::

አንድ ቀን በጣም ተናደድኩና ከእናቴ ጋር ተጣላን:: ‹‹ለምንድነው እንዲህ ሲሏት ዝም የምትዪ? ጭራሽ አንችም እኮ አብረሽ እንደተሳሳተች ነው የሚመስልሽ! እስኪ ምን የተለየ ነገር አያችሁባት?›› እያልኩ ተቆጣሁ:: በአገራችንም በአካባቢያችንም ልማድ ልጅ አዋቂዎችን ስለማይመክር እኔኑ ተቆጡኝ:: ‹‹ወሬ ለምዶ!›› የሚል ቁጣ ነው የተረፈኝ:: ከዚያ በኋላ ያለኝ አማራጭ ውስጤ እየተናደደ መታዘብ ብቻ ሆነ!

አቃቤ መነኩሴ ከመሆኗ በፊት የምትሳሳታቸውን መደበኛ ስህተቶች እንኳን እንድትሳሳት ሊፈቅዱላት አልቻሉም:: ያንኑ የጠረጠሩትን ነገር ስለሆነች የምትሳሳት መሰለቻቸው:: ራሳቸው የሚሳሳቱትን ስህተት እንኳን እሷ ስትሳሳት አዕምሮዋ ስለተቃወመ ነው ብለው ራሳቸውን አሳመኑ:: ‹‹ዛሬ እሮብ ነው ወይስ ሐሙስ?›› ብላ ከጠየቀች አለቀላት:: አፋቸውን ይዘው ከንፈር መጠጣ ነው:: ራሳቸው እኮ እሮብ ቀን ሐሙስ ነው ብለው ብዙ ነገር ይሳሳታሉ፤ እሷ ግን ቢያንስ ጠይቃለች:: እንዲህ አይነት ከእሷ የባሰ ስህተት እየሰሩ እሷ ስትሳሳት ግን ያ የጠረጠሩት ነገር ነው ብለው ይደመድማሉ::

በዚያ ድርጊታቸው እኔ እናደድ የነበረው አንድን ሰው ደጋግመው እንደዚያ ካሉት ወደ እብደት ይሄዳል በሚል ፍርሃት ነው:: አንድን ጤነኛ ሰው ሁላችንም እየተረባረብን አብደኻል ካልነው የአዕምሮ መረበሽ ነው የሚያጋጥመው:: ‹‹የምርም ጤነኛ አይደለሁም እንዴ?›› ብሎ ማሰብ ይጀምራል:: መገለል ሲደርስበት የትኛውም ሰው ውስጡ ይረበሻል፤ የተናገረውን ሁሉ እንደ ስህተት ሲቆጥሩበት ልክ ያልሆነ መስሎ ነው የሚታየው::

የአገር ቤቱን ትዝብቴን ምናልባትም ያልተማረ ማህበረሰብ ውስጥ ስለሆነ ነው ብየ ነበር:: ዳሩ ግን የተማረ እና የሰለጠነ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ደግሞ ከዚህ የባሰ አስተዋልኩ:: እውነታው ሌላ ሆኖ ሳለ የሚያራግቡት ግን እነርሱ የሚፈልጉትን ነው:: ገጸ ባህሪውን ምሳሌ እንውሰድና፤ በስንቱ ሥራ የለቀቀው በራሱ ፈቃድ መሆኑን ቢያምኑም ተባረረ የሚባለው ወሬ የተሻለ ይጣፍጣቸዋል ማለት ነው:: እነዚህ ነገሮች ከአሉባልታ ልማድ የመጡ ናቸው::

እነዚህ ነገሮች ናቸው እየተንከባለሉ አድገው እንደ አገርም አደጋ የሆኑት:: ትንሽ ከተሰማ ያንን በእጥፍ ማጋነን ነው:: እንዲህ አይነቱን ነገር እናቴ ‹‹ወደቀ ሲሉ ተሰበረ›› ስትል እሰማት ነበር:: ወደቀ ሲሉ ተሰበረ አባባል ነው፤ እንዲህ የሚባሉትም አጋነው የሚናገሩ ሰዎችን ነው:: ለምሳሌ አንድ ሰው ቢወድቅና ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ቢነሳ እንደተሰበረ ተደርጎ ይወራል:: በዚህ ምሳሌነት የሆነ ነገር ሲሆን ጨመርመር ተደርጎ ይወራበታል::

አንዳንድ ጊዜ ማህበረሰባችን አሉባልታ ሲያናፍስ ነባራዊ ሁኔታዎችን እንኳን አያገናዝብም:: ይህን የሚገልጽልኝ ከአንደኛው የአቶ ልደቱ አያሌው መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ:: በአንዲት የኢትዮጵያ ከተማ ውስጥ (ደብረሲና መሰለችኝ) አንድ ተወዳጅ ምግብ ቤት ነበር:: ምግብ ቤቱን ተወዳጅ ያደረገው ጥሩ የዶሮ አሮስቶ ይሰራ ስለነበር ነው:: በዚህ ሥራውም የምግብ ቤቱ ባለቤት ጥሩ ገቢ ያገኛል::

በኋላ ግን መነሻው ምን እንደሆነ እና ማን እንደጀመረው የማይታወቅ አሉባልታ መነዛት ጀመረ:: ይሄውም ሰውየው እኮ የሚያቀርበው የዶሮ ሥጋ ሳይሆን የአሞራ ሥጋ ነው የሚል አሉባልታ በሰፊው መወራት ተጀመረ:: በሂደትም ገቢው ቀንሶ ምግብ ቤቱ እስከ መዘጋት ደረሰ::

ሰዎች ልብ ያላሉት ነገር ዶሮ በማርባትና አሞራ በማደን መካከል ያለውን ልዩነት ነው:: አሞራ በየዕለቱ ሊያገኝ አይችልም:: አሞራ ማደን ዶሮ ከማርባት በላይ ይከብዳል:: ሰውየውን ማመን ቢቀር ነባራዊ ሁኔታውን እንኳን ማገናዘብ አልቻሉም::

እንግዲህ የአሉባልታ ልማዳችን እንደዚህ ነው:: አንድን ነገር ደጋግሞ በማስወራት እውነት ማስመሰል ማለት ነው:: በእንዲህ አይነት ሁኔታ የግለሰቦችን ስምና ስብዕና ማበላሸት ማለት ነው:: በታዋቂ ሰዎች፣ በፖለቲከኞች (የአገር መሪዎችን ጨምሮ) ያላሉትን ነገር ብለዋል በማለት ልክ እንደ እውነት ተደርጎ ይወራል:: ለዚያ ነገር ግን ተጨባጭ መረጃ የለም:: ወይም የተናገረውን ነገር በማጣመም ወደቀ ሲሉ ተሰበረ የሚባለውን አይነት ማጋነን መጨመር ማለት ነው:: ሰውየው የተናገረበት ዓውድ ሲታይ ከተነዛው አሉባልታ ጋር በፍፁም የማይሄድ ማለት ነው:: በተለይም ለዚያ ሰው ጥላቻ ያላቸው አካላት እውነታውን ቢያውቁትም አዛብተው በሚፈልጉት መንገድ ይተርኩታል:: እየተደጋጋመ ሲሄድ እውነት ይመስላል ማለት ነው::

እንዲህ አይነት ነገር በሰዎች ልቦና ላይ መረበሽን ይፈጥራል:: ሰዎች ችግር ቢደርስባቸው እንኳን (ለምሳሌ አዕምሮውን ቢታመም) በጤነኛ ሰው ዓውድ በማውራት ወደ ጤነኛነት እንዲመለሱ ማድረግ እንጂ ከንፈር መምጠጥ ችግሩን ያባብስባቸዋል:: ወቀደ ሲባል ተሰበረ ከማለት የወደቀውን እናንሳ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *