ራስወርቅ ሙሉጌታ
አርብ ረፋድ ላይ ነበር የበዓሉ ድካም ከሥራ ጋር ተደርቦ ድብርት ስላስያዘኝ አምስት ሰዓት አካባቢ ሻይ ለመጠጣት ከቢሮዬ ወጥቼ አራት ኪሎ አደባባይ ስደርስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩሊቲ በኩል ትንሽዬ ግር ግር ብጤ ነገር አየሁ። ወደ አጀቡ እየቀረብኩ ስሄድ ምክንያቱ የመኪና አደጋ መሆኑን ከአልፎ ሂያጆች ሰማሁ። ወዲያውም የተገጨውን ልጅ አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ይዘውት ቢሄዱም የግጭቱ መነሻ የእኔ የሁልጊዜ ግምት ነበርና የዛሬ ብእሬን እንዳነሳ አነሳሳኝ። ወጣቱ የጎዳና ላይ ሸቀጦች ነጋዴ ሲሆን ለመኪና አደጋ ሊዳረግ የቻለውም ከደንብ አስከባሪዎች ሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር እንደነበር ከሚያለቅሱት ጓደኞቹና ከፊል ኀዘን ከተሰማቸው ሌሎች የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሰማሁ።
በሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ተጨናንቀው ከሚውሉት የአዲስ አበባ አደባባዮች መካከል መገናኛ አንዱ ነው። እኔ ደግሞ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ይህንን አደባባይ በተለይ እግር መረገጫ በሚጠፋበት ጠዋትና ማታ ላይ እየሰመጥኩ እወጣበታለሁ፡፡ እናም ሁልጊዜ በአራት ኪሎ የተከሰተው ዓይነት አደጋ ሊገጥም እንደሚችል ይሰማኝ ነበር። እኔ የምለው ግን ይህንን ችግር ጨርሶ ማስቀረት እንኳን ባይቻል በየቀኑ እየተባባሰና እየተስፋፋ ሲመጣ ለመገደብ ለመቆጣጠር ያልተቻለው ለምን ይሆን ?
በነገራችን ላይ በየቀኑ መገናኛ አደባባይ አካባቢ የማየው የድብብቆሽ ትእይንት ሁልጊዜ መልስ የማላገኝለትን ጥያቄ ሲያጭርብኝ ኖሯል። ረፋድ ላይ ከየመንደሩ ውስጥ የተጠቀለሉ ሸቀጦችን ይዘው ወደ አደባባዩ የሚቀላቀሉትን ወጣቶች ያየ ሰው ቦታው ለመንገድነት የተተወ ሳይሆን መደበኛ ገበያ የሚካሄድበት ነው የሚመስለው። እነዚህ ነጋዴዎች ከኤሌክትሮኒክስ ምርት እስከ አልባሳትና ከምግብ ቁሳቁስ እስከ የመዋቢያ ዕቃዎች በዓይነትና በብዛት መሀል መንገድ ላይ ዘርግተው ሲሸጡ ይውላሉ።
ታዲያ በየደቂቃዎች ልዩነት የደንብ አስከባሪዎች አልያም ፖሊሶች ሲደርሱባቸው ዕቃቸውን ተሸክመው መንገደኛውን ልጅ አዋቂ ሳይሉ እየገፈታተሩት ከሚርመሰመሱት መኪናዎች መካከል ገብተው ይወሸቃሉ። ይሄ ክስተት በተለይ ለመገናኛና ለሜክሲኮ አደባባዮች የቀን ከቀን ትእይንት ከሆነ ዓመታትን አሳልፏል። ታዲያ እነዚህ ሩጫዎች ሲካሄዱ ሁሌም ነገሮች ሁሉ በሰላም አይጠናቀቁም በአንድ ወገን ከላይ እንደጠቀስኩት ዓይነት የመኪና አደጋ ራሳቸው ሕገወጥ ነጋዴዎቹ ላይ እንዲደርስ የሚያደርግ ሲሆን እነሱም አነሰም በዛ እያንጠባጠቡት የሚሄዱትን ዕቃዎች ደንብ አስከባሪዎቹ ይወስዱባቸዋል። በተጨማሪ የእነሱ ጦስ ተሽከርካሪዎች ያለ ማስጠንቀቂያ ፍሬን እንዲይዙ ስለሚያደርጓቸው መኪናዎቹንም እርስ በእርስ እንዲጋጩ ያደርጓቸዋል። በዚህ አጋጣሚ ተገፍቶ የሚወድቀውም ሰው ሆነ ዕቃውን የሚጥለው ጭንቅላቱን እየወዘወዘ ከመሄድ ውጪ ምንም ሊያደርገው የሚችል ነገር አይኖርም።
ታዲያ ይሄ ግርግር ከየመንገዱ ዳርቻ ቆመው በተስፋ ለሚጠብቁትና ሲሳይ ለሚጥልላቸው ጩልሌዎች ትልቅ አጋጣሚ ነው። ሁል ጊዜም ፖሊሶች ወይንም ደንብ አስከባሪዎች ሲንቀሳቀሱ ሕገወጥ ነጋዴዎቹ ያላዩት እንዲያዩና ዕቃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያሰሟቸው ኮዶች ፉጨቶችና ጩኸቶች አካባቢውን ትንሽ ቀውስ የተፈጠረበት ከተማ ያስመስለዋል። ይህንን የግርግር አጋጣሚ በመጠቀምም በየዳርቻቸው ቆመው የነበሩት ሌቦች አብረው እየተሯሯጡ በየሰዉ ኪስና ቦርሳ ውስጥ በመግባት የሚደርሳቸውን ለመውሰድ መጣደፍ ይጀምራሉ። በግርግሩ ከመገፋት ራሱን ለመጠበቅ የሚደናበረውና አንዳንድ ጊዜም የተለየ ነገር የተፈጠረ መስሎት አካባቢውን የሚቃኘው መንገደኛ ሁሉ ደግሞ የሌቦቹ ሲሳይ ለመሆን ይበቃል ማለት ነው። ካለማጋነን አብዛኛዎቹ የአደባባይ ላይ ስርቆቶች የሚፈጸሙት በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታና ታክሲ ውስጥ ለመግባት በሚደረግ ግፊያ ወቅት ነው።
ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ እያደረሰ ያለውን ቀውስ አንድ በአንድ ዘርዝረን ብናይ የችግሩን አሳሳቢነት ለመረዳት ብሎም ለመፍትሄውም ለመረባረብ መነሻ የሚሆነን ይመስለኛል። ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በመጀመሪያ ደረጃ በሕጋዊ መንገድ በንግዱ የተሰማሩ ግብር ከፋይ ዜጎችን እየጎዳና ተስፋ እያስቆረጠ በመንግሥትም ላይ እምነት እንዲያጡ እያደረገ ሲሆን የከተማ ገጽታንም የሚያጠለሽ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ነው። በዋናነትም መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ቢነገዱ ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ እያሳጡትም ይገኛል።
እዚህ ላይ በርካታ ፋብሪካዎች እንዴት እንደ ሆነ ባይታወቅም ምርታቸው በስፋት በጎዳና ላይ ሲቸረቸር በሚመለከተው አካል ለምን ተብሎ መጠየቅ ያለበትም ይመስለኛል። ለምሳሌ በርካታ የጫማ ፋብሪካዎች በሕጋዊ መንገድ ግብር እየከፈሉ ሱቅ ከፍተው ሲሸጡ ከእነሱ ያልተናነሰ ምርት አምርተው ከክፍለ ሀገር ለመጡ ወጣቶች በማስረከብና በጎዳና ላይ በማስቸርቸር ሀብት እያጋበሱ ያሉት በርካቶች ናቸው።
እስከ ቅርብ ጊዜ በጎዳና ላይ የምናገኘው ምርት በተለምዶ ኮንትሮባድ የተያዘ ከጉምሩክ የወጣ ነበር የምንባለው። በጣም የሚገርመኝ ይሄ ሁሉ ሸቀጥ ኮንትሮባንድ የሚያዝ ከሆነ እንዴት ዋናዎቹ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች አይከስሩም? ካልከሰሩ ደግሞ ቢያንስ የተያዘባቸውን አስርና ከዚያ በላይ እጥፍ አስገብተው ያካክሱታል ማለት ነው። ልብ በሉ ይሄን ያህል ኮንትሮባንድ የሚገባ ከሆነ አልያም የሚሞከር ከሆነ የሀገራችን የሰላምና ጸጥታ ጉዳይስ እንዴት ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ምርቶቹ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ከሆነ ደግሞ ይህን ያህል አምራች መንግሥት የሚያመርተውን ሳያውቅ የሚሰራ ከሆነ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ ሕጋዊዎችን እየተጫነ እየተሹለከለኩ የሚሰሩ ሕገወጦችን እያፈረጠመ ነው ለማለት ያስደፍራል። ይሄ እንዲህ መንግሥትን በየግቢው በተሰሩ መጋዘኖችና ላስቲክ ለብሰው በቆሙ ሼዶች ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሚጠቁምም ይመስለኛል።
ወደቀደመው ነገር ልመለስና በጣም ግራ የሚያጋባኝና ሁሌም የሚያናድደኝ ደግሞ የደንብ አስከባሪዎችና የፖሊሶች ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ነው። ማንኛውም ሰው ሄዶ ቢመለከት ፖሊሶቹም ሆነ ደንብ አስከባሪዎቹ ከልባቸው ሕገወጥ የጎዳና ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚፈልጉ አይመስሉም። ይሄን እንድል ያስገደደኝን የራሴን ምልከታ እንደሚከተለው ላስፍርላችሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ በደንብ አስከባሪዎችም ሆነ በፖሊሶች በኩል ወጥ የሆነ ሥራ ሲሰራ አይታይም፡፡ አንዳንድ ቀን የደረሱባቸውን ሕገወጦች ሲይዟቸው ዕቃቸውን ነጥቀዋቸው ሲሄዱ እንመለከታለን ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝም ብለው መንገዱን እንዲለቁ ብቻ አባረዋቸው ሲመለሱ ይስተዋላል። አብዛኛውን ጊዜ ዳር ቆመው በርቀት እየተጨዋወቱ ሲመለከቱ ማየትም የተለመደ ነው። በጣም የሚገርመው፣ የሚያስደንቀውና የሚያበሳጨው ደግሞ ሕግ አስከባሪዎቹ እነዚህን ሕገወጥ ነጋዴዎች ሮጠው መያዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ማየት ነው። ልብ በሉ የተለያዩ ነገሮችን የሚዘረጉበትን ትልቅ ፌስታል ከነ ዕቃው አንጠልጥለው አልያም ተሸክመው የሚሮጡትን ወጣቶች ሴቶች ጭምር ሳይቀር አንድ በእጁ ዱላ ብቻ የያዘ የሕግ አስከባሪ አባሮ መያዝ አቃተው ማለት ምን ያህል አሳማኝ ሊሆን ይችላል?
ሌላው ነገር የእነዚህ ሕገወጥ ነጋዴዎች እንቅስቃሴ ግልጽና የሚታወቅ ነው። ጠዋት ያን ሁሉ ዕቃ ተሸክመው አደባባይ ወተው የእግረኛና የመኪና መተላለፊያ ዘግተው እስኪዘረጉ ድረስ ለምን ይጠበቃል? የደንብ አስከባሪዎቹም ሆነ ፖሊሶቹ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እነዚህ ቦታዎች ላይ ቀድመው በመገኘት ሳይጀምሩት ለማስቆም ለምን አይሞክሩም? የእኔ የዘወትር ጥያቄዎች ናቸው።
በቃ ጨዋታው ይሄ ስለሆነ በከተማዋ ባጠቃለይ የጎዳና ላይ ንግድ በሚገርም ፍጥነት እየተስፋፋ ሲሆን አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ደግሞ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ትምህርታቸውን ትተው አልያም ትምህርት ከሀብት በኋላ ብለው በመጡ ወጣቶች ነው። አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን መንግሥት ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ቢችል የእነዚህ ልጆች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ወይንስ መንግሥት አሁንም በየጥጋጥጉ ትንሽ ዳስ እየቀለሱ እንዲነግዱ እየፈቀደ ሊቀጥል ነው?
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእሳት ማጥፋት በመውጣት ችግሮችን ከመሰረቱ ማድረቅ እንደሚገባ ሁሉም የሚስማማበት ይመስለኛል። ታዲያ በቀን በቀን ያሁሉ ደንብ አስከባሪ በጠራራ ፀሐይ እየተሯሯጠ ከሚውል ለምን ዋናዎቹን የማደን ሥራ አይጀመርም። ለምሳሌ አንድ ወይንም ሁለት የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን በመያዝ ምርቱን ከየት እንዳመጡት በማጣራት እነዚያን ሕገወጥ ነጋዴዎች ቆንጠጥ የሚያደርግና የሚያስተምር ቅጣት መቅጣት። እግረ መንገድም ገቢዎች እያጣ ያለውን ገቢ እንዲያገኝ ማስቻል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለአንድ ሌሊት በተመሳሳይ ካለ ፈቃድ ብር እየተቀበሉ የመጋዘን ሥራ በየግቢያቸው የሚሰሩትንም አከራዮች ለጸጥታና ሰላምም አስጊ ስለሆነ ጎብኘት ማድረግ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል እኛም እንደ ማህበረሰብ የሞባይል ቻርጀር እንኳን ለመግዛት ዋጋው ስለሚቀንስልን ቀድመን የምንሄደው እዚያው ሕገወጦቹ ጋር ነው። በእርግጥ ተመሳሳይ ምርት በርካሽ እየተሸጠ ወደመደበኛው ሄዶ ጨምሮ መግዛት በሰውኛ አስቸጋሪ ውሳኔ ቢሆንም የወደፊት የከተማችንን ሰላምም ሆነ የእኛን ህልውና በማሰብ መክፈል ያለብንን ለመክፈል እንደ ሕዝብ መዘጋጀት ያለበን ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ግን ሕግ የማስከበር ሥራን ለሚሰሩት ሰዎች የምንመች መሆን አለብን አንዳንድ ሰዎች ለምን ያባርሯቸዋል ለምን ይነጥቋቸዋል እያሉ የሚሰነዝሩት አስተያየት ለነጋዴዎቹ የልብ ልብ የሚሰጥና በሥራው እንዲቀጥሉ የሚገፋፋ ብቻ ሳይሆን ትክክል ነን የሚል ስሜት ስለሚፈጠርባቸው ከሕግ አስከባሪዎችም ጋር ትንቅንቅ ውስጥ እንዲገቡ በር የሚከፍት ነው። ብንችል ባለን አቅም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ እየተጠቀምን መረጃ ማድረስ ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ። ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013