ሰሞኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ‹‹በፓርቲው ስብሰባ ላይ ተናገሩት›› ተብሎ በአማተር የሐሰት መረጃ አቀናባሪዎች የተዘጋጀ ድምጽ አዳምጠናል፤ አዳምጠንም ብዙ ታዝበናል። የሐሰት መረጃው ይፋ ከሆነ በኋላ በተመለከትናቸው ዓይነተ ብዙ ምላሾች አማካኝነት ደግሞ ብዙ ተዛዝበናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተናገሩት ተብሎ በሐሰት የተቀነባበረውና ‹‹ሾልኮ ወጣ›› የተባለው ድምጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ወቅቶች ከተናገሯቸው ሃሳቦች ተለቅመው በቅንብር የተሰራ ድምጽ ነው። ድምፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከሰጡት ማብራሪያ፣ የክልሎች የምርጫ ዝግጅትን በሚመለከት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ካደረጉት ውይይት እንዲሁም በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ካቀረቡት ሃሳብ የተወሰዱ ሃሳቦቻቸውን በእነ ቆርጦ ቀጥሎች በመቆራረጥና በመገጣጠም የተሰራ ‹‹የልጅ ጨዋታ›› ዓይነት ተግባር ነው።
መረጃው የሞኝ ቀልድ ነበር። ‹‹የሞኝ ቀልድ›› ያልኩበት ምክንያት ምንም ዓይነት የድምጽ ቅንብር ባለሙያ ሳያስፈልግ መረጃው ከተለያዩ ንግግሮች ተቆራርጦ የተቀጣጠለ መሆኑን በቀላሉ ማወቅ እየተቻለ እንኳ ‹‹ከባድ መረጃ ነው … አደገኛ መረጃ ነው … ብዙ ምስጢር የያዘ መረጃ ነው …›› የሚል ማስታወቂያና ማጠናከሪያ ሲሰራለት ስለነበርና ይፋ ከተደረገ በኋላም ‹‹ … በመረጃው እውነተኛነት ላይ ጥርጣሬ አይግባችሁ … ›› የሚል ድርቅ ያለ ‹‹ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ›› ዓይነት ተራ ዘመቻ ስለተመለከትን ነው።
የመረጃውን ይፋ መሆን ተከትሎ ዜጎች የተለያዩ አስተሳሰቦችንና አቋሞችን አንፀባርቀዋል። በአንድ በኩል የመረጃውን ሐሰተኛነት የኮነኑ ወገኖች እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እጅግ አሳፋሪና ፋይዳ ቢስ እንደሆነ ሲገልፁ፤የመረጃውን ሐሰተኛነት በቀላሉ ማረጋገጥ እየተቻለ እንኳ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነት አቋም የያዙ ሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖች ደግሞ በተቃራኒ ወገን ሆነው ‹‹መረጃው ትክክል ነው›› የሚል የጅል ጨዋታ ይዘው ተመልክተናል።
ይበልጥ የሚገርመውም መረጃው የሐሰት ስለመሆኑ ብዙ ጥናትና ማጣሪያ እንደማያስፈልገው በግልጽና በቀላሉ እየታወቀም የመረጃውን ሐሰትነት መቀበል ያልፈለጉት ግለሰቦችና ቡድኖች ጉዳይ ነው። እነዚህ ወገኖች ‹‹ሾልኮ ወጣ›› የተባለው የሐሰት መረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መድረኮች ከተናገሯቸው ንግግሮች የተወሰዱና የተቀናበረ እንደሆነ የተቀናበረውን ድምጽ ለመስራት ግብዓት የሆኑትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች እየተመለከቱ እንኳ የመረጃውን ሐሰትነት ማመን አልፈለጉም። እንዲያው ሌላው ሁሉ ይቅርና አቀናባሪዎቹና የውሸት መረጃቸውን ያመኑላቸው አካላት፤ የፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባን በፓርላማ አባላት ጭብጨባ በማጀብ አቀናብሮ መስራት እጅግ የበዛ የሞኝ ሥራ እንደሆነ አላወቁም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ብልጽግና ፓርቲም መረጃው ሐሰት ስለመሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ይህን የሃሰት መረጃ ያሰራጩ አካላት ዓላማ ህዝብን ማሳሳት፣ ማደናገር፣ የሕዝብን አብሮ የመኖርና የመቻቻል እንዲሁም የአንድነት ስሜት መጉዳት መሆኑን አስረድተዋል። በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን ለመሸርሸር እንዲሁም የሕዝብና የመንግሥትን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተሰራጨው መረጃ ላይ በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የተነሱ ጉዳዮች አለመኖራቸውንና የተሰራጨውም መረጃ መሰረተ ቢስ አደናጋሪ የሐሰት መረጃ መሆኑንም ጠቁመዋል። ‹‹ … ሰሞኑን ኃላፊነት በጎደላቸው ሃሰተኛ የመረጃ ምንጮች አማካኝነት ‹የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባን አስመልክቶ ከሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ ሾልኮ የወጣ ነው› የሚልና በሀሰተኛ የመረጃ ምንጮችና ሚዲያዎች እየተላለፈ የሚገኘው ድምጽ ፍጹም ሃሰት የሆነ፤ ምንም አይነት መሰረት የሌለው፤ የሥራ አስፈፃሚው ስብሰባ ከእነዚያ ድምጾች ውስጥ አንድም የሚገናኝ ቃል የሌለው፤ በተለያዩ ወቅቶች የፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ካደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ የተወሰዱ ቃላትን ቆርጦ በመቀጣጠልና በመገጣጠም ትርጉም የሚሰጥ አረፍተ ነገር እንዲመስል በማድረግ ሕዝብን ለማደናገር የተሞከረ እጅግ በጣም እኩይና አደገኛ ተግባር ነው …›› ብለዋል።
ሐሰተኛ መረጃዎችን የማቀናበርና የመቀበል ድርጊት በብዙ ምክንያቶች ይፈፀማል። የጭፍን ጥላቻና ጭፍን ተቃውሞ እሳቤ/ድርጊት ሰለባ መሆን (ኢ-ምክንያታዊነት) ከምክንያቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው። በተለይም የተቀነባበረው የሐሰት መረጃ ሐሰተኛነቱ እየታወቀና ሐሰት ስለመሆኑም በቂ ማስረጃዎች ከቀረቡ በኋላም እንኳ መረጃው ሐሰት መሆኑን ማመን ያልፈለጉ ወገኖች ድርጊታቸው እነዚህ የጭፍን ጥላቻና ጭፍን ተቃውሞ እሳቤ/ድርጊት ሰለባ ስለመሆናቸውና ኢ-ምክንያታዊነት እንደተፀናወታቸው ማሳያ ነው። ችግሩ እንደቀላል የሚታይ ስላልሆነ በጉዳዩ ላይ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ይገባል።
የማኅበረሰብ ጥናትና የስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ መነሻቸው ስሜት እንጂ ምክንያት አይደለም። ስሜት የሚገፋቸው ሰዎች ለመደገፍም ይሁን ለመቃወም ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት ነገር ሃሳብን፣ ርዕዮተ ዓለምን፣ የማስፈፀም ብቃትን ወይም ክሂሎትን አይደለም። እንዲህ ዓይት ሰዎች የድጋፋቸው ወይም የተቃውሟቸው ምክንያት ሃሳብ ወይም ተግባር ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም የሚያነሳሳቸው ሃሳቡን ያመነጨው ሰው ማንነት ሲሆን ይስተዋላል። የተፈፀመው ድርጊት የቱንም ያህል በጎ አልያም መጥፎ ቢሆንም በጭፍን ከመደገፍና ከመቃወም ወደ ኋላ አይሉም።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ የመኖር አኩሪ ታሪክ ቢኖራቸውም ይህ ድንቅ መስተጋብር ግን በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ምክንያታዊ እሳቤን መፍጠር አልቻለም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ለጭፍን ድጋፍና ለጭፍን ተቃውሞ የሚመች ነው። በቅንነት የሚመክርና የሚተች እንዲሁም ከስህተት የሚገስጽ ሰው/ቡድን እንደጠላት ይቆጠራል። ለእውነት መታመን፣ ጥፋቶች እንዲታረሙ በቅንነትና በምክንያታዊነት ተቀናቃኝን ያለ ጥላቻ መተቸት ‹‹የድክመትና የፍርሃት ምልክት›› ተደርጎ ይታያል። ለአገርና ለወገን የሚበጅ ግሩም ሃሳብ ያላቸው ወገኖች በጭፍን ጥላቻና ተቃውሞ ምክንያት ድምፃቸው እንዲታፈን ተደርጓል። በጭፍን ጥላቻና ድጋፍ ምክንያት አገሪቱ ብዙ እድሎችን አባክናለች። በአጠቃላይ ኋላ ቀሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅኝት ለምክንያታዊነት አይመችም።
ይህ የምክንያታዊነት መንጠፍ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘመናት ብዙ ዋጋዎችን እንድትከፍል አድርጓታል። ጭፍን ተቃውሞና ጭፍን ድጋፍ አገሪቱ ያገኘቻቸውን የለውጥ እድሎች በሚገባ እንዳትጠቀምባቸው መሰናክል ሆነውባታል።
ይህ የኢ-ምክንያታዊነት አስተሳሰብ ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ዋጋ እያስከፈለን ዛሬ ላይ ደርሷል። ‹‹ማን አለ?›› እንጂ ‹‹ምን አለ?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠትን ትኩረት ነፍገነዋል። በቂ ባልሆነ ምክንያትና ማገናዘብ የታጀበው የድጋፍና የተቃውሞ ባህላችን እንደ አገር ያገኘናቸው በርካታ የለውጥ እድሎች እንዲከሽፉ አድርጓል። ይህም አገራችን መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
ይበልጥ የሚያስገርመውና ግራ የሚያጋባው ነገር ደግሞ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን አደገኛ ተግባራችን ዛሬም ትምህርት ለመውሰድና ለመሻሻል አለመሞከራችን ነው። አሁናዊ ሁኔታችን ከወቅታዊ ነባራዊው የዓለም ሁኔታ ጋር ተደምሮ የትናንቱን የሚያስመሰግን እንደሆነ ትናንትናን ኖረው ያለፉና ዛሬም ያሉ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ትናንት ዋጋ ያስከፈለን አስተሳሰባችንና ተግባራችን ዛሬ መሻሻል ሲገባው ከትናንት የባሰ ከሆነ በነገሩ ተስፋ መቁረጥ ብዙም ላያስገርም ይችላል።
ይህ ነገሮችን በቅጡ ሳይገነዘቡ የመደገፍና የመቃወም አባዜ ኅብረተሰባዊ መለያችን ለመሆን እየተቃረበ መምጣቱ ከትዝብት አልፎ ጭንቀትን የሚፈጥር ነው። ምክንያታዊ አስተሳሰብ እየቀጨጨና አወንታዊ አክቲቪዝምም ተዳክሞ ቦታውን ለሐሰተኛ ጽንፈኛ ቅስቀሳና ንቅናቄ እየለቀቀ መሄዱ እንደ አገር እስካሁን ካስከፈለን ዋጋ ወደፊት የበለጠ ሊያስከፍለን እንደሚችልም ጠቋሚ ነው።
አንድ ማኅበረሰብ የማያቋርጥና አዎንታዊ የሆነ ለውጥና መሻሻል የሚያስመዘግበው ምክንያታዊ አስተሳሰብን ሲያዳብር ነው። ምክንያታዊ አስተሳሰብን ያላሰፈነ ማኅበረሰብ ጉዞው የኋልዮሽ ጉዞ እንጂ የመሻሻልና አወንታዊ ለውጥ የማስመዝገብ ሊሆን አይችልም።
ምክንያታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ከቤተሰብ ይጀምራል። ኅብረተሰብን በስነ ምግባር መግራትና ማነፅ እንዲሁም የእውነትን መንገድ እንዲከተል መምከር ለምክንያታዊ እሳቤ መስረፅ ትልቅ ግብዓት በመሆኑ ስነ ምግባርን ማስተማር ዋና ሥራቸው የሆኑት የሃይማኖት ተቋማት ለእሳቤው መስረፅን ጉልህ አስተዋፅኦ አላቸው።
መገናኛ ብዙኃን በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰው ተደራሽ የመሆን እድል/ባሕርይ አላቸው። ይህን እድል በመጠቀም ስለምክንያታዊ እሳቤ ማስተማር ትልቅ ኃላፊነታቸው ሊሆን ይገባል። ምክንያታዊ አስተሳሰብን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ መቅረፅንና ማስተማርንም ችላ ማለት አይገባም።
አክቲቪዝምም (እኛ አገር ሲደርስ ጉድ ሆነ እንጂ በታደሉት አገራት “አክቲቪዝም” የማህበረሰብ አንቂነት” ሚናን መጫወት፤ “አክቲቪስት” ደግሞ “የማህበረሰብ አንቂ” ማለት ነበር) ቢሆን የራሱ ዓላማ ቢኖረውም ምክንያታዊነት ያልታከለበት አክቲቪዝምና እንዲህ ዓይነቱ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ፍትሀዊ/ተገቢ ምክንያት ያላቸውን ጉዳዮች ትኩረት እንዲነፈጋቸውና ውሃ እንዲበላቸው ማድረጉ አይቀርም።
የጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰቦች ምንጭ የሆኑት ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ በምክንያታዊ የሐሳብ የበላይነት እስካልተሸነፉና እንደ ሕዝብ/ማኅበረሰብ ነገሮችን ሰከን ብለን የመመርመር ባህል እስካላዳበርን ድረስ፣ በተሳሳቱ መንገዶች ደግመን ደጋግመን ጥፋት ውስጥ እንደምንመለስና ችግር ውስጥ እንደምንቆይ እርግጠኛ ሆኖ ለመናር ብዙም አያዳግትም። እንደማኅበረሰብ የተጠናወተን የጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ አባዜ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ለውጥ ውጤት አልባ ያደርገዋል። ኢ-ምክንያታዊ ድጋፍና ተቃውሞ የለውጥ ፀር መሆናቸውንም ልንገነዘብ ይገባል!
መጪው ጊዜ የምርጫ ወቅት መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል። በምርጫ ወቅቶች የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እጅግ ይበዛል። ሰከን ብሎ ማሰብና ማመዛዘን ካልተቻለ ሐሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ሂደት ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው። ሐሰተኛ መረጃዎች መራጮች በአጠቃላይ ዜጎች ስለእጩዎች፣ ስለመንግሥትም ሆነ ስለህብረተሰባቸው ትክክለኛ መረጃ እንዳይኖራቸው የማድረግ አደጋን ያስከትላሉ። በሴንትራል ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ (University of Central Florida) የስነ ልቡና መምህር የሆኑት ዶክተር ክሪሳሊስ ራይት ሐሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ወቅት ያላቸው ተፅዕኖ ከሌሎች ጊዜያት የጎላ እንደሚሆን ዩኒቨርሲቲያቸው ያደረገውን ጥናት በመጥቀስ አስረድተዋል። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች ከሐሰተኛ መረጃዎች ሁሉ ቅድሚያ እንደሚይዙም ጠቁመዋል። ስለሆነም ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያዎች ቀዳሚ የመረጃ ምንጮቻችሁ ሊሆኑ አይገባም›› በማለት አጥብቀው መክረዋል።
እነዚህ አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ሲያሻቸው ‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር››፣ ሲፈልጉ ‹‹ዲያስፖራ››፣ ሌላ ጊዜ ‹‹አክቲቪስት››፣ ‹‹ጋዜጠኛ … ነን›› የሚሉ አካላት ናቸው። ይባስ ብሎም በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ያሉ ‹‹የሹም ዶሮዎች›› ሆነው ይገኛሉ። በእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ግንዛቤ መሰረት መረጃን ከእነርሱ በስተቀር የሚያውቅ ሌላ ግለሰብ የለም፤ የምስጢራዊ መረጃዎች ባለቤቶች፣ የመረጃዎቹ ተንታኞችና የመረጃዎቹን ውጤት ወሳኞች እነርሱ ናቸው፤‹‹ከውስጥ ሰው የደረሰን ነው› በማስባልም ከደህንነት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ያስወራሉ፤ መረጃው ሐሰት እንደሆነ እየታወቀ እንኳ ‹‹እውነት ነው›› ብለው ድርቅ የሚሉ አስገራሚ ፍጡራን ናቸው።
እነዚህ አካላት እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን የሚያሰራጩባቸው የራሳቸው ምክንያቶች ቢኖሯቸውም አንድ የማይካድ ሃቅ ግን አለ፤ ይኸውም ከሌሎች በተቀበሉትም ይሁን በራሳቸው ፍላጎት፣ አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ የሕዝብን መብትና ደህንነት አደጋ ላይ መጣላቸው ነው።
ከማኅበራዊ ሚዲያዎች አማራጭ መስፋትና የግልና የቡድን ጥቅማቸውን ማሳካት ከሚፈልጉ ወገኖች ፍላጎት ውስብስብነት አንፃር የሐሰተኛ መረጃዎች መበራከት የሚጠበቅ ቢሆንም ከዚህ ቀደምም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የጣሉና ማን እንዳሰራጫቸው በግልጽ የታወቁ ሐሰተኛ መረጃዎች ሲነገሩ ተመልክተናል። በተለይ በጥር ወር 2013 ዓ.ም ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጤንነትና የደህንነት ሁኔታ የተሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ የሚረሳ አይደለም። ይሁን እንጂ እነዚያን የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች በግልፅ እየታወቁ ሳለ ሰዎቹ የንጹሃንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችሉ መረጃዎችን ሲያሰራጩ እንኳንስ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይቅርና ኮስተር ባለ ዓይን ያያቸው አንድም የመንግሥት አካል አለመኖሩንም ታዝበናል። መረጃ አሰራጭዎቹን አደብ የሚያስገዛቸው አካል አለመኖሩን ተመልክተንም ‹‹… እንዲህ ዓይነቱን መረጃ እንዲናገሩ/እንዲጽፉ ተልዕኮ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል አለ እንዴ?›› ወደሚል ግምታዊ ጥያቄም አምርተን ነበር።
መንግሥት የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እጅግ አደገኛ የሐሰት መረጃዎች ሲሰራጩ ዝምታን መምረጡ የሚያስገርምና ተስፋ የሚያስቀርጥ ቢሆንም ሕዝቡም የራሱ ኃላፊነት አለበት። የመረጃዎቹን ምንጮች ታማኝነት መገምገም፣ ምንጮቹ ከዚህ ቀደም ስለነበራቸው ልምድ/ታሪክ ማጣራት፣ የመረጃዎቹ ዓላማዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰላሰል፣ የታወቀ የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እስከሚሰጥ ድረስ መረጃዎቹን ለሌሎች አለማጋራት፤ እንዲሁም አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረግ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው። እነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች ሐሰተኛ መረጃዎቹ ሊፈጥሩ የሚችሏቸውን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይችሉ እንኳ አደጋዎቹን ለመቀነስ ግን ያስችላሉ። በተጨማሪም ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት በሐሰት መረጃ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል!!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013