ኃይለማርያም ወንድሙ
በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ገጻችን በዚህ ዘመን ህዝቡ ገንዘብ እያዋጣ የልማት ስራዎችን እንደሚሰራው ሁሉ በ19 ተመሳሳይ ስራዎች ይሰሩ እንደነበር የሚያመለክቱ ዘገባዎች ይዘን ቀርበናል፡፡ ይህም ለልማት መሰባሰብና ገንዘብ ማዋጣት ሕዝቡ ቀደም ሲል ሲተገብረው እንደነበረ የሚያስረዳ ነው፡፡ ሌሎች ሊነበቡ የሚችሉ ዘገባዎችንም አካተን ይዘን ቀርበናል ፡፡
ነቀምቴዎች ለወንበር
መግዣ ፰ ሺ ብር አዋጡ
ነቀምቴ (ኢ.ዜ.አ) በነቀምቴ ከተማ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት አዲስ ለመዘገባቸው ፯፻፳፩ ተማሪዎች መቀመጫ ስለታጣ ወላጆች ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ፰ ሺ ብር ለማዋጣት ተስማሙ፡፡ በዕለቱም ስብሰባ ፬፻፶ ብር ተሰብስቦ ገቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ቀደም ብሎ ፬፻፶ ብር መዋጣቱ ተገልጧል፡፡ ወይዘሮ አስናቀች በረደድ የተባሉትም ሴት ከወላጆች ጋር ካዋጡት ሌላ በ፴፭ ብር መቀመጫ ገዝተው ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም ወላጆች ባደረጉት ስብሰባ፤ የወላጆች ኮሚቴ መርጠዋል፡፡
(መስከረም 8 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
በሲዳሞ ጠ.ግዛት ለልማትና ለትምህርት ቤት ገንዘብ ይዋጣል
ይርጋለም በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት የሸበዲኖ ወረዳ ሕዝብ በስዊድን መንግሥት የርዳታ ጓድ ጋር በመተባበር በ68000 የ፩ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማሠራት ባቀደው መሠረት ከሚያዋጣው 34000 ላይ 2000 አዋጣ፡፡ የቀረውንም ገንዘብ እስከ አንድ ወር ድረስ ጨርሶ እንደሚከፍል አቶ አጥናፉ ከበደ ገለጡ፡፡
ከዚህም በስተቀር በዚሁ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በጀምጀም አውራጃ የቅዶ ቫስኬቶ ትምህርት ቤትን ለማስፋፋት በታሰበው መሠረት ሐጂ ኢብራሂም እስማኤል ከአሁን በፊት ከለገሱት 50 ብር ሌላ በተጨማሪ የ 77.ከ10 ሣንቲም ዕቃ ሰጡ፡፡ ፪ኛ ድሆች ተማሪዎችን በሥራቸው በማስተማር ላይ መሆናቸውን የትምህርት ቤቱ ተጠባባቂ ዲሬክተር አቶ ደሳለኝ ሞጣሎ አስረዱ፡፡
የአለታ ወንዶ ወረዳ ሕዝብ ደግሞ ለልማት ሥራ የሚያዋጣውን ገንዘብ ቀጥሎ 385 ብር አዋጣ፡፡ እስከዛሬም ለልማት ሥራ 73 268ከ12 ሣንቲም ያዋጣ መሆኑን የወረዳው ዋና ጸሐፊ አቶ ከበደ ገብረየስ ገለጡ፡፡
(ጥቅምት 10 19 60 የወጣው አዲስ ዘመን)
የአዳባ ሕዝብ ለ30ሺ ብር ቃል ገባ
አዳባ (ኢ.ዜ.አ)በባሌ ጠ.ግዛት የአዳባ ወረዳ ግዛት ሕዝብ ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና የጤና ጣቢያ ለማሠራት ባላባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ውይይት አድርገው 30ሺ ብር ለማዋጣት ተስማማ፡፡
ከዚህም ገንዘብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግራዝማች ወልደ ማርያም በድሉ ፩፻ ብር፤ አቶ ዓለሙ ገለቱ ፩፻ ብር አቶ ተፈራ ዱባለ ፩፻ ብር፤ በድምሩ ፫፻ ብር በዕለቱ ስብሰባ ገቢ መሆኑን የወረዳው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ተፈራ ዱባለ ገለጡ፡፡
(ጥቅምት 12 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
ያጠመዱት ገደላቸው
ሐረር (ኢ-ዜ-አ) በጋራ ሙለታ አውራጃ ሞጆ በተባለው ቀበሌ ሁለት ሰዎች አንበሳ ለመግደል ጥይት አቀባብለው ባጠመዱት ጠብመንጃ ሁለቱም ሞቱ፡፡ አሊ ተሌና ከለፍ ከቢራ፤ የመጀመሪያው ሰው በሬ በአንበሳ ስለተበላ አንበሳውን ለመግደል ወጥመድ አበጁ፡፡ አንድ ጠመንጃ ከጫካ ወስደው ካቀባበሉ በኋላ፤ በአፈሙዙ ላይ ሥጋ አደረጉ በማግሥቱ ሔደው ቢመለከቱት ሥጋው የለም፡፡ አንበሳውም ስላልተገደለ ምናልባት ጠመንጃው ከሽፎ ይሆናል በማለት አሊ ቱሌ ከጠመንጃው አፈሙዝ በኩል ሆኖ ምላጩን ነካው፡፡ ከዚያም የተቀባበለው ጥይት ባርቆ አሊን አቆሰለው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላም ሞተ። ከሊፍ ከቢራ ደግሞ በአጠገቡ ስለነበረ ጥይቱ ተፈናጥሮ ሆዱን ስለመታው ለመሞት በቅቷል ሲሉ የጋራ ሙለታ አውራጃ ዋና ጸሐፊ ባላምባራስ ለማ ወንድም አገኘሁ አስረዱ፡፡
(ጥቅምት 12 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
፲ ዓመት እንጨት የተፈለጠበት
ቦምብ ፈነዳ
ደብረማርቆስ፤ (ኢ.ዜ.አ) በሞጣ አውራጃ ገንገርታ ማርያም ቀበሌ ዘመረ ተፈራና ሽፈራው ዘመረ የተባሉትን አባትና ልጆች የወደቀ ቦምብ ፈንድቶ አቆሰላቸው፡፡
ዘመረ ከአሥር ዓመት በፊት ይህን ፈንጂ ከዱር አግኝቶ እቤቱ ከወሰደ በኋላ የእንጨት መፍለጫ አድርጎ ሲጠቀምበት መቆየቱ ታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ጥቅምት ፮ ቀን በዚሁ ብረት ሲቀጠቅጥ ከቆየ በኋላ ፈንድቶ አባትና ልጁን ሊያቆስላቸው ችሏል፡፡ ቦንቡ ከፈነዳ በኋላ ፍንጣሪው ፬፻፶ ብር ግምት ያለው የቆርቆሮ ክዳን ገነጣጥሏል፡፡
(ጥቅምት 10 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013