አስናቀ ፀጋዬ
በሀገሪቱ እየተከሰቱ ካሉ የአካባቢ ችግሮች የመሬት መራቆት፣ የአፈር መከላት፣ የብዝሃ ህይወት ሃብት መመናመን፣ የከርስ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ መቀነስ እንዲሁም የስርዓተ ምህዳር ግልጋሎት መዛባት የመሳሰሉት ከደን ሃብት መመናመን ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገሪቱን የደን ሃብት ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተደረገው ጥረት የሚያረካና ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። ለዚህም ህብረተሰቡን የሚያሳትፍና ነባር እውቀቱን የሚጠቀም የደን አስተዳደር ስርአት አለመኖር እንደ ዋና ምክንያት እንደሚጠቀስ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ሆኖም ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርአትን በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች በመዘርጋት የደን ጥበቃና እንክብካቤ መካሄድ እንደተጀመረና ከለውጡ ወዲህ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብርን በመተግበር የተመናመነውን የደን ሽፋን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
ደን በስፋት ከሚገኝባቸው የሀገሪቷ ክልሎች ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ክልል ሲሆን በክልሉ በተለይ የተፈጥሮ ደን በስፋት ይገኝባቸዋል ተብለው ከተለዩ ቦታዎች ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ስር የሚገኘው የኢሉአባቦራ ዞን በዋናነት ይጠቀሳል።
በዚህ ዞን ሰፊ የተፈጥሮ ደን ክምችት ቢኖርም የደኑ ይዞታ ከአርሶ አደሮችና አልሚ ባለሃብቶች በሚገባ ተለይቶ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ የተደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ ይነገራል።
በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የኢሉአባቦራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አማረች ክፍሌ እንደሚገልፁት፤ በዞኑ በአብዛኛው የሚገኘው የተፈጥሮ ደን ሲሆን በሰው የተተከለውን ሁለት ሺ ሄክታር ደን ጨምሮ ከ646 ሺህ ሄክታር በላይ ይጠጋል።
በአሁኑ ወቅትም ደኑ በአብዛኛው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጥበቃ እየተደረገለት የሚገኝ ሲሆን በተለይ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ
አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርአትን ተግባራዊ በማድረግና ደኑን ህብረተሰቡ በባለቤትነት ይዞ እንዲጠብቅ እየተደረገ ነው። በተለይ ሞኖ ወሰሌ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ የሚገኘውና 251ሺ ሄክታር ስፋት ያለው ሰፊ ደን ሙሉ በሙሉ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እየተጠበቀ ይገኛል።
በዚህ ደን ውስጥ አርሶ አደሩ ቡና በማብቀልና በንብ ማነብ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ደኑን ማልማት፣ መጠቀምና ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲያካሄዱ ተደርጓል። በሌሎች ወረዳዎች ላይም 69 ለሚጠጉ የተደራጁ ማህበራት ደኖቹ ተላልፈውላቸው እየተንከባከቡ እንዲያለሙበት ተፈቅዷል።
የተፈጥሮ ደኖች በስፋት በሚገኙባቸው ሌሎች ሰባት ወረዳዎችም ስራው በስፋት እየተሰራበት ይገኛል። ፅህፈት ቤቱም ከሌሎች የመንግስት አካላት ጋር በመሆንና ያሉትን ችግሮች በመለየት በህግና ተቀራርቦ በመነጋገር እንዲፈቱ ጥረት እያደረገ ነው።
እንደ ሃላፊዋ ገለፃ ፅህፈት ቤቱ በደን ውስጥ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን አርሶ አደሮቹ ደኑን በምን መልኩ መጠበቅ፣ ማልማትና መጠቀም የሚችሉበት የውል ስምምነትም ፈጥሯል።
በውል ስምምነቱ መሰረት ደኑን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ በደኑ ውስጥ የሚገኙ የደን ውጤቶችን ወደገበያ አውጥተው እንዲቀርቡ እንዲሁም ደኑ በተመናመነባቸው አካባቢዎች እንዴት ማልማት እንዳለባቸው ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣቸዋል።
በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችም በማህበራት ተደራጅተው የራሳቸውን ምርት ጥራቱን በጠበቀና ገበያው በሚፈልገው መልኩ እንዲያቀርቡ ከፅህፈት ቤቱ ጋር የሚሰሩ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቴክኒክና ሙያዊ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
አርሶ አደሩ እጁን ከደኑ ሰብስቦ በራሱ ማሳ ላይ አምርቶ የሚያገኝበትን ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
ከዚህም በፊት ከነበረው ሁኔታ በተሻለ ህብረተሰቡ ከደኑ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል። የራሳቸውን ወፍጮ ቤት የከፈቱና የጭነት መኪናም የገዙ ማህበራት አሉ። እነዚሁ መንግስታዊ ድርጅቶች በነዚህ የተደራጁ ማህበራት ላይ በመስራታቸው ብዙም ያልታወቀው የኢሉአባቦራ የተፈጥሮ ቡናም ሁለተኛ ደረጃ የመሆን እድል አግኝቶ ማህበራቱን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ሃላፊዋ እንደሚሉት ከዚሁ የኢሉአባቦራ ዞን የተፈጥሮና በሰው የተተከሉ የደን ሃብቶች ጋር በተያያዘ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደኑ የተከለለ ቢሆንም የተከለለው ደን መሆኑ በቦርድ ኮሚቴ አለመፅደቁ ሲሆን ከለላው ቢፀድቅ ምን ያህል አርሶ አደር በደኑ ውስጥ ገብቶ እየተጠቀመ እንዳለ መለየትና ከደኑም በአግባቡ ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ ይቻል ነበር።
ሆኖም አርሶ አደሩ ደኑን እንዲጠቀም ስምምነትና ፍቃድ ስላልተሰጠው አልፎ አልፎ የደን መመናመን ይታያል። ይህም ሊሆን የቻለው የደን ከለላው በቦርድ ኮሚቴ ባለመፅደቁ ነው። ይህም ገና በሂደት ላይ ያለና በቅርብ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በማይገባባቸውና ጥብቅ በሆኑ የደኑ አካባቢዎች ቡና አልሚዎች ያለፈቃድ የመግባት ችግርና በህብረተሰቡ በኩልም አልሚዎቹን ለህግ እንዳይቀርቡ የመደበቀ ችግር ይታያል።
ይህም በሂደት ደኑን ሊያመናምነውና ሊያራቁተው ይችላል። ለዚህም ይህን የሚያሰራው አካል በቅርበት ያለመከታተል ችግር መሆኑ በምክንያትንት ይጠቃሳል። በህብረተሰቡም በኩል የራሱን ደን ከመትከል ይልቅ ወደ ደኑ በመሄድ ቡና የመትከል አዝማሚያዎች ይታያሉ። ይህም ደኑን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፉ ጉዳይ ላይ ስጋት ሆኗል።
እነዚህን ችግሮች ከመቅረፍ አኳያም ከዞኑና ከወረዳዎቹ አስተዳደሮች ጋር በመሆን በደኑ አካባቢ ከፍተኛ ችግር እንዳለና ሁሉም በዚሁ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተሉ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ወይም ቡና በደን ውስጥ ያለፈቃድ ከመተከሉ በፊት ግንዛቤ እንዲሰጥና ቦታው ተጠንቶ እንዲጣራ ንግግር እየተካሄደም ነው።
ችግሮቹ በሚታዩባቸው ቦታዎች ላይም ደኑ ውስጥ የገቡ አርሶ አደሮች ግንዛቤ ተሰጥቷቸው እንዲወጡ እምቢ ያሉትን ደግሞ ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህም ሂደት አብዛኛዎቹን ለህግ ማቅረብ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013
Read more about Gynecomastia Surgery Insurance here priligy 30mg price