ተገኝ ብሩ
ዛሬ ታመመ ያልነውን ብሶበታል ህክምና ያሻዋል ያልነውን መውጋታችንን ቀጥለናል። የምንወጋው ጦር አይደለም፤ የምንሰብቀው ሳንጃ አይደለም። ስህተትን በመንገር ጥራዝ ነጠቅነትን በማመልከት የሚታረምበትን መንገድ መጠቆም እንጂ። አዎን በመድፌያችን ስህተቶችን ጠቁመን ከትክክለኛ መስመር የሚወጡትን እየወጋጋን ከህመማቸው የሚወጡበትን መንገድ እንጠቁማለን። ታክሲዎች የአብዛኛዎቹ ገጠመኞቻችን መነሻ፤የጉዟችን መናገሻ ናቸውና እነሱ ላይ ያየነውን ስህተት አመልክተን ከህመማቸው ይፈወሱ ዘንድ ወጋ ወጋ ልናደርጋቸው ወደድን።
የታሪፍ ጭማሪ፣ ትርፍ መጫን፣ አዳዲስ የሚወጡ ህግና ስርዓቶች መጣስ፣ተሳፋሪን ማመናጨቅ፣በአጠቃላይ ህግና ስርዓትን መጣስ ደንብን አለማክበር ላይ ስማቸው የሚነሳ ከታክሲዎች ያያለ መጓጓዣ ሌላ አለ? እንጃ! በዚህች ሰፊ አገር ሰፋፊ የህግ መጣስ ተግባራት ቢስተዋሉም፣ የከተሜው ዋንኛ አጋዥ የሠርቶ አዳሪው አድራሽ መላሽ የሆኑት ታክሲዎች በህግ መጣስ ብዙ ይታማሉ። በተለይም ሚኒባስ ታክሲዎች።
ባንፈልግም ከእርነሱ ጋር መገናኘት ግድ ይለናልተገኝ ብሩ ባንወድም በጣሱት ህግ ስንበደል፣በተላለፉት ደንብ ስንጎዳ ከርመናል። “ታሪፉ ይሄን ያህል ነው ትርፍ አልከፍልም” ስንል “ክፈል ካልሆነ ውረድ፤ እንደውም በአቋራጭ ነው የሚሄደው አንተን አላሳፍርህም” ይሉናል። መሀል ከተማ ላይ ህግና ስርዓት አስከባሪ በየመንገዱ ቆሞ በሚታይበት ኃላፊነት የተሰጣቸው ተራ አስከባሪዎች ቆመው ገንዘብ በሚቀበሉባቸው አደባባዮች ጭምር ነው ይሄን እያደረጉ ያሉት።
እዚህ ላይ ተሳፋሪም አለ ለመብቱ ሲቆረቆር የተመለከቱት ተሳፋሪ “አሁን ለአንድ ብር ነው የምትከራከረው እኛ እንከፍልልሀልን።” ብለው መብቱን በጠየቀ ለምን መብትህን ጠየክ ስለምንስ ትከራከራለህ የሚል የህገወጦቹ አጋዥ ሆኖ ያርፈዋል። እንደዚህ ዓይነቱ መብቱን ተነጥቆ እያየ በግዴለሽነት አልፎ ይባስ ብሎ ህግ ለማስከበር የሚጥረውን የሚወርፍ የስርዓት አልባ ተባባሪ ሆኖ ሲታይ ይገርማል።
የታክሲ ታሪፍ የዛኔ ኮሮና እንደገባ ማሯሯጥ ሲጀምረን፤ የምናደርገውና የምንሆነው ባሳጣን ሰሞን ታክሲዎች የተሳፋሪ ቁጥር በ1/2ኛ ቀንሰው እንዲጭኑ ታሪፉ ደግሞ እጥፍ እንዲሆን ተወስኖ ነበር። አብዛኞቹ ይህን አድርገውትም ነበር። በእርግጥ ህጉን ላክብር ብለው ሳይሆን የዛኔ ጠንከር ያለ ዕርምጃውን ፈርተው ተሳፋሪውም ከቤት አልወጣ ብሎ ከመሳፈር መታቀቡ፤ የወጣውም ህጉን ሳይሆን ኮሮናን ፈርቶ አይሆንም ይላቸው ነበር።
ከሁኔታዎች መቀያየር በኋላ ኮሮና ቀንሶ ሳይሆን ይበልጥ ሲሰፋ የሰው ቁጥር ጨምራችሁ ጫኑ። ዋጋውም ወደነበረበት ይመለስ ነገር ግን የመጨረሻው ወንበር 3 ሰው ብቻ አድርጉ ለዚህ ደግሞ ከተሳፋሪው ላይ መጠነኛ ጭማሪ አድርጉ የሚል ህግ ወጥቶ ተግብሩ ተባሉ። ምን ዋጋ አለው ይሄን ደንብ ለመጣስ ከአንድ ሳምንት በላይ አልፈጀባቸውም። 3 አደርጉ የተባሉት አራት ሰው ባለ ሁለት ሰው መቀመጫ ደግሞ በሰው ላይ ሰው መደራረባቸውን አልተውም።
የኮሮና ሰሞን ታሪፍ መቀበል አሁንም የቀጠሉበት ረዳቶች አሁን በየታክሲው ላይ አሉ። መልስ ስጠኝ ተብሎ ካልተለመነ እንደ አገልግሎት ሰጪ እንካችሁ ብሎ የሚሰጥ አልፎ አልፎ ነው የሚገኝ። አንዳንዴም መልስ ስጥኝ ሲሉት የሚገረምም ከዚያም አልፎ ለፀብ የሚጋበዝም አይጠፋም። ኧረ በህግ ተው ረዳቶች ተሳፋሪ ከሌለ የእናንተ ሥራ የለም እኮ ደንበኞቻችሁን አክብሩ እንጂ፤ ተው።
እነዚህ የሚኒባስ ታክሲዎች የሚጥሱት ህግና ደንብ ከላይ የዘረዘርኩት ብቻ አይደለም፤ ሌላም ጉድ አለ። በትራፊክ አደጋ በአፍሪካ ከፊት በደረጃ የሆነችው አገራችን ለትራፊክ አደጋው መቀነስ መፍትሔ ይሆናል የምትለውን ደንብና ስርዓት አውጥታ ብትተገብርም አልተሳካላትም። የሚወጡ ህጎች ይጣሳሉ፤ በዚያም ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እንደ ዋዛ ይቀጠፋል። እነዚህም ታክሲዎች ህግን ጥሰው ተሳፋሪና ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡበት ዕድል ሰፊ ነው።
ከተሽከርካሪው ፊት ለፊት (ጋቢና) የሚቀመጥ ተሳፋሪ የደህንነት ቀበቶ እንዲያጠልቅ ግዴታ ተጥሎበታል። የአብዛኛዎቹ ታክሲዎቻችን ቀበቶዎች ግን በትክክል የሚሠሩና አደጋውን የሚከላከሉ አይደሉም። አደጋ ከፊት ቢከሰት ተሳፋሪው ላይ ጉዳት እንዳይከሰት ከማድረግ ይልቅ አዘናግተው የባሰ ጥፋት የሚያደርሱ ናቸው። ከፊት ወንበር (ጋቢና) የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች ከአሽከርካሪው ውጪ ማለቴ ነው ብዙውን ጊዜ ሁለት ናቸው። ነገር ግን በበር በኩል ያለው እንጂ መሃል ላይ የሚቀመጠው ተሳፋሪ ቀበቶ አጥልቅ የሚለው ማን ነው። የሚያጠልቀውስ ቀበቶስ የታለ። አንዱን አድርግ ለዚያውም የማይሠራ ቀበቶ ሌላኛውን ተው ይሆናል? ጎበዝ። ኧረ ተው ልክ አይደለም።
ለማስመሰል ተሳፋሪው እንዲያደርግ የታዘዘውን ማስክ ትራፊክ እነሱን እንዳይቀጣ ብቻ ተሳፋሪውን ሲገባ ሳይሆን እንዲያደርግ የሚነግሩ ሹፌርና ረዳቶች በየታክሲው ይገጥሙናል። የህዝቡ ጤና መሆን አለመሆን ቁብ አይሰጣቸውም እነሱ የሚያገኙት ገቢ ከፍ ማለት እንጂ የደንበኞቻቸው ምቾት ማጣት አልያም ለበሽታ መዳረግ ምን አገባኝ ባይ ናቸው።
ታክሲዎቹ ስርዓትና ደንብ ጥሰው መመሪያን ተላልፈው ጉዟቸውን እንዳሻቸው እያደረጉ ቀጥለዋል። ህግ ከተጣሰ፤ ስርዓት ከተናደ ልክነት ብሎም አግባብነት ይነጥፋል። ስርዓት አልበኝነት ነግሦ፣ መተዳደሪያው ተገርስሶ፣ ልቁ ተወድሶ እውነት ይልከሰከሳል፤ የሚታይ ልክነት ይጠፋል። አገር እና ህዝብ ምሶሶ ያጣል። ያለ ህግና ደንብ ተግባር ውል ለሌለው መጨረሻ ያደርሳል።
የወጣውን ህግና ደንብ ቢያከብሩና በተፈቀደላቸው መሰረት ቢሠሩ ግን ምን ይሆን የሚጎልባቸው። ብር አይደል የሚጎልባቸው። ተገቢውን ገቢ እስኪ በተገቢው መንገድ ሠርተው ያገኛሉ። ትርፉን ካላጋበስኩ፤በግድ ከእጃችሁ ካልመተረፍኩ ይባላል። ህግ ስትጥሡ አንድ ህግ አስከባሪ ቢገጥማችሁ የምታወጡት ወጪ ከዚያ በግድ ከምትሰበስቡት ሰዎችን አንገላታችሁ ከምትቀበሉት እጅጉን ይልቃል ፤ አናስላ እንጂ ጎበዝ። ትርፍን ሰብስቦ ይበልጥ ከማጉደል የሚገባን ይዞ በሰላም ስለሰላም ወደፊት መንዳት አያዋጣም ትላላችሁ? እኔ ያዋጣል ባይ ነኝ። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013