ማህሌት አብዱል
የተወለዱት አዲስ አበባ በቀድሞው ስሙ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ነው። ያደጉት ደግሞ ሰንጋ ተራ አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት። በመቀጠልም በልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 11ኛ ክፍል ተምረዋል። ይሁንና 11ኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ስር ለነበረው የመምህራን ማስልጠኛ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን ለመመልመል ሲባል በተቋቋመው በዕደ ማርያም መሰናዶ ትምህርት ክፍል ገብተው ለአንድ ዓመት ሰለጠኑ። ዩኒቨርሲቲው ያወጣውን ፈተናም አልፈው ትምህርት ክፍሉን ተቀላቀሉ። ይሁንና ብዙም ሳይቆዩ በሚሰጠው ትምህርት ደስተኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ከዚያ ይልቅም የቢዝነስ ትምህርቶችን የመማር ፍላጎት አድሮባቸው የዝውውር ጥያቄ ለትምህርት ክፍሉ ያቀርባሉ። ነገር ግን ዝውውሩን ለማድረግ የሚያስፈልገውን 550 ብር ለመክፈል ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
ግና እድል ፊቷን አላዞረችባቸውም። ብዙም ሳይቆዩ በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አየር ሃይል በአብራሪነት መቀጠር ለሚፈልጉ ተማሪዎች በወጣው ማስታወቂያ ላይ ተመዘገቡ። ውድድሩን አልፈውም በአየር ሃይሉ ተቀጠሩ። ለሁለት ዓመታት ከሰለጠኑ በኋላ በአየር ሃይሉ ድጋፍ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የሶስተኛ እና አራተኛ ዓመት የኒቪርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
በቢዝነስ ዲግሪያቸውን ያዙ። በአየር ሃይል ሁለት ዓመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ አብዮቱ ሲፈነዳ የደርግ መንግስት የለውጥ ሃዋሪያ ሆነው ብሔራዊ ባንክ ተመደቡ። ባንኩ በሚያስተዳድራቸው ባንኮች ሁሉ የደርግ ተጠሪ ሆነው ለአራት ዓመታት አገለገሉ። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ቡና ገበያ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ። ይሁንና ከሶስት ወራት በኋላ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ።
በኮርፖሬሽኑ በአመራርነት ባገለገሉባቸው 13 ዓመታት ለድርጅቱ ስኬት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው የሚነገርላቸው እኚሁ ሰው ታዲያ በስሩ የነበረውን የቡና ገበያ እስፖርት ክለብ ከማደራጀት ጀምሮ አሁን ለደረሰበት ገናና ዝና እና ተወዳጅነት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ ይጠቀሳል። ክለቡን በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው እንደገዛ ልጃቸው ያሳደጉት እኚሁ የአገር ባለውለታ ታዲያ በተለይም በአገሪቱ የእግር ኳስ እድገት የማይናቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ይህም በስፖርቱ ቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ከበሬታን አስገኝቶላቸዋል።
በሌላ በኩል ግን ከደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት ጀምሮ ያለፈው ሥርዓትን በገንዘብ ትደጉም ነበር በሚል ተደጋጋሚ እስርና ከስራ መባረር የደረሰባቸው ሲሆን በተለይም አማልጋሜትድ በተባለው የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጠረው በሚሰሩበት ወቅት አሁን ድረስ ተገቢውን መልስ ማግኘት ባልቻሉበት ሁኔታ ለአራት ዓመት ከዘጠኝ ወር ታስረው ለእንግልት ተደርገውም ነበር። ይህ ብቻ አይደለም፤ የክለባቸው ደጋፊዎች በሜዳ ውስጥ በሚያደርጉት አተካራና በሚፈጥሩት ፀብ ሳይቀር ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ታስረው የከፋ እንግልት አጋጥሟቸውም ነበር። እኚህ ታላቅ የስፖርት አባት ታዲያ ይህንና ሌሎችንም የህይወት ገጠመኞቻቸውን በመጽሐፍ መልክ ከትበው ለአንባቢ ለማቅረብ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣም የዛሬው የዘመን እንግዳ አደርጓቸዋል። ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት ከመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– የቡና ገበያ ስፖርት ክለብ አመሰራረት ምን እንደሚመስል ያስታውሱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– ክለቡ ቡና ገበያ ከመባሉ በፊት የንጋት ኮከብ እየተባለ ነበር የሚጠራው። የስም ቅያሬው የመጣው ክለቡ በኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ተነሳሽነትና መንግስትም በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ከወሰነ በኋላ ነው። በሶስተኛ ዲቪዚዮን ይጫወት የነበረውን ይኸው ክለብ በተለይም በሰራተኛው ጥረት ስያሜውን ወደ ቡና ገበያ የእግር ኳስ ቡድን ከመቀየር ባለፈ በአገሪቱ ስመጥርና ጠንካራ ቡድኖች መካከል እንዲሰለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። በተጨማሪም ክለቡን በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ውስጥ የከተተው የኢትዮጵያ መንግስት የክለቦችን አደረጃጀትን መለወጥ አለብኝ በሚል በመወሰኑና ሁሉም ክለቦች በመንግስት ስር እንዲታቀፉ በማድረጉ ነው።
በዚያ መሰረት ክለቡ የቦርዱ ሰራተኞች በሚያደርጉለት ድጎማ እየተጠናከረ መጣ። አመሰራረቱ ይህንን ይመስላል።
አዲስ ዘመን፡- ከኮርፖሬሽኑ የወጡበት አጋጣሚ ምን ነበር?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡- በ1983 ዓ.ም ህወሓት ይዞት በመጣው የነጻ ገበያ ስርዓት ምክንያት ድርጅቱ እንዲፈርስ በመደረጉ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ለደርግ መንግስት ትደግፍ ነበር በሚል ለሶስት ሳምንታት ታስሬ ነበር። ከዚያም በኋላ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈለገ ሲያስረኝ ነበር። ፓርቲ ውስጥ እንድገባ ቢጠይቁኝም አሻፈረኝ በማለቴ በህወሓት አመራሮች ጥርስ ተነከሰብኝ። በዚህ ምክንያት ከቡና ኮርፖሬሽን እንድለቅ ተደረኩኝ። ኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ኩባንያ ገባሁኝ። ለአራት ዓመታት የሽያጭና ማከፋፊያ ክፍል ዳይሬክተር ሆኜ ሰራሁኝ።
በነገራችን ላይ በኩባንያው እየሰራሁኝ ሳለሁም ድርጅቱ ከመንግስት ጋር በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ ገብቶ ታስሬ ነበር። በተለይም ከማዳበሪያ ሽያጭ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር። በወቅቱ ታዲያ ለእርሻ የሚሆኑ ማዳበሪያና ኬሚካል የመሳሰሉትን ግብዓቶች በብዛት በማስመጣት ለገበሬው እናከፋፍል ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ገበሬ የሚያመርተውን ስንዴና በቆሎ መግዛት ጀመርን። የመንግስት ካድሬዎች ይህንን ሲያዩ እንደአስጊ ድርጅት ቆጠሩት። ስለዚህ ምክንያት እየተፈለገ ከድርጅቱ ጋር በየጊዜው ጭቅጭቅ ይፈጠር ነበር። ይህን ተገን አድርገውም እኔን አሰሩኝ።
አዲስ ዘመን፡– ምን የተለየ ወንጀል ሰርተው ነው ለእስር ተዳርገው የነበሩት?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– ምንም የሰራሁት ወንጀል አልተገኘብኝም ነበር። የሚገርምሽ አንድም ቀን ፍርድ ቤት ሳልቀርብ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር ነው በወህኒ ቤት ያቆዩኝ። የታሰርኩበት አጋጣሚም እሰራበት የነበረው አማልጋሚትድ ኩባንያ ለሩዋንዳ 10ሺ ቶን በቆሎ ለማቅረብ ጨረታ ላይ ተወዳደረና አሸነፈ። ይህንን በቆሎ በመንግስት እርሻ ድርጅት ቦርድ ጋር በመሆን ገዛን።
ርክክብ ሳናደርግ ግን የእርሻ ሰብል ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ያንን ሁሉ በቆሎ በኪራይ ካስቀመጥንበት እርሻ ሰብል መጋዘን በአስቸኳይ እንድናስወጣ ትዕዛዝ ሰጡ። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለአገር ሊያስገኝ የሚችለውን ይህንን ሽያጭ መንግስት ከማበረታታትና ከመደገፍ ፈንታ እንደወንጀለኛ ያዋክበን ጀመር።
ከዚህም ባሻገር ትላልቅ የእርሻ ድርጅቶች ደግሞ የገቡትን ኮንትራት አናከብርም አሉ። ስለዚህ ያቺን አስር ሺ ቶን ለማግኘት የድርጅቱ ባለቤት አቶ ገብረየስ በጣም ጎበዝ ሰው ስለነበሩ ተሯሩጠው ዛምቢያ በቆሎ ለመግዛት ይሄዳሉ። እኔ ደግሞ ከኬኒያ ለመግዛት ልሄድ ስል ኢሚግሬሽን ትፈለጋለህ ብሎ አሰረኝ። በዚያ ሁኔታ ያለምንም ክስ ነው እንግዲህ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር የታሰርኩት። ከዚያ በፊትም እንዲሁ ሰበብ ፈልገው አስረውኝ ነበር። በኋላ ደግሞ በኳስ ምክንያት አስረውኛል።
አዲስ ዘመን፡– በኳስ ምክንያት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– እንደምታውቂው የቡና ደጋፊ በአብዛኛው ወጣት ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ በስሜታዊነት የሚፈጠሩ ችግሮች አይጠፉም። አንድ ጊዜ ከሐዋሳ ከነማ ጋር ስንጫወት መለስተኛ ረብሻ ይነሳል። በማግስቱ ጠርተው አሰሩኝ። በዚህ ወቅትም አንድ ወር ከሁለት ሳምንት አሰሩኝ። እናም ደጋፊ ለደጋፊ በፈጠረው ፀብ እኔን አሰሩኝ።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ከሚታወቁበት ጉዳዮች አንዱ በቡና ስፖርት ክለብ መውደቅ መነሳት ለረጅም ዓመታት በፅናት ተስፋ ሳይቆርጡ ክለቡን ሲደግፉ መቆየትዎ ነው። እንዳው ለመሆኑ የፅናትዎ ሚስጥር ምንድን ነው?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– ምን መሰለሽ፤ በተለይም ክለቡን ከንጋት ኮከብ ወደ ቡና ገበያ ካዛወርንበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ሃላፊነት ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ ነበርኩኝ። በወቅቱ ደግሞ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ስለነበርኩኝ ሰራተኛው በሙሉ በእኔ ላይ ነበር ሃላፊነቱን የጣለው። በመሆኑም ድርጅቱ ሲፈርስ ዝም ብሎ ማለፍ አላስችል አለኝ።
ከመንግስት ባለቤትነት ሲወጣ የክለቡ ህልውና ተጠብቆ የሚቀጥልበትን ነገር ከብዙ ሰዎች ጋር በመሆን እያፈላለግን ነው የቆየነው። ክለቡ በቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ይደገፍ ነበር። እኔ ደግሞ በስራ አጋጣሚ ቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ጋር ቅርበት ስለነበረኝ ለማቀርብላቸው ጥያቅ በጎ ምላሽ ነበር የሚሰጡኝ። እናም በእኔ እምነት በእነሱ ዘንድ የነበረኝ ተቀባይነት ለክለቡ ቀጣይነት አስተዋፅኦ ያደረገ ይመስለኛል። ጥሩ ውጤት አምጥቶልናል።
ስለዚህ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ክለቡን ይዤ በፅናት እንድቀጥል ምክንያት የሆነኝ ያለኝ ቁርጠኝነት ነው ብዬ ነው የማምነው። ከዚያ ውጭ ምንም ሚስጥር የለውም። ከዚያ በኋላም ሀበሻ ቢራ ስፖንሰር ሆኖ መጣ። ቡና ባንክም ስፖንሰር ሆኗል። አሁን ደግሞ ቤቲካ የሚባል ድርጅት ስፖንሰር እሆናለሁ ነው። በአጠቃይ ሁላችንም ክለቡን በቁርጠኝነት እዚህ አድርሰነዋል።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለረጅም ዓመታት ተቀናቃኝ የሆኑ ቡድኖች ናቸው። የእነዚህ ክለቦች አመራሮች ሜዳ ውስጥ ካላቸው ባላንጣነት ባሻገር ከሜዳ ውጭ ወዳጆች እንደሆናችሁ ይነሳል። ለዚህ ደግ የእርስዎ በጎ አስተዋፅኦ እንዳለበት ይጠቀሳል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ቢያስረዱን?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– ሲጀመር ቡና ወደ እግር ኳሱ ሲገባ ብዙ ትላልቅ ክለቦች ነበሩ። ለምሳሌ መቻሬ፣ ኤልፓ፣ ኦሜድላና ጊዮርጊስ ነበሩ። እኛ በወቅቱ ወደ ጨዋታው የገባነው 51ኛ ሆነን የነበረ ቢሆንም የአቅም ክፍተት ስለነበረብን ወረድን። በዚህ ምክንያት የቡና ማኔጅመንት ቦርድ ተሰበሰበና ቁጭ ብለን ተወያየን። ከዚያም ክለቡን ለማጠናከር ወሰንን። ያን ጊዜ ደግሞ ከእግር ኳስ ባሻገር በአምስት የስፖርት ዘርፎች መወዳደር ይጠበቅብናል። እንዳልኩሽ፣ ማኔጅመንቱ ተወያየና ስማችን ከተጠራ አይቀር ተበላሽቶ መቅረት የለበትም የሚል ድምዳሜ ያዝን።
እናም የተሟላ ሃይል ይዘን ለመግባት ተዘጋጀን። የነበሩንን የእግር ኳስ ተጫዋቾችና አሰልጣኝ ቀየርን። በአትሌቲክሱም፤ በወንድም፤ በሴትም ከመቼውም በላይ ተጠናክረን ድንቅ ብቃት ያላቸውን ቡድኖች ይዘን መጣን። በእግር ኳሱ በኩል የአዲስ አበባ ተመልካች አይቶት የማያውቀው ብቃት አሳየን። ትላልቆቹን ቡድኖችን ሳይቀር በሰፊ የጎላ ልዩነት ስናሸንፍ ስማችን ገነነ። በዚህ ምክንያት በመቻሬና በጊዮርጊስ መካከል የነበረው የደርቢ ስሜት በጊዮርጊስና በቡና መካከል ሆነ።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ፌደሬሽኑ ለእኛ አዲስ ነው። ፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉ ተመራጮች ለጊዮርጊስ ወይም ደግሞ ለመቻሬ ነበር የሚያደሉት። በተለይም ሜዳ ላይ የሚሰጡትን ፍትሃዊ ያልሆነ ዳኝነት ተመልካቹ በግልፅ ያይ ስለነበር ለእኛ ድጋፉን ይሰጥ ጀመር።
እኛም ያለምንም ፍርሃት ችግሮችን ስንጋፈጥ ቆይተናል። ነገር ግን ከግጭት ይልቅ ተመካክሮ መስራት ጥቅም አለው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን። የእኛም ሆነ የጊዮርጊስ አመራሮች ተመካክሮ መስራቱ ለኳሱ እድገት ይበልጥ ይጠቅማል የሚል እምነት ያዝን። ከግጭቱ ምንም ውጤት አይገኝም በሚል ወደ ትብብርና ምክክር መጣን። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ሜዳ ላይ እነሱ ለእኛ፤ እኛም ለእነሱ አንተኛም።
አዲስ ዘመን፡– ጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወቅት እንደመሆኑ እስቲ በእርስዎ ጊዜ የነበረውን የበዓል አከባበር ሂደት ምን እንሚመስል ያስታውሱን? እግረ መንገዶንም የልጅነት ህልሞ ምን እንደነበር ይግለፁልን?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– በቀጥታ እንዲህ እሆናለሁ የሚል ምኞት አልነበረኝም። ነገር ግን የተወለድንበት አካባቢ የድሮ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ስለነበር አውሮፕላን ሲነሳና ሲያርፍ የማየት እድሉ ስለነበረን ፓይለት የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። በአብዛኛው ልጅ ግን እኔን ጨምሮ ትምህርቱ ስኬታማ ለመሆን ነበር ጥረት ያደርግ የነበረው። ሰከንደሪ በጥሼ የሚል ምኞት ነበረን። ምክንያቱም ሰከንደሪ ከበጠሽ ኮሌጅ የመግባት እድሉ አለሽ። ያንን ህልሜን አሳክቻለሁኝ።
ወደ ሌላኛው ጥያቄሽ ሳልፍ እኔ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ጥምቀትም ሆነ የመስቀል በዓል ልዩ ድባብ ነበረው። እጅግ በጣም የተከበረና ህዝቡ ሁሉ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ ወጥቶ የሚጨፍርበት የተለየ ድምቀት ነበረው። ሁሉም እንደባህሉና ቋንቋው ይጨፍራል፤ ይጫወታል። ምን አልባትም አልፎ አልፎ አንዱ የያዛትን ሴት የተመኘ እንደሆነ ግጭት ሊነሳ ይችላል።
ይሁንና አሁን ላይ እንደመጣው በብሄርና በጎሳ የተነሳ ምንም አይነት ግጭት ተነስቶ አያውቅም። ሌላው ይቅርና ቦርዲንግ ትምህርት ቤት ስንገባ ከተለያዩ አካባቢዎች ተመልምለን ቢሆንም አንዳችን የአንዳችን ብሄር አሳስቦን አያውቅም። ሲጀመርም ሰው መሆናችን እንጂ ስለብሄራችን ምንነት አንጠይቅም ነበር፤ ነውርም ጭምር ነው። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ተቀይሯል። ሁሉም በጎሳው ጉያ የሚጠለልና ሌላውን እንደባዕድ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህንን ሳይ በጣም ነው የማዝነው።
አዲስ ዘመን፡– በዚሁ አጋጣሚ እስቲ የህወሓት መራሹን የኢህአዴግ መንግስት 27 ዓመታት አመራር በእርስዎ እይታ ምን እንደሚመስል ይግለፁልን?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– እንደ አጠቃላይ እነዚያ 27 ዓመታት በኢኮኖሚው፤ በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ ኑራችን ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰው ያለፉ፤ የባከኑ ጊዜያት ናቸው። በተለይም በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሚባል አደጋና ጉዳት ተከስቷል ባይ ነኝ። የተገበሩት ፖሊሲ ለሚፈልጉት ወገን ብቻ የሚያደላ ስርዓት የፈጠረና አድሏዊ ነበር። እንደእኔ ግምት እንዳውም እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ ፕራይፔታይዜሽን ያልጀመሩት ለራሳቸው ጥቅም ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንዲረዳቸው ነው። የሚገዛውም፤ የሚሸጠውም ነገር በቁጥጥራቸው ስር እስከሚያስገቡት ድረስ ነው። ውሎ ሲያድር በኢኮኖሚው ላይ ያሳረፉት አሉታዊ ተፅእኖ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ሁላችንም የዚህ ችግር ሰለባ ነበርን። ምክንያቱም ዛሬ ድረስ ለመፍታት አዳጋች የሆነ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ነው ያደረሱት።
በተጨማሪም የሃብትና የኢኮኖሚ ክፍፍሉ ፍትሃዊ አልነበረም። ከሁሉ በላይ ግን ትልቅ ጉዳይ በዘርና በጎሳ ህዝባችን ከፋፍሎ ህብረት እንዳይኖረው ማድረጉ ነው። አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በኢትዮጵያ ቀርቶ በዓለም ላይ እንኳን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነፍሰጡሮችንና ሕፃናትን ሳይቀር የሚያርድበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ይህንን ስታዪ በሰው ልጅ ላይ ምን አይነት ጭካኔ ሊደርስ ይችላል? ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ አይገባውም ነበር። ለሶስት ሺ ዓመታት የራሱን ባህልና ስልጣኔ ያዳበረ፤ ተቻችሎ የኖረ፤ ጥንታዊ ታሪክና ቅርሶች ባለቤት የሆነ ህዝብ በዚህ ደረጃ እርስ በርስ በዘር ተከፋፍሎ እየተጫረሰ ለዓለም መጥፎ ገፅታውን የሚያላብስበት ሁኔታ መፈጠር አልነበረበትም።
የቀደሙት አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሱት፤ አጥንታቸውን የከሰከሱላት አገር ዛሬ ላይ በሚያሳፍር ሁኔታ በድንበር ተከፋፍለን እርስበርስ በጠላትነት እየተጠባበቅን መኖር ከልብ ያሳዝነኛል። እናም ህወሓት ሲሰራ የኖረው አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር ፈፅሞ የማይግባባትና በጠላትነት የሚተያይባት አገር ለመፍጠር ነው።
ለነገሩ ድሮም ጀምሮ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ነው የምንሰጣችሁ ሲሉን እኛ አልገባንም እንጂ። ቀድሞውንም ይህንን ለመፍጠር ነበር አልመው የተነሱት። አሁን ላይ በየቦታው አንዱ አራጅ ሌላው ታራጅ ሆኖ ሥታዪ ምን ያህል ቁልቁል ወርደን እንዳለ ለመገመት ያዳግትሻል። እናም ከዚህ ለመውጣት ከባድ ፈተና ይጠብቀናል። አሁን ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትሽን እንኳን እንድትጠይ የሚያደርግሽ ነው።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት በጁንታው አባላት ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ እንዴት ያዩታል?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– ይህንን ጥያቄ መመለስ የምፈልገው እንደ አንድ ሃይማኖተኛ እና ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው። ህወሓቶች ስልጣናቸውን ከተነጠቁ በኋላ ኢትዮጵያን ለዘላለም እኛ ብቻ ነን መግዛት ያለብን በሚል በራሳቸው ኩርፊያ ይዘው ነው ወደ መቀሌ የሄዱት። በምክርም ሆነ በልመና ሊመለሱ አልቻሉም። እንደምታስታውሽው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እዛ ድረስ ሄደው ሊያስታርቁ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በዘረፋችሁት አትጠየቁም የያዛችሁትን ይዛችሁ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በሰላም ኑሩ ቢባሉም አሻፈረኝ ማለታቸው ነው።
ግን በእብሪት አብደው ስለነበር በየቦታው እሳት እየለኮሱ የሰው ደም ሲያፈሱ ነው የቆዩት። የህዝቡ እንባና ደም እግዚአብሄር ደጃፍ ደርሶ ኖሮ ፈጣሪ በሰፈሩት ቁና እንዲሰፈሩ አደረጋቸው። ለእኔ ይህ የሆነው በፈጣሪ ሃይል እንጂ በሰው አይደለም። በነገራችን ላይ እብሪት የሚመጣው ራስሽን ከመርሳት ጭምር ነው። የሌለሽን ነገር እንዳለሽ አድርገሽ በመቁጠር የምትንቀሳቀሺ ከሆነ የማትወጪው ችግር ውስጥ ነው የሚጥልሽ።
ይህ ደግሞ ልክ እንደ ጎሊያድ እነሱም ባላቸው መሳሪያ ክምችት የጦር ሰራዊትና የገንዘብ አቅም ተማምነው ብዙ ታበዩ። በሶስት ቀን አዲስ አበባ እንገባለን የሚል ትዕቢታዊ ውሳኔ ወስነው ነው ወደዚህ የገቡት። የህወሓት ጁንታዎች ያመናቸውን ወታደር እና ንፁህ ዜጋ ሲያርዱና ሲገድሉ የነበሩት ጎሊያድያዊ በሆነ እብሪት ተነስተው ነው።
ውጤቱ ግን እንዳሰቡት ቀላል አልሆነላቸውም። የተከበረው የመከላከያ ሰራዊታችን ድል ነስቷቸዋል። አሁን እነዚህን ወንጀለኞች አድኖ የመያዝና ለህግ አሳልፎ የመስጠት ተግባር ነው። በመውደቂያቸው መባቻ መሰረተ ልማቶችን በሙሉ ያወደሙትም የትግራይ ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ በማለም ነው። ግን የኢትዮጵያ አምላክ ድጋፍ እነዚህን የሰላምና የአንድነት ጠንቆች ማስወገድ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ አሁን ላይ በመንግስት ሊፈታ ይገባል የሚሉት መሰረታዊ ችግር ካለ ያንሱልኝና ውይይታችን በዚህ እናብቃ?
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– የእኔ ትልቁ ስጋት የተረኝነት አዝማሚያ እንዳይመጣ ነው። ከመጣ እንደገና ሌላ ውድቀት ነው የሚሆነው። ሁለተኛው ደግሞ አሁን ያለው ህገ መንግስትን ይዛ ከቀጠለች አሁን የተከሰተው ችግር በእጅጉ አይሎ እንዳይመጣ ነው። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ይህን ያረጀ ያፈጀ ህገ መንግስት ይዛ መቀጠል አትችልም። ምክንያቱም አስቀድሜ እንደገለጽኩልሽ በዚህ ህገ መንግስት ምክንያት ኢትዮጵያዊነት በዳር በድንበር እየተከለለ ብዙ ፈተና ውስጥ ወድቀን ነው የቆየነው። ነገ እኮ እኔ አንቺ ሰፈር ስመጣ ሰፈርህ አይደለም ውጣ ልትይኝ ነው!።
ስለዚህ የዘር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር ተነቅሎ መጣል አለበት። ለዚህ ደግሞ ነባሩን ህገ መንግስት ማስወገድ ይጠይቃል። ሶስተኛው እኛ አገር ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ያሳስበኛል። ለዚህች አገር ይህ ሁሉ ፓርቲ መኖር ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። እንዴትስ አድርገን ነው የምንስማማው? እናም የምርጫ ቦርድ አንድ መድሃኒት ሊያበጅለት ይገባል የሚል አቋም ነው ያለኝ። ትንሽ ሰብሰብ ብለው ለአገራቸው ዲሞክራሲ እድገት መስራት አለባቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
መቶ አለቃ ፍቃደ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋች ሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013