ታምራት ተስፋዬ
በአዲስ አበባ ከተማ በህዝብ ቁጥር እድገትና ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ምክንያት ከከተማዋ የሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ በመጠንም በአይነትም ጨምሯል። ይሄ ቆሻሻ በተገቢው መንገድ እየተሰበሰበና እየተነሳ ነወይ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳ ምላሹ ቆሻሻን በአግባቡ ያለመያዝ፣ ያለማጓጓዝና ያለማስወገድ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል። በአይንም ይታያል።
በዚህም ምክያት ዜጎች ለተለያዩ የጤና እክሎች ከተማውም ለንጽህና ጉድለት ተዳርጓል።
በእርግጥ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት ባይቻልም የከተሞችን የጽዳት ስርዓት በማሻሻል ከተሞች ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንዲሆኑ መንግስት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል።
የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊያሻሽሉ የሚችሉ እቅዶችን በማውጣትም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስጀምራል። ቆሻሻን በስርዓትና በየፈርጁ በመለየት መልሶ ለጥቅም ለማዋል የሚያስችሉ የጊዜያዊ ደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያ ፕሮጀክቶችም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።
ከሶስት አመት በፊትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝም የከተማዋን የጽዳት ሥራ በተቀናጀ መልኩ መፈፀምና የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች ግንባታዎችን የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት በአሁን ወቅት በመዲናዋ የተለያዩ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች እየተገነቡ ናቸው። አንዳንዶቹም ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ለመሆኑ ፕሮጀክቶቹ አሁን ላይ ያሉበት ደረጃ ምን ይመስላል፣ ወቅታዊ ፈተናዎቻቸውስ ምንድነው ? የሚል ጥያቄ በማንሳት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሮ ነበር። በዚሁ ወቅትም ፕሮጀክቶቹ የሚገነቡባቸው ክፍለ ከተሞች አመራሮች የፕሮጀክቶቹ የግንባታ አፈፃፀም እያነከሰ ስለመሆኑ መታዘብና ምላሽ ማግኘት ችለናል።
የዝግጅት ክፍሉ በዚህ ሳይወሰንም ግንባታው ለምን ተጓተተ የሚል ጥያቄን በማንሳት ፕሮጀክቶቹን በበላይነት ለሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ የጥናት፣ የምርምርና የማማከር አገልግሎት ዳይሬክተር ለአቶ ታከለ ዴሲሳ ጥያቄ አቅርበናል።
አቶ ታከለ እንዳሉት፤ የከተማዋን የጽዳት ስራ በተቀናጀ መልኩ መፈፀምና የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ጊዜያው የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች ግንባታ የተፀነሱና በግንባታ ምእራፍ የተጀመሩት በ2010 ዓ.ም ነው።
ፕሮጀክቶቹ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን ፈር ለማስያዝ ብቻ ሳይሆን በቆሻሻ መሰብሰብና በመለየት ላይ የተሰማሩ ማህበራት በፀሃይና በዝናብ ከመደብደብ ለመገላገልና የሚሰበሰቡ ቆሻሻዎችም በፀሃይም ሆነ በዝናብ በስብሰው መጥፎ ጠረን እንዳያመጡ እንዲሁም በንፋስ ተበታትነው ከተማዋን እንዳይበክሉ ለማድረግ የታቀዱ ናቸው። ቆሻሻን ለመለየትና መልሶ ለመጠቀም እንዲቻል ያግዛሉ ተብሎም ታሳቢ ተደርጓል።
በወቅቱ በከተማ ደረጃ በአስሩም ክፍለ ከተሞች 80 የሚሆኑ ቦታዎች ላይ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማካሄድ መታሰቡን የሚጠቁሙት አቶ ታከለ፣ በአሁን ወቅትም 39 አካባቢዎች ላይ ጣቢያዎቹ እየተገነቡ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የፕሮጀክቶቹ ግንባታዎች የተጀመሩት በኤጀንሲው አስተባባሪነት እና የኮንስትራክሽን ቢሮን ጨምሮ በሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳትፎ እንደ ከተማ ነው። ይሁንና በ2011 የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አደረጃጀት ሲፈጥር በከተማ ደረጃ በአንድ ፕሮጀክት ተይዘው የነበሩ የጣቢያ ግንባታዎች ሃላፊነት ለከተማው ኮንስትራክሽን ቢሮ ተሰጥቷል።
የኮንስትራክሽን ቢሮ ፕሮጀክቶቹን ለብቻው መቆጣጠር ስለማይችል ለክፍለከተሞች አስተላልፏል። ቢሮው በባለቤትነት እየመራና ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ ፕሮጀክቶቹን ለክፍለ ከተሞችም አውርዷል።
ከፋይናንስ ቢሮ ጋር በመነጋገር በአንድ ኮድ በከተማ ደረጃ ተይዘው የነበሩ የቅብብሎሽ ጣቢያ ፕሮጀክቶች በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ የተለያየ ኮድ እንዲከፈትላቸውና በጀት እንዲለቀቅላቸው ተደርጓል። ይሕን ተከትሎም ክፍለ ከተሞቹ በጀት እያስፈቀዱ ኮንትራት እያስተዳደሩ እንዲቀጥሉ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።
‹‹ፕሮጀክቶቹ ሲታቀዱ በሶስት ወር ይጠናቀቃሉ ተብለው ነበር፤ ይሁንና ሶስት አመት አስቆጥረዋል›› የሚሉት አቶ ታከለ፣ ይሁንና በአሁን ወቅት 39 በሚሆኑ አካባቢዎች ጣቢያዎቹ እየተገነቡ መሆኑንና ከእነዚህ መካከልም ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ብቻ ስለመጠናቀቃቸውም ይጠቁማሉ።
ፕሮጀክቶቹ በሶስት ወር ታስበው በሶስት አመት አለመጠናቀቃቸው ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውም በግማሽ ቀንሷል። ፕሮጀክቶቹ ሲፀነሱ በወቅቱ በከተማዋ ደረጃ በአስሩም ክፍለ ከተሞች 80 የሚሆኑ ቦታዎች ላይ ታሳቢ የተደረጉ መሆናቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ ከሶስት አመት በኋላ ማለት ነው በመገንባት ላይ ከሚገኙትም ሆነ ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መረዳት እንደሚቻለው ታዲያ የፕሮጀክቶቹ የግንባታ አፈፃፀም እጅግ አዝጋሚ ነው። ለመሆኑ የዚህ መንቀራፈፍ ችግር ምን ይሆን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ታከለ በሰጡት ምላሽ፣ ከመነሻውም የፕሮጀክቶቹ አጀማመር ክፍተት ነበር። የዲዛይን፣ የቦታ አቅርቦትና ሌሎችም ምክንያቶች ለፕሮጀክቶች መጓተት አብይ ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህ ባሻገር በወቅቱ በከተማዋ ደረጃ በአስሩም ክፍለ ከተሞች 80 የሚሆኑ ቦታዎች ላይ ታሳቢ ይደረግ እንጂ ወደ ትግበራ ሲገባ በጀት ተይዞ፣ ቅድመ ክፍያ ተከፍሎባቸውና ለኮንትራክተር ተሰጥተው ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረጉት 39 ቦታዎች ብቻ ናቸው።
የጤናም ሆነ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በእርግጥም መዘግየታቸውን የሚስማሙበት አቶ ታከለ፣ ይሁንና በአሁን ወቅት በከተማ አስተዳደርና በከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ በተለይም ቅድመ ክፍያ የተከፈለባቸው 39 ቦታዎች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው በሚል ስለመወሰኑ ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
ይሕን ተከትሎም አስፈላጊና ጠቃሚነታቸው ታምኖበት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎቹ እየተመረቁና አንዳንዶቹም ወደ ትግበራ መግባታቸውን የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከአምስት ፕሮጀክቶች አራቱ መጠናቀቃቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በመገንባት ላይ ከሚገኙት መካከል አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ከ60 እስከ 70 በመቶ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ የእስካሁኑን የመዘግየት ሂደት ለመለወጥ በተደረሰው ውሳኔም‹‹39 በዚህ አመት መጠናቀቅ አለባቸው የሚል እቅድ ተይዛልም›› ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ ስለፕሮጀክቶቹ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላትም፣ በዚህ ምክንያት የተፈጠሩ መዘግየቶችን ለማስወገድ በተከታታይ መድረክ ስለ ፕሮጀክቶቹ አላማና ጥቅም ውይይት መግባባት ላይ በመድረሱ ይህ ችግር ፈር እየያዘ ስለመምጣቱም ተናግረዋል።
በሶስት ወር ታስበው በሶስት አመት ያልተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች በፍጥነት መጠናቀቅና የታለመላቸውን ግብ ማሳካት ግድ ይላቸዋልና ኤጀንሲ በቀጣይ ምን እንዳሰበ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አቶ ታከለ ኤጀንሲው የፕሮጀክቶቹን ግንባታ እንዲፋጠን ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ደከመኝ እንደማይል ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013