ሰላማዊት ውቤ
ጎንደር ከተሜነትን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ያስተዋወቀች ናት። ብዙ ፀሐፍትም የከተሞች እናት እያሉ የሚጠቅሷትና ታሪካዊት ከተማ ስለመሆኗ ይነገርላታል። ከተማዋ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ናት።
ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከሀገራችን ዋና መዲና አዲስ አበባ ያላት ርቀት መጠን ደግሞ 738 ኪሎ ሜትር ያህል ነው።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደገለፁልን በአሁኑ ወቅት 700 ሺህ ነዋሪዎች አሏት። የቆዳ ስፋቷ ከአምስት ሺ 600 ሄክታር በላይ እንደሆነም ይታወቃል። ‹‹የአቢሲኒያዋ ፓሪስ›› ተብላም በመሞካሸት ትጠራለች።
ከ250 ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ዋና የመናገሻ ከተማ ሆና አገልግላለች። ጎንደር የሕዝብ ቁጥሯ በፈጣን ሁኔታ እየጨመረ ከመጡ ከተሞች አንዷ ናት። የሀገር ውስጥ መረጃ ብቻ ሳይሆን የዓለም ባንክ የ2018 መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ውስጥ በሕዝብ ቁጥር ብዛት ሁለተኛ ነች። የሕዝብ ቁጥሯ የጨመረው በተለያየ ምክንያት ሲሆን አንዱ ከውልደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገርላታል።
ሁለተኛው ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር በመባል ሰፊ ቦታ ከመያዟ ጋር ተያይዞ ከገጠር ወደ ከተማ ከሚመጣ ፍልሰት ጋር የተያያዘ ነው። ሶስተኛው የቱሪስት መስህቦች መገኛ ከመሆኗ ጋር ሲቃኝ በሚያማልል ውበቷ ቀልጦ ከሚቀር የሀገር ውስጥ ዜጋ ጋር ይሰናሰላል።
በመቶ ኪሎ ሜትር ውስጥ ሦስት በዩኒስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባት ከተማ ናት። ከእነዚህ መካከልም ቀዳሚው የፋሲል ግንብ አብያተ መንግስታት ሲሆን ቀጣዩ የሰሜን ተራራ ብሄራዊ ፓርክ፣ ሦስተኛው የእንስሳትና ዕፅዋት ብዝሀነትን የተመለከተው ነው። ከሦስቱ ባሻገርም ባህል፣ ታሪክና ሐይማኖታዊ ቱፊት ከፍ ያለባት ከተማ ነች።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ የባህል፣ የዕምነት ይዘቶች የሚስተዋሉባት እንደመሆኗ በዩኒስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ያስመዘገበችውም አላት። ኃላፊው እንዳጫወቱን ነገስታት በዘመናቸው የየራሳቸውን አብያተ መንግስታት ገንብተው ያለፉባት ናት።
ከአንድ ድንጋይ ብዙ ህንፃዎችን ፈልፍሎ የመቅረጽ የረቀቀ ጥበብ ልህቀት የታየባትና ተፈጥሮ የዚሁ ታሪክ መዳረሻ እንድትሆን ያደለቻት ውብና የማትጠገብ ከተማ ናት። በአብዛኛው የታሪኳ መነሻ የሚያደርገው ከ1632 ከአፄ ፋሲል ንግስና በኋላ ያለው ነው። 400 ዓመት እየተባለ የሚጠራውም ወቅት ከአፄ ፋሲል ንግስና በኋላ ያለው ዘመን ነው።
ከተማዋ በተለይ የ44 ታቦታት መገኛ እንደመሆኗ ከሀገራችን አካባቢዎች ለየት ባለ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ይከበርባታል። ይሄንኑ በዓል ለማክበርም ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የመጡ እንግዶችን የምታስተናግድ ከተማ በአሁን ወቅትም የጥምቀት በአልን በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ትገኛለች።
የጥምቀት በዓሉን ለማድመቅ በየዓመቱ ታቦታቱ በሚያድርባቸው ሥፍራዎች የሚደረገው ሰፊ ዝግጅት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል። የጥምቀት የታቦታቱ መውረጃ አካባቢዎች ዝግጅት እየተደረገባቸው ይገኛሉ። ለዓይን ሳቢና ማራኪ በሚሆን መንገድ አምረው ደምቀውና ተውበው እንዲታዩ የሚደረጉባቸው የተለያዩ ባህላዊ ደርዛቸውን ያለቀቁ ማስዋቢያዎች ጥልቅ ዝግጅት እንደተደረገባቸው ማሳያዎች ናቸው።
የታቦታቱ ማደሪያዎች ከተሰሩ እጅግ ረጅም ዘመን እንዳስቆጠሩ ይነገርላቸዋል። የተሰሩት በአፄ ፋሲል ዘመነ መንግስት ጊዜ ሲሆን በአቅራቢያቸው የተንጣለለ የመዋኛ ገንዳም ይገኝበታል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ጎንደር ስምንት ባለ ኮከብ ሆቴሎች ባለቤት ናት። እነዚህ ሆቴሎቿ እንግዶቿን ለማስተናገድ በተለየ ሁኔታ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል። በመሆኑም ለዝግጅቱና ለመስተንግዶው እነዚህ ሆቴሎቿ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ።
ሆቴሎቿ በከተማዋ ውስጥ የሆቴል ቱሪዝም ተብለው የሚጠቀሱ ትልቅ ሀብቶቿ ናቸው። በሦስቱም የጎንደር ዞኖች መጠኑ አሁን ላይ ይህን ያህል ማለት በሚያስችል ደረጃ ባይገለፅም ከፍተኛ ሀብት አለ። ጎንደር ከሆቴል ቱሪዝም በተጨማሪ ብዙ ሀብቶች ያሏት ስትሆን ነጭ ወርቅ እየተባለ የሚታወቀው የሰሊጥ ምርቷ አንዱ ሀብቷ ነው።
እሳቸው ነጩን ብቻ ጠቀሱት እንጂ ጎንደር ቀይና ጥቁር ወርቅ ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ሰሊጥ ዓይነትም መገኛና መናኸሪያ ናት ማለትም ይቻላል።
በመሆኑም ይህ ሀብቷ ከሆቴልና ቱሪዝም ዋንኛ ሀብቷ ቀጥሎ ሁለተኛው ገቢ የምታገኝበት ምንጭ ብሎ መጥቀስ ይቻላል። ጎንደር ከሰሊጥ በተጨማሪም የተለያዩና ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ግንባታ ጭምር የሚውሉና የጀርባ አጥንት የሆኑ የተለያዩ የቅባት እህሎች ይመረትባታል።
ወደ ውጪ በመላክ የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኝ ጥጥና ሌሎችም በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረትባት ከተማ ነች። በአጠቃላይ በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ ያላት ገቢና እንቅስቃሴ የከተማዋን ዕድገት ሊያሳልጥና ሊያፋጥን የሚችል ዳጎስ ያለ እጅግ ከፍተኛ የሀብት ክምችት ነው።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ እንደሚናገሩት ጎንደር ይህን የሀብት ክምችቷን አመጣጥና ዕድገቷን ለማስቀጠል ትችል ዘንድ የሚረዳት ሥራ በሁሉም አቅጣጫ እየተሰራ ይገኛል።
በሀገር ውስጥና በውጪ ያለ የግንኙነት ስርዓቷን አቀናጅቶ ማስቀጠል ደግሞ እየተሰሩ ካሉት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል።
ግንኙነቷ እንደ ሀገር ሲቃኝ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚያገናኛት የመሰረተ ልማት ያላት ከተማ ናት።
ከውጪ ሀገራት ጋር ያለ የእህትማማች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ በተጀመረው አግባብ አጠናክሮ ለመቀጠል እየተሰራ ነው። ከጎንደር ከተማ ጋር እህትማማችነት የተፈራረሙ ግዛቶች አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ፈረንሳይ ውስጥ አሉ። ከተማዋ ከእነዚህ ከተሞች ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አቻ ከተሞች ጋር የአጋርነትና የመደጋገፍ ስምምነት አድርጋለች። አንዱና ዋናው የሁሉም ከተሞችና ክልሎች መዲናና ንግስት ከሆነችው ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር ያለው ግንኙነት ነው።
ይሄ ግንኙነት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በነበሩ ጊዜም ተጠናክሮ የቀጠለበት ሁኔታ ነበር። አሁንም ከምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ጋር ግንኙነቱን ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል። ጎንደር አዲስ አበባን ጨምሮ እንደ አምቦ ካሉና ከሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ሌሎች መስኮች ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት አላት።
በእነዚህና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የተጀመሩ የአጋርነት ግንኙነቶችን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋት ዕቅድ ይዛለች።
ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ አፋር ክልልና ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ትግራይ ውስጥ ካሉ ከተሞች ጋር ግንኙነቷን የማስፋት፣ የአጋርነት፣ የመተጋገዝ፣ አብሮ የመቆም ሀሳቧ ዕድገቷ የጋራ የኢትዮጵያ ዕድገት መሆኑን ተገንዝባ የመንቀሳቀሷ ማሳያ ነው።
ከንቲባ ሞላ እንደሚሉት በቀጣይ ከከተሞች ጋር በጋራ በመሆንም ሆነ እንደ ጎንደር ከተማ ንግድ የማሳለጥ፣ በወጣቱ ዘንድ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ ባህልን፣ ኪነ ጥበብ የማሳደግ፣ ሰላምን የማስጠበቅ ሥራዎች አጠናክሮ የማስኬድ ዕቅድ አለ።
‹‹ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሰራው ሥራ ለኢኮኖሚ መነቃቃት የራሱ አስተዋጽኦ አለው›› የሚሉት ከንቲባ ሞላ ሁሉም ነገር ያለ ሰላም ዋጋ እንደማይኖረውም ይገልፃሉ። በመሆኑም በቀዳሚነት እየተሰራ ያለው ሥራ የራስንና የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ ነው። በዚህም አሁን ላይ ሰላሟ አስተማማኝና ዘላቂ መሆን ጀምሯል።
ነገር ግን ፈፅሞ አሁንም ወንጀል አልጠፋም። እዚህም እዛም የሚታዩ ስህተቶች ቢቀንሱም አልተፈቱም። ህገ ወጥነት የለም ማለትም አይቻልም። ስለዚህም ጎንደር ለዚህ ዓይነተኛ መፍትሄ የሚሆንና የተፈጠረውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል የፀጥታ መዋቅር እንዲሁም እራሱ የሰላም ሰራዊት የሆነ የከተማ ሕዝብ በመገንባት ሂደት ላይ ነች።
አክለውም አንድ በርካታ የሕዝቦቿ መዋዕለ ነዋይ ፈስሶባት ለተገነባች ከተማ ዘላቂ ሰላም ከልማትም፣ ከኢንቨስትመንትም ከቱሪስት መስህብና ከሁሉም ነገር በላይ ነው። በመሆኑም ሕብረተሰቡ የሚይዘውን የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ የከተማዋን ዕድገት በሚያሳልጥ መልኩ የሚያራምድበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም እየተሰራ ይገኛል።
ሌላው ከዚሁ ጎን ለጎን በዋንኛነት በጎንደር ከተማ ደረጃ እንዲሁም ከእህትማማች ከተሞች ጋር እየተሰራበት ያለ ጉዳይ የወጣት የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው።
እንደ ከንቲባው ገለፃ ጎንደር ከተማ ላይ ከሰባት ሺህ በላይ የዲግሪና የዲፕሎማ ምሩቃን አሉ። ምሩቃንና ምሩቃን ያልሆኑ ሲጨመሩ በጎንደር ከተማ ያለው የሥራ አጥ ቁጥር እስከ 45 ሺህ ይደርሳል። ይህ በቅርቡ የተመረቁትን የ2012 ዓ.ም ተመራቂዎችን አያካትትም።
ለእነዚህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የንግድ እንቅስቃሴው፣ ቱሪዝሙ፣ ኢንቨስትመንቱ አጠቃላይ እንዲሁም በመንግስት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ ለዚህም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ተይዟል።
በጀቱ ይሄን የሥራ ዕድል ፈላጊ ተደራሽ እንዲያደርግ ብድር ወስዶ ጥሪት ቋጥሮ የወሰዱትን ብድር የመመለስ ባህል ማዳበር ግድ ይላል። ከዚህ አንፃር ቀደም ሲል የነበረው ባህል ክፍተት ነበረበት። ይህን ባህል ለመቀየርና በተመለሰው ብድር ቀሪውን ሥራ ፈላጊ ወጣት ተደራሽ ለማድረግ የግንዛቤ ፈጠረ ሥራ እየተሰራ ነው።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ላቀው አያሌው እንደሚሉት ከተሞችን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዓይነተኛ መፍትሄ ነው።
ጎንደር ከተማም ከሚያዝያ 21-28 ቀን 2009 ዓ.ም የተካሄደውን ይህን ፎረም የማዘጋጀት ዕድል ገጥሟት ነበር። ፎረሙ ከተማዋን በአፈ ታሪክና በፎቶ ለሚያውቋት የሀገራችን ህዝቦች ጎንደር ማን ናት የሚለውን እውነታ ማሳየት የተቻለበት አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
ከዚህም በላይ የከተማዋን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በማስተዋወቅና የገፅታ ግንባታ ስራ በመስራት ፎረሙ ሲካሄድም ሆነ ከተካሄደም በኋላ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
በትንሹ ፎረሙ በተካሄደበት ቦታ ላይ ለመናፈሻነት የሚያገለግሉ ከ200 በላይ የሚሆኑ በኮንክሪት የተሰሩ መቀመጫዎች ለከተማ ነዋሪዎች ተሰርተዋል ብለዋል። በመጨረሻም ሁሉም ነገር ለከተሞች ዕድገት በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013