ዳ ፍሬህይወት አወቀ
እንዴት እንዴት ነው ነገሩ ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰሰ›› አይነት ነገሮች ከሰሞኑ ተቀያይረዋልሳ። ለወራት ስራ የበዛበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕለት ተዕለት አይነኬ የተባሉትን እና ትናንት ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ የሚመስሉትን ነገር ግን በምግባራቸው ቀሊል ሆነው የተገኙትን የህወሓት አማፂ ቡድኖች ከገቡበት ጎሬ እያወጣ ለህግ እያቀረባቸው ይገኛል።
መቼም ‹‹የቀበጡለት ሞት አይገኝም›› አይደል ተረቱ። ይህው ሞታቸው እንደ ሰማይ እርቆ ቅሌታቸው ገሀድ ወጥቶ በአደባባይ ይታይ ጀምሯል። የዚህ ሰሞን ሰበር ወሬዎችም የእነዚሁ ባለስልጣናት መደምሰስና በቁጥጥር ስር መዋል በመሆኑ ህዝቡ ካደመጠውና ከተመለከተው ሰበር ወሬ ተጨማሪ ሌሎች ሰበሮችን በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ህዝቡ እየተመለከተ ባለው ሰበር ወሬዎችም እጅጉን ከመደመሙ የተነሳ ‹‹ሰው የዘራውን ያጭዳል›› የሚለውን ብሂል ደጋግሞ ሲናገር ይደመጣል። ምክንያቱም አሁን ከየጥሻው እየተለቀሙ የሚቀርቡት የህወሓት ጁንታ ቡድኖች ትክክለኛ መገለጫ ናቸውና ነው።
ኢትዮጵያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲመሯት የነበሩት እነኚህ ግፈኞች እጅጉን ፈሪና ራስ ወዳድ መሆናቸውም በገሀድ እየታየ ያለበት ጊዜ አሁን ነው። እንደው ማን ይሙት ትናንት የስልጣን ቁንጮ ላይ ሆነው ሀገሪቷን እንዳሻቸው ሲያደርጓት ኖረው ዛሬ እጃቸውን ለካቴና ይዘረጋሉ ማን አለ፤ ይህ ጊዜስ ይመጣል ብሎ ማን አሰበ፤ ዳሩ ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ታላቁ መጽሀፍ እነሆ አይነኬዎች ተነኩ።
ይሆናል ያልተባለው ሆነና አቦይ ስብሃት ነጋን የሚያህል ታላቅ ቀላል ሰው በቁጥጥር ስር ውለው በአደባባይ ታዩ።
አቦይ ስብሃት ነጋ በጁንታው ቡድኑ ትልቅ ቦታ የነበራቸውና ኢትዮጵያን ለመበታተን አቅደው በመከላከያ ሠራዊት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ካደረጉ ዋነኛ የጁንታው አመራሮች መካከል ቁጥር አንድ ተጠቃሽ ናቸው።
ዳሩ ምን ዋጋ አለው የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውምና ይህው ቀን ጥሏቸው፣ ቆሌ ርቋቸውና ብርክ ይዟቸው ጣዕረ ሞት መስለው በአደባባይ ከመታየት አላስጣላቸውም። በሀገር ላይ ላሳዩት ክህደትና በህዝብ ላይ ለሰሩት ግፍ እንዲህ ሆነው መታየታቸው በራሱ ትልቅ ድል ነውና እነሱን ካላሳፈራቸው እኛ እቴ ‹‹ሰው የጁን አያጣም›› እያልን አትኩረን እናያቸዋለን።
የህወሓት ጁንታ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ እጁን ያነሳ ዕለት ያኔ መጨረሻው እንደሆነ ቢታወቅም ይህን ያህል የከፋና የከረፋ ማንነታቸው ግን እንዲህ ተገላልጦ ይወጣል ብሎ የጠበቀ አልነበርም።
ዳሩ ‹‹ላታመልጪኝ አታሩጭኝ›› ሆነና ነገሩ ከጀርባ በወጉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላሰለሰ ጥረት በየተራ እየታደኑ መውጣት ጀምረዋል። ጀግንነት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ቢሆንም እነርሱ ግን ከጥንት ጀምረው የኖሩበትና ብቻቸውን ተዋግተው ኢትዮጵያን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ወራሪ ሀይል መታደግ ችለናል አይነት ተረክ ሲተርኩ ኖሩ።
ጦርነት ለእኛ የገበጣ ጨዋታ ያክል የለመድነው፣ የኖርንበትና ቀላል ጉዳያችን ነው በሚል በሌላኛው ተረካቸውም ጆሯችን አደሙት። ዳሩ ምን ዋጋ አለው አፍታም ሳይቆዩ እጃቸውን ለካቴና ለመስጠት በቁና ጨለምተኛ አስተሳሰባቸው ጨልሞ ልናየው በቃን።
እጃቸውን ለካቴና መስጠታቸው ደግሞ ሲመሩት ለነበረው ጀግና ሕዝብ ምን ያህል እራስ ወዳድ እና ፈሪ እንደሆኑ በግልጽ ማሳየት ችሏል። ለዓመታት መኖር ሳይሆን የመሰንበት ያህል የሚያንገሸግሽ ኑሮን እንዲገፋ የፈረዱበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ እነርሱን በዚህ ሁኔታ መመልከቱ ልባዊ እርካታ ቢሰጠውም ከሁሉም ነገር የሚቀድመው ሰብዓዊነት ነውና እንደሰው አሳዛኝ ክስተት መሆኑ አይታበልም።
‹‹አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል›› ነውና ነገሩ እነዚህ የህወሓት አማፂ ቡድኖች ሀገሪቷን ቦጥቡጠው ግጠው በአጥንት ቢያስቀሯትም ይህ አልበቃ ብሏቸው በጀመሩት የክፋት ጉዞ ይህው በጅብ ጎሬ ገብተው በረሀብና ውሃ ጥም ተቃጥለው ምቾት ጎድሎባቸው ታይተዋል።
እነኚህ ለሰማይ ለምድሩ የከበዱና በሀገሪቱ የመጨረሻው የስልጣን እርከን ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲምነሸነሹ የቆዩ ሰዎች በዚህ ደረጃ ወርደውና ተዋርደው መመልከት እንደሰው ያውም እንደ አባት እና እናት እጅግ ልብ የሚነካ ትዕይንት ነው።
በሰብዓዊነት ከማዘን ባለፈ ግን ማንም ሰው ከህግ በታች እንደሆነና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት እንዲሁም ሌሎችም ከዚህ እንዲማሩ ማድረግ የሚችል ታላቅ ክስተት መሆኑ አያጠራጥርም።
ይሁንና ሰው የሆነ ሰው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የፈለገውን አማርጦ ካልተመገበና በህዝብ ላይ ግፍ ካልሰራ እንዲህ ያለ መጎሳቆል ይደርስበታል ብሎ ማሰብ ግን ይከብዳል። ምክንያቱም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በላቡ ወዝ ጥሮ ግሮ ቢያገኝ ሽሮ በልቶ ቢያጣም ጥሬ ቆርጥሞ የሚያድር ወዛም ህዝብ ነው።
እነዚህ ስግብግብ እራስ ወዳዶች ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ላብ ከኖሩበት የምቾትና የድሎት ዓለም ለአንዲት ቅጽበት ቢሰወሩ እንዲህ ከሰውነት ተራ ወጥተው፤ ማስፈራሪያ አውሬ መስለው መታየታቸው ለምን ይሆን ብለን ብንጠይቅ ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻል ይሆናል።
ነገር ግን አምኖና ታምኖ በተመራላቸው ይሁን ባላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሸፍጥ በመስራት ለዓመታት ያስቆጠሩት ግፍ ዛሬ ላይ ለመድረሳቸው የምክንያቶች ሁሉ ቁንጮ ምክንያት ነው። ‹‹የግፍ ግፍ አንገፍግፍ›› እንዲሉ የሰሩት ሥራ እያንገፈገፈ ብርክ እንዲይዛቸው አድርጎ ከፊቱ ከከዱት ህዝብ ፊት አቁሟቸዋል።
የህወሓት አማፂ ቡድኖች የኢትዮጵያን ህዝቦች በመከፋፈል ሴራ እየጎነጎኑ ኖረዋል። በሴራቸውም ሀገር የመበታተን አደጋ የተጋረጠባት ለመሆኑ ብዙ ሀገር ወዳዶች ሲናገሩ፣ ሲጽፉና ሲሞግቱ ታይተዋል፤ ተደምጠዋል፤ ተነበዋል።
አብዛኛዎቹም እውን እየሆኑ የጠራ ጨረቃ መስለው ታይተዋል። ይህ እውነት በገሀድ መታየት ከመቻሉ ባለፈ ልንማርበት እንደሚገባም የብዙዎቻችን እምነት ነው። ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ አሁን አገሪቷን እየመራ ያለው ኃይል ከዚህ ምን ይማራል? የሚለው ሊሆን ይገባል። ዛሬ ነገ መሆኑ ላይቀር ከትላንት በመማር ዛሬ ላይ አዲስ ታሪክ መስራት ይገባል።
እርግጥ ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ አትፈርስ ይሆናል፤ ነገር ግን በማትፈርሰዋ ኢትዮጵያ ውስጥም ሊገነቡ የሚገባቸው ስሞች ሁሉ መፍረስ የሌለባቸውና ዘመን ተሻጋሪ መሆን ይኖርባቸዋል።
ዛሬ ላይ የምናወድሳቸው የጥንት ጀግኖቻችን በሙሉ ትናንት በሰሩት ታሪክ ነውና ሁሌም እንደሚባለው እያንዳንዳችን ከማለት ባለፈ በተሰማራንበት ዘርፍ ሁሉ ለትውልድ የሚቀር መልካም ስራ ሰርተን ብናልፍ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን እንድናለን።
ያን ማድረግ ባንችልና ከታሪክ ካልተማርን ግን የህወሓት አማፂ ቡድኖች በክብር ሲታዩበት በነበረው የቴሌቪዥን መስኮት ዛሬ ላይ ወርደው ተዋርደው እንደታዩት ሁሉ ታሪክን መድገም ይሆናል። እናም አሁን ከፈጠነው ፈጥነን፤ ከተራመደው ሮጠን ተሸቀዳድመን በምድራችን እየሆነ ያለውንና በሰዎች ላይ ሰዎች ያደርጉታል ተብሎ የማይታመነውን ዘግናኝ ድርጊቶች እናውግዝ።
ለሀገር አንድነትና ሰላም ለአብሮነት ዘብ በመቆም የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማፋጠን እንትጋ። ይህን በማድረግ ሰው የሚረሳውን ነገር ግን ታሪክ የማይረሳውን አሻራ በማኖር ለኢትዮጵያችን ውለታ ልንውልላት ይገባል። ለዚህም ጊዜው አሁን ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013