አዲሱ ገረመው
የቀይ ነገር ጥላቻ /ፎቢያ ነው የሚሉት ነጮቹ/ አለብኝ፤ እንዲያም ክፉኛ ተጠናውቶኛል። በተለይ በተለይ ቀይ መኪና አልወድም፤ አሁን አሁን ደግሞ ከመኪና አልፌ ቀይ የሚባል ነገር ጠልቻለሁ። ቀይ ነገር የአደጋ ምልክት እንደሆነ ነው አዕምሮዬ ውስጥ የተቀረጸው፤ ደግሞም ነው እንጂ፤ ቀይ ሽብር፣ ቀይ መብራት (የትራፊኩን)፣ ቀይ ካርድ ከአደጋና ከቅጣት ጋር የተያያዙ ናቸው። ቀይ መስመርስ ያው አይደል፤ ሲታለፍ ማለቴ ነው። ቀይ መስቀልስ ቢሆን ከአደጋ በኋላ የሚደርስ አይደል፤ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ።
ከዓመታት በፊት ይሄ ሲኖ ትራክ ነው “ሲኖ ጭራቅ” የሚባል ተሽከርካሪ ገና ኢትዮጵያ እንደገባ ያደርስ የነበረው አደጋ በአዕምሮዬ ውስጥ ስለተቀረጸ ቀይ መኪና ሳይ የሲኖ ትራክ ዘረመል ያለባቸው ይመስሉኛል። ነጭ ሲኖ ትራክ ቢኖርም እኔ ያው እንደ ቀይ እያዩት ነው።
አሁን ላይ ማንኛውንም ቀይ ተሽከርካሪ ሳይ እፈራለሁ። መኪና ለመሳፈር ጠብቄ ቀይ ከሆነ ወደ መንገዱ አልገባም። መግባት የግድ ቢሆንብኝ እንኳን ከማውቀው ሰው ጋር ካልሆነ በቀር አልገባም። መኪናውን ከተሳፈርኩበት ጀምሬ እስከ መዳረሻዬ ሰውነቴ ይርዳል፤ ይንዘፈዘፋል። ልቤም ይመታል፤ ራሴን ያዞረኛል፣ እመንገድ ላይ ጭው ይልብኛል፤ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር የሚጋጭ ይመስለኛል።
በእርግጥ ማንኛውም ሰው የአንዳች ነገር ፍርሀት እንደሚኖረው ስለማምን ፍርሀቴን እንደ ችግር አላየውም። በቀይ መኪና ከመጓዝ ራሴን አቅቤው ከመኖር ውጪ ምን አደርጋለሁ።
በአንድ ወቅት ሲኖ ትራክ ሹፌር ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት ፈለገና “ማዘር እለፉ” ሲላቸው ሴትየዋ “ልጄ መጀመሪያ ሞተር አጥፋልኝ ከዛ እሻገራለሁ” ማለታቸውን ሰምቻለሁ።
ነገሩ ፌዝ ቢመስልም እውነታው ግን ከፍ ያለ ነው። ማንም ሰው ሲኖ ትራክን አያምንም። ተሽከርካሪው ያለ ምንም ምክንያት አንዳች ትርዒት ያሳየ ይመስል በራሱ ጊዜ ክብልል እያለ እየወደቀ ማን በአጠገቡ ሊያልፍ?
ረጅም መንገድ በመኪና ከተጓዝኩ ቆየት ብያለሁ። እነዚህን ሲኖዎች ደግሞ የማየው ከአዲስ አበባ ውጭ ባላቸው ሰፊ እንቅስቃሴ ነው።
እና በቅርቡ ዳግመኛ ከአዲስ አበባ ወጣ ስል የሲኖው የመጥፎ ትዝታ ብቻ ሳይሆን ለማየት የሚቀፉ አወዳደቁንም ጭምር ለማስተዋል በቃሁ (አይ እዳዬ)፤ በጉዞ ወደ ደብረ ማርቆስ በመኪና አደጋ ከታጀበው አሰቃቂ የመንገድ ላይ ትእይንቶች ጋር፤
ዴንማርክን (ደብረ ማርቆስ) ለማየት ከስምንት ሰዓታት በላይ ተጉዘናል።
የጉዞአችን ምክንያት ደግሞ ብሄራዊ ቤተመዛግበትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ያዘጋጀውን የንባብ ሳምንት መሳተፍ ነው። በዚች አጭር ጽሁፌ የማተኩረው በጉባዔው ዝርዝር ሁኔታ ላይ አይደለም።
ይልቁንም እስከመዳረሻችን የነበረውን ክስተት እንጂ። ከጅምሩ ስንነሳ ዴንማርክ የሚያደርሰን መኪና እጅጉን ቀርፋፋ ከመሆኑ የተነሳ ምሳ የበላነው ጫንጮ ላይ ነው።
ሁልጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ የተሽከርካሪዎች ከራማ ይለወጣል። ዳሩ የኛ ሹፌር ለመንገዱ አዲስ ስለነበር መኪናውን የሚጎትተው እንጂ የሚነዳው አይመስልም። ሌሎች ግን ከብርሃን የፈጠነ እሽክርክሪት መንገዱን ይንሸራሸሩበታል። አባጣ ጎርባጣ የለ ብቻ እንዳሻቸው ይነዱታል።
ዘገምተኛው መኪና ሁሉ ያለኔ ፈጣን የለም በማለት ደርሶ በየመንገዱ ሲንከባለል ነው የሚታየው። ምናለበት በመንከባለል ቢያልፍለት የስንቱንስ ህይወት ቀጠፈ መሰላችሁ።
ከፊት ለፊታችን ያለው ሲኖ ትራክ ትልቅ ሲጃራ እንደሚያጤስ ሰው ጭሱን እያበነነው ይበራል። በወቅቱ ሙቀትና በጭስ ደከምከም ያለው አስፓልቱም አሽንቀጥሮ ጥሎት የሉሲን አጽም እንዳስመሰለው ያየነው ከደቂቃዎች በኋላ ነው። ከሁለት ዛፎች መሀል ተወሽቆ የአወዳደቅ ወጉን በነጻነት ይሰልቃል።
ከወደቀው ሲኖትራክ አለፍ ብለን እዚህም እዚያም የወዳደቁ ቀይ መኪኖችን በብዛት አየን።
(የሲኖ ትራክ ዘመድ አዝማድ ናቸው)፤ የመንጃ ፈቃድ በብድር በማውጣት በምድረ ኢትዮጵያ የመንዳት ብቃት ማረጋገጫን የመግዛት አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያውያን ያረጉትን ያጡ ሹፌሮች ናቸው እነዚህን መኪኖች የሚያሽከረክሩት።
አንዳንዱ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው መንጃ ፈቃድ ገዘቶ ሲኖትራክ ላይ የሰፈረ የሚመስለው።
እርሱ ላይ ምን እንደሚሰፍርበት ባይታወቅም። ከአባይ ወዲህ ማዶም ከአባይ ወዲያ ማዶም የሲኖ ግልበጣ ትዕይንት በየመንገዱ ይታያል። የግድ ውደቁ ተገልበጡ ብሎ ያዘዛቸው አካል ያለ ይመስላል። መገልበጥ በሀኪም ትዕዛዝ የተሰጣቸውም ይመስላል።
“ይህንን መኪና (ሲኖ ትራክን) አነዳድ የትራፊክ ፖሊስ ግብረ ኃይል አላየውም እንዴ?” ሲል አብሮኝ ከነበሩት አንዱ ጠየቀ። “በዚህ አካባቢ ከፍጥነት ወሰን በላይ ቢያሽከረክር በግላጭ ተገኝቶ በዋዛ እንደማይታለፍ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ሲኖ ትራክ ግን እንዲህ በግላጭ እና በነጻነት ያለምንም ተቃውሞ እየተነዳ በመገኘቱ አንዳች ነገር መኖሩን ያመላክታል።
” አልኩት። እውነት ነው ትራፊክ ፖሊሱ በሌላ ጉዳይ ላይ ተጠምዷል። አሽከርካሪ የሚቀጣበት ሁኔታና መስፈርት በግልጽ አይታወቅም። ቅጣቱ ሹፌርን ከማስተማር ይልቅ ለተጨማሪ አደጋ ማበረታቻ ይመስላል።
እና ለማንኛውም የሲኖው ልዩ ትዕይንት ከአድካሚው ጎዞአችን ጋር ቀጠለ። አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፈን አባይ በረሀን ተሻገርን። በየመንገዱ የምናየው የሲኖ ግልበጣ ግን ከሀዘንም በተጨማሪ ግርምትን ይጭራል። ስለ አነዳዴ አስተያየት ካሎት…የሚል ጽሁፍ ከጀርባ የለጠፉ ነገር ግን ከመሬት ተላትመው ጎማቸው ወደ ሰማይ ያቀና ሁሉ አሉ።
ሰውዬው ካልተረፈ ለማን ተደውሎ አስተያየት እንዲሰጥ ይሆን? ደግሞስ ስለ አወዳደቄ ብለው ቢለጥፉ አይሻልም ወይ? ከሁሉም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ የሚል ጥቅስ ለጥፎ የወደቀው ተሽከርካሪ እጅጉን ያዝናናል።
አንጀትም ይበላል። እውነት ነው፤ የገዛ ሹፌሩ ስራውን እንዳይሰራና በአጭሩ እንዲቀጭ ሲያደርገው ምን ይበል? እንዲህ እያለን በራሳችን ላይ እየቀለድን የሰውን ነፍስ በከንቱ ማባከናችንን ሳስበው ያመኛል።
ሲኖ ትራክ በሌሎችም በራሱም እያደረሰ ባለው የግፍ አደጋ ላይ ብሶት አለኝ። ለተሽከርካሪው ያለኝ የጥላቻ ስሜት እያደገ በመምጣቱ ጭምር ነው ቀይ ነገር ሳይ የምፈራው።
መቼም ችግሩ የተሽከርካሪው ሳይሆን የአሽከርካሪው እንደሆነ ይታወቃል። መኪናውማ ራሱን በራሱ አያሽከረክር፤ መሪ አይዝ፤ ነዳጅ አይሰጥ…. ያው ችግሩ የአሽከርካሪው ነው።
አሽከርካሪዎቹ ለምን ኃላፊነት እንዳለባቸው እንደማያስቡ ይገርመኛል። የሰው ልጅ ከትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ከስህተትም ይማራል።
ታዲያ ይሄ ሁሉ አደጋ ሲደርስ ለምን መማር አልተቻለም? ወይስ እንደ ስህተት አልተቆጠረ ይሆን? ሹፌሩ መንጃ ፈቃድ ኖረው አልኖረው መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ግን የተንሸዋረረ ስለመሆኑ፤ ዳኛና ምስክር አያሻውም። እናም የትራፊክ ፖሊስ አይኖች የሹፌር እጅ ከማየት ይልቅ የሚደርሰውን አደጋ ያስተውሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013