ምህረት ሞገስ
ወጣት አሸናፊ መንግሥቴ ይባላል። የአስኮ አካባቢ ነዋሪ ነው። ወደ አራት መቶ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መጋዘን እያሠራ ይገኛል። በቤተሰቦቹ መሬት ላይ ከሰባት ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን መጋዘን ሲያስገነባ ከሲሚንቶ እና የብረት ዋጋ ማሻቀብ በተጨማሪ እርሱ እንደሚናገረው ትልቅ ፈተና የሆነበት የውሃ ችግር ነው።
በእርግጥ ውሃውን የፈለገው ለግንባታ በመሆኑ የግድ ንፅህናው የተጠበቀ ለመጠጥ ውሃ የሚያገለግል መሆን አይጠበቅበትም። ደግሞም ለውስኑ የመጋዘን ግንባታ የምንጭ ውሃ ጉድጓድ ቆፍሮ ግንባታውን ለማከናወን አቅም የለውም።
ስለዚህ ዋነኛ አማራጩ በየቤቱ የሚሰራጨው የቧንቧ ውሃን መጠቀም ብቻ ነው። የአካባቢው የውሃ ስርጭት ደግሞ እጅግ ችግር ያለበት እና እንኳን ለግንባታ ለቤት ውስጥ መጠቀሚያም የሚበቃ አይደለም።
ወጣት አሸናፊ፤ ውሃው የሚመጣው በወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጄሪካን በ10 ብር የሚገዛ በመሆኑ በአካባቢ ለግንባታ የሚሆን ውሃ ማግኘት ብርቅ ነው።
ስለዚህ እርሱ ለሚያከናውነው ግንባታ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ቡራዩ አካባቢ ሄዶ ወይም አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ ለአምስት ሺህ ሌትር አንድ ሺህ ብር ከፍሎ ውሃ አስጭኖ ያስመጣል።
ይህ ግንባታው ሲከናወን የሚያወጣውን ወጪ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ለግንባታው ጥንካሬ የሚያስፈልገውን ውሃ ማጠጣት የማይችልበትን ሁኔታ ስለፈጠረበት የግንባታው ጊዜ እንዲዘገይ አስገድዶታል።
በተስፋ ከቀን ወደ ቀን ይሻሻላል ብሎ ቢጠብቅም ውሃ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ እየጠበበ በመምጣቱ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን በግዢ ውሃ ማሠራቱን ቀጥሏል። ነገር ግን ግንባታውን ለመጨረስ ጫፍ ቢደርስም በተደጋጋሚ በጭንቅላቱ ውስጥ የአዲስ አበባ የውሃ እጥረት ችግር ሳይፈታ ለዓመታት የዘለቀበት ምክንያት እና ችግሩ መቼ እንደሚቃለል ጥያቄ ፈጥሮበታል።
ወይዘሮ ተቋም ወልዴ በተወሰነ መልኩ የወጣት አሸናፊን ጥያቄ ይጋራሉ። በእርግጥ እርሳቸው በሳምንት አንድ ቀን አንዳንዴም በሳምንት ለሁለት ቀን የቧንቧ ውሃ ያገኛሉ።
የውሃ ማጠራቀሚያ (ታንከር) ያለው ሰው ደግሞ በአካባቢያቸው ብዙ አይጎዳም። ውሃውን ተጠቅሞበት ሳይጨርስ ውሃው በሳምንቱ ስለሚመጣ አይቸገርም።
ሌሎች እንደርሳቸው ያሉ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር የሌላቸው ግን በጣም ይቸገራሉ። ከዚህ አንፃር ሲታይ የውሃ እጥረት ተቀርፎ በየዕለቱ ውሃ የሚገኝበት ጊዜ እየናፈቃቸው እንደሚገኝ ገልጸው የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ የከተማዋን የውሃ ችግር በማቃለል በየቀኑ ውሃ የሚገኘው ከመቼ ጀምሮ ነው በሚል እንድንጠይቅላቸው ገልጸውልናል።
የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ስርካለለም ጌታቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ውሃን የማልማት ሥራ ከባድ ነው። እንደቀላል ነገር በአንድ ጊዜ ይህ ተደርጎ ችግሩ በዚህ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሊቀረፍ ይችላል የሚባል አይደለም ብለውናል።
ነገር ግን ተቋሙ በቻለው አቅም እየሠራ መሆኑንም ይገልፃሉ። የተጠቀሱት አካካቢዎች የውሃ ችግር እንዳለ ተቋሙ ያውቃል፤ ችግሩንም ለመፍታት እየሠራ ነው ሲሉ ነግረውናል።
ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚመለክተው በጥያቄ አቅራቢዎቹ አካባቢ ማለትም ለአስኮ እና ለሸጎሌ በሚቀርቡ አካባቢዎች በጊዮን በረኪና፣ በፍራንሲስኮ፣ በሸገር መናፈሻ፣ እርሻ ሰብል ፣ በሸጎሌ እና ዳንሴ የተባሉ ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ማወቅ ተችሏል።
ባለስልጣኑ በከተማው የከፋ የውሃ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም፤ የተጀመሩ ጉድጓዶች በቶሎ እንዲጠናቀቁ ፤ የተጠናቀቁት ደግሞ ወደ ተጠቃሚው በቶሎ እንዲደርሱ እየተሠራ መሆኑም ተገልጹዋል።
ሆኖም ምንም እንኳ ጉድጓዶች ተቆፍረው ለስርጭት ዝግጁ ቢሆኑም አገልግሎት በሚሰጡባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚቋረጥበት ጊዜ አገልግሎቱም አብሮ የሚቋረጥ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ባለስልጣኑ በ2013 ዓ.ም ለደንበኞቹ 575 ሺህ ሜትር ኪዩብ የማምረት አቅም ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ በጀት ዓመት በሁለት ቢሊዮን ብር በጀት የ55 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማልማት መቶ ሺህ (100,000) ሜትር ኪዩብ ውሃ ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።
ባለስልጣኑ እቅዱን ለማሳካት ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም 9 ጉድጓዶችን በማልማት በቀን 20,000 ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ውሃ ስርጭት ስርዓቱ ማስገባት መቻሉም ታውቋል። ቀሪ 80 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ድረስ ወደ ስርጭት ለማስገባት እየሠራ መሆኑ ተገልጹዋል።
ነገር ግን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ የጉድጓድ ተቆፍሯል ወሬ ህብረተሰቡን እንደማያረካው ይታወቃል። መሰረታዊው ጉዳይ ህብረተሰቡ ውሃውን የማግኘቱ ጉዳይ ስለሆነ፤ይህን ለማድረግ ተቋሙ ከባድ ሥራ እየሠራ መሆኑን መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ በራሱ ከሚሠራው ሥራ እና ካለበት እጥረት ባሻገር ሌሎች ጉዳዮችም በውሃ ስርጭቱ ላይ እክል የመፈጥሩ ዕድልም አለ። የመንገድ ሥራ፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በነባር መንገድ ላይ የሚገኘው ከፍተኛ የውሃ መስመር የማዘዋወር ሂደት የውሃ ስርጭት ከሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች መካከል የሚገኙ መሆናቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ባለስልጣኑ የመዲናዋን የመጠጥ ዉሃ እጥረት ለመቅረፍ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ወደ ስርጭት የሚገነቡ የውሃ ልማት አማራጮች ላይ እቅድ በመያዝ ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ሲባል፤ ከነባር የገጸ-ምድር ፣ የከርሰ-ምድር እና አዳዲስ የውሃ አማራጮችን ጨምሮ ከመቶ ሃምሳ አምስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በላይ በማምረት ለማሰራጨት የታቀደ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013