Mኣr
መቸም አንዳንድ ነገሮች ከሌሎች ለየት የሚሉበት የራሳቸው ልዩነትን አያጡም። የአለምን ቋንቋ እንኳን ብንወስድ 10ሺህን ደፍኗል እየተባለ ነው።
በእያንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ቃላትም ልክ እንደ ቋንቋዎቹ ሁሉ ቁጥራቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን ይህ ሁሉ ደግሞ ከወርቃማው ፖለቲካዊ “ማንነት” (እጅግ የሚጠሉት ደግሞ የዘር ፖለቲካ ይሉታል) ጉዳይ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ፣ በ”ልዩነት” (“እኔ ከሁሉም ልዩ ነኝ” ከሚል ዘመን አመጣሽ የሰከረና የከሰረ ፖለቲካ) ህብረ-ቀለማት ያሸበረቀ “–ኢዝም” ላይ የተገነባ ዘመን አመጣሽ ሽቀላ ምክንያት ነው እየተባለ በየጓጥ ስርጓጉጡ ሳያንስ በየታችኛውና ላይኛው ምክር ቤታት ሁሉ በሹክሹክታ እየተናፈሰ ነው አሉ።
(ይህ የ”አሉ” ጉዳይ ከፌስቡክ መንደርተኞች ጎራና ጉራ እንዳያስመድበን ዝቅ ብለን እናብራራዋለን።)
በተመሳሳይ፣ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ባሉ ቃላት፣ በቃላቱ ላይ በሚመሰረቱ ሐረጋት ወዘተ ላይም ልዩነቶች አሉ።
ከልዩነቶቻቸውም አንዱ ከሚያስተላለፉት መልእክት ባሻገር በሚፈጥሩት ስሜትና በሚያወጡት ዜማ ነው። ለዚህም አንዱ እዚህ የመረጥነውና በርእስነት የሾምነው “ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር።” የሚለው ነው።
“ሟች ከመሞቱ በፊት … ነበር።” የሚለው አገላለፅ በእርግጥ “ምን አይነት አገላለፅ ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ መልሱ “አልተጠናም” ሲሆን፤ “ለምን አይነት ተግባቦታዊ ፋይዳ ሲባል?” ለሚለውም ከግል ግምትና ስሜት ያለፈ መልሱን “ቁጭ” ማድረግ ለጊዜው ከባድ ነው።
ከባድ ይሁን እንጂ ግን አውዱን ተከትለን፣ “በፊት” የሚለውን አስምረንበትና “ድህረ-” እና “ቅድመ-”ን በጉያችን ይዘን፤ “ሟች”ን አስበን፤ “ከሞት በኋላ” እና “ከመሞቱ በፊት” ያለውን የሰው ልጅ ሰብእና፣ ሁኔታና ይዞታ (እንደ ባለሙያ ሳይሆን ለደንቡ ያህል) በአእምሯችን ጓዳ ሸሽገን (ቆንጠር እያደረግን በማውጣት እየተጠቀምን) ጥቂት ነገሮችን ማለት እንደሚቻል ስድስተኛው የስሜት ህዋሳታችን ነግሮናልና በተነገረን መሰረት “እነሆ በረከት” ብለናል።
ይህ ፀሀፊ “ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር።” የሚለውን የሰማው ከአንድ ስድስት አመት በፊት ታክሲ ውስጥ ሆኖ ከሾፌርና ረዳት ምልልስ ነው። ይመስለኛል ሾፌሩ አንድ “ቀዥቃዣ” አቋርጣለሁ ብሎ ጥልቅ ሊልበት ነበር፤ በፈጣሪ (በሾፌሩ አልተባለም) ኃይል ለጥቂት ተረፈ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ “ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር።” ለጆሮ የበቃው፤ ዛሬ ደግሞ በጋዜጣ አማካኝነት ለንባብ።
እዚህ ላይ የተተረከለትን ሰው ሁለት ሰብእናዎችን ማሰብ ተገቢ ነው፤ “ሟች ከመሞቱ በፊት …” እና “ሟች ከሞተ በኋላ …” – ከላይ “ድህረ–” እና “ቅድመ–” ያልነውን ማለት ነው። እናስብ እንጂ የዛኑ ያህልም ቶሎ ብለን ከማንችለው ማጥ ውስጥ ሳንገባ ልንወጣ የሚገባን ጉዳይ አለ።
እሱም ካቅማችን በላይ ከሆነው ከ”ድህረ-ሞት”። “ሟች ከሞተ በኋላ” እንዲህ … እንዲህ … እያልን ለማውራት ሁሉም ነገር የለንምና አንባቢን ይቅርታ እየጠየቅን ወደ “ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር።
” እና “የሞተበትን ምክንያት” አንስተን እንጨዋወታለን። እንዴት “ሟች ከመሞቱ በፊት …” እያልን በተቃራኒው “እንጨዋወታለን” ይባላል? የሚል ትሁት አንባቢ ካጋጠመ መልሳችን የታክሲ ሾፌሩና ረዳቱን ጭውውት ከማስታወስ ባለፈ፣ በቅድሚያ የተጫወተው እራሱ “ሟች ከመሞቱ በፊት …” ነውና በቂ ምክንያት አለን ማለት ስለሆነ ለወቃሽ/ታዛቢያችን የምንሰጠው መልስ ይኸው ነው የሚሆነው።
እዚህ ላይ አንዳንድ አንባቢያን አለን፤ “ድርቅ” ያልን። “መረጃ”፣ “ማስረጃ” ምንትሴ እያልን ፀሀፍትን የምናዋክብ። እዚህ ገፅ ላይ ግን የሚዋከብ የለም፤ የተጠየቀውን “መረጃ” እና “ማስረጃ” ቁጭ እንጂ። “ጥቀስ” ከተባለም ይጠቅሳል። “ጥራ” ከተባለም ይጠራል።
“ማን?” ከተባለም “ሴኩቱሬ ጌታቸው እና ኩባንያው” ይላል። “ምክንያት” ከተባለም እንደሚከተለው ያብራራል።
ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም በትግራይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ የሰሜን ዕዝ ላይ በጁንታውና በእራሱ ከሀዲ የሰራዊቱ አባላት እጅግ አሰቃቂና አሳዛኝ ግድያ ተፈፀመበት (“የማይካድራው ጭፍጨፋ” በሚል የሚታወቀው)።
ተግባሩንም የጁንታው ነባር አባል ሴኩቱሬ ጌታቸው በጁንታው ሚዲያ ብቅ በማለት “መከላከያው ላይ መብረቃዊ እርምጃ ወሰድን” በማለት ድሉን ለአለም አወጀ። ይህ የአሁኑ ነው። ቅድመ 1983 ስ???
“ከአቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ጋር በአካል አንተዋወቅም። ትውውቃችን ባልተለመደ መልኩ በሚዲያ ነው። ታሪኩ 30 ዓመት ወደ ኋላ ይወስደናል።
ሁልጊዜ የህወሃት/ኢህአዴግ ከጫካ የሚተላለፍ ሬዲዮ አዳምጥ ነበር። ከሚያስተላልፉት ጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በየቀኑ ገደልንና ማረክን የሚሉት የኢትዮጵያ ሰራዊት ቁጥር ስላስገረመኝ በ1983 የፋሲካ በዓል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ወጥቼ እነዚህ ሰዎች የገደሉትን ሰው ስደምረው ‘የኢትዮጵያ ህዝብ አልቆ ገና ከሚመጣው ትውልድ ሁለት ሚሊዮን ተበድረን ሞተናል ማለት ነው’ የምትል ቀልድ ቢጤ ተናገርኩ።
ታዲያ በማግስቱ በሚተላለፈው የህወሃት ሬድዮ ላይ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው እንዲህ ሲል መለሰልኝ። ‘አቶ ታማኝ ቁጥሩን አዲስ አበባ ስንመጣ እንተሳሰባለን’ አለኝ። እንዳለውም አዲስ አበባ ገቡ፤ ግን ከእርሳቸው ጋር በአካል ሳንገናኝ ቁጥሩንም ሳንተሳሰብ ቀረን።
አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ዋናው የሚታወቁበት ነገር ህወሃት ፈተና ሲገጥመው ወይም ፈተናውን ሲሻገር ቴሌቪዥን ላይ የሚቀርቡት እሳቸው ነበሩ። ለካ ‘ነበር’ እንደዚህ ቅርብ ነው?” (ከታማኝ በየነ ፌስቡክ ገፅ (ጃንዋሪ 7 ፖስት ያደረገው) ላይ የተወሰደ)
እንግዲህ “ሟች ከመሞቱ በፊት …” በጆሮና አይን ምስክሮች ይህንን የሚመስል ሲሆን፤ “ሟች ከሞተ በኋላ …” ደግሞ የምናውቀው ነገር ስለሌለ ለአንድዬ ሰጥተንና ምስክሮቹ ከተናገሩት ጠቅሰን እናልፋለን።
“አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ተገድሏል” መባሉን ተከትሎ “ከተናገርኸው ሁሉ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን [ክህደትና አሰቃቂ ግድያ] የገለጽኸው አይረሴና የምትታወስበት ይሆናል! ቢያንስ አንድ እውነት ተናግረሃል። ምናልባትም የንጹሃንን ደም ተናዘዝ ብሎህ ይሆናል!” (ከBelay Manaye) ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ።
“ጊዜው በ1975 ዓ.ም በመስከረም ወር በመምህርነት ተመድበን ትግራይ ክ/ሀገር መቀሌ ከተማ ወደ አውራጃዎች ለመደልደል እጣ ስናወጣ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ሴኩቱሬን ያየሁት። በባዮሎጂ በዲፕሎማ ተመርቆ በእጣ ሽሬ አውራጃ ተመደበ።
እስከ አክሱም ድረስ በዳኮታ ተጉዘን ከዚያም ወደ ተመደብንበት አውራጃ ተለያየን። ጊዜው የጦርነት ወቅት ስለነበር እነሱ ወደ ሽሬ በኮንቮይ ታጅበው ሲሄዱ ትሀት በከፈተችው ውጊያ ይማረካሉ። ሌሎች ጓደኞቻችን ሲቆስሉ እሱ ተረፈ።
በመጨረሻ ትሀት ምርጫ ስትሰጣቸው ሌሎች ‘ወደ ሥራችን መልሱን’ ሲሉ ሴኩቱሬ ግን ቃል የገባለትን ሙያ ወደ ጎን ትቶ ‘ከእናንተ ጋር እታገላለሁ’” አለና ተቀላቀለ። “ይህን ያህል ዓመት ቆይቶ በመጨረሻ [ማይካድራውን በተመለከተ] የሰጠው መግለጫ በጣም አሳዛኝ ነበር።
ሰሞኑን የሥራውን አግኝቷል። ነፍስ ይማር (Wase Moges ከተባሉ ሰው የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ)።
“ሟች ከመሞቱ በፊት …” ብለን ስንነሳ ያለ መረጃ፣ ማስረጃና ምክንያት የመሰላቸው በርካቶች “ነበሩ”፤ ወይም “ነበርን”።
በታክሲ ሾፌርና ረዳቱ (በፍቅር ስሙ “ወያላው”) በተገኘና በተዋስነው ርእስ የጀመርነው ወግ እዚህ ላይ አበቃ። በሌላ “ሟች ከመሞቱ በፊት …” እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013