ይቤ ከደጃች.ውቤ
ወንድ ዝንጀሮ ወንድ ሲወለድ /ወንድ ግልገል ዝንጀሮ/ አይወድም ይባላል፤ ያሳድደዋል፤ ይገድለዋል አሉ።
በዚህ ክፉ ሰአት ግልገሉን የምትታደገው እናት ብቻ ናት፤ አባት ይህን ሁሉ የሚያደርገው ሲያድግ ይቀናቀነኛል የሚል ስጋት ስለአለው ነው ይላሉ።
ሰው ወይም የሚፈጥረው ቡድን ግን እንዲያ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ማሰብ የሚባል ነገር አለና። ማሰብ ብቻም አይደለም መመራመርም አለ።
ይህ እንግዲህ መሰረተ ሃሳቡ ነው። ሰው በዚህ መሰረተ ሃሳብ ሲለካ ሲገመገም ብዙ የሚቀረው ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ ብዙ ነው።
ሰው ዝርያውን በውሃ ቀጠነ ካሳደደ ፣ ከገደለ፣ መቆሚያ መቀመጫ ከከለከለ ከዝንጀሮው በምን ይለያል። አንድም ቡድን ሌላውን ቡድን ወይም ግለሰብ በዚህ ልክ ወይም ከዚህም በከፋ መልኩ ካሳደደ ከገደለ ወዘተ. እንደዚያው ነው። እኔ ጁንታውን በዚህ ልክ አየሁት።
ለነገሩ በዝንጀሮ ዋሻና ገድል ተጸንሶ አድጎና ጎልምሶ በአንድ ክፉ የፖለቲካ ዘመን በአሜሪካ አዲስ አበባ ግባ ተብለሃል ተብሎ ቀን ሰጥቶት ጎርፍ ይዞት ከተማ ገብቶ ከተማና ከተሜን ሀገርን አይሰሩ ሰርቶ መልሶ ዋሻና ገደሉ የገባ ከዝንጀሮው ምን በምን ይለያል።
ሰው ተገርቶ ሰውነቱን ካላወቀ፣ ወደ ጫካ የገባበት መሰረታዊ ምክንያት ቢኖረውም ከተማ ሲገባ ጥያቄው መመለሱን አይቶ እንደ ሰው እንደ ማህበረሰብ ካላሰበ ከአውሬው በምን ይለያል።
ጁንታው በረሃ በትግል ወቅት እያለ የአይናችሁ ቀለም አላማረኝም ያላቸውን የትግል ጓዶቹን እየገደለ፣ እያሳደደ ነው የኖረው፤ ለዚያም በተኙበት እየገደለ። የመንግስትን ስልጣን በያዘባቸው በእነዚያ 27 ዓመታትም ይሄው የአውሬ ባህሪው በርትቶበት ሌሎች እንዳይደርሱበት ምን ያልፈነቀለው ድንጋይ አለ።
ህዝብንና መንግስትነት ላይ ያስቀመጡትን ፈረንጆች ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንዲሉ ለማታለል ያልሰራው ድራማ የለም።
ሀገር በጋራ እንምራ ብሎ በስደት ያሉትንና በሀገር ውስጥ አኩርፈው የተቀመጡትን ሰብስቦ ብዙ አለ። አንድም ሳያደርግ እነሱም አውራው እንደሞተበት ንብ አንዳንዶቹ ብን ብለው ጠፉ፤ አንዳንዶቹም ማሊያ ቀየሩ፤ ለእሱ አደሩ። ዴሞክራሲ ተነሳሁ ስትል ዘጭ አለች።
ሊፈታተኑ የሞከሩት ተበሉ። ይፈታተናሉ ተብለው የተጠረጠሩት ታሰሩ፣ ተገረፉ፤ የደረሱበትም ጠፋ። 27 ዓመት ከዚህ ውጪ ሌላ ምን ተሰራ፤ ይሄው ነው።
ዝንጀሮ ምን አጠፋ ታዲያ። ወንድ ልጁን ወይም ወንድ የዝንጀሮ ግልገል ቢያሳዳድ ምን አጠፋ!!
ጁንታዎቹ በዱር ተጋድለው በለስ ቀንቷቸው ሥልጣን ሲይዙ ከህዝብ መስማማት ያልቻሉት የዱር ጠባያቸው ስላገረሸባቸው ነው።
እንደ ፈረስና አህያ መገራት ያልቻሉት ፤ ከዱር ያመጡትን እኩይ ባህርያቸውን በከተማና በሀገር እንተግብር ማለታቸው በየጊዜው ሲያጋጫቸው ነበር። ታዲያ ዳኛም ቀማኛም ሲሆኑ ከህዝቡ እንዴት ይስማሙ?
የደደቢት ደደቦች ከበረሃና ከጫካ መጥተው ሀገር ለ27 ዓመታት መርተው ከሚጣፍጠው ቤተመንግስት እንደገና ወደ ጫካ የተቀየሱት (የተመለሱት) አውሬ ፀባያቸው ከህዝብ ጋር ስላጋጫቸው ነው፤ የተገራ ባህሪ ስላልነበራቸው አውሬነታቸው እያገረሸባቸው ስላሽቸገራቸው ነው። እኩይ ፀባያቸው የትዕቢት የትምክህት ምሳሌ ነበር።
ጁንታውና አመራሮቹ በዝቅተኝነት ስሜት (በጠባብነት) የተጠቁና ነፍጥ የታጠቁ (ነፍጠኞች) ስለነበሩ በጎጥ ጥግ መሸሸግ ቢወዱም ደጉና ሀገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን አሳልፎ ሰጣቸው።
ትህነግና የትግራይ ህዝብ አይነጣጠሉም፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው እያሉ ሲቦተልኩ ቢኖሩም፣ የትግራይ ህዝብ ራሳችሁን ቻሉ አላቸው፤… ስለቴን ሰምቶኛል… ብሎ እንደፍጥርጥራችሁ አላቸው።
በማይካድራ ሳምሪ የሚባል ወጣት አውሬ አዘጋጅተው ሰዉን የፈጁት ያስፈጁት የመተከልንም እልቂት ከመጋረጃ ጀርባ የመሩት ጁንታዎቹ ናቸው። በትግራይ ክልል በማይካድራ የአማራ ብሔር ተወላጆች ባነጣጠረ ጥቃት በአንድ ቀን ብቻ ከ600 በላይ ንጹኃን ዜጎች በማንነታቸው ተጨፍጭፈዋል።
በየጊዜው ጅምላ መቃብሮች ይገኙ ስለነበረም አንዳንድ መረጃዎች ይህ አሀዝ ከአንድ ሺ በላይ እንደሚደርስ ያመለክታሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተሰነዘረ ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት፣ በአመዛኙ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ መረጃዎች መጠቆማቸው ይታወሳል።
በታዋቂው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስተባበርም ይጠረጠራሉ፤ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ግድያውን ተከትሎ በ40 የኦሮሚያ ከተሞች ግጭቶች ተከስተዋል፤ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ቢያንስ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ በግለሰቦች፣ በንግድ ድርጅቶችና በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሟል።
ለውጡ በመጣ ማግስት በሀገሪቱ ላይ የፈጸሙት ጥፋት እና ደባ ሲነቃበት እና የመረረ ነገር መምጣቱን ሲረዱ መቀሌ መሽገው ሲያቅራሩ የነበሩት ጁንታዎቹ ፣ጦርነት ከኛ በላይ ላሳር ነው አሉ። ለኛ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታ ነው ያሉት።
አየነው! የሀገር መከላከያ ሰሜን እዝን አጥቅተው ግብአተ መሬታቸውን አጣደፉት፤ ልክ እንደ ደሃ ቀብር፤ የረባ ፍታት የለው፤ የህይወት ታሪክ የለው ፣ወዘተ አፈር መልሶ ወደ መጡበት መመለስ ያለ።
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ባደረገው ዘመቻ እንዳይነሳ ሆኖ የተሰባበረው ጁንታው ፣እንደ ጁንታ ሊቀጥል የሚችልበት እድል ካበቃ ቆይቷል።
ይሁንና የአህያ ነፍስ ቶሎ አይወጣም እንደሚባለው እጃቸውን ያልሰጡበት ሁኔታ ድሉን ሙሉ ሳያደርገው ቆይቶ ነበር። በቅርቡ ደግሞ የትህነግ መስራቹን አቦይ ስብሃትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮቹ ከዚያው ካፈራቸው እንደገናም ከተጠጉት ዋሻ እየተለቀሙ ወጥተዋል። የተቀሩትም ቢሆኑ እጣፈንታቸው ይሄው ነው።
በየቴሌቪዥን ሰሌዳ በየጋዜጣ ምስላቸው ፀአዳ መስለው ሲታዩ የነበሩት የጁንታው ዋና ዋና አመራሮች ፤ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ፊታቸው ገርጥቶ አቧራ በላያቸው ላይ ሠፍሮ ጎዳና ተዳዳሪ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ቦዘኔ መስለዋል ብል አጋነንከው የሚለኝ የለም።
ለህግ ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ አውሬ ፀባያቸውን ለመግራት ማረሚያ ቤትን ያዩታል የሚል እምነት አለኝ።
ሌሎች ከእነዚህ እኩይ ተግባር ከተጠናወታቸውና በመከላከያና በሌሎች የደህንነት ሃይሎች ከተለቀሙት እና እየተለቀሙ ከሚገኙት ያልተገሩ ቡድኖች ትምህርት በመቀሰም ባህሪያቸውን ይገራሉ ተብሎ ይታመናል።
ይህ ብቻም አይደለም ያልተገራ ባህሪ ይዘው ህዝብ ላይ የሚሳፈሩ ቡድኖችም ወደዚህች ሀገር አይመጡም የሚል እምነት አለኝ። ካልተገራው ቡድን መጨረሻ ይህን ይማሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2013