ሰላማዊት ውቤ
በምግብ ራስን መቻል፣ ከውጪ የሚገባውን ስንዴ በማስቀረት በሀገር ውስጥ በቂ ስንዴ ማምረት፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን እንዲሁም አዳዲስና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮችን የዕውቅናና ሽልማት ባለቤት ካደረጓቸው ስራዎቻቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ለቋሚ የግብርና እና ለተፈጥሮ ሀብት ሥራ ትኩረት መስጠት፣ መስኖ ተጠቅሞ በዓመት ሦስቴ ማምረት፣ የተበጣጠሱና ኩታ ገጠም ማሳዎችን ሰብሰብ አድርጎ በክላስተር በማደራጀት አንድ ዓይነትና ገበያ ተኮር ምርቶችን በጋራ ማልማትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁ ዕውቅና አግኝተውባቸዋል።
ተመራማሪዎች፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርቡ ባለሀብቶችና ባለድርሻዎች የዕውቅናውና ሽልማቱ ተቋዳሾች ነበሩ።
ከክልሉ አደአ ወረዳ የመጡት ቀነኔ ቀጀላ በዕለቱ በማህበር ደረጃ ከተሸለሙትና ዕውቅና ካገኙት አንዷ ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት ማሳቸው ከሁለትና ሦስት ቃዳ አይበልጥም። በአካባቢያቸው የሚገኙት የብዙዎቹ አርሶ አደሮች ማሳ ስፋትም ከእሳቸው ማሳ ጋር ተመሳሳይ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት በዚህ ማሣ ክረምት ጠብቀው በዓመት አንዴ ያመርቱት የነበረው ምርት የዓመት ቀርቶ የሦስት ወር ቀለባቸውን እንኳን መሸፈን አይችልም ነበር።
ሽፋኑ ዓመቱን እንዲያደርሳቸው ለማስቻል በጥምር ግብርና በመሰማራት በእንስሳት እርባታና በጓሮ አትክልቱም ሲደግፉት ቆይተዋል። ይሄም ሆኖ የፈለጉት አልሞላላቸውም።ባለፉት ሁለት ዓመታት ታዲያ በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ድጋፍ ይሄን ታሪካቸውን የሚቀይር ስልጠና ወሰዱ።
በአካባቢው ኩታ ገጠም ማሳ ካላቸው አርሶ አደሮች ጋር 20 ሆነው ተደራጁ። በፓፓያ ቋሚ የግብርና ሥራ ጀመሩ። ከአንድ እንጨት ብቻ ከሰባት እስከ ስምንት ሺህ ብር ያገኛሉ። ፓፓያ እስኪደርስ እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ አላሉም።
ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎችን በዓመት ሦስቴ በመስኖ ያለማሉ። እነዚህና ሥራቸውን የሚያቀላጥፉላቸውና ጉልበታቸውን የሚቆጥቡላቸው ምርት ለመዝራት፣ ለማጨድ፣ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል።
አርሶ አደር ፈይሳ ጉታ ከአርሲ ዞን ከጦሳ ወረዳ ከጉቻ ቤባዶሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው የመጡት። የተሸለሙትና ዕውቅና ያገኙት ኩታ ገጠም ማሳ በክላስተር አድርገው በማረስ ከውጪ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት ደግፈው በመሳተፋቸው ነው።
ቀደም ሲል እሳቸው ባሉበት በዚህ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች በዚህ መልኩ ተሳትፈው ውጤታማ እንሆናለን የሚል ዕምነት አልነበራቸውም።
ውጤታማ መሆን የሚቻለው ሁሉም በየግሉ ሲሮጥ ይመስላቸው ነበር። በጋራ ማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያመጣ የነበራቸው ግንዛቤ አናሳ ነበር። አሁን ላይ ግን የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያዎች ሳያሰልሱ በፈጠሩት ግንዛቤ አስተሳሰባቸው ተለውጧል።
ለውጡ የመጣው ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ የክልልና የፌዴራል አመራሮች ደጋግመው አርሶ አደሩንና ማሳውን በመጎብኘታቸውና በማበረታታቸው ነው ይላሉ። አብዛኛው ያለው ማሳ የተበጣጣሳ ከመሆኑ አንፃር በክላስተር ማልማቱ ዳጎስ ያለ ገቢም እንደሚያስገኝ ተረድተዋል። በመሆኑም ሁሉም ስንዴን በክላስተር በማምረት ሂደቱ ተሳትፏል ብለዋል።
‹‹የዋንጫም የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘታችን በቀጣይ ሥራውን የበለጠ እንድንሰራ አድርጎናል›› ያሉን በዚሁ በስንዴ ምርት የቡድን ተሸላሚ አርሶ አደር ሰለሞን ለማ ናቸው።
አርሶ አደር ሰለሞን እንደነገሩን የመጡት ከአርሲ ዞን ከሎሌ ጡሳ ወረዳ መልካ ጀብዱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው።
ከውጪ ወደ ሀገራችን የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት ዓላማ አድርገን ነው በስንዴ ምርት በክላስተር ደረጃ እየተሳተፍን ያለነው ብለውናል። ተሳትፎው እርስ በእርስ ትስስር እንደፈጠረላቸውና በግልም በቀን ሶስቴ እስከመብላት በማድረስ ሕይወታቸውን እንደቀየረላቸው ገልጸዋል።
ውጤታማ ለመሆን ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያ ምርጥ ዘር መጠቀማቸውን አጫውተውናል። ሌሎች አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች በክላስተር ምርት መሳተፍ ውጤታማ እንደሚያደርግ እንዲረዱ ተሞክሯቸውን እንደ ቡድን ማካፈላቸውንም ነግረውናል።
ከዘር እስከ ምርት ስብሰባ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመዋል። በዚህም ጊዜና ጉልበታቸውን መቆጠብ ችለዋል። ከምርት ብክነትም ድነዋል።
በነገራችን ላይ በዕውቅናውና በሽልማቱ ዋዜማ በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ለሁለት ቀናት የቆየ የግብርና ግብዓት አውደ ርዕይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ተከፍቶ ነበር። ዓላማው ግብዓቶቹን ተደራሽ ላልሆኑ አርብቶና አርሶ አደሮች ማስተዋወቅ ነው።
ተመራማሪ አብዲሳ ተሾመን በአውደ ርዕዩ ነው ያገኘናቸው። ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ስር ካለው ከአሰላ ምርምር ነው የመጡት። እንዳስተዋልነው የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በአውደ ርዕዩ በማቅረብ ተሳትፈዋል።
ያስተዋወቁት በከብት የሚጎተት ባለ አራት መስመር በትራክተር የሚጎተት ባለ ስድስት መስመር የስንዴ መዝሪያ ነው። መዝሪያው ስድስት በሬ ስድስቴ የሚመላለስበትን በአንዴ ያከናውናል። በተጨማሪ አብሮ ማዳበሪያም ወደ ማሳው በማስገባት ያገለግላል።
በ120ና በላይ የፈረስ ጉልበት እንደሚጎተትም አስረድተውናል። ተመራማሪው ድንች ከመሬት ውስጥ እየቆፈረ የሚያወጣም አቅርበዋል።
ሌላ ድንች በትራክተር የሚያወጣና ባለስምንት መዝሪያ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ተሰርቶ ስራ ላይ ለመዋል መዘጋጀቱን ገልጸውልናል።
ሌላው ያቀረቡት የጤፍ፣ ስንዴና ገብስ መውቂያ እብቅም ከጤፍ ይለያል። በበሬ እስከ ሶስት ቀን ድረስ የሚወስደውን ጤፍ በሰዓት ሶስት ኩንታል ይወቃል። በሰዓት ስንዴ አራት ኩንታል ከ70 ኪሎ፣ ገብስ ደግሞ ሦስት ኩንታል ተኩል ይወቃል።
አቶ አህመድ መሐመድ የሃይቲ ትሬዲንግ ሀውስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅራቢ ገበያና ሽያጭ ኃላፊ ናቸው። አቶ አህመድ እንዳሉት አርሶ አደሩ ነቀዝን ለመከላከል ይጠቀም የነበረው ኬሚካል ነበር።
ሆኖም ኬሚካሉ በአርሶ አደሩ ላይ የካንሰርና የቆዳ በተለይ በሴት አርሶ አደሮች ላይ ከወሊድ ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ያመጣል። ይሄን በጥናት በመለየት አየር በማሳጣት ዘዴ ሻጋታና እርጥበት እንዳይኖረው በማድረግ ነቀዝን ሙሉ ለሙሉ የሚከላከል ዋህበል የተሰኘና ከፕላስቲክ የተሰራ የነቀዝ መከላከያ አቅርበዋል።
‹‹ቴክኖሎጂው አርሶ አደሩ ለዘር የሚሆን እህል እንዲኖረውና ያስቀመጠው በነቀዝ በመበላሸቱ ለዘር ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ያስቀራል›› ያሉን ተሳታፊ ከጅማ ዞን ሊሙ ወረዳ ነው የመጡት። አርሶ አደር ሱልጣን መሐመድ ይባላሉ።
እንደሳቸው የቡናን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉና የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አናሳ ናቸው። በመሆኑም በተመራማሪዎች ሊታሰብበት እንደሚገባም መክረዋል።
አቶ እንዳልካቸው ንጋቱ የአዳማ ወተት ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በአውደ ርዕዩ ቺዝን ጨምሮ ፍሌቨር፣ ቅቤ፣ እርጎና ከአሥር ያላነሱ ምርቶች አቅርበዋል።
እነዚህን ምርቶች የሚያመርተው ፋብሪካቸው ለ60 ቋሚና ለ30 ጊዚያዊ ሠራተኞች በአጠቃላይም በሂደቱ ለሚያልፉ ለ36ሺ የክልሉ ነዋሪዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል።
እንደነገሩን አዳማ ላይ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ሦስት ዓመታት ወስዶባቸዋል። ባለሀብቱ አውደ ርዕዩ በአጭር ጊዜ የበለጠ ምርታቸውን ለብዙ ደንበኞች ለማስተዋወቅ ረድቷቸዋል።
እርሳቸው እንደሚያስታውሱት ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት አርሶና አርብቶ አደሩ የገበያ ትስስር ስላልነበረው በክረምትና ጾም ወቅት ወተቱን ይደፋ ነበር።
ለሚደፋ ነገር ባላመርትስ ብሎ ሥራ ይፈታ እንደነበርም ያስታውሳሉ። በሰዓት 1ሺ500 ሊትር ወተት የሚያመርተው ፋብሪካቸው ፊቱን ወደ ሥራ እንዲመልስና የድካሙ ፍሬ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል።
ለዚህ ደግሞ ከግለሰብ እስከ ሕብረት ሥራ ማህበራት ዘልቆ ወተት መረከቡ እንደ አብነት ይጠቀሳል። ሳይበላሽ መልሶ ለአገልግሎት እንዲውል ማስቻሉም እንዲሁ ይወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ‹‹የዘንድሮ የግብርና ዕቅድ እንዲሳካ ሁሉም በአንድነትና በቁጭት ተረባርቧል›› ብለዋል።
አሰራሩን ለሚያዘምኑና ዘርፉን በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የሚደግፉ ተሳታፊዎች፣ በአጠቃላይ ለ607 ግንባር ቀደም አርሶና አርብቶ አደሮች ዕውቅናና የዋንጫ ሽልማትም ሰጥተዋል። በወቅቱም ‹‹ግብርናውን ከመሰረቱ ለማዘመን በቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ በዘላቂነት ይሰራል›› ብለዋል።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የክልሉ መንግስት ከመቼውም በላቀ ሁኔታ ሲሰራ መቆየቱን ነው የተናገሩት። በነዚህ ዓመታት በክልሉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂ በስፋት በመጠቀም ከኋላ ቀርነት አሠራርና ከደህነት መላቀቅ መቻሉንም ተናግረዋል።
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በሀገሪቱ የግብርና ለውጥ ዓይነተኛ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ክልሉ ከ500 ሺህ በላይ ሠራተኛ፣ በሳል አመራርና ምሁራን ይዞ ከእንግዲህ በደህነት ውስጥ እንደማይቀጥልም አበክረው አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አሠራርን ማቀላጠፍና የአርብቶ አደሩንና የአርሶ አደሩን የተዛባ የአኗኗር ዘይቤ ማዘመን ግድ የሚልበት ወቅት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በዚህ መንገድ ለመጓዝ አመራሩ፣ ባለሙያው፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ከኋላ ቀር አሰራርና የዚሁ ተገዢ ከነበረ አስተሳሰብ ለመጽዳት ራሱን መፈተሸና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ጋር ከተቃኘ አሠራር ጋር መላመድ እንደሚገባውም መክረዋል።
‹‹ተስፋ ሰጪ ጅምር ወደፊት በማራመድ ዓላማችንን በማሳካት ለሕዝባችን ክብር ማጎናጸፍ አለብን›› ብለዋልም አቶ ሽመልስ። ለዚህም አመራሩና ባለሙያው ተቀናጅተው ወደ ልማት መግባት አለባቸው።
በክልሉ በግብርና ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ለውጥ ወሳኝ እንደሆነም መረዳት ይኖርባቸዋል።
‹‹ አሁን ላይ አርሶና አርብቶ አደሩ ክልሉን በማልማት በሰላም እየደገፈ ይገኛል። የህወሓት ጁንታ የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ ሲያደርግ ለቆየው ጥረት ምላሽ በመንፈግ ትኩረቱን ልማቱ ላይ አድርጎ ቆይቷል።
ይሄም የሚያስመሰግነው ከመሆኑ ባሻገር በክልሉ በሁለቱ ዓመታት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት ለማምጣት አስችሎታል።›› ብለዋል።
‹‹ከሁለት ዓመታት በፊት በክልሉ በአማካይ ይገኝ የነበረውን 140 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርት ወደ 170 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ መቻሉ ለተገኘው አመርቂ ውጤት ማሳያ ነው›› ያሉት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ናቸው ።
እንደ ኃላፊው በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ቀደም ብሎ በኩታ ገጠም ይለማ የነበረውን 300 ሺህ ሄክታር ማሳ ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል። እንደ ክልል በሁለት ዓመታት በግብርናው መስክ የተከናወነው ሥራ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የውጪ ምርቶችን በማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤት በማስገኘት ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል።
በአፈር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ-አረም ኬሚካልና በሜካናይዜሽን ሥራ የተሻለ ውጤት አስገኝቷል። አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣ ቡናና ቅመማ ቅመም እንዲሁም መደበኛ መስኖ ልማት ባለፉት ሁለት ዓመታት መሰረታዊ ለውጥ ከተገኘባቸው ይጠቀሳሉ።
በቢሮው አማካኝነት 350 የእርሻ ትራክተርና 80 ኮምባይነሮች ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ መደረጉ ለውጡን አፋጥኖታል።
እንደ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ማንኛውም ሥራ ዕውቀትን መሰረት አድርጎ መሰራቱም ውጤት ለማስመዝገብ ጉልበት ሆኗል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2013