ወርቅነሽ ደምሰው
ኢትዮጵያ በጥንታዊ የስልጣኔ ጥበብ ቀደምትና የአኩሪ ባህል ባለቤት እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ለዚህ ምስክር የሆኑት እነ አክሱምና ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የታሪክ ተምሳሌትነቷን የሚያረጋግጡ ናቸው። ይቺ በስልጣኔ ቀደምት የሆነች ሀገር ወደፊት መጥቃ የስልጣኔ ማማ ላይ እንዳትደርስ ሰቅዘው ከያዟት ነገሮች መካከል በተለያዩ ጊዜያት ሲፈራረቁባት የነበሩት የመንግሥታት ባህሪና ርዕዮተ ዓለም አገዛዝ ሥርዓቶች መሆናቸው ይነገራል። በእያንዳንዱ መንግሥታት አገዛዝ ሥርዓት የሚወጡ አዋጆች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በሀገሪቱ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ዙሪያ የራሱ የሆነ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ ነው።
በዚህም ሀገራችን የህብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል መሠረታዊ የሆኑ እንደ መኖሪያ ቤት ያሉ ፍላጎቶችን ለማሟላት አስቸጋሪና ፈታኝ የሆኑ ውጣ ወረዶችን እያሳለፈች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። የህዝብ ብዛት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይ በከተሞች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በእጅጉ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። በሀገራችን ገዝፎ የሚታየውን ይህን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ የመጠለያ ቤት ፍላጎት በየጊዜው ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ መንግሥት በራሱ አቅም ቤት በመገንባት የህዝቡን የቤት ፍላጎትን ለማሟላት እጅግ አዳጋች እየሆነ መምጣቱን በተለያዩ ጊዜያት እየገለጸ ይገኛል።
በተለይ በመዲናችን በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በርካታ ጊዜያት ሊፈጅ እንደሚችል ይነገራል። ታዲያ ይህንን ችግር ከሥር መሰረቱ መቅረፍ ባይቻልም በሀገራችን በተለያዩ የመንግሥት አገዛዞች የተለያዩ አዋጆች ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች እየወጡ ለህብረተሰቡ የመኖሪያ ቤት ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደነበረ ይታወቃል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለውን እንኳን ብናይ በወታደራዊ ደርግ መንግሥት በህብረተሰቡ መካከል ያለውን የኑሮ መራራቅ እንዲቀራረብና ህብረተሰቡ ተደራጅቶ አገሩን ለማስቀደም እንዲችል በሚል የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሊቀመንበሩን ሥልጣን ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 2/1967 ዓ.ም በአንቀፅ 6 መሠረት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት በማድረግ የሰፊውን የከተማ ነዋሪ ህዝብ የቦታና የመኖሪያ ቤት ችግር ብሶት በማስወገድ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ መብቱን የሚያጎናጽፈውንና የጥቂት ባለሀብቶችን ብዝበዛ የሚያስቀረውን አዋጅ ቁጥር 47/67 ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም ደርግ በመላ ኢትዮጵያ አውጇል።
ይህም የቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው እየናረ ጣሪያ በነካበት በዚህ ወቅት በአዋጅ 47/67 መሰረት የተወረሱ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች ዛሬ ላይ ለአያሌ ምንዱባንና አቅመ ደካሞች መጠለያና መውደቂያ ሲሆኑ የተወረሰባቸው ግለሰቦችም ምትክ የመንግሥት የኪራይ ቤት እንዲያገኙ መደረጉ ይታወቃል። በአንጻሩ በአዋጁ የተወረሱ በርካታ ቤቶችን በተመለከተ ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት ግልጽ መመሪያ ያላስቀመጠበት ሁኔታ መኖሩ ይገለፃል።
‹‹በዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን ይዘን የቀረብነው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም አካባቢ ከ39 ዓመት በላይ ስንኖርበት የነበረ በደርግ ጊዜ በተወረሰ በቤታችን ምትክ ማካካሻ ቤት በኪራይ ቀመስ ውል የተሰጠን ቢሆንም፤ አሁን ቤቱን ያለ አግባብ ተነጥቀን ጎዳና ላይ ልንወድቅ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ተጋላጭ ልንሆን ነው›› በማለት ህዝብና መንግስት ይፍረደን ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቡ ግለሰብ ቅሬታና ታሪክ ይመለከታል። ዝግጅት ክፍሉም ፍርዱን ለእናንተው በመተው፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮና ምሬት በማዳመጥ ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየትና ምላሹን ጨምረን እንደሚከተለው ልናስቃኛችሁ ወደድን።
የቤቱ አሰጣጥ
ወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማሪያም ይባላሉ። በደርግ ጊዜ በይርጋለም ከተማ በቀድሞው ወረዳ 1 ቀበሌ 06 የቤት ቁጥር 245 በሚል የሚጠራ በስማቸው የተመዘገበ ቤት ነበራቸው። በወቅቱ ወታደራዊው መንግስት ደርግ በ1967 ዓ.ም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት ለማድረግ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ቤታቸው ተወረሰባቸው። በዚህም በይርጋለም ከተማ ያለው ቤታቸው በመወረሱ ምክንያት በምትኩ ለዚያ ቤት ማካካሻ የሚሆን ቤት በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ስሙ በቀጠና 5 በከፍተኛ 13 ቀበሌ 03 የቤት ቁጥር 997 በኪራይ ተሰጣቸው።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ቤት በይርጋለም ከተማ ባለው ቤት ምትክ ማካካሻ የተሰጣቸው ሲሆን፤ የዚህን የኪራይ ውል በወቅቱ ከነበረው የቀድሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳዳር ድርጅት ጋር በኪራይ ውል ቁጥር 045/1252/74 ዓ.ም በየዓመቱ በሚታደስ የፀና የቤት ኪራይ ውል መሰረት ቤቱን ተረከቡ።
በወቅቱ በነበረው በኪራይ ውሉ ላይ አከራይ ተብለው የቀረበው የቀድሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ሲሆን፤ ለተከራይ ወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማርያም እና የባለቤታቸው ስም ተብሎ ለተጠቀሰው አቶ ገዛኸኝ ፍሬው የተሰጠ ነው። አከራይ የተቀጠሰውን አዲስ አበባ ከተማ ቀጠና 5 በከፍተኛ 13 ቀበሌ 03 የቤት ቁጥር 997 የሆነውን ቤት ለተከራዩ በወር ብር 144 (አንድ መቶ አርባ አራት ብር ) ሂሳብ በዚህ ውል ቁጥር 045/1257/74 አከራይቷል ካለ በኋላ፤ ምንም እንኳ ለኪራይ የተሰጠው ቤት ኪራይ 144፤ ቢሆንም በይርጋለም ከተማ የተወረሰባቸው ቤት 85 ብር የተገመተ በመሆኑ ልዩነት ብር 60 ከ 45 ብር ይከፍላሉ በሚል በኪራይ ውሉ ላይ ተቀምጧል።
በዚሁ የኪራይ ውል ላይ የአከራይና የተከራይ ግዴታዎችና መብቶች ተጠቅሰው በዝርዝር የተቀመጠበት ሁኔታን ያሳያል። በዚህ መሠረት ተከራይ ወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማሪያም ከ1974 ጀምሮ በዚሁ ቤት እየኖሩ ሳለ በይርጋለም ከተማ የሚገኘው ቤታቸው በወቅቱ በመሐንዲሶች የተተመነው የኪራይ ተመን ዋጋ ከ85 ብር በላይ በመሆኑ ተመኑ ከቤቱ አንጻር ዝቅተኛ ነው ሲሉ ረጅም ጊዜ ሲከራከሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ ጉዳያቸውን ሲያይ የነበረው ፍርድ ቤት በሁለቱ ቤቶች መካከል ያለው የዋጋ ተመን እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል።
በዚህ መሠረትም በኪራይ ውሉን የሚጠበቅባቸውን እየከፈሉ ግዴታቸውን እየተወጡ ሲኖሩ ቆይተው ፤ በ2002 ዓ.ም ቤታቸውን አስመልክቶ ለመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ የኪራይ ውል እንዲታደስላቸው በተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያሳየው በወረዳ 13 ቀበሌ 03 በቁጥር 997 የተመዘገበውን ቤት ይዘው የሚገለገሉበት ወይዘሮ ደብሪቱ ሣህለማርያም የቤቱ የኪራይ ውል እንዲታደስላቸው ስለጠየቁ የቤቱን ሁኔታ በተመለከተ እንደሚከተለው ቀርቧል ይላል።
ወይዘሮ ደብሪቱ ሣህለማርያም በይርጋለም ከተማ በከፍተኛ 1 ቀበሌ 06 የቤት ቁጥር 245 የሆነ የግል ቤት ስለነበራቸው አሁን በያዙት በኤጀንሲው ቤት እየተካካሠላቸው ይኖራሉ። በዚህም መሠረት የግል ቤታቸውን ከአዋጅ በኋላ ብር 42.00 (አርባ ሁለት ብር) እንደሆነ ግለሰቧ የቤቱ ኪራይ ትክክል አይደለም እንደገና ይገመት በማለት በኪራዩን ብር 85.00 ከፍ አድርገው በማስገመታቸው በ85 እና በብር 42 መሃል ያለውን ውዝፍ እንዲከፍሉ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በፍርድ ሸንጎ ተከሰው ጉዳዩ በክርክር ላይ እያለ በክፍለሃገር ያለ የግል ቤት ያላቸው እየተካካሠላቸው የሚኖሩ ግለሠቦች ከየካቲት 1985 ዓ.ም ጀምሮ ማካካሡ ቆሞ ሙሉ ኪራይ እንዲከፍሉ በወጣው መመሪያ መሠረት ሲጠየቁ ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በፍርድ ቤት ተከሠው ለረዥም ጊዜ ክርክር ከተካሄደበት በኋላ የከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀን 29 ህዳር 1997 በዋለው ችሎት ተከሣሽዋ ቀድሞ ሲደረግላቸው በነበረው የቤቱ ኪራይ እንዲካካስላቸው ወስኗል።
የከፍተኛ ፍርድ ቤት በሠጠው ውሣኔ መሠረት የህግ አገልግሎት ግለሠብዋ የግል ቤታቸውን መረከብና አለመረከባቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቤታቸውን የሚረከቡ ከሆነ የኤጀንሲውን ቤት መልሠው ለማስረከብ ግዴታ እንዲገቡ ተደርጎ የቤት ኪራይ ውል ሊታደስላቸው እንደሚችል በ21/6/99 በቁጥር 90/13-03-997/299 ለቀጠናው ደብዳቤ ተጽፏል።
ፍረዱልኝ ባይ አቶ ዮናስ ለዝግጅት ክፍሉ ያመጡት ሰነድ እንደሚያመለክተው፤ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ‹‹ለረዥም ጊዜ ያልከፈሉትን ውዝፍና የወቅቱን የኪራይ ልዩነት ካስከፈልን በኋላ እዳ የሌለባቸው መሆኑን ውላቸው ሊታደስላቸው እንደሚችል ለዋና ክፍሉ በ22/5/99 በቁ. 4/2049/99 ደብዳቤ መጻፋችንን እያስታወስን፤ አሁንም የቤቱ ዝርዝር ሁኔታ ከላይ እንደገለጽነው ሆኖ የቤቱንም ኪራይ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2002 ዓ.ም አጠናቀው የከፈሉ ስለሆነ ሁኔታው ታይቶ አስፈላጊው ይፈጸምላቸው ዘንድ እንጠይቃለን›› ማለቱን ሰነዱ ያመለክታል።
ወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማሪያም ከ1974 ጀምሮ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው እስከ 2003 ዓ.ም ለ29 ዓመታት በዚሁ ቤት ወልደው ከብደው ሲኖርበት እንደነበር ማስረጃዎቻቸው ያሳያሉ።
አሁን በቤቱ እየኖሩ ያሉ አቤቱታ አቅራቢ
የቅሬታ አቅራቢ አቶ ዮሴፍ አበበ ይባላሉ። የሟች የወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማሪያም ልጅ ናቸው። አቶ ዮሴፍ እንደሚናገሩት፤ አሁን ያሉበትን ቤት የደርግ መንግሥት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት ለማድረግ ባወጣው በአዋጅ 47/67 መሠረት እናቴ በህይወት ሳለች በይርጋለም ከተማ የምትኖርበትን የራሷ ቤት ለመንግሥት እንድትሰጥ በመደረጉ ምክንያት በምትኩ የቀድሞ ስሙ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የሚያስተዳድራቸው ኪራይ ቀመስ ማካካሻ የሚሰጡ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 997 ልዩ ስሙ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም አካባቢ መናፈሻ ገባ ብሎ የሚገኝ ቤት የተሰጣቸውና በኪራይ ውል 1974 ዓ.ም መሠረት የተፈጸመ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሆኖም ግን በይርጋለም ከተማ ያለው መንግሥት የወረሰው ቤት በመሐንዲሶች ብር 85 የተገመተ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በኪራይ ቤት የተሰጣቸው ቤት የዋጋ የኪራይ ተመን ብር 144 ነበር። በሁለቱ ቤቶች ተመን መካከል ያለው የዋጋ ተመን ልዩነት ምክንያት ቅሬታ የገባቸው እናታቸው በይርጋለም ከተማ ያላቸው ቤትና በአዲስ አበባ ከተማ ከተሰጣቸው ቤት በመጠንና በስፋት እኩል አይደለም በማለት ‹‹የተወረሰብኝ ቤት ትልቅ ስለሆነ የዋጋ ግምት ሊስተካከል ይገባል እንዲሁም በዚያ ምትክ ካርታ ሊሰጠኝ ይገባል›› በማለት ረጅም ዓመታትን በፍርድ ቤት ሲከራከሩ መቆየታቸውን ይናገራል።
ጉዳያቸው እልባት ሳያገኝ ረጅም ጊዜ የተከራከሩ ቢሆንም፤ በ1997 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አግኝቶ የሁለቱን ቤቶች የቤት ኪራይ ልዩነት መጠን እየከፈሉ እንዲጠቀሙ እንዲተወሰነላቸው የሚናገሩት አቶ ዮሴፍ፤ ቤቱን እናታቸው በተወረሰባቸው ቤት ምትክ ያገኙት ኪራይ ቀመስ ማካካሻ መሆኑ ተጠቅሶ የሁለቱን ቤቶች የኪራይ የውል ኪራይ ልዩነት መጠን ያህል እየከፈሉ እንደነበር ይናገራሉ።
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ የተሰጣቸው ቤት የኪራይ ዋጋ ብር 144 ሲሆን፤ በይርጋለም የሚገኘው መንግሥት የወረሰው ቤት በመሐንዲሶች
የተሰጠው የግምት ዋጋ ብር 85 ነው። ስለዚህ በሁለቱ ቤቶች መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት መጠን ብር 60 ከ45 ሣንቲም እንዲከፍሉ ግዴታ ተጥሎባቸው በየዓመቱ የሚታደስበት ውል መሠረት እየከፈሉ መኖራቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ደብሪቱ ይርጋለም የሚገኘው ቤታቸው በመሐንዲስ የተወሰነው ውሳኔ ዋጋ ‹‹ ከ85 ብር በላይ ነው›› በሚል ለረጅም ጊዜያት ያደረጉት ክርክር ውሳኔ ሳያገኝ ቢቀርም በ1997 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰነው ውሳኔ ቤቱን በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት በማካካሻ መሆኑን ገልፆ፤ ውሳኔ ያስተላለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ዮሴፍ እንደሚሉት፤ በቅርብ ጊዜ በ1985 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ እነዚህን የኪራይ ቤቶች አስመልክቶ በተጻፈ ደብዳቤ በክልል 14 ውስጥ የሚገኙ ኪራይ ቤቶች ሌላ የተለየ መመሪያ እስኪመጣ ድረስ ባሉበት ይቆዩ የሚል እንደነበር ይናገራሉ። በ2002 እንዲሁም ለኤጀንሲ በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት የኪራይ ውሉ ለማደስ ጥረት ቢያደርጉም በወቅቱ የነበሩ የኪራይ ቤቶች አመራሮች ይህንን ችግር ሳይፈቱላቸው በመቅረታቸው ጉዳያቸው ረጅም ጊዜ በእንጥልጥል ቆይቷል። በዚህም የተነሳ ሲበሳጩ የነበሩት እናታቸው፤ በየጊዜው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሄድ ክርክራቸውን ሳያቋርጡ ቢቀጥሉም በቤቱ ክርክር ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት ሲጉላሉና ሲንገላቱ ቆይተው፤ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት በ2003 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ቅሬታ አቅራቢ አቶ ዮሴፍ አበበ ገለጻ፤ በ1976 ዓ.ም ተወልደው በዚሁ ቤት አድገዋል። ከእናታቸው ጉያ ሳይወጡ ከእናታቸው ጋር አብረው በአንድነት እየኖሩ ሳለ እናታቸው በመታመማቸው ምክንያት እሳቸውም እናታቸውን እያስታመሙ በውሉ መሠረት የሚጠበቅባቸው የመንግሥት የቤት ኪራይ ሳያቋርጡ በየወሩ እየከፈሉ እናታቸው በ2003 ዓ.ም ባደረባቸው ህመም ህይወታቸው አልፏል።
ከእለተ ውልደታቸው ጀምሮ እስከ እድገታቸው ድረስ በዚሁ ቤት ተወስነው ለ37 ዓመታት የኖሩት አቶ ዮሴፍ፤ በዚሁ ቤት ወግ ማዕረግ አይተው ለትዳር የበቁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ባለ ትዳርና የልጅ አባት ናቸው። አቶ ዮሴፍ፤ ሌላ የአእምሮ ህመምተኛ እህታቸውን ጨምረው አራት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ሲሆን፤ በመንግሥት መስሪያ ቤት በሹፌርነት ሙያ እየተዳደሩ ይገኛሉ።
እናታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ቀንበር በእርሳቸው ላይ በመውደቁ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በማለት ቤተሰብ ከማስተዳደር በዘለለ የሚጠበቅባቸውን የቤት ኪራይ ሳያስተጓጉሉ በየወሩ ለመንግሥት እየከፈሉ ቆይተዋል።
ከእናታቸው ሞት ጋር ተያይዞ የወራሽነት መብት ለማረጋገጥ ‹‹ሟች ወልዳ ተንከባክባ አስተምራ ለቁም ነገር አብቅታኛለች እና ልጅነቴና ወራሽ መሆኔ ይረጋገጥልኝ ›› ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ማስረጃ መሠረት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁ.1898/03 ላይ በ23/5/2003 ዓ.ም በተሰጠ ውሳኔ መሠረት አቶ ዮሴፍ የሟች ወይዘሮ ደብሪቱ ሳህለማሪያም ልጅ ስለመሆናቸው በፍርድ ቤቱ አረጋግጠዋል።
በዚህ መሠረት የፍርድ ቤት የወራሽነት ይገባኛል የመብት ጥያቄ ይዘው የመንግሥት የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ዘንድ ቀርበው በተደጋጋሚ በመመላለስ ህጋዊነታቸውን ለማረጋገጥ ሙከራ ቢያደርጉም አቤቱታቸውን ቢያሰሙም በወቅቱ የነበሩት ኃላፊዎች ሊሰሟቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
ቤቱ በአዋጅ 47/67 በሚባለው በደርግ የተወረሰ ማካካሻ ቤት በመሆኑ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የመንግሥት ሳይሆን በራሳቸው በይርጋለም ከተማ በእናታቸው ስም የተመዘገበ ቤት ምትክ የተሰጠ ቤት ነው ብለው ለማስረዳት ያደረጉት ሙከራ ሰሚ አልባ ከመሆኑም ባሻገር፤ እንዲያውም እናታቸው ሳይቀሩ የኪራይ ውል የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ ቤቱን በህገወጥ መንገድ ነው የያዛችሁት ስለዚህ ቤቱን መልቀቅ አለባችሁ በማለት በተለያዩ ጊዜያት ሊያስወጧቸው መሞክራቸውን ይናገራሉ።
አሁንም ይህ ችግር ሳይቀረፍ በመቅረቱ ምክንያት ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ቤቱ የእናንተ አይደለም መልቀቅ አለባችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ቤቱን በማሸግ በሃይል ቤቱን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ ይህ ለምን ይሆናል ብለው ሲጠይቁ ቤቱን በጉልበት እንደያዙት እየተነገራቸው መሆኑን እና ጫናና ግፊት እየበዛባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
የቅሬታ አቅራቢው ዝርዝር አቤቱታ
ቅሬታ አቅራቢው አቶ ዮሴፍ እንደሚናገሩት፤ እናታቸው ከሞቱ በኋላ ወደ መንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ እየተመላለሱ በፍርድ ቤት የተሰጣቸው የወራሽነት መብት ለማስጠበቅ የሚያስችለውን ውሳኔ በ2003 ዓ.ም አያይዘው ለኤጀንሲው ገቢ አድርገዋል። በወቅቱ አንዲት አክስታቸው የወራሽነት መብት ይገባኛል በሚል ክስ በመመስረታቸው ምክንያት ቤቱ በፍርድ ቤት እግድ እንዲቆይ ተደርጓል።
ከዚያም የፍርድ ቤቱ እግድ ሳይነሳ አክስታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ መለየታቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን የቤቱ ኪራይ እንዳይቋረጥ ወቅቱ እየጠበቁ በየወሩ ለመንግስት ሲከፍሉ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህንን ሂደት ለማስቀጠል ህጋዊ ወራሽነታቸውን ለማረጋገጥ በሚችሉበት ወቅት እሳቸው ከ2009 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ከሦስት ዓመት በላይ ለሥራ ጉዳይ ክፍለ ሀገር መቆየታቸውን ይናገራሉ።
በእነዚህ በሥራ በቆዩባቸው ዓመታት ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ምክንያት ተጠቅሶ የተጻፈ ደብዳቤ፣ የቤተሰብ ወራሽነት የተረጋገጠበትና የኪራይ ውል ማስረጃዎች ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ ፤ እናታቸው ውል ከፈጸሙ ጊዜ 1974ዓ.ም ጀምሮ በቤት ኪራዩ ውል መሠረት አንድ ጊዜ እንኳን ሳይቋረጥ ኪራይ እየከፈሉ መቆየታቸውን ይገልጻሉ ።
የቤት ኪራዩን በየጊዜው ለመክፈላቸው ማስረጃ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነት በ2013 ዓ.ም በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ቁጥር 2028429 በቀን3/2/2013ዓ.ም ከሐምሌ 12 እስከ ጥቅምት 13 ድረስ 160.27(አንድ መቶ ስልሣ ብር ከ27 ሳንቲም) መክፈላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ደረሰኝ እንዳላቸው አሳይተዋል።
ሆኖም ግን በድጋሚ በዚሁ ዓመት በህዳር ወር መግቢያ አካባቢ ምክንያቱን በማያውቁት ሁኔታ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቱ የእናንተ አይደለም፤ የኪራይ ውል ስለሌላቸው ህጋዊነት የላችሁም፤ የገባችሁት በህገ ወጥ መንገድ ሰብራችሁ ነው በሚል ምክንያት ክርክር አንስቶ ከነቤተሰቦቻቸው አውጥተው ጎዳና ላይ ሊጥሏቸው እንደነበር ይገልጻሉ።
ኮርፖሬሽኑ ዘንድ በመሄድ በተደጋጋሚ ‹‹ከነቤተሰቦቻችን ሜዳ ላይ አውጥታችሁ አትጣሉን ይህንን ሁሉ ቤተሰብ ይዤ የት ልግባ ህጉስ ለምን አይፈቅድልኝም›› በሚል ቅሬታቸውን ቢያሰሙም ደጅ ቢጠኑም ለማስረዳት ቢሞክሩ ሰሚ ማጣታቸውን ይናገራሉ።
‹‹የኮርፖሬሽን ሠራተኞች መጥተው ቤቱን ያለአግባብ በሃይል አሽገውት ይሄዳሉ። ይህ ተግባራቸው እያንገላታን ላልተፈለገ ወጪ እየዳረገን እና በነጻነት የመኖር ሰብዓዊ መብታችንን የሚጥስ ነው›› ካሉ በኋላ፤ በወቅቱ አቶ ዮናስ እግድ እንዳላቸው ገልፀው ከፍርድ ቤት ያመጡትን ቢያሳዩም ቤቱን ለማሸግ የመጡት ሰዎች በግድ ሃይል በመጠቀም አሽገው መሄዳቸውን ተናግረዋል።
እርሳቸው በወቅቱ ‹‹እኔ ምንም መግቢያ ቀዳዳ የሌለኝ ሰው ነኝ። ቤቴ እንዴት ይታሸጋል›› በማለት ሰብረው መግባታቸውን እና ታስረው 1ሺህ ብር መቀጣታቸውን ገልጸዋል። ጨምረውም በእርሳቸው ሥር የሚተዳደሩ የቤተሰብ አባላት ይዘው እንዴት ሜዳ ላይ እወድቃለሁ ብለው ጉዳዩን በድጋሚ ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰዱት ይናገራሉ።
በዚህ መሠረት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 14ኛ ፍ/ብሔር ችሎ ከሳሽ ከውልም ሆነ ከህግ የመነጨ መብት የሌለውና ክሱን በተገቢው ጊዜ ያልቀረበ በመሆኑ ምክንያት ብይን መስጠቱን ይጠቅሳሉ።
እንደ ቅሬታ አቅራቢ ገለጻ፤ እነርሱ በኪራይ እንዲኖሩበት የተሰጠው ቤት በአዋጅ 47/67 መሠረት በይርጋለም ከተማ የሚገኘው የቤት ምትክ የተሰጠ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ቤቱን በበላይነት ያስተዳድር እንጂ በቤቱ ላይ ሙሉ መብት እንደሌለው ጠቅሰው፤ የሚያስተዳድርበት ምክንያት ያንን በሁለት ቤቶች መካከል ያለውን የዋጋ ተመን ልዩነት ኪራይ ውሉ መሠረት ለመቀበል ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹እኛ ይህንን መኖሪያ ቤት ከተቀበልን በኋላ የምንጠቀመው ለመኖሪያነት አገልግሎት እንጂ ለሌላ አልነበረም›› ካሉ በኋላ፤ በቤቱ ላይ የጨመሩትና የቀጠሉት ምንም ነገር በሌለበት እና እንደቤታቸው እያዩ ሲኖሩ ቆይተው ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ ግራ የሚያጋባቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
ቅሬታ አቅራቢው እንደሚሉት ‹‹እኔ ይህንን የምለው አላግባብ የሰውንም ሆነ የተቋምን ስም ለማጠልሸት ዓላማ ኖሮኝ ሳይሆን መብቴ ያለአግባብ እንዲነጠቅ ስለማልፈቅድ ነው›› የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ አሁን ላይ እርሳቸው በሚኖሩበት ቤት አጠገብ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥር ያሉ አራት ክፍት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እስካሁን ለማንም ያልተሰጡ መሆናቸውን እና እነዚህ ቤቶች የመንግሥት ሠራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይሆን ቤቶቹን ሲኖሩባቸው የነበሩት በጣም ሀብታም ሶስትና አራት ቤት ያላቸው እና ቤቶች እያከራዩ የሚኖሩ መሆናቸውን በማስታወስ፤ እንዲህ ተደራራቢ ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች እያሉ እነርሱ ግን ተቋሙ ፋይሉን በዘመናዊ መንገድ ባለማደራጀቱ እና በኋላቀር አሠራሮቹ ምክንያትና ከሰነድ አያያዝ ጋር በተያያዘ በሚታዩ ክፍተቶች መጎዳት የሌለባቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ተቋሙ በየዓመቱ የቤት ውል እድሳት ሲያደርግ የተቋሙ ሠራተኞች እና ባለሙያዎች ቤት ድረስ በመምጣት ቤቱን አይተው ገምግመው ማረጋገጥ እያለባቸው የቤት እድሳት መከናወን ቢኖርበትም፤ ቤቶቹ ተጨማሪ ግንባታዎችና ከመንግሥት እውቅና ውጪ ወደ ሌላ የሚካተቱበት ወደ ግል የሚዞርበት ሁኔታ ያለ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህ ባለበት ሁኔታ ተቋሙ ራሱን ዘመናዊ ባለማድረግ የተነሳ በተፈጠረ የአሠራር ክፍተት ዜጎችን ለእንግልት መዳረግ የለበትም። ህግና መመሪያውን ጥሶ በየምክንያቱ እነርሱን ከቤት ለማስወጣት የሚፈለግበት ምክንያት ቤቱ ከእነርሱ በላይ የተቸገረ አካል ኖሮ ለመስጠት ሳይሆን ለሌላ ዓላማ ለማዋል ታሰቦ ነው ይላሉ።
ህጋዊነታችን የሚገልጽ ማስረጃ እያለ ነጋ ጠባ ሁከት በመፍጠር ከቤታቸው ሊያስወጧቸው የሚፈልጉ መሆኑን እና ስለዚህ ከነቤተሰቦቻቸው ጎዳና ላይ ሳይወድቁ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ሳይጋለጡ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸውን ሲሉ ይጠይቃሉ።
‹‹እኛም የሀገሪቱ ዜጎች ነንና እንደማንኛውም ዜጋ ጉዳያችን ጊዜ ተሰጥቶት ተጣርቶና ታይቶ በቤታችን በሰላም እንድንኖር ይፈቀድልን ›› የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ በአሁኑ ሰዓት ወላጆቻቸው በማረፋቸው ምክንያት ከጎናቸው ሆኖ የሚያግዛቸው ዘመድ የሌለ በመሆኑና የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦቻቸው ለሥራ ያልደረሱና የአእምሮ ህመምተኛ እህት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በሹፌርነት በሚያገኙት አነስተኛ ደመወዝ ኑሮ ከእጅ ወደአፍ ሆኖባቸው በሚገኝበት በዚህ ሰዓት ከቤት ልቀቁ መባላቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
ስለዚህ ይህ ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት እንደማንኛውም ሰው መብታቸው ተጠብቆ ተወልደው ባደጉበት ቤት ያለምንም ስጋትና ሁከት ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ እንዲመቻቸላቸው ሲሉ ለህዝብና ለመንግስት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምላሽ
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረ መድን ስለጉዳዩ ተጠይቀው እንደሚገልጹት፤ ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት የታየና ብይን የተሰጠበት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ፍርድ ቤት ብይን በሰጠው ጉዳይ ላይ ተቋሙ የሚሰጠው አስተያየት የለም፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብሏል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 05/2013