ራስወርቅ ሙሉጌታ
ወይዘሮ ሰላማዊት ማሞ ትባላለች ትውልዷም እድገቷም አዲስ አበባ እምብርት አራት ኪሎ አካባቢ ነው። ሰላማዊት ገና በልጅነት እድሜዋ የገጠማት ችግር ብዙዎችን ከቤት በማዋል የሰው እጅ ጠባቂና ፍሬ አልባ የሚያደርግ ቢሆንም እሷ ግን በራሷ ብርታትና ጥረት እንዲሁም በቤተሰቦቿ ጠንካራ ክትትል ዛሬ ከራሷ አልፋ ለሌሎችም ለመትረፍ በቅታለች። ይህንን ሁሉ ለማድረግ የተጓዘችበት መንገድ ግን የሷ ጽናትና ብርታት መጨረሻውን አሳመረው እንጂ እንዲህ ቀላል አልነበረም።
ሰላማዊት ከልጅነቷ ጀምሮ ያሳለፈችውን ዘመን እንዲህ ታስታውሰዋለች። ሰላማዊት ተወልዳ ከአመት በላይ እስኪሆናት ድረስ ሙሉ ጤነኛና እንደ ልብ በእግሯ ድክ ድክ እያለች የምትጫወት ልጅ ነበረች። በአንድ ወቅት ግን ከፍተኛ የትኩሳት ህመም ገጥሟት ስለነበር ወደ ሆስፒታል በማቅናት ለአንድ ዓመት አልጋ ይዛ ለመተኛት ትበቃለች። በዚህ ወቅት ነበር መነሻው ምን እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም ለእግር አካል ጉዳተኝነት ለመዳረግ የበቃችው። በወቅቱ አባቷ በጦር ግንባር በግዳጅ ላይ ስለነበሩ እናቷ ጌጣ ጌጦቻቸውን ከመሸጥ ጀምሮ በርካታ ሙከራዎችን በማድረግ ጤናዋን ለመመለስ በሁሉም አቅጣጫ ቢሞክሩም ሳይሳካ ይቀራል ።
ይህም ሆኖ ቤተሰቦቿ ያደርጉላት የነበረው ክትትልና የሞራል ድግፍ እንደማንኛውም ልጅ ከእኩዮቿ ጋር ያሻትን ተጫውታ እንድታድግ በር ከፍቶላታል። ያ ዘመን ደግሞ ለእሷ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ዛሬ ላለችበት ሁኔታ መሰረት የጣለላትም ነበር «ገመድ ዝላይ ሳይቀር እጫወት ነበር» የምትለው ሰላማዊት በርካታ ጊዜያት የአካል ድጋፏን ስትጫወት ትሰብር እንደነበር ነገር ግን ጓደኞቿ ተንሸራታ ስትወድቅ ተሰብሮባት ነው እያሉ ያስተባብሉላት እንደነበር ታስታውሳለች። የበታችነት ስሜት እንዳያድርባት በማለት ቤተሰቦቿ እኩል ስራ ያዟታል እሷም ትሰራለች። ስራ ስትሰራ ደግሞ ከምትታዘዘው የሚያደክሙትንና ብዙ ልፋት የሚጠይቁትን ትመርጥ ነበር።
በዚህም ታላቅ ወንድሟ “ይደክምሻል አትችይም” ሲል እሷ ደሞ “የማልችለው የለም” እያለች ሁል ጊዜ ከእሱ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ትገባ ነበር። እናቷ የሚንከባከቧትን ያህል አላግባብ አጥፍታ ስትገኝ ደግሞ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ጥሩ አድርገው ይቀጧትም ነበር ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የነገ ተስፋዋ እንዳይጨልም በማለት እድሜዋን ሳያዛንፉ ያለባትን ችግር ምክንያት ሳያደርጉ በወቅቱ የትምህርት ገበታ እንድትቀላቀል አድርገዋት ነበር። በዚህም በዳግማዊ ምንሊክ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርቷን ተከታትላ ለማጠናቀቅም በቅታለች። ሰላማዊት በትምህርት ቤት ቆይታዋም ከእሷ ብርታት ባለፈ ጓደኞቿና መምህራኖቿ በጥሩ ሁኔታ ይንከባከቧት እንደነበር ታስታውሳለች። ከዚህ በኋላም ናሽናል ኮሌጅ በመግባት በቢዝነስ ኢንፎርሜሽን ሲስተም በዲፕሎማ ለመመረቅም በቅታለች። የኮሌጅ ትምህርቷን በጀመረችበት ወቅት ግን ሁኔታዎች እንደ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቷ አስደሳች አልነበሩም።
ጊቢው አዲስ ስለሆነባትም የመጀመሪያዎቹን ወራት ታሳልፍ የነበረው ከሰው በመገለል ብቿዋን ነበር። አንዳንድ ጊዜም አብረዋት የሚማሩትን እሷ በድፍረት ተጠግታ አብራቸው ልታወራ ልትጫወት ስትሞክር ያሳዩዋት የነበረው ሁኔታ ደስታ ስለማይሰጣት እሷም ትመርጥ የነበረው መገለሉን ነበር። ከወራት በኋላ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለባት ስለወሰነች በመተላለፊያ ደረጃዎች ላይ በመቀመጥ ትከታተላቸው ጀመረች። አንዲት ብስራት የምትባልና ዛሬም ድረስ ጓደኛዋ የሆነች ልጅ ቀርባ ታናግራት ትጀምራለች። ከእሷ ጋር መግባባት ከጀመረች በኋላ ግን ከሌሎቹም ጋር ያላት ግብቡነት እየጨመረ መምጣት ይጀምራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ታካሂድ በነበረው የስነ ጽሁፍ ውድድርና የግጥም ማንበብ እንቅስቃሴ ነገሮች ሁሉ እየተስተካከሉ እንደ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቷ ሁሉ እዚህም ያለው ማህበረሰብ ቀላልና ተግባቢ እየሆነላት ይመጣል።
ቤተሰቦቿ ያደርጉላት የነበረው ድጋፍና ክብካቤ በአካባቢዋ ላሉ ነዋሪዎችም ምሳሌ ስለነበር የሰፈሩ ሰው ይቀበላት የነበረው እንደ እናትና አባቷ ጠንካራ ጎበዝ አድርጎ ነበር። «ጥላዬን ካላየሁ አልያም መስታወት ፊት ካልቆምኩ አካል ጉዳተኝነቴን አላስታውሰውም ነበር» የምትለው ሰላማዊት በአካል ጉዳተኝነቴ እንዳልሳቀቅ፤ ማድረግ የፈለኩትንም ነገር ለማድረግ እንዳልገደብ የቤተሰቦቼ ክትትል በር ከፍቶልኛል ትላለች።
በዚህ አይነት የትምህርት ጊዜዋን ያን ያህል አስቸጋሪ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ ብትችልም ተመርቃ ስራ ለመቀጠር መንቀሳቀስ ስትጀምር ግን ነገሮች እንዳሰበቻቸው ቀላል ሳይሆኑ ይቀራሉ። ምክንያቱ ደግሞ የእሷ አቅም ማነስ አልያም ብቁ ሆኖ አለመገኘት ሳይሆን ተማሩ የሚባሉትን ሰዎች ጨምሮ በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያላቸው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ ነበር። «ምንም እንኳ የስራ አጥነቱ ችግር ሁሉንም የሚመለከት ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ግን ምንም የማይገናኝና ብቃት ቢኖረውም አካል ጉዳተኛን ቀጥሮ ለማሰራት ፍራቻ አለባቸው» የምትለው ሰላማዊት ገጠመኞቿን እንደሚከተለው ታስታውሳለች።
አንዳንድ ተቋማት የትምህርት ማስረጃዎችን ሲቀበሉ በአንድ ጥግ የአካል ጉዳተኛ እያሉ ከሚጽፉት ነገሮች ጀምሮ በርካታ ማግለሎች ይስተዋላሉ። በዚህም ምክንያት ለስራ ቅጥር ሲኬድ አንዳንዶቹ አቀባበሎችና ሁኔታዎች በጣም ተስፋ የሚያስቆርጡ ስለነበሩ የትምህርት ማስረጃዎቿን በአካል ተገኝታ ከማቅረብ ይልቅ በሰው እንዲገባ ታደርግም ነበር። ይህም ሆኖ ለፈተና መቅረቡ የግድ በመሆኑ ሊታወቅ በሚችል መልኩ እንዳታልፍ ትደረግ የነበረበት ጊዜ ነበር።
በአንድ ወቅት የግድ ስራ መጀመር ስለነበረባት በአንድ የምታውቀው ተቋም ውስጥ ከደረጃዋ ወርዳ ለመወዳደር ትሄዳለች፤ እዛ ደርሳም ከሌሎች አመልካቾች ጋር ተሰልፋ ተራ ደርሷት ስትገባ የስራ ቅጥሩን የሚፈጽመው ባለሙያ ስራውን ግን ታውቂዋለሽ? እንዴት ልታመለክች መጣሽ? ሲል በመደነቅና በማናናቅ ይጠይቃታል። ሰላማዊት ከዚህ በፊት የተቋሙን አገልግሎት ትጠቀም ስለነበር ያንኑ በማስታወስ «አገልግሎታችሁን ስጠቀም አካል ጉዳተኛ ነሽ ብላችሁ አላስቆማችሁኝም፣ አሁን ለስራ መቀጠሩ እንዴት ትከለክሉኛላችሁ። በምንስ መስፈርት በምንስ ህግ ነው የማታወዳድረኝ» በማለት መነጋጋር ብትጀምርም የሰውየውን ግትርነት በማየት ምንም ለውጥ እንዳማታመጣ ስትረዳ ወደ ዋና ስራ አስኪያጁ ታቀናለች።
እዛም ስትደርስ ራሱ ቀጣሪው ያገኛትና በድጋሚ ብቁ ስላልሆንሽ ልቀጥርሽ ፈቃደኛ አይደለሁም በማለት ሊመልሳት ይሞክራል። አሁንም እሱን በማለፍ የሰራተኛ ቅጠር አዋጁን በመያዝ ምክትል ስራ አስኪያጁ ጋር ትደርሳለች ነገር ግን እዛም አመርቂ መልስ ሳይጣት ይቀርና ተመልሳ ወደ ዋና ስራ አስኪያጁ ይመሯታል።
ዋና ስራ አስኪያጁ ነገሩን በማመዛዘን ባመለከተችበት ሳይሆን በሌላ ቦታ ቅጥሩ እንደሚገባት ቢወስኑም እሷ ግን በዛ ሁኔታ ከተነጋገረቻቸው ሰዎች ጋር መስራት ስላልፈለገች ቅጥሩን ለማቋረጥ ትወስናለች። በአሁኑ ወቅት የምትሰራበት ተቋም በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዙሪያ የሚሰራ በመሆኑ መተሳሰቡ መደጋገፉም እንዳለ በመግለጽ አብዛኛው አካል ጉዳተኛ ከብቃት ማነስ ሳይሆን ማግለሉን ለመቋቋም ችግሩን የሚረዳ ተቋም ውስጥ መስራት እንደሚመርጥ ትናገራለች።
በተመሳሳይ ግጥም፤ መጣጥፍ፤ ልብወለድ መጻፍ የምትወደው ሰላማዊት በአንድ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ የግጥም ውድድር ላይ ለመሳተፍ ስትሄድ ከእሷ በፊት የገባ አካል ጉዳተኛ ተወዳዳሪን ተቀባዩዋ ወረቀቱ ላይ አካል ጉዳተኛ ብላ ስትጽፍበት ያየችው ነገር ዛሬም ድረስ እንደሚረብሻትና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት እንዲስተካካል በዙ መሰራት እንዳለበት ትናገራለች።
ሰላማዊት በአሁኑ ወቅት ስፖርት ኤንድ ኬር በሚባል ድርጅት በሴክሬተሪ ካሸርነትና በሌሎች የሂሳብ ነክ ፕሮጀክቶችም ላይ በአስተዳደርነት እየሰራች ሲሆን የሁለት ልጆች እናትም ለመሆን በቅታለች።
አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞች ትዳር በመመስረት ቤተሰብ ለማፍራት የሚገጥሟቸው በርካታ መሰናክሎች አሉ የምትለው ሰላማዊት ምንም ቢሆን ግን ብርታቱና ጽናቱ ካላቸው ካሰቡበት ለመድረስ እንደሚችሉ የራሷን ተሞክሮ በማንሳት ትመክራለች። በመጀመሪያ ወደ ትዳር ለመግባት የሚያስሩም የሚያሰጉም ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በጥንቃቄ መታለፍ አለባቸው እንጂ በፍራቻ ታስሬ መቀመጥ ስላልነበረብኝ ደፍሬ በመግባቴ ዛሬ ለመኖሬ ምክንያት የሚሆኑኝን ሁለት ወንድ ልጆችም ለማፍራት በቅቻለሁ። ባለቤቴም እኔነቴን የተቀበለና በራሴ እንዲተማመን የሚደግፈኝም በመሆኑ በምኖረው ህይወት ደስተኛ ህይወት በመምራት ላይ እገኛለሁ ትላለች።
ከሁሉ በላይ ግን አካል ጉዳተኞች በስራ ብቻ ራሳቸውን እንዲችሉ ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው አግብተው ወልደው ቤተሰብ መስርተው እንዲኖሩ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት የምትለው ሰላማዊት። በመጀመሪያ ደረጃ የእምነት ተቋማት ከስብከታቸው ጀምሮ ትኩረት ሊሰጡበት የሚገባው ነገር አካል ጉዳተኝነትን እንደ እርግማን ማየትን፤ የሚፈጸሙ የሃይማኖት ሥርዓቶችንና ጸሎቶችን የሚያካሂዱባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት፤ ተመጽዋች እንዲሆን ሳይሆን ስራ እንዲሰሩ እንዲጣጣሩ ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋል።
በመንግስት በኩልም እንዳጠቃላይ ጥሩ ፖሊሲዎች የወጡ ቢሆንም የማስፈጸሚያ አዋጆችና መመሪያዎች ላይ ሰፊ ጉድለት አለ። በርካታ ዓለም አቀፍ ህጎች ተፈርመው ተቀምጠዋል። በመሆኑም፤ እነዚህን በየደረጃው ማሟላትና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቃል። በቤተሰብም ረገድ አካል ጉዳተኞችን እቤት ወስጥ በማስቀመጥ ያላቸውን አቅም እንዳያወጡ እንዳይጥሩ ማድረግ በስፋት ይስተዋላል። አንዳንድ ጊዜም ምንም ሳይጎድል ለማሳደጊያ ድርጅት የሚሰጡም አሉ። ይሄ ሁሉ ከጥላቻ በመነሳት ሳይሆን ከተሳሳተ ባህልና ከማህበረሰብ ተጽእኖ ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የሚያደርጉት ነው።
በተጨማሪ አንዳንድ ቤተሰቦች አካል ጉዳተኞችን ትምህርት ቤት መላክ የመጨረሻ ግባቸው ያዳርጋሉ፤ ሻል ያሉት ደግሞ ስራ እንዲጀምሩ ሊያበረታቱና ሊገፋፉ ይችላሉ። ነገር ግን ትዳር እንዲመሰርቱ ልጆች እንዲወልዱና ቤተሰብ እንዲመሰርቱ የሚመክሩት በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው በመሆኑም ከዚህ አመለካከት ከይሉኝታ ከባህል በመውጣት አካል ጉዳተኞችንም እንደ አንድ ሙሉ ሰው በማየት በትክክለኛ የህይወት መንገድ እንዲጓዙ መምከርም መደገፍም ይጠበቅበታል።
እንደ ማህበረሰብም ሞራል እንኳን ለመስጠት የማይደፍሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወገን ሰው አንድ ነገር ስለሌለው ሁሉንም ነገር ማድረግ የማይችል አድርገው ይመለክታሉ። በሌላ በኩል አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሞራል የሚነካ ነገር የሚናገሩም የሚያደርጉም አሉ። ትዳር ለመመስረት አካል ጉዳተኝነት እንቅፋት ሊሆን አይችልም። ነገር ግን የማህበረሰብና የቤተሰብ ተጽእኖ ብዙ ነገሮችን እያበላሸ ይገኛል። ይሄ የተዛባና የተሳሳተ የማህበረሰብ አመለካከት በአካል ጉዳተኞች ላይ ብቻ የሚወሰንም አይደለም። በትዳር ምስረታ ወቅት አንዳንዱ በዘር በሃይማኖት እየተነሳ ጣልቃ የሚገባም እንዳለም ይታወቃል።
በመሆኑም ከሁሉም በላይ ራሱ አካል ጉዳተኛው ያለበትን ፈተና ለማለፍ በሞራልም በተግባርም ዝግጁ ሊሆን ይገባል። እኔ ምንም ያቅተኛል ብዩ ስለማላስብ በአሁኑ ወቅት ሁለት ልጆቼን ጨምሮ አምስት ቤተሰብ እያስተዳደርኩ እገኛለሁ።
ሁሌም የማስበው ነገር ግን ትናንት ስላሳለፍኩት ውጣ ውረድ ሳይሆን ነገ ላደርገው ስለምችለው ነገርና ላመጣ ስለምችለው ለውጥ ብቻ ነው። ሌሎችም አካል ጉዳተኞች የሌላቸውን ከማሰብ ይልቅ ከማህበረሰብ ተጽእኖ በመውጣት ማድረግ ያለባቸውን ቢያደርጉና መሆን ያለባቸውን ቢሆኑ ይሻላል ስትልም ሰላማዊት ምክሯን ታስተላልፋለች።
አዲስ ዘመን ጥር 05/2013