ገብረክርስቶስ
ከጁንታው የመቃብር ላይ ጽሁፎች
የሐይቁ ከረሞፋ መስጂድ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ያኔ ክፉ ደግ ያልለየሁ ሕጻን ነበርኩ። ቀኑን በውል ባላስታውሰውም ወርሃ-ሚያዚያ ማገባደጃ 1983 ዓ.ም ይመስለኛል። በእነዚያ ከባድ ጊዜያት የሆኑት ነገሮች ሁሉ እንደቅርብ ትውስታ ትናንት ያለፉ ያክል ሆነው ነው በሕሊናዬ ሰሌዳ ደምቀው የሚታወሱኝ።
ተወልጄ ያደኩበት የያኔው የወሎ ጠቅላይ ግዛት አካባቢ (በደሴ አቅራቢያ ሐይቅ ከተማ) በደርግ እና በትህነግ መራሹ ሰራዊት መካከል ተደጋጋሚና ከባድ ጦርነቶች የተካሄዱበት ስፍራ ነበር።
በወቅቱ ታዲያ አንድ ጊዜ ደርጎቹ ሲያሸንፉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወያኔ መራሹ ኃይል ሲያሸንፍ ድል ወዲያና ወዲህ ነበረች። ጦርነቱ ከባድ እልቂትን አስከትሏል።
የአገሬው ሰው “ተሀት” ይላታል ወያኔን – ደንበኛው የደደቢት የማለዳ ስሟ “ተጋድሎ ኃርነት ሕዝቢ ትግራይ” – ተአህት ስለነበር ነው የኛ አካባቢ ሰው ተሀት ይላት የነበረው። በአማርኛው “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትህነግ)” ነበር ስሟ።
ታዲያ “ተሀት መጣች” የተባለ እንደሆነ አካባቢው በሽብር ይናጣል፤ በጦርነት ምድሪቱ ቁና ትሆናለች። ወላጆች ጭንቅ ይገባሉ።
የተባራሪ ጥይት ሲሳይ እንዳንሆን እኛን ሕጻናትን አልጋ ካለ በየአልጋው ስር፤ አለዚያም ዙሪያውን ሳጥን፣ ብረት እና እንጨት እንደመከለያ ሰርተው ይደብቁናል። ልጆች ብርክ ይይዘናል።
የ1982 እና የ1983 ዓ.ም. ቀኖቻችን እንዲህ ነበሩ። በተለይ ቀኑን በትክክል ባላስታውሰውም በ1983 ዓ.ም የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በአገር አማን ትምህርት ቤት ሳለን ድንገት “ተሀት” ደርሳ ከተማዋ በጦርነት መናጥ ስትጀምር በፈጣሪ ተዓምር እግሬ አውጭኝ ሮጠን ነበር ወደየቤታችን የገባነው።
እናም ከእነዚያ የምጥ ቀኖች በአንደኛው ለዛሬ ከተነሳሁበት ርዕስ ጋር የሚገናኝ እውነት ሐይቅ ከተማ ላይ ተከሰተ – ጦርነቱ ተጧጡፎ ሕዝቡም በየቤቱ ጭንቅ ይዞት “እግዚኦ”፣ “ያ አላህ” እያለ ሲማጠን ዋለ። የኋላ ኋላ ጦርነቱ ጋብ ሲል ህዝቡም የተደበቀበትን የፍርሃት ቆፈን እያራገፈ ወጣ ወጣ ማለት ጀማመረ።
ከተማዋ ዛሬ ድረስ እንደተበደሉት የአማራ ክልል ከተሞች ሁሉ ያኔም የበሬ ግንባር የምታክል የአምባሰል አውራጃ መናገሻ ነበረች። ብዙም ሳይቆይ “ከረሞፋ ተደበደበ፤ ከረሞፋ ተመታ፤ ከረሞፋ ፈረሰ” የሚሉ ወሬዎች ከዚያም ከዚህም መናፈስ ጀመሩ።
“ከረሞፋ” ማለት በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኘው መስጂድ መጠሪያ ነው። “ከረሞፋ” የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ወደ አማርኛ አቻው ሲመለስ አሮጌው በር ማለት ነው።
ወሎ በተለይም ደቡቡ አካባቢ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ፍጹም በማይበጣጠስ የደም ትስስር የተሰናሰለበት ድንቅ ሕዝባዊ ሕብር ያለበት ነው። በዚህ የተነሳ የቦታዎች ስያሜዎች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛም ነው የተሰየሙት። “ከረሞፋ” ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው።
እናም በዚያ ቀን “ከረሞፋ ተመታ” ሲባል የከተማው ሕዝብ ለማየት ነቅሎ ወጣ። እኛም ወጥተን አየን። የሕዝቡ ብዛት የጦርነት ወቅት አይመስልም ነበር። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የመስጂዱ ሚናራ (ረዥሙ የመስጊዱ ክፍል) በአንድ በኩል ክፉኛ ፈርሷል።
እኔ ሕጻን ስለነበርኩ በወቅቱ የተሰማኝን ስሜት በእርግጠኝነት መግለጽ አይቻለኝም። አዋቂዎቹ (ቤተሰቦቼን ጨምሮ) የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማቸው አስታውሳለሁ፤ ዛሬም ድረስ የምናወጋው ትውስታችን ነው።
“እንዴትና በማን ተመታ?” የሚለው የወቅቱ ቁልፍ መነጋገሪያ ነበር።
ያኔ የተረጋገጠውና እስከዛሬም ድረስ መስጂዱ ካሳለፋቸው ጥቁር ታሪኮች ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው እውነታ ይህ ነው – የትህነግ ወታደሮች “አስመራ በር” እና “ጫጩቶ” በሚባሉት የከተማዋ ጥግጋት፤ የደርግ ወታደሮች ደግሞ ከወዲህ ማዶ “ሸህ ሙሳ ጎራ” እና “ዳውቻ” በሚባሉት ስፍራዎች በኩል ሆነው ውጊያ ያካሂዳሉ።
ከዚያም የትህነግ ወታደሮች ወደከተማዋ ዘልቀው ይጠጋሉ። ወዲያው ትህነጎቹ አንድ እግሩ የተቆረጠ ወታደራቸውን ከመትረየስ መሳሪያ ጋር በከረሞፋ ሚናራ ላይ በሸክም ያወጡታል።
ቆራጣው ትህነግ ታዲያ መትረየሱን በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው ወደ ሸህ ሙሳ ጎራ አጥምዶ የደርግ ወታደሮችን አጨዳቸው።
የደርግ ወታደሮች መትረየሱ ጥይቱን የሚተፋው ከከረሞፋ መስጅድ ላይ መሆኑን ሲያውቁ ወዲያው “በከባድ መሳሪያ” የመስጂዱን ሚናራ እንዳልነበር አደረጉት። (በምን ዓይነት ከባድ መሳሪያ እንደሆነ ያኔም ሆነ ዛሬ በትክክል የሚነግረኝ አላገኘሁም) ያ እግረ-ቆራጣ የትህነግ ወታደር ከሚናራው ፍርስራሽ ጋር አመድ ሆኖ ቀረ።
ከረሞፋ ውብ መስጂድ ነው። በጣም የሚያስደንቅ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የታየበት ልዩ መስጂድ ስለመሆኑ መናገሬ ጉንጭ ማልፋት ይሆንብኛል፤ የሚያውቁት በውበቱ ይስማማሉ።
እንዲያውም ልጆች እያለን ያኔ ከቀያቸው ወጣ ብለው ወደ ደሴ እና ወደ አዲስ አበባ ይበልጡንም ወደ አረብ አገራት ዘልቀው የተመለሱ ሰዎች የመስጂዱ አሰራር ጂዳ እና መካ ካሉት ጋር ይተካከል እንደሁ እንጂ ያኔ በኢትዮጵያ እንደዚያ የሚያምሩ መስጂዶች በጣት የሚቆጠሩ እንደነበር ሲያወሩ እናደምጥ ነበር።
የከረሞፋ ሌላው ውበት ደግሞ ወዲህ ነው – መስጂዱ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቤተክርስቲያን ጎረቤት ነው። በመልካም ጉርብትና ዝናቸው እንደናኘው እንደ መርካቶዎቹ አንዋር እና ቅዱስ ራጉኤል ማለት ነው።
ከረሞፋና ዮሐንስ በአጥር ነው የሚለያዩት (ያኔ አጥር አልነበራቸውም፤ አሁን ነው አጥር የተሰራው) የዮሐንስን ቅዳሴ የከረሞፋ አሊሞች፤ የከረሞፋን አዛንና ሰላት የዮሐንስ ካህናት ያደምጣሉ።
ትህነግ ይህንን የመሰለ መስጂድ ነበር ለእኩይ ዓላማዋ በመጠቀም ለጥቃት እንዲጋለጥ ያደረገችው። የመስጂዱ መመታት ደግሞ ሙስሊሙን ብቻ አልነበረም ያሳዘነው፤ ክርስቲያኑንም ጭምር እንጂ። ኢትዮጵያውያን በተለይም ወሎየዎች በዚህ አይታሙም።
መስጂዱ በዚህ መልኩ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወያኔ ወደ ቤተ መንግስት ገባች። ከረሞፋ ግን ከነጉዳቱ ቆይቶ ጊዜውን ባላስታውስም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ተጠግኖ ወደ ቀደመ ይዞታው ሊመለስ ችሏል።
“እርጥብ ሬሳ ደረቁን ያስነሳ” ይባላል። ዛሬ ላይ የቅርብ ዘመድ አልያም ብርቱ ወዳጅ ሲሞት ቀደም ብሎ ሞቶ የተቀበረውን ወዳጅ ዘመድ ስሙን እያነሳሱ ማልቀስ በአገራችን የተለመደ ባህል ነው።
እኔም በቅርቡ በትግራይ ክልል በሚገኘው የአልነጃሺ ታሪካዊ መስጂድ ላይ የተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ ከከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በሕሊናዬ ጓዳ የኖረውን ጥቁር ታሪክ እንዳስታውስ አስገደደኝ።
አልነጃሺ – ዳግማዊ ከረሞፋ
ከቀናት በፊት ተደጋግሞ ሲገለጽ እንደሰማነው የአልነጃሺ መስጂድ በትግራይ ክልል በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በጦር መሳሪያ ጉዳት ደርሶበታል።
በትህነግ እጅ የጎረሱ እና የዘረፋውን ጠበል የተቋደሱት በውጭ የሚገኙ ደጋፊዎቿ ከተቀበረች በኋላ መስጂዱን የመከላከያ ሰራዊት በጦር መሳሪያ እንደመታው አድርገው ለማወናበድ ይጥራሉ።
“ግራ የገባው ያጣ መላውን፤ግራ ያጋባል ደሞ ሌላውን” እንደሚባለው የእኩይ ግብር አባቶቻቸው በትግራይ ምድር እንደዝንጀሮ ገደል ለገደል እየተለቀሙ ሲታደኑ መላ-ቅጡ ቢጠፋባቸው የሀሰት ዘገባ በማሰራጨት ሕዝብን ግራ ለማጋባት ሲጥሩ ይስተዋላል።
እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። ወያኔ በአልነጃሺ ላይ ያደረገችው ተንኮል ከሰላሳ ዓመታት በፊት በሐይቁ ከረሞፋ ላይ ያደረገችው ዓይነት ነው። ይህንን ደግሞ የመስጂዱ ኢማሞችና ነዋሪዎችም ጭምር ያረጋገጡት ሐቅ ነው።
የነጃሺን መስጂድ አውቀዋለሁ። ቅዱሱን ስፍራ በእግሬ ረግጬ የእምነቱ ተከታይ ባልሆንም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያዎቹን የነቢዩ ሙሃመድን ሱሃባዎች መቃብር ዘይሬአለሁ። በኢትዮጵያዊነቴም ኮርቻለሁ። ይህ ስፍራ ታዲያ የጦርነት ሰለባ ሊሆን ባልተገባው ነበር።
ትህነግ በሕይወት ዘመኗ በትግልም ሆነ በሥልጣን ስለዕምነትና ስለዕምነት ቦታዎች ክብር ለይስሙላ ትግለጽ እንጂ ግበሯ ግን በሐይቁ ከረሞፋ እና በትግራዩ ነጃሺ ላይ ያደረገችው ነው። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በአብያተ-ክርስቲያናት ላይ የፈጸመችውም አይዘነጋም።
“በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት የተነሳ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት” የሚል ቃል በቅዱሱ መጽሀፍ ውስጥ ሰፍሯል።
ሕዝብ መቼም ቢሆን ክፉ ሆኖ አያውቅም፤ አይሆንምም። ነገር ግን ከሕዝብ የወጡ ጥቂቶች በዕኩይ ዓላማና ምግባራቸው ምድሪቱን ለጥፋት፣ ሕዝቡንም ለስቃይ ይዳርጋሉ።
የሕወሓት ቡድን መሪዎችም እንዲሁ ናቸው። ጉሮሯቸው እንደ መቃብር የተከፈተ፤ በምላሳቸው እየሸነገሉ የዘረኝነት መርዝ የሚረጩ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ የደበቁ፤ አፋቸው መራራ የሆነና እግራቸው ደምን ለማፍሰስ የፈጠነ እንዲሁም የሰላምን መንገድ የማያውቁ፤ ፈጣሪን የማይፈሩ ነበሩ።
ድርጊታቸው ሁሉ ይህንን ነበር የሚገልጸው። በሐይቁ ከረሞፋ እና በአልነጃሺ መስጂድ ላይ የፈጸሙትም ይህንኑ ነበር።
የጦርነት ወንጀል
የጀኔቫ ኮንቬንሽን እና ይህንን ተከትሎ እኤአ በ1977 ዓ.ም የጸደቁት ፕሮቶኮሎች በጦርነት ወቅት በንጹሃን ሰዎችና የጦርነቱ አካል ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት ማድረስ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን መጻረር ነው።
የጦርነቱ አካል ያልሆኑ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ በጦርነቱ ውስጥ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የሌላቸው ናቸው።
በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ በጦርነት ወቅት ለእነዚህ ነገሮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግና የጦርነት ዒላማ እንዳይሆኑ አጥብቆ ያስገነዝባል።
እነዚህ የጦርነት አካል ያልሆኑ ነገሮች የሚባሉት ባህላዊ ስፍራዎችና ዕቃዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች (ውሃ፣ መብራት፣ ግድብ ወዘተ)፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመሳሰሉት ናቸው።
በዚሁ መነሻ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 270 ሥር በሰላማዊ ሕዝብ (ነገሮች) ላይ የሚፈጸም ጥቃት ወንጀል መሆኑን ደንግጓል። በሕጉ መሰረት በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ታሪካዊ ሐውልቶችን፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ወይም የማምለኪያ ቦታዎችን ማውደም፣ መውሰድ፣ ከጥቅም ውጭ ማድረግ፣ ለራስ ማድረግ ወይም እነዚህን ነገሮች ለወታደራዊ ዓላማ ማዋል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የጦርነት ወንጀል በመሆኑ በከባድ ቅጣት ያስቀጣል።
በእነዚህ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትና የአገራችንን የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች መነጽርነት በመታገዝ ሕወሓት በአል-ነጃሺ መስጂድ እና በአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት ላይ የፈጸመውን ድርጊት ስንመለከት በእርግጥም እነዚህን የአምልኮ ቦታዎች ለወታደራዊ ዓላማ ሲጠቀምባቸው እንደነበር እንገነዘባለን።
በመሆኑም እነዚህ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ያደራጁ፣ ያዘዙ፣ ወይም ድርጊቱን የፈጸሙ አልያም በማናቸውም መንገድ ተሳትፎ ያደረጉትን ሁሉ መንግስት ለፍትህ ሊያቀርባቸው ይገባል ማለት ነው።
የሆነው ሆኖ አሁን ሕወሓት ተቀብራለች። ኢትዮጵያም ለግማሽ ምዕት ዓመት ተቆራኝቷት ከኖረው ሾተላይ ተገላግላለች። በሕወሓት መቃብር ላይ ደምቀው ከሚነበቡት ወንጀሎች መካከልም ይሄኛው አንዱ በአልነጃሺ ላይ የፈጸመችው ሆኗል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥር 05/2013