ለምለም መንግሥቱ
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውን ለማፋጠን ቴክኖሎጂን መጠቀም የውዴታ ግዴታ እየሆነ መጥቷል። ቴክኖሎጂዎችን ከሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ባገናዘበ ሲተገበር ውጤታማነቱ ከፍተኛ እንደሚሆን የዓለም ተሞክሮ ያሳያል።
በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ጥቅም ላይ ሲያውሉ የፈጠራ ፍቃድ ካላቸው ጋር ስምምነት ፈጥሮ በጋራ መሥራት፣ አዳዲስ ፈጠራ ያላቸውን ማሰልጠን፣ ለጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍ ማድረግ፣ የውድድር መንፈስ መፍጠር፣ እውቅና መስጠት፣ ከሌሎች ሀገሮች ጋር የልምድ ለውውጥ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር መፍጠር፣ ቴክኖሎጂን ሊመራ የሚችል አቅም ያለው ተቋም ማቋቋም እንደሚጠበቅባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ የመሬት ሀብትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ላላቸው ሀገሮች ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባራት ሲያከናውኑ እንደሆነ ይመከራል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አቅሟን ለማሳደግ ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር የተቆራኘ ሥራ በማከናወን ላይ ትገኛለች። ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው ከጅምር ያለፈ እንዳልሆነ ይተቻል። በቴክኖሎጂ ሽግግር እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተጠቃሽ ነው። በአሁኑ ጊዜ በግንባታ ልምድ ያላቸው ትላልቅ ኩባንያዎች በመንገድና በህንፃዎች በግዙፍ ግንባታ ላይ ተሰማርተዋል። መንግሥት በዘርፉ በቂ አቅም ለመፍጠር የቴክኖሎጂ ሽግግሩ አስፈላጊ ነው ብሎ ቢያምንም የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ለመሆኑ ኢትዮጵያውያኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ከነዚህ ኩባንያዎች ጋር አብሮ የመሥራት ልምዳቸው ምን ይመስላል? የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዘርፉን ምን ያህል እያገዘው እንደሆነና የዘርፉ ባለሙያዎችም ያገኙት ተሞክሮ ምን ያህል እንደጠቀማቸው፣ ተሞክሮውን በተግባር ላይ በማዋል እያከናወኑ ስላለው ተግባር ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርገናል።
በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን ያካፈሉን የሳምኮል ኢንጂነሪንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳሙኤል ሳህለማርያም የቴክኖሎጂም ሆነ የእቅም ግንባታ ሽግግር ተፈጥሯል ብለው አያምኑም። እርሳቸው እንዳሉት አሁን ባለው አሰራር የሀገር ውስጥ ተቋራጩ እነርሱ ሲሰሩ በማየት ብቻ ካልሆነ በትክክለኛው መንገድ ፍኖተካርታ (ሮድ ማፕ) ተዘጋጅቶ፣ በመመሪያ ተደግፎ ቴክኖሎጂውን ከሚያሸጋግረው አካል ጋር ሥራውን በትብብር ወይንም በከፊል በሚደረግ ስምምነት እየተከናወነ አይደለም። ከዚህ አንጻር የቴክኖሎጂ ሽግግር አለ ለማለት አያስደፍርም። እንደባለሙያም አሰራሩን አይቀበሉም። እንደውም በተቃራኒው ከውጭ ኩባንያዎቹ ጋር የሚሰሩ ተቋራጮች አቅማቸውን ቀንሰው ነው የሚወጡት።
ኢንጂነር ሳሙኤል የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመስራታቸው አቅም የሚያጡበትን ምክንያት እንዳስረዱት፤ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷ ውስጥ በስፋት በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩት የቻይና ኩባንያዎች በመሆናቸው በብዛት ሥራዎች የሚሰሩት ከእነሱ ጋር ነው። የውጭ ሀገር ኩባንያዎቹ ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሰጧቸው ሥራ ከተረከቡት ሥራ ውስጥ የተወሰኑትን ሥራዎች በመስጠት ወይንም ንዑስ ተቋራጭ ሆነው እንዲሰሩ ነው የሚያደርጓቸው። የሚሰጧቸው ሥራዎች ቴክኖሎጂን የሚያሸጋግሩ ዋና ዋና እንደ ኤሌክትሮሜካኒካል፣ የፍሳሽ መውረጃ (ሳኒታሪ) እና ሌሎች ሳይሆን፣ እነርሱ ቢሰሩትም ባይሰሩትም እሴት የማይጨምርላቸውን መርጠው የኮክሪት ሙሌት ፣ ብረት ማጣመምና ሌሎች አነስተኛ ሥራዎች ነው የሚሰጧቸው።
የውጭ ኩባንያው ከወሰደው ጠቅላላ ሥራ እያንዳንዱን በመቶኛ አስልቶ ሲሰጠው ነው ቴክኖሎጂ ተሸጋግሯል፤ ባለሙያውም ዕውቀቱን አዳብሯል ማለት የሚቻለው።
ክፍተቶቹ እንዳሉ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር አልተፈጠረም ማለት ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ ኢንጂነር ሳሙኤል በምሳሌ በማስረዳት በሰጡት ምላሽ ከውጭ ኩባንያ ጋር በንዑሥ ተቋራጭነት ሥራ የጀመረ አንድ ኮንትራክተር በአመቱ ወይም በሁለት ዓመቱ የውጭ ኩባንያ ሊሰራ የሚችለውን የመሥራት አቅም ሲገነባና ልምዱን ያገኘበትን ኩባንያ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን ሲችል ቴክኖሎጂው መሸጋገሩ በተግባር ይታያል። ወይንም ይረጋገጣል። የውጭ ኩባንያው ቴክኖሎጂ፣ ዕውቀት፣ የገንዘብ አቅም ይዞ የሚመጣ በመሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዕድል እንጂ ሥጋት መሆን አልነበረበትም ሲሉም ያስረዳሉ።
ተወዳዳሪ እንዳይኖራቸውና ሁሌም እነርሱ ብቻ ተፈልገው እንዲመጡ ከመፈለግ የተነሳ እንደሆንም ተናግረዋል።
በተለይም አሉ ኢንጂነር ሳምሶን፤ በመንገድ ሥራ ከውጭ ተቋራጮች ጋር የሰሩ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች እንዳልተጠቀሙ ያስታውሳሉ።
የውጭ ተቋራጮቹ በወቅቱ አስፈላጊውን ክፍያ በመፈጸም በኩልም ክፍተት እንዳለባቸውም ይናገራሉ። እርሳቸውም እኤአ በ2016 ልምድ ለማግኘት ብለው ኤስ ኤ ደብሊው ኢንፍራስትራክቸር ከሚባል የህንድ ኩባንያ ጋር ከሀዋሳ ጭኮ ድረስ ይሰራ በነበረው የመንገድ ሥራ ላይ ድርጅታቸው ንዑስ ተቋራጭ ሆነው ለመሥራት ተስማምተው ያሰቡትን ልምድ ሳይሆን ያገኙት ተቋራጩ በሀገር ላይ ኪሳራ አድርሶ ነው ወደ መጣበት የተመለሰው።
በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለሚመለከተው የመንግሥት ተቋም በማሳወቅና ችግሩንም በጋራ ለመፍታት ስላደረጉት ጥረትም ኢንጂነር ሳሙኤል ሲናገሩ፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮትራክተር ሥራ ተቋራጮች ማህበር ቦርድ አባል በነበሩበት ወቅት ጉዳዩን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል። የህግ ክፍተቱ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ባይፈታውም በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ግን አንድ እርምጃ ተኬዷል። ባለሥልጣኑ የንዑሥ ተቋራጭ ኮንትራክተር አስተዳደር መመሪያ አውጥቷል። በመመሪያው በግልጽ በማስቀመጥ ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርጓል። በሌሎችም የግንባታ ዘርፍ እንዲህ አይነት እርምጃዎች ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክስን ኮትራክተር ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚደንት ኢንጂነር ግርማ ሃብተማርያምም የኢንጂነር ሳምሶንን ሀሳብ ይጋራሉ። መንግሥት እንዳሰበው ከውጭ ኩባንያዎቹ ሙሉ ለሙሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተገኝቶበታል ብለው አያምኑም። የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በግል ጥረታቸው ሥራዎችን በማየት እራሳቸውን ለማብቃት የሚያደርጉት ጥረት ካልሆነ በስተቀር አብዛኞቹ ኩባንያዎች እውቀታቸውን ለማካፈል ፍቃደኛ አይደሉም።
በጥረታቸውም አግኝተዋል የሚባለው በህንፃ ግንባታ ላይ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ እና የፍሳሽ መውረጃ (ሳኒተሪ) እንዲሁም አልፎ አልፎ በመንገድ ሥራ ላይ የሚያገኙት እውቀት ካልሆነ በቂ አይደለም። በብዛት የጉልበት ሥራውን እንጂ ለወደፊት አቅም የሚገነባ እውቀት የሚገኝበትን ሥራ ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች እየሰጡ እንዳልሆነና አብዛኛውን ሥራ በራሳቸው ባለሙያ እንደሚሸፍኑ ነው የተናገሩት። ቴክኖሎጂው ስለሚያግዛቸውም ለግባታው የሚጠቀሙትን ግብአትን በማሽን በመጠቀም የሚሳተፈውን የሰው ኃይል ይቀንሳሉ።
በመንገድና በህንፃ ግንባታ ሥራ ላይ ከተሰማሩት የውጭ ኩባንያዎች መካከል በቻይናውያኑ በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት አጥብቀው በማውሳት ሥራቸው ድብቅ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሌላው ለቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅፋት ነው ብለው እንደተግዳሮት ያነሱት የግንባታ ግብአቶች ላይ የሚሰፍረው ገላጭ ጽሁፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታገዘ አለመሆኑን ነው።
በሁሉም የግብአት ዕቃዎች ላይ የሚጠቀሙት ቋንቋ በቻይንኛ በመሆኑ ስለዕቃዎቹ በቀላሉ አንብቦ መረዳት አይቻልም። በስፋት ሥራ የሚሰራው ከእነርሱ ጋር በመሆኑ በጣም አስቸጋሪ ነው። የቻይናውያኑ ኩባንያዎች በሚያደርጉት ነገር የተበሳጨ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ለዚሁ ብሎ ቻይና ድረስ በመሄድ ቋንቋ ተምሮ መምጣቱን አስታውሰዋል። ሁሉም ባለሙያ እንደግለሰቡ ማድረግ አይችልም፤ ደግሞም አይጠበቅበትም። በሌሎች ኩባንያዎች ግን ይሄ አይስተዋልም። እንግሊዝኛ ቋንቋን በተጨማሪ ይጠቀማሉ።
የኢንጂነር ግርማ ቅሬታ በሁሉም ኩባንያዎች ላይ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በጠየኳቸው ጊዜ ‹‹እውነት ለመናገር ከሆነ ሁሉንም በአንድ ላይ መፈረጅ ያስቸግራል። ለምሳሌ ጃፓኖች በውሃ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ሲሰሩ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በመቅጠር ጭምር ነው የሚሰሩት። ግብአቶቻቸውም ገላጭ የሆነ ጽሁፍ የሚያሰፍሩት በእንግሊዝኛ በመሆኑ አስቸጋሪ አይደለም›› ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ማህበሩ የሚያያቸውን ክፍተቶች ለሚመለከተው ክፍል በማቅረብ በኩል እስከምን እንደሄደ ኢንጂነር ግርማ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በሰጡት ምላሽ ክፍተቱ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ተቋራጮች ሊሰሯቸው የሚችሏቸው ሥራዎች ለውጭ ኩባንያዎች እየተሰጡ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ የማህበሩ የቦርድ አባላት ጥያቄ በማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በህንፃ ግንባታ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና በመንገድ ሥራው ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንዲያውቀው ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጥያቄውን መሠረት አድርጎ ማሻሻያዎችን አድርጓል። የውጭ ኩባንያው ከሚወስደው የመንገድ ሥራ 40 በመቶውን የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ንዑስ ተቋራጭ ሆኖ እንዲሰራ በማድረግ ጥሩ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል። ያልተለወጠው በህንፃ ግንባታ ላይ ያለው በመሆኑ ተሞክሮ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መወሰድ አለበት።
ባለሙያዎቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ሆኖ መንግሥት በዘርፉ የጀመረው የቴክኖሎጂ ሽግግር አንድ እርምጃ ሄዷል። በዚህ የውድድር ዘመን ደግሞ ፈጥኖ ወቅቱ የሚጠይቀውን አሟልቶ በመገኘት አብሮ መራመድ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ኩባንያዎቹን በመጠበቅ የራስ ጥረት ሳይታከል እስከምን ድረስ መጓዝ ይቻላል? ኢንጂነር ግርማ ሃሳቡን እንዴት እንደሚያዩትም ጥያቄ ቀርቦላቸው ‹‹ተገቢ ጥያቄ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷ ገና በለውጥ ሂደት ላይ ስለሆነች መንግሥት አቅሙን ለመገንባት ያደረገው ጥረት የተሳካ ነው ለማለት አያስደፍርም። ለግንባታ ሥራ የሚውሉ ማሽኖችን ከውጭ ሀገር ለማስገባትና የተከላ ሥራ ለማከናወን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ማነቆ ሆኗል። ይሄ ደግሞ እንኳን አቅም ካላቸው ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ሥራውንም በአግባቡ ለመወጣት ዕድል አይሰጥም።
የዋጋ ማስተካከያ ባለመደረጉ ብዙ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ምክንያት ሆኗል። አሁን ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መኖሩ ችግሩን የከፋ አድርጎታል። ተደራራቢ ችግሮቹ ደግሞ የግንባታ ዕቃን እያናረው ይገኛል። በየጊዜው ክፍተቶችን እየፈተሹ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ ካልተቻለ። ውድድሩ እየጨመረ ይሄዳል ለአብዛኛው የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ሥጋት እየሆነ ይሄዳል›› በማለት በምላሻቸው አስረድተዋል።
ኢንጂነር ግርማ እንደሚሉት የውጭ ስራ ተቋራጮች በገንዘብ አቅም በኩል የመንግሥታቸው ድጋፍ አላቸው። በቴክኖሎጂም የታገዙ ናቸው። በመሆኑም በውድድሩ ለማሸነፍ ለእነርሱ ቀላል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት አቅም ውስን በመሆኑ ድጋፉ አነስተኛ ነው። ስለዚህ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል መፍትሄው ሊተገበር የሚችል ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ መመሪያ ማውጣት ነው።
በውጭ ኩባንያዎች ላይ የሚስተዋለው ቴክኖሎጂን የማሸጋገር ክፍተት የሀገር ውስጥ ተቋራጭም የሚያሰራቸውን ባለሙያዎች በማብቃት በኩል በተመሳሳይ እንደሚስተዋልበት ይተቻሉ። የራሱን በራሱ ማብቃት ካልቻለ የውጭውን ለመውቀስ ምን አንደበት ይኖረዋል? ኢንጂነር ግርማ እንዳሉት፣ ‹‹መንግሥት የግንባታ ዘርፉን እየረዳ እንደሆነ አይካድም። ለሥራው የሚያስፈልጉ ገልባጮችን፣ ክሬኖችን፣ ፒካፖችን የመሳሰሉ ከውጭ ከቀረጥ በማስገባት የተቋራጩን አቅም ለመገንባት ጥረት እያደረገ ነው። በተደረገልን ድጋፍም በዘርፉ ላይ የምንገኘው አብዛኞቻችንም አድገንበታል።
ይሁን እንጂ በየጊዜው እያሽቆለቆለ የመጣው የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የኮቪድ መከሰት፣ ግዥ ኤጀንሲ በአግባቡ ኃላፊነቱን አለመወጣቱና በተያያዥ ጉዳዮች ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ባለማደጉ ከራሱ አልፎ ሌሎችን ማብቃት ከሙከራ ያለፈ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም››ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክስን ኮትራክተር ሥራ ተቋራጭ ማህበር 1984 የተመሠረተ ሲሆን፣ ከሁለት ሺህ በላይ አባላትን ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው። ይሁን እንጂ በተቋራጭ ሥራ ላይ የተሰማሩት ከአስር ሺ በላይ እንደሚሆኑ ነው ኢንጂነር ግርም የገለጹልን። ማህበሩ የአባላትን ቁጥር ለመጨመር ስትራተጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013