በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም እንደ ሀገራችን ተመልካች፣ አድማጭና አንባቢ በማስታወቂያ የተማረረ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። አንዳንድ ማስታወቂያዎችማ እልህ ውስጥ የገቡ እስኪመስል ድረስ ተመልካች አድማጩን ከቴሌቪዥን ቻናል፣ ከኤፍ ኤም ኤፍ ኤም እንዲሁም ከህትመት ህትመት እያሳደዱት ነው።
አንዳንድ ተመልካች፣ አድማጭና አንባቢም በማስታወቂያዎች ተገፋፍቶ አገልግሎቱንና ምርቱን ከመግዛትና ከመጠቀም ይልቅ በእልህ በተቃራኒው የሚወስንበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም።
አንዳንድ ጊዜማ ለማስታወቂያ ከሚገፈግፉት ረብጣ ብር ቀነስ አድርገው የአገልግሎትና የምርታቸውን ጥራት ማሻሻል፣ ዋጋቸውን ከሕብረተሰቡ የመክፈል አቅም አንጻር ቢያጣጥሙ እና የሰራተኞቻቸው የስራ ደህንነት ለማሻሻልና ደመወዝ ቢያስተካክሉ እስከማለት ያደርሳል።
ለነገሩ ይህ አስተያየት የቤት ስራቸውን ጥንቅቅ አድርገው ለትክክለኛ ማስታወቂያ የሚመጡትን አይመለከትም።
ባለማስታወቂያና ባለስፖንሰር ድርጅቶች ሚዲያውንና ጋዜጠኛውን ቡዳ እንደበላው ሲያስለፈልፉት ውለው ያድራሉ። ይህ አልበቃ ብሏቸው ድርጅቶችን ያስደስቱ እየመሰላቸው ማስታወቂያዎች መረን ወደለቀቀ ግንትና ፈጠራ ከፍ ማለታቸው ሕዝቡን ለድንጋሬ እየዳረጉት ነው።
ማስታወቂያ አስነጋሪዎችና ስፖንሰር አድራጊዎች ከሚያጋንኑትና ጣል ከሚያደርጉበት ውሸት ላይ ሚዲያዎች ደግሞ ጣል ሲያደርጉበት ምርቱና አገልግሎቱ መሆኑ ቀርቶ የሆነ ለማመንና ለመቀበል ወደሚቸግር ነገር ይወርዳል።
እነዚህ ሚዲያዎች ለአድማጭና ተመልካቹ ምን ያህል ንቀት እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። አንዳንድ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ለግሉ የንግድ ማህበረሰብ አርዓያ መሆን ሲገባቸው የተጋነነና የውሸት ማስታወቂያ መስማትና ማየት ይበልጥ ያበግናል። ሰሞኑን ኢትዮ ቴሌኮም “ 4G በመላው አዲስ አበባ “ እያለ የሚለፍፈው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
ለቴሌ አዲስ አበባ ማለት ፒያሳ፣ 22፣ ቦሌና አራት ኪሎ ብቻ ነው ማለት ነውም ያስብላል። ከመሀል ከተማ ወደ ዳር በተወጣ ቁጥር እንኳን 4G ፤ 2Gም ብርቅ በሆነበትና ምንም አይነት የመሰረተ ልማት ባልተገነባበት “ 4G በመላ አዲስ አበባ “ ብሎ ነገር ነጭ ውሸትና” ንጉስ “ በሚባለው በደንበኛ ማላገጥ ነው። ስለ አገልግሎትና ምርቶች ጥራት፣ ብቃትና አዋጭነት እጅግ በተጋነነ ሁኔታ ከመቅረቡ የተነሳ ሸማቹ ለተሳሳተ ውሳኔ ሲዳረግና ሲማረር መስማት የዕለት ተዕለት ገጠመኝ እየሆነ ነው።
በተጋነነና ሕጋዊ ባልሆነ ማስታወቂያ ስንቱ ለጤና ችግር እንደተዳረገና ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ የቆጠባትን ስንቱ በአደባባይ እንደተዘረፈ ቤቱ ይቁጠረው። የሚያሳዝነው የንግድ ሚኒስቴርም ሆነ የሸማቾችን መብት ለማስከበር የተቋቋመው መስሪያ ቤት አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙና አንብበው እንዳላነበቡ ዝምታን መምረጣቸው ነው ።
ሌላው የመደበኛ ሚዲያን /ሜንስትሪም ሚዲያ/ ማለትም የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የጋዜጣን ፤ ተመልካች፣ አድማጭና አንባቢ ብዛት እያጠና የትኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ ብዙ ተመልካች ፤ የትኛው ሬዲዮ ጣቢያ ደግሞ ከፍ ያለ አድማጭ፤ የትኛው ጋዜጣ በአንባቢዎቹ እንደሚመረጥ በየጊዜው የሚያጠና ፣ ደረጃ የሚሰጥ ገለልተኛ ተቋም / ሬቲንግ ኤጀንሲ / በሌለበት ድርጅቶች በምን መመዘኛ ማስታወቂያዎችን ለሚዲያዎች እንደሚሰጡና ስፖንሰር እንደሚያደርጉ ለመግለፅ ይቸግራል።
ለሀገርና ለትውልድ ቀጣይነት ሌት ተቀን ከሚማስኑ ሚዲያዎች ይልቅ እንቶ ፈንቶውንና አሸር በሸሩን ሲለፍፉ የሚውሉ ሚዲያዎች ማስታወቂያ በማስታወቂያና ስፖንሰር በስፖንሰር የሚሆኑበት አግባብ በራሱ እንቆቅልሽ ከመሆኑ ባሻገር በቲፎዞና በደላላ የተከበቡ በጣት በሚቆጠሩ ሚዲያዎች ማስታወቂያውን በሞኖፖልነት እየተቆጣጠሩት ነው።
ማንነታችንን በጉልበት ቀምቶ “እኛን ሆናችኋል“ ሌላ ጊዜ” ቀላል ነው ! “እያለ በዚያ ሰሞን እያላገጠብን ስለነበረው ነውረኛ የዲኤስቲቪ ማስታወቂያ አስተያየቴን ከመሰንዘሬ በፊት ስለ ዲኤስቲቪ ታሪካዊ ዳራና ማንነት ላጋራችሁ።
ዲኤስቲቪ የዲጂታል ሳታላይት ቴሌቪዥን / ምህጻረ ቃል ሲሆን ፤ ንብረትነቱ ደግሞ መልቲቾይስ ለተሰኘ ኩባንያ ነው። ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የቀጥታ የሳታላይት ስርጭት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
(የዘመን አቆጣጠሮች በሙሉ በጎርጎሮሳውያን ናቸው፤) ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ በደቡብ አፍሪካ በመለጠቅ በናይጄሪያ የሚገኙ ናቸው። በኬኒያ፣ ጋና፣ አንጎላ ፣ ዚምባቢዌ ፣ ዛምቢያ ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪሺየስ፣ ማላዊ ፣ ታንዛኒያ ፣ ሌሶቶ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፣ የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ጋቦን፣ ስዋዚላንድና ቦትስዋና ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል።
ዋና መቀመጫውም ፈርንዳሌ ፣ ጋውተንግ ደቡብ አፍሪካ ነው ። ታሪካዊ ዳራው ከዚህ አልፎ ወደ ኋላ ይወስደናል። በደቡብ አፍሪካ ኤም ኔት የተባለ የክፍያ ቴሌቪዥን በ1986 ዓ.ም ናስፐርስ በተባለ ኩባንያ ተጀመረ ።
ለሰባት ዓመታት ይህል በዚህ ኩባንያ ሲመራ ከቆየ በኋላ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ናስፐርስ በመሰረተው መልቲቾይስ የተሰኘ 2ኛ ተደጓሚ ድርጅት መመራት እንደ ጀመረ መረጃዎች ያትታሉ ። መልቲቾይስ የዲኮደር ሽያጭ ፣ የአካውንት አስተዳደር፣ የደንበኛ አገልግሎት ፣ ወዘተረፈ. ይሰጣል።
እንግዲህ ዲኤስቲቪ በይፋ ስራ ከጀመረ ባለፈው መስከረም መጨረሻ 26 ዓመት ሆኖታል። ኤም ኔት፣ ኤምጂኤም፣ ቲኤንቲ ፣ ኤስሲአይ – ኤፍአይ ፣ ዩኒቨርሳል፣ ሱፐርስፓርት ኢኤስፒኤን፣ ካርቶን ኔትወርክ፣ ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ፣ ሲኤንኤን እና ስካይ ኒውስ ኢንተርናሽናልን በማዕቀፍ ይዞ ስርጭት የጀመረው ዲኤስቲቪ ኋላ ላይ ደብሊው 4 ሳታላይትን ከኩ ባንድ ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገራት እና ለህንድ ውቅያኖስ ደሴቶችን መድረሰ ቻለ።
በማስከተልም ኢንተራክቲቭ ቴሌቪዥን በ2000 ዓ.ም ፣ ዱዋል ዲኮደር በ2003 ዓ.ም ፣ ዲኤስቲቪ ፒቪአር ዲኮደር እና ዲኤስቲቪ ኮምፓክትን በ2005 ጀምሯል ።
በ2008 ዓ.ም ደግሞ የሀይ ዴፊኒሽን ስርጭቶችን በኤችዲ ፒቪአር ዲኮደር ፤ በዚሁ ዓመት ኤክስትራ ቪው ዲኮደርንና ኤም-ኔት ኤችዲ ቻናልን ለደንበኞቹ አድርሷል። በተለይ በ2010 ዓ.ም በኢንተርኔት ፕሮቶኮል የዲጂታል ቪዲዮን እና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል።
በአጠቃላይ ዲኤስቲቪ ከ200 በላይ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችን በስሩ የያዘ ሲሆን ፤ ስድስት አይነት የተለያዩ የዋጋና የሽያጭ አይነቶች ሲኖሩት ፤ በሀገራችንም ዲኤስቲቪ ፕሪሚየም በ2600 ብር፣ ሜዳ ፕላስ በ1300 ብር፣ ሜዳ በ550 ብር፣ ቤተሰብ በ380 ብርና ጎጆ በ220 ብር እንደሚባሉት አይነት መሆኑ ነው።
ሆኖም መልቲቾይስ ኢትዮጵያ እነዚህ አገልግሎቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ተብለው የተዘጋጁ አድርጎ በማስታወቂያው ቢነግረንም፤ እውነታው ግን እነዚህ የሽያጭና የዋጋ ማዕቀፎች የዲኤስቲቪ አሰራር እንጂ በተለይ ለኢትዮጵያ ተብሎ የተዘጋጁ አይደሉም።
የዛሬውን መጣጥፌን ለመጫጫር ምክንያት ወደ ሆነኝ ጉዳይ ስመለስ ፤ አየሩን ፣ ቴሌቪዥኑንና ማህበራዊ ሚዲያውን የተቆጣጠረው የዚያ ሰሞን ማስታወቂያ ነው።” እኛን የሆነው ማነው !?“ እያለ ሲነዘንዘን፣ መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጣን እና ለተወሰኑት ደግሞ ልብ ሰቃይና ጥያቄ ሆኖ ባጅቶ መጨረሻ ላይ “እኛን ሆኖ“ የተገኘው ዲኤስቲቪ ነው ።
ማስታወቂያዎቻችን ውሸት፣ ግነትና ኩሸት የተጫናቸው ናቸው የምለው ለዚህ ነው። ዲኤስቲቪ እኛን ሊሆን ቀርቶ በአጠገባችን አይደርስም። እኛን መሆን ቀርቶ እኛን መምሰል አይችልም ። እኛን ሊሆን የማይችልባቸውን የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ። የመጀመሪያው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነው።
ወርሀዊ ክፍያው ከ2600 እስከ 220 ብር ሆኖ እያለ በምን ሒሳብ ነው እኛን ኢትዮጵያዊያንን የሚሆነው። የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንደቋጥኝ ተጭኖን ለሸገር ዳቦ ሰልፍ ዶሮ ሳይጮህ እየወጣን ፣ ለልጆቻችን ምሳ መቋጠር ፣ ዩኒፎርም ማሰፋት ፣ የጽህፈት መሳሪያ መግዛት ተስኖን እርጥባን ሆነን እያለ እንዴት እንዴት ሆኖ ነው ከደቡብ አፍሪካና ከናይጀሪያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው እና ከሀገራችን ባለጠጋዎች ጋር ተጃምለን ዲኤስቲቪን የምንሆነው እሱም እኛን የሚሆነው።
ሁለተኛው የእኛ የኢትዮጵያውያንና የዲአስቲቪ ማንነት ለየቅል የመሆኑ ጉዳይ ነው። የዲኤስቲቪ የልቦና ውቅር የተመሰረተው በቅኝ ተገዥነት ወይም ገዥነት ሲሆን የእኛ የኢትዮጵያውያን ግን ሉዓላዊነታችንን በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሳናስደፍር የኖርን ኩሩ ሕዝብ የራሳችን ባህል፣ ወግና ማንነት ያለን ስለሆነ ከቅኝ ገዥዎችም ሆነ ተገዥዎች ማንነት ጋር አንድ የሚያደርገን ነገር የለም። ከእስፖርት ውጭ ያሉ የሳታላይት ቴሌቪዥኑ አብዛኛዎቹ ከባህላችንና ወጋችን ጋር የሚጋጩ መሆናቸው ለዚህ ጥሩ እማኝ ናቸው ።
ከሁሉም በላይ የማስታወቂያው ነውርና ድፍረት የአንድን ሕዝብ ማንነት ወስዶ እኛን ሆኗል ማለቱ ነው። እንዴት እንዴት ተደርጎ ነው የአንድ ህዝብ ማንነት ተክዶ የአንድ ሳታላይት ቴሌቪዥን ማንነትን የሚወርሰው!? የሰው ልጅ መገኛን ፣ ሉሲን ፣ መስቀልን ፣ ጥምቀትን፣ አክሱምን፣ ላሊበላን ፣ ፋሲልን ፣ ሶፎሞርን ፣ የሀረር ግንብን ፣ ወዘተረፈ. በልኩ ሰፍቶ ወደ ዲኤስቲቪ ማንነት የሚያወርደው የሚያሳንሰው ማን አይዞህ ቢለው ይሆን።
በምን ስሌትስ ነው ዲኤስቲቪ ኢትዮጵያንን የሚሆነው!? ማስታወቂያ እኮ ነው ምን ችግር አለው !? አትሉኝም መቼም።
ዲኤስቲቪ የኢትዮጵያን ባለጠጋዎችና የተወሰኑ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ዓመታት ቢቆጠሩም ብዙኀኑ ግን በዲኤስቲቪ ቤቶችና በሆቴሎች እንደ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያሉ ስፖርታዊ ውድድሮችን ከመከታተል ባለፈ ተጠቃሚነቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
የትምህርትና የስፖርት ቻናሎችን እንኳ እንዳይከታተል ዋጋው ዛሬም እንደሰማይ እንደራቀው ነው። ዋናው ምክንያት የዋጋው አይቀመሴነት ነው። ከሞላ ጎደል ለደቡብ አፍሪካና ለናይጀሪያ ደንበኞቹ አገልግሎቱን የሚሸጥበት ዋጋና ለኢትዮጵያ የሚያቀርብበት ዋጋ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።
የእነዚህን ሀገራት የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርትን ሆነ የዜጎቻቸውን የነፍስ ወከፍ ገቢ ብንመለከት ከእኛ ጋር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለው።
ታዲያ ይህን ከግምት ውስጥ ማስገባት ሳይችል፣ በቅጡ ሳያውቀን ነው እኛን የሆነው፤ እኛንም እሱን ያረገው !? በተለይ በናይጀሪያ ደንበኞች ላይ ዲኤስቲቪ የዋጋ ግሽበትን ሰበብ እያደረገ በየጊዜው የሚጭንባቸውን ያልተገባ ጭማሪ ቢያማርራቸው የሀገሪቱ የሸማቾች መብት ጥበቃ ኮሚሽን ጣልቃ እንዲገባ እስከመጠየቅ ደርሷል። ኮሚሽኑም የዲኤስቲቪን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አግዶታል።
ይሁንና ዲኤስቲቪ ላለፉት 20 ዓመታት የመካከለኛ ገቢ ባላቸው አብዛኛዎቹ ናይጀሪያውያን ዘንድ ቤተኛ ነው ማለት ይቻላል። መካከለኛ ገቢ ያላቸው ናይጀሪያውያን ቁጥር ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ በመሆኑ የደንበኞቹ ብዛት ያን ያህል እየቀነሰ ነው።
ዲኤስቲቪ ግን ዋጋ ከጨመረ ወደኋላ ስለማይል ቁጥራቸው እየተመናመነ ካለው ደንበኞቹ ጋር በየጊዜው ጦርነት ቀረሽ ግጭት ውስጥ እየገባ ነው። ናይጀሪያውያን የዲኤስቲቪን የግል ኩባንያነትና በፈለገ ጊዜ ዋጋ የመጨመር መብት እንዳለው እንኳ አምነው መቀበል አይፈልጉም ።
ገበያውን በሞኖፖል የመቆጣጠሩ ጉዳይም እንዲሁ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህ በናይጀሪያውያንም ሆነ በደቡብ አፍሪካውያን መካከለኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ዘንድ ዲኤስቲቪ የማንነታቸው አካል እስከመሆን መድረሱን ያመለክታል።
የእነዚህ ሀገራት ደንበኞቹን “ እኛን ሆነዋል ! “ ቢላቸው በተወሰነ ደረጃ ሊያስኬድ ይችላል። በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ደንበኞችን መነሻ በማድረግ ብቻ መላ ኢትዮጵያውያንን “ እኛ ሆነዋል! “ ማለት ግን ውሃ አያነሳም። ዲኤስቲቪ ሳይውል ሳያድር ይህን የተሳሳተ መደምደሚያውን ማስተካከል ይጠበቅበታል።
ሆኖም በሳተላይት ቴሌቪዥን ዘርፍ በአማራጭነት መምጣቱ በራሱ መልካም ቢሆንም ዋጋው እጅግ ውድ በመሆኑ “መካከለኛ ገቢ” አላቸው ተብለው የሚወሰዱትን ኢትዮጵያውያንን እንኳ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም። የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ በቀጥታ ማስተላለፉ በጠራ ቀረጻና ድምጽ ለመከታተል ከማስቻሉ ባሻገር ቤትኪንግ ከተሰኘ ኩባንያ ጋ በመተባበር ሊጉን መደገፉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
የዲኤስቲቪ የእግር ኳስ ቀጥታ አስተላላፊዎች ( ኮሜንታተርስ ) ኳሱን የመተንተን እውቀትና ልምድ ስላላቸው ለሊጉ ተሳታፊዎችም ሆነ ለኳሱ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ለተጫዋቾችም የመታየት አጋጣሚ ስለሚፈጥር በሌሎች ሊጎች የመጫወት እድል ሊያስገኝ ስለሚችል ይበል የሚያሰኝ ነው። የተጫዎቾቻችንን አመለም አደባባይ ማስጣት ጀምሯል።
ሆኖም የዲኤስቲቪ ታሪፍ የኢትዮጵያውያን ሸማቾች የመክፈል አቅም ከግምት ያላስገባ ከመሆኑ ባሻገር አንዳንድ ቻናሎች ደግሞ ከሀገሪቱ ማንነትና ባህል ጋር የሚጋጩ ናቸው። በአንጻሩ አስተማሪ የሆኑ ዘጋቢ ፊልሞች የሌሉት ሲሆን ብዙ ተመልካች የሌላቸው (ሬቲንጋቸው) እዚህ ግባ የማይባል የቻይና፣ የሕንድና የአፍሪካ ቻናሎች ደግሞ የትየለሌ ናቸው። ለዚህ ነው የሁሉም የዲኤስቲቪ ፓኬጆች ታሪፍ የተጋነነ ነው የምንለው።
ሆኖም የአገልግሎትና የሸቀጥ ሸማቾችን መብትና ጤና የሚያስጠብቅ ተሟጋችና ተቆርቋሪ ባለመኖሩ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ዋጋ እንዳሻቸው ይቆልላሉ።
የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንም ሆነ ንግድ ሚንስቴር ነጻ ገበያ ነው ብሎ ገበያውን ስድ ለቆ ሸማቹን መከላከል አልቻለም። እንኳን በእኛ ሀገር በምዕራባውያን ገበያም ነጻ ገበያ ብሎ ዋጋ እንዳሻ መጨመር የለም።
ሌላው ይቅርና የትርፍ ህዳግም ይወሰናል። ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላት የሸማቾችን መብት ማስጠበቅ ላይ ዛሬ ነገ ሳይሉ ሊሰሩ ይገባል። የሸማቾች መብት ጥበቃ ዱቄት ከመስፈር ዘይት ከማቅረብ በላይ ነውና ።የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቅ ማህበር አሁኑኑ !?
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013