አዲሱ ገረመው
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ በ300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደምትገኘዋ የአማራ ክልሏ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ ለሥራ ጉዳይ አቅንቼ ነበር ። በአገርኛ ተዘዋዋሪ ቅጽል ስም (ማነው ተዘዋዋሪን ለፈንድ ብቻ ያደረገው) «ዴንማርክ» ተብላ የምትጠራው ደብረ ማርቆሳችን የነዋሪዎቿን ኑሮ ምቹና የተረጋጋ ለማድረግ የአዲስ አበባ እና ሌሎች እህት ከተሞች ወግ ነክቷት የባጃጅ ሰልፍን እየተገበረች መሆኗን ለጥቂት ቀናት ከተማዋ ውስጥ ዞር ዞር ባልኩ ጊዜ ተመለከትኩ፡፡
የደብረ ማርቆስ የዩኒቨርሲቲ እግረኛ ማህበረሰብ ያለምንም ውጫዊ ተጽዕኖ በራሱ ጥረት ይህንን ሰልፍ በከተማዋ የተከለውና ተንከባክቦ ያሳደገው ይመስለኛል ።ምክንያቱም ደግሞ ሰልፉ የሚጀምረው ዩኒቨርሲቲው በራፍ ላይ ነው ።ከከተማዋ ጥቂት ፌርማታ የሚወስደውን ባጃጅ ለማግኘት ብዙ ሰዓት ተሰልፈው ይጠብቃሉ ።ይህንን የባጃጅ ሰልፍ የተመለከተ ሰው መንገድ ላይ ሳይሆን ትምህርት ቤት ውስጥ ያለ ሊመስለው ይችላል ።
ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል የሚባለው ሰልፉን ስመለከት ሌላ ጉዳይ አዕምሮዬ ላይ ስለመጣ የጽሑፌን አቅጣጫ አስቀየረኝ ።የባጃጁን ሰልፍ ጉዳይ ሌላ ጊዜ የምመለስበት ሆኖ፤ ለዛሬው ግን የደብረ ማርቆሱን የባጃጅ ሰልፍ ተንተርሼ በትምህርት ቤት ውስጥ ቀድሞ ይተገበሩ የነበሩ የሰልፍ ሁነቶችና ጭብጦቻቸው አሁናዊ ገጽታ ምን ላይ እንደሆነ ለመታዘብ ሞከርኩ ።
በእርግጥ አሁን አሁን በብዙ ትምህርት ቤቶች ዘንድ ተሰልፎ ሰንደቅ ዓላማ መስቀልና ማውረድ ከቀረ ሰነባብቷል አሉ ።በዚህ አጋጣሚ በትምህርት ቤት ሰልፍ እንድማር ብዙ ለጣሩልኝ መምህሮቼ ያለኝን አክብሮት ስገልጽ በታላቅ ደስታ ነው ።በተለይም የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህሮቼ በሰንደቅ ዓላማ ክብር ላይ የሚያደርጉት ንግግርና እንቅስቃሴ በፍጹም አይረሳኝም፡፡
ያኔ በትምህርት ቤት ሰልፋችን በክፍል ውስጥ የማይገኙ ብዙ ትምህርቶችን የምንማርበት ወሳኝ ክፍለ ጊዜ ነበር ።አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ከጨረስኩ በኋላ ግን ከምወደው ሰልፍ ጋር እንደተለያየሁ ይኸው ሰባት ዓመት አለፈኝ ። ኢትዮጵያዊ መንፈሳችን የላላው ሰልፍን ከተሰላፊዎች (ተማሪዎች) ጋር አብሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገባ፤ ወደ ሌሎች ተቋማትም እንዳይስፋፋ ስትከለክል ይሆን እንዴ?
በዚህ ዘመን ከተማሪዎች ይልቅ በየትምህርት ቤቱ የተሰቀሉ ድምጽ ማጉያዎች ለሰንደቅ ዓላማችን የተሻለ ክብር አላቸው ማለት ያስችላል፤ ተማሪና መምህር የተውትን ብሔራዊ መዝሙር እነርሱ ያለማቋረጥ ይዘምራሉና ። አሁን ላይ ከሰንደቅ ዓላማ ይልቅ ለታክሲ አሊያም ለስኳርና ዘይት ሰልፍ ከፍ ያለ ክብር መስጠት ተጀምሯል ።ለሰንደቅ ዓላማ የሚደረገው ሰልፍ ሁሉ ወደ ሌላ ዓላማ አልባ ሰልፍ ተቀይሯል ።ለከንቱ ጉዳዮች ከመሰለፍ ለዓላማ መሰለፍ እንዴት ሸጋ ነበር ።
ዛሬ ላይ ከጥቅስ በዘለለ ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠው ክብር እንዲያንስ ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱት ውስጥ ትምህርት ቤቶች ዋነኞች ናቸው ።ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫቸው ያላደረጉ፤ ተገቢውን ክብርና አብሮት የማይሰጡ እንዲሁም የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ የማይወጡ ትምህርት ቤቶች በርክተዋል ።በዚህ ዘመን ተሰልፈው ብሔራዊ መዝሙር ዘምረው ወደ መማሪያ ክፍል የሚገቡ ተማሪዎችን ማየት ይናፍቃል ።ምክንያቱም ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ሰንደቅ ዓላማ በምድረ ግቢው ውስጥ ከመስቀል ባለፈ ተማሪዎቻቸው ብሔራዊ መዝሙሩን እንዲዘምሩ አያደርጉም ።የሰንደቅ ዓላማ ሰልፉም የለም ።ለይስሙላ ብቻ ውስን ተማሪዎች በሞንታርቦ ከማጀብ ውጪ፡፡
የአገሩ ጉዳይ የሚገደው፣ እንደሚገደው የሚያውጠነጥን ሰው በተለይም የትምህርት ተቋማት የሰንደቅ ዓላማውን ሰልፍና ዝማሬ ሊያስተገብሩ ግድ ይላቸዋል ።ወገን ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚነበበው እኮ የአገሩ አስተዳደር ነው ።አገሪቱ የምትመራባቸው መርሆዎች ናቸው ።
የአገሪቱ ታሪክ ነው ።ታሪክ ብቻ ሳይሆን መጻኢ ተስፋም ጭምር ነው ።ሰንደቅ ዓላማው የነፃነት አርማ፣ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ማሳያ ነው ። ከባንዲራው ጀርባ የሚነበቡት እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ናቸው ።ታዲያ ትምህርት ቤቶች ይሄንን ስለምን ዘነጋችሁ?
ዘመኑን ላስተዋለ ሰው የሕይወታችን ህልውና ምሥጢሩ ያለው በሰልፍ እጅ ላይ ይመስላል ።ሰልፍን የሚጠሉ ሕይወትን ይጠላሉ ።ገንዘብ አለኝ የሚል ሰው ልጆቹን ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀልና ለማውረድ ጊዜ ሰጥተው በማያሰልፉ ወይም ብሔራዊ መዝሙር በማያዘምሩ ትምህርት ቤቶች ዘንድ ባያስተምር እመርጣለሁ ።
ለልጅ ረብጣ ብር እየከፈሉ ቋንቋ እንዲችሉ ወይም ኮምፒዩተር መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ የተለያዩ ብሔረሰቦችና በእኩልነት በአንድነት ለመኖር የሚኖራቸውን ተስፋ የሚገልጸውን አርማም ጭምር እንዲማሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
የመጫወቻ ሰፊ ሜዳ፣ የተደራጀ ቤተ ሙከራ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት ብቻ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቢኖር ግብረ ገብነት ከሌለው ምን ይሰራል ።ወዳጄ የመማር አስኳሉ ሰልፍና አሰላለፍ ነው ።አገራዊና ወገናዊ ዓላማ የሌለው ሰው ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረው አይችልም ።ሰንደቅ ዓላማ የሌለው ሰው ሰልፍ የለውም ።ሰልፍ የተለየው ሕይወት ደግሞ በራሱ የሞተ ነው ።
ለእንዲህ ዓይነቱ አገራዊ ርእይና ዓላማ ለሌለው ሰው ከጨርቅነት ባሻገር ያለውን የሰንደቅ ዓላማ ምሥጢር የሚያይበት ጤነኛ ዓይን የለውም ።ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀልና ለማውረድ የሚደረገውን ሰልፍም የሚያየው እንደጊዜ ማሳለፊያ ወይም እንደ ትርኢት ነው ።እና ትምህርት ቤቶች ትውልድ አገራዊ ቅኝት ውስጥ ካልገባ እንደምትጠየቁበት አታውቁምን? በየወሩ ክፍያ መሰብሰብ ላይ ብቻ አታተኩሩ ።
አንዳንዴ ትምህርት ቤት ውስጥ የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት ሲካሄድ አንዳንድ መምህራን ጭምር “ይደክመናል” በሚል ፈሊጥ ከተቀመጡበት ቦታ እንኳን እንደማይነሱ እንሰማለን ።ይህ ጉዳይ ወደ ሕግ ቦታ ቢደርስና የወንጀል ምርመራ ይጣራ ቢባል ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ፤ ከመሰናዶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከርዕሳነ መምህራን እስከ መደበኛ መምህራንና ተማሪዎች በወንጀል ከመጠየቅ ማን ይተርፍ ነበር? ዳሩ ከሳሽም ተከሳሽም የለ፡፡
ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር ቀርጸን እናሳድጋለን የምትሉ ትምህርት ቤቶች ግቢያችሁን ፈትሹ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013