በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በ1960ዎቹ የወጡ ዜናዎችን መርጠናል፤ እድሮች በቀብር ማስፈጸም ላይ መስራት የለባቸውም፤ከዚህም ወጣ ብለው አባላት ሲታመሙ ሲቸገሩ መርዳት በአካባቢ ልማት መሳተፍ አለባቸው ሲባል እንዲሁም በአካባቢያችሁ ሰላምና ደህንነት ላይ ምከሩ ሲባሉ አዲስ ነገር ይመስለናል፡፡ይህ ግን ፊትም ያለ ስለመሆኑ በ1960ዎቹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጣ ዘገባ ያመለክተናል፡፡ ከውጪ ዜናዎችም በ158 ዓመት ረጅም ዕድሜያቸው 34 ሚስቶች አግብተው 203 ልጆች ስለወለዱት ኬንያዊ (145ቱ ሴቶች ናቸው) የሚያትት ዜና ይዘናል፡፡
የዕድር ወኪሎች ስለልማትና ፀጥታ ተወያዩ
አ.አ. ኢ.ወ.ም/በመስፍነ ሐረርና አርበኞች መንገድ መካከል ለሚገኙ ፭ ሺህ ዕድርተኞች የተወከሉ የሰፈር ሽማግሌዎች ጳጉሜ ፭ ቀን እሁድ ከጧቱ ፫ ሰዓት በወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ጠቅላላ ስብሰባ አድርገው ፤ ስለሠፈራቸው ልማትና ፀጥታ ጥበቃ ተወያይተዋል ።
በስብሰባውም ላይ የአካባቢው ሠፈረተኞች ፤የ፯ ዕድሮች አጠቃላይ ፕሬዚዳንት አቶ አማረ ሙላት በሠፈሩ ውስጥ የሚገጥመው የማኅበራዊ ኑሮ ችግር የሚወገድበትን የሠፈሩ አዛውንቶች በኅብረት ማስወገድ ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀጥሎም የዕድሮቹ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፍስሐ ሀብተ ሥላሴ የአካባቢው ሕዝብ በኅብረት በመሥራት የቀበሌውን ንጽሕናና ፀጥታ መጠበቅ ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል ።በቀበሌው ሕዝብ በኩል ተወክለው የመጡት ሽማግሌዎቹም በየተራ ንግግር አድርገዋል፡፡እንዲሁም የአካባቢው ንጽሕና የቀበሌው ፀጥታ የሚጠበቅበትንና በተለይም ለበዓሉ ሰሞን ያለፈቃድ ያልተመረመሩ ከብቶች እንዳይታረዱ ምክርና ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ መሆናቸውን ተወያይተው የሚቀጥለው ቀጠሮ ለመስከረም 20 እንዲሆን ተወስኗል ።
(መስከረም 1 ቀን 19 60 የወጣው አዲስ ዘመን)
የሲዳሞ ጠ/ግዛትለልማትሥራ ፷፩ሺ ፰፻፯ ብር ተዋጣ
ይርጋ ዓለም፤(ኢ/ወ/ም) በክቡር ሌተና ጄኔራል ኢሳይያስ ገብረሥላሴ የሲዳሞ ጠ/ግዛት እንደራሴ አሳሳቢነት የተቋቋመው የልማት ሥራ መዋጮ ፤61 807 ብር ከ50 ሣንቲም ፤ደረሰ ።
ይህም ገንዘብ የተሰበሰበው በጀምጀም አውራጃ ገዥ በፊታውራሪ ለማ ወልደ ጻዲቅ ሊቀመንበርነት ፤መስከረም ወር ፶፱ ዓ/ም/ እስከ ሰኔ ፴ ቀን ፶፱ ዓ/ም/ ድረስ ነው፡፡
ከዚሁ ውስጥ የአረጋ ወረዳ ግዛት ሕዝብ 36 999 ፤ከ50ሣንቲም ፤የአዶ ወረዳ ግዛት ሕዝብ 7 800 ፤የአሮሬሳ ወረዳ ግዛት ሕዝብ 5361 ፤የአዶላ ወረዳ ግዛት ሕዝብ 3628 ፤የዋደራ ወረዳ ግዛት 1706 ፤የክብረ መንግሥት ከተማ ሕዝብ 756 ያዋጣ መሆኑን የአውራጀው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ መኰንን አበበ ገለጡ ።
(መስከረም 1 ቀን 19 60 የወጣው አዲስ ዘመን)
ዝንጀሮዎች ሰው ገደሉ
ጎፋ (ኢ-ወ-ም) በገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት በጎፋ አውራጃ በጎፋ ወረዳ ኮስቲ በተባለው ቀበሌ ሺበሺ ሴንሳ የተባለው ፲፪ ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ የበቆሎ ሰብል ሲጠብቅ ዝንጀሮዎች በቆሎውን ለመብላት መጥተው ሊያባርራቸው ቢሞክር ተሰብስበው በመያዝ እየጎተቱ የገደሉት መሆኑን የአውራጀው ፖሊስ አዛዥ በጽሑፍ መግለጣቸውን ዋናው ጸሐፊ አቶ ታደሰ ለገሠ አስታወቁ ።
(መስከረም9 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
ባለ ፻፶፰ ዓመት ዕድሜ ሰው በኬንያ ተገኙ
ከናይሮቢ፤(ኤ-ኤፍ-ፒ) ዕድሜዬ ፩፻፶፰ ዓመታት ነው ፡፡እ/ኤ/አ/ በ፲፰፻፶፱ ዓ/ም/ ወደ አፍሪካ ከመጡት ከሊቪንግስተንና ከሌሎችም ተገዢዎች ጋር ተገናኝቻለሁ የሚሉ አንድ ኬንያዊ ገበሬ በአሁኑ ጊዜ ባላቸው አሥር
ጋሻ መሬት ላይ የተለመደ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ይገኛሉ።በናይሮቢ አቅራቢያ የሚገኙት ሳምሶን ሻኰራጐ ፤በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሚገኙት ብዙ ዓመታት የኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚበልጡ አንጋፋ ናቸው፡፡
በታንዛንያ ውስጥ ዓይናቸውን ተቀድደው ሕክምና ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ በቅርቡ የተደረገላቸው ምርመራ እንደሚያመለክተው ዓይናቸው ድኗል፡፡
የርሳቸው አባት የናሳላንድ ጎሣ ባላባት ሲሆኑ ከነበራቸው ፴፬ ሚስቶች ፩፻፵፭ ሴት ልጆችና ፶፰ ወንድ ልጆች አስወልደዋል ።ከእነዚህ መካከል ፩፻፶፰ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሻኰራጐ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው ።
ሻኰራጐ እ/ኤ/አ/ በ፲፰፻፺፮ዓ/ም ተጠምቀው ፕሮቴስታንት እስከሆኑ ድረስ ሦስት ሚስቶችና ፲፮ ልጆች ነበሯቸው፡፡ነገር ግን ፕሮቴስታንት ከሆኑ በኋላ ሁለቱን ሚስቶቻቸውን ፈተው በአንድ ተወስነው ሲኖሩ እ/ኤ/አ/ ፲፱፻፳ ሚስታቸው በመሞታቸው በ፲፱፻፴፬ በ፩፻፳፭ ዓመታቸው አራተኛ ሚስት አግብተው አራት ህፃናት አስወልደዋል ።አራተኛ ሚስታቸውም በወሊድ ሞተዋል።
(መስከረም 17 ቀን 1960 የወጣው አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013