«ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ወንጀለኛ መሆኑን መንግሥት ካወጀ በኋላ ያልታሰረ ግለሰብ የለም፡፡ ልዩነቱ መንግሥት ቀለብ እያቀረበለት በመንግሥት እስር ቤት መሆኑና እራሱን ማሰሩ ነው፡፡ በእኔ እምነት ሁሉም ታስረዋል፡፡ እንዲያውም በመንግሥት እስር ቤት የታሰሩ ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው እየጠየቁዋቸውና ስፖርት እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ ራሳቸውን ያሰሩ ግን ይህንን ዕድል አላገኙም፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወንጀል ሰርቶ ተሸሽጎ የሚቀር የለም » በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነበር፡፡
ይህ ታላቅ እውነታ በአንክሮ ሲታሰብ ያስገርማል፡፡ ብዙዎቻችን ጥፋተኞችና ወንጀለኞች ታስረው ሲንገላቱ ካላየን በስተቀር እየተቀጡ አይመስለንም፡፡ እውነታው ግን እርሳቸው እንዳሉት ነው፡፡
የህግ የበላይነት በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ከህግ በታችና እኩል መሆናቸውን የሚያመላክት ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን፤ የህግ የበላይነት ማንም ዜጋ ሃይል ባለው አካል እንዳይጠቃ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ያለ ህግ የበላይነት የመንግሥት ስርዓትም የዜጎች መብትም ከንቱ ናቸው። በየትኛውም አገር መንግሥት ሆነ ሃያል ነን ብለው የሚያስቡ ሃይሎች በህግ ካልተገደቡ ታላቅ አደጋን ያስከትላሉ፡፡ ፈላጭ ቆራጭነት ይሰፍናል፤ አድሎአዊነትም ይነግሳል፤ ዘረፋ ይስፋፋል፡፡ ተረጋግቶ መኖርና ወጥቶ መግባት ይናፈቃል፡፡
በየትኛውም ጊዜ በየትኛውም ስፍራ የአገራት መንግሥታት የህግ የበላይነትን ለድርድር አቅርበው አያውቁም። ዜጎች በህግ የበላይነት ካልተዳደሩ አዋጅ፣ ህግና ደንብ ወይም መመሪያ ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም። የህግ የበላይነት ሲጣስ በአገር ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ተፅዕኖን ያስከትላል። ይህ በመሆኑም ዜጎችና እነርሱን የሚያስተዳድረው መንግሥት የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ታላቅ አደራ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ሕግ በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የዋስትና መብት የሚከለክል ህግ ሆኖ ሳለ አንዳንዶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ተይዘው በዋስትና ይለቀቃሉ፤ አንዳንዶች ዋስትና ተከልክለው ፍርዳቸው እየተጓተተ በእስር ይንገላታሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ዘርፈው ባገኙት ገንዘብ በተቀናጣ ህይወት ካለ ተጠያቂነት ሲንደላቀቁ፣ ልጆቻቸው ውድ ክፍያ የሚከፈልበት ትምህርት ቤት ሲማሩ፣ ለትንሽ ህክምና ውጭ አገር ሲመላለሱ ይታያል። ‹‹መንግሥት በሚከፍላቸው ደመወዝ ነው! ›› እንዳይባል መንግሥት የሚከፍላቸው ደመወዝ መጠኑ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የተቀናጣ ኑሮ ከየት መጣ? ብሎ የሚጠይቅ ያለመኖሩ ሚዛናዊነትን የሚያጎድል ነው፡፡
የአገርን ልማት እያደናቀፉ፣ የህዝብ የኑሮ ደረጃ አሳዛኝ በሆነበት ወቅት ከህዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ እነርሱና ቤተሰባቸውን ያንደላቀቁ አልጠግብ ባይ ሌቦችን መቅጣት « ሙስና የአገሪቱና የሥርዓቱ አደጋ ነው፣ ሙስናን የሚሸከም ማሕበረሰብ መፍጠር የለብንም» ከሚል መንግሥት የሚጠበቅ ነው።
ይህ በመሆኑም ባለፉት ወራቶች በአገሪቱ ከፍተኛ የሌብነት ወንጀል የፈፀሙ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችን በህግ የመጠየቅ እንቅስቃሴ ሲጀመር በሌብነት ወንጀል የላቀ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች መደበቂያ ፈልገው ከወንጀል ለማምለጥ ከመሞከር ባሻገር የሌብነት ጥፋታቸውን በብሄር ላይ ጥቃት እየተፈፀመ በማስመሰል ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሞክሩ ታይቷል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበረው የመንግሥት አስተዳደር ልቅ በሆነ መንገድ በዝርፊያ ተሰማርተው የነበሩት ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ ካልሆኑ እነርሱን የሚከተለው ትውልድ ሌብነት ነውር መሆኑን ዘንግቶ እንደ በጎ ሥራ በመቁጠር እርሱም ሊፈፅመው እንደማይነሳሳ ምንም ማስተማመኛ ሊኖር አይችልም፡፡
ይህ በመሆኑም የአገርንና የሕዝብን ንብረት ከሌቦች ለመታደግ የህግ የበላይነትን በሁሉም መስክ ተግባራዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሌቦች ካልተያዙ በሰላም እየኖሩ ከመሰላቸውና የሕግ ተጠያቂነት የማይመጣባቸው ከመሰላቸው ሃሳባቸው ዘላቂ እንደማይሆን ሕዝብም መንግሥትም ጊዜው ሲደርስ ሊጠይቃቸው እንደሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከሕግ ለማምለጥ በተለያዩ ሥፍራዎች መሽገው የሚገኙ ሁሉ ይህ የመሰወር ድርጊታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እራስን ከማሰር የተለየ ባለመሆኑ ለጊዜው ከሕዝብና ከመንግሥት መሰወራቸው ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ዓይነት ተግባር እየፈፀሙ እንዳሉ ተገንዝበው ራሳቸውን ከማሰር ነፃ አውጥተው በመደበኛው ሕግ መዳኘትና ከዘወትር ሰቀቀንም የመዳን ምርጫው የእነርሱ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011