ዓለማችን በየዘመኑ በርካታ አምባገነን መሪዎችና በየደረጃው በአመራር ላይ ያሉ አረመኔ ገዳዮችን አስተናግዳለች ። ለአብነትም በዓለም ላይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያን እንዲጨፈጨፉ ያደረገው ቁጥር አንድ አምባገነን አዶልፍ ሂትለር፣ በአረመኔነቱ አቻ የማይገኝለት ጆሴፍ ስታሊን፣ የኡጋንዳው ሰው በላይ ኢዲ አሚን ዳዳ፣ የኢራቁ አምባገነን መሪ ሳዳም ሁሴን፣ የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊና ሌሎች ተጠቃሽ ናቸው ።
እነዚህ መሪዎች ከላይ ዋናውን መንበር ይቆጣጠሩ እንጂ ከነሱ ስር በመሆን የራሳቸው መረብ የዘረጉና ሕዝባቸውን የጨፈጨፉ አምባገነኖች መኖራቸውም በየዘመኑ የታየ እውነታ ነው ።ለምሳሌ ከአዶልፍ ሂትለር ጀርባ በመሆን በርካታ አይሁዳውያንን ሲያስጨፈጭፍ የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ እና በሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለብዙ ዜጎች እልቂት መንስኤ የነበረው ሌቪሪየንቲ ብሪያ ተጠቃሽ ናቸው ።
እነዚህና መሰል አምባገነኖች ታዲያ በዘመናቸው ሰዎችን ለማይገባ ሞትና እንግልት በመዳረግ አቻ የሌላቸው ናቸው ። አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሙትም ሰዎች ወደሞት እንዲሄዱ የሚያነሳሳና የሚገፋፋ ፕሮፓጋንዳ ነው ።ነገር ግን እነሱ ሌሎች ወደሞት እንዲሄዱና የነሱን ዕድሜ እንዲያራዝሙላቸው ያደርጋሉ እንጂ ራሳቸው ለመሞት ዝግጁ አይደሉም ።ለነሱ መግደል እንጂ መሞት ፈጽሞ አይታሰብም ።እነሳዳም ሁሴን እና ሙአመር ጋዳፊ ያንን ሁሉ ሕዝብ ካስጨፈጨፉ በኋላ በዚያ መልኩ በአሳፋሪ ሁኔታ በቁጥጥር ስር የዋሉበትና የተገደሉበት መንገድም ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው ።
ለ17 ዓመታት በትጥቅ ትግል ወቅት በርካታ ወጣቶችን ሲያስፈጁ የነበሩትና ከዚያም በኋላ በ27 ዓመታት የመንግሥታዊ አስተዳደር ሥልጣናቸው አገር ሲመሩ የቆዩት የጁንታው አመራሮችም በነዚህ ጊዜያት ሁሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል ።ከበርካቶች ሞት በስተጀርባም ስማቸው ይነሳል ።እነሱ ግን
እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ የሕይወት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ አይደሉም ።ለዚህ ደግሞ የሴራው አውራ ስብሃት ነጋ ትልቅ ምሳሌ ነው ።
አቶ ስብሃት ነጋ ህወሓትን ከመሰረቱ ጥቂት ታጋዮች ግንባር ቀደሙ ነው ።በትጥቅ ትግሉ የመጀመሪያ ጊዜያትም ድርጅቱን ከፊት ሲመራ ቆይቷል ።ድርጅቱ ባሳለፋቸው የ17 ዓመታት የትግል ወቅቶችም ይህ ሰው ትልቅ ሚና ነበረው። በተለይ በድርጅቱ ውስጥ ለተፈፀሙት ልዩ ልዩ ሴራዎችና ለተሰዉ ንፁሃን ዜጎች ይህ ሰው በቀጥታ እጁ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነሳል ። የትግሉ አንድ አካል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ከዓመታት በፊት በፃፉት መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት ድርጅቱ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የመብት ጥያቄ ያነሱ በርካታ አባሎቹን እየበላ የመጣ ነው ።በዚህ ውስጥ ደግሞ ይህ ሰው ግንባር ቀደም ሚና ነበረው ።ከዚህም በተጨማሪ ኢዲዩን የመሳሰሉ ድርጅቶችን በሴራ በማጥፋትና መሪዎቻቸውን በግፍ በማስገደል እንዲገደሉ በማድረግ ለተሰራው ግፍ የዚህ ሰው እጅ ረጅም እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ከዚያ በኋላም ቢሆን በ27 ዓመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን አቶ ስብሃት ነጋ እጅ የማይፈነቅለው ድንጋይ የማይሰራው ሃጢያት እንዳልነበር ብዙዎች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው ።ለአብነትም በ1993 በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ልዩነት ውስጥ አቶ ስብሃት ነጋ የሴራው አካል በመሆንና አምባገነንነት ይበልጥ ስር እንዲሰድ በማድረግ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም፡፡
ቀንደኞቹ የህወሓት ጁንታ አመራሮች ላለፉት 46 ዓመታት ከወጣቱ ጀርባ አልጠፉም ።በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ጥይት የሚመታው ከነሱ ፊት ያሉትን ንፁሃን ዜጎች እንጂ እነሱን አይደለም ።በነዚያ የደርግ የትግል ዘመናትም የትግራይ ሕዝብ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ልጆቹን ለጦርነት ሲገብር እነዚህ የጁንታ አመራሮች ከኋላ ሆነው ሌላውን ለጦርነት ከመማገድ በዘለለ አንዳችም ጭረት አልገጠማቸውም ።
እነዚህ የጁንታው አመራሮች በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ያገኙትን ሁሉ ለእኔ በሚል ስግብግብ ስሜት ከታገሉለት ዓላማ ውጪ በዘረፋና በግድያ የኖሩ ናቸው ።የማይጠረቃው ሆዳቸው እና ለግፍ የማይቦዝነው እጃቸው ማብቂያ በሌለው ዘረፋና ግድያ ተሰማርቶ እንታገልልሃለን ያሉትን ሕዝብ ጭምር ሲያስከፉና ሲረግጡ ኖሩ ።ነገር ግን የግፍ ጊዜው ሲደርስ እነሱ በተራቸው ፅዋቸው ሞልቶ ፈሰሰ ።
እነዚህ የጁንታው አመራሮች ከ46 ዓመታት በኋላም ሞትን እንደሸሹ ናቸው ።ዛሬ ግን ትናንት አይደለምና በሕዝብ ውስጥ መደበቅ አይቻልም ።ምክንያቱም ትናንት በደል ያንገበገበው ሕዝብ ከጎናቸው ሆኖ ወደሥልጣን ቢያወጣቸውም ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሰሩት ግፍና መከራ ግን አጋልጦ እንዲሰጣቸው እያደረጋቸው ነው ።እነሆ የአምባገነኖች መጨረሻም ተይዞ ለፍርድ መቅረብ ነው ።
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም