ኪነጥበብ ሀገራችን የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል!

ኪነጥበብ ለአንድ ሀገር ዕድገት የማይተካ ሚና ይጫወታል። ኪነጥበብ አስተሳሰብን ያርቃል፤ አስተሳሰብ ደግሞ የፈጠራ አቅምን በማጎልበት ዕድገትን ስለሚያመጣ ሁለቱ ተመጋጋቢዎች ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ለጥበብ ትኩረት የሰጠ ሀገር ፈጠራዎች ይበራከታሉ፤ ምናባዊ ዕይታዎቹ ይሰፋሉ፤ የማስተዋል አቅሞች ይጠናከራሉ በሂደቱም ዕድገት እና ብልፅግና እውን ይሆናል። ከዚህ በተቃራኒ ለጥበብ ቦታ የነፈጉ ሀገራት ምናባዊ አቅማቸው የተዳከመ ስለሚሆን በረባ ባልረባው ወደ አለመግባባት እና ግጭት ስለሚገቡ ዕድገት እና ብልፅግናንም ማረጋገጥ ይሳናቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከተለያዩ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩትም ጥበባት ለሀገር ማንነት እና ዕድገት ቁልፍ ናቸው። ባህላዊ ሀብትን ጠብቀው ያቆያሉ። ለማኅበራዊ አንድነት አበክረው በመሥራትም ብዝኃነት ላላቸው ማኅበረሰቦች ድምፅ ይሆናሉ።

በትምህርት ረገድም ጥበባት ፈጠራን እና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ያሳድጋሉ። በኢኮኖሚ ረገድም ጥበባት ፈጠራን፣ ቱሪዝምን እና ሥራ ፈጠራን የመምራት አቅምም አላቸው።

ኢትዮጵያውያን ለጥበብ ቀናዒ ልብ አላቸው። ነፍሳቸው ለጥበብ የተሰጠች ነች። ኢትዮጵያውያን ጀግንነታቸውን፤ አብሮነታቸውን፤ መከፋት መደሰታቸውን፤ ልማት ተግዳሮቶቻቸውን በጥበብ የመግለጽ ባህል አላቸው።

እንደየዘመናቱም ጥበብን ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲጠቀሙባት ኖረዋል። የሀገር ሉዓላዊነት ሲደፈር፤ የኢትዮጵያን ክብር እና ዝናን ዝቅ ለማድረግ ሲሞከር፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ወዘተ ጥበብ ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ ሀገር ታድጋለች፤ ኢትዮጵያውያንን ለድል አብቅታለች።

ሆኖም ጥበብ ካላት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እና ጠቀሜታ አንጻር ኢትዮጵያውያን አስበን እና አልመን ጥበብን ለዕድገታቸው እና ለብልፅግናችን መነሻ አድርገን ስንጠቀምበት አንታይም።

ጥበብ ዕድገት እና ብልፅግናን የማረጋገጥ ኃይል ያለው ቢሆንም ይህንን ብርቱ አቅም ሳንጠቀምበት ለዘመናት ኖረናል። ጥበብ አብሮነትን በመስበክ፤ ወንድማማችነትን በማጎልበት፤ የሥራ ባህልን በማነቃቃት እና ዜጎች የጋራ ራዕይ እንዲኖራቸው በማነቃቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለወጠች ሀገርን መፍጠር ይቻላል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ለጥበብ የተሻለ ትኩረት መሰጠቱ ባለሙያዎች ያላቸውን እምቅ አቅም በማውጣት ለሀገራቸው እድገት እና ብልፅግና የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያበረታታ ነው። የሚሠሩ ልማቶች ጥበብ እና ጥበበኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

ስለዚህም በጥበቡ መስክ የተሰማሩ ሙያተኞች ለሀገራዊ ማንነት እና ዕድገት ትኩረት በመስጠት ሊሠሩ ይገባል። በተለይም በነጣጣይ ትርክት ምክንያት የተዳከሙትን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማከም እና እንደገና አብሮነት እና አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ የጥበብ ባለሙያዎች ሙያዊ አቅማቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።

ኪነ ጥበብ በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይችላል። ለውጡ ወንድማማችነትን፤ አንድነትን፤ ሰላምን እና ልማትን ከፊቱ አድርጎ የሚጓዝ በመሆኑ ይህ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ ጥበበኞች ሙያዊ አስተዋጿቸውን ሊያበረክቱ ይገባል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነፃነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው። በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል። ሰላም የእሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው። ስለዚህም እነዚህ እሴቶች ተጠናክረው እንዲወጡ እና የማንነታችን መገለጫ ሆነው ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ኪነጥበብ የማይተካ ሚና ይጫወታል። ከሰሞኑ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ባደረጉት ውይይት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ባለሙያዎቹ ጥበብን ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በሚገባ እንዲጠቀሙ መክረዋል።

ስለዚህም የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተፈጠሩትን ሰፊ ዕድሎች በመጠቀም እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጠቢባን ሀገራችን የጀመረችውን የዕድገት ጎዳና በማፋጠን ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You