ታምራት ተስፋዬ
ኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 44/1 ማንኛውም ሰው ንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይሁንና በከተሞቻችን የሚስተዋለው የሕዝብ ቁጥር እድገትና ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ምክንያት የሚመነጨው የእርጥብና ደረቅ ቆሻሻ በመጠንና በአይነት ጨምሯል፡፡
ቆሻሻን በአግባቡ ያለመያዝ፣ ያለማጓጓዝና ያለማስወገድም ድክመት ዜጎችንም ለተለያዩ የጤና እክሎች ተጋላጭ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ለከተማ ስነ ምህዳር አለመጠበቅ ምክንያት ሆኖ ዘልቋል፡፡
ይህ ድክመት መፍትሄ እየራቀው በሄደ ቁጥርም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራው የዚያኑ ያህል መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡በመሆኑም የዘርፉን አሰራር ማሻሻል፣ የአደረጃጀት ክፍተት መፈተሽ፣ ለዘርፉ የሚያስፈልግ ሁሉን አቀፍ የትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በማከናወን የሕብረተሰብን አመለካከት መቀየር የግድ ይላል፡፡ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት በማሳተፍ ዘርፉን ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ማስተሳሰር ከተቻለ ደግሞ ኪሳራን ወደ ትርፍ ለመቀየር አይቸግርም።
መረጃዎች እንደሚመላክቱት ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው የሚጣለው ቆሻሻ እንደ ሀብት ተቆጥሮ በሚፈለገው ደረጃ ለኢኮኖሚ አገልግሎት እየዋለ አይደለም ።በእርግጥ በቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ ረገድ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እየተስፋፉና ለዜጎች የስራ ዕድል እየተፈጠሩ ይገኛሉ ።
ለኢንተርፕራይዞችም እየተከፈለ ያለው የአገልግሎት ክፍያ በዋናነት ከህብረተሰቡ የሚሰበሰብና ከመንግስት የሚመደብ ፋይናንስ እንጂ ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር ዘርፉ በሚያመነጨው ፋይናንስ አይደለም። ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም፣ ሪሳይክል በማድረግና ሌሎችም ስራዎች ላይ ዜጎች ተሰማርተው እንዲሰሩ ብሎም ዘርፉ ራሱን እንዲችል የማድረግ ተግባር እጅግ ደካማ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ዘግይቶም ቢሆን የችግሩን አሳሳቢነት ተመልክቶ የከተሞችን የጽዳት ስርዓት በማሻሻል ከተሞች ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንዲሆኑ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምራል ። ከጥንካሬው ይልቅ ድክመቱ ጎልቶ የሚስተዋለውን የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎች ጀምራል።
የደረቅ ቆሻሻን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችሉ የጊዜያዊ ደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ አካባቢዎች መገንባትም የዚህ አንድ አካል ነው። የጣቢያዎቹ ግንባታም ቆሻሻን በስርዓትና በየፈርጁ በመለየት መልሶ ለጥቅም ለማዋል ሲባል ታልመው የሚገነቡ ናቸው።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ከሶስት አመት በፊት የከተማዋን የጽዳት ሥራ በተቀናጀ መልኩ መፈፀም የሚያስችል የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያ የግንባታ መሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች እየተገነቡ ናቸው ። አንዳንዶቹም ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሁለት ጊዜያዊ ጣቢያዎች ለምረቃ መብቃታቸው የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ለመሆኑ ፕሮጀክቶቹ አሁን ላይ ያሉበት አፈፃፀም ምን ይመስላል፣ ወቅታዊ ፈተናዎቻቸውስ የሚል ጥያቄን በማንሳት በተለይም የፕሮጀክቶቹን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወቅታዊ ምስል ለመመልከት ሞክሯል፡፡
ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የክፍለ ከተማው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ከበደ፤ በክፍለ ከተማው በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረገድ ስለሚሰሩ ተግባራትና ስለተገኙ ውጤቶች በተለይ የደረቅ ቆሻሻ ማቆያ ፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ጥንካሬም ሆነ ድክመት በስፋት አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ መስፍን ገለፃም ፣ በአሁን ወቅት በክፍለ ከተማው በ15 የሽርክና ህብረት ስራ ማህበራት፣880 በላይ በሚሆኑ የመንገድ ጽዳት ባለሙያዎች፣ከሁለት እስከ አምስት ሺ በሚደርሱ የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚ ነዋሪዎች ከተማን ውብ ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻም በአመት 102 ሺ 72 ቶን እንደሚገመትና ከዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነው ማስወገድ ብቻ ሳይሆን መልሶ ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ መስፍን፣ቆሻሻን በአግባቡ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን መልሶ ወደ ሃብትነት ለመቀየርና ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ በተለይም ስራ የመፍጠር ተግባርም በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
ክፍለ ከተማው ቆሻሻን ወደ ረጲ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እያጓጓዘ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት አቶ መስፍን፣ በየወረዳው በተመረጡ ቦታዎች በአምስት መቶ ካሬ ስፋት ላይ ለ24 ሰዓት ቆሻሻው የሚቆይበትና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረግበት ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ማቆያ ጣቢያ ለመገንባት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ ረገድም በክፍለ ከተማው መገንባት የጀመሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንና በተለይ የሶስቱ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከ70 እስከ 100 በመቶ መድረሱን ያመላከቱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣‹‹በወረዳ አምስት የሚገኘው ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ማቆያ ፕሮጀክት ተጠናቋል፣ ወረዳ 10 እና 12 የሚገኙትም ከ 70 እስከ 90 በመቶ ግንባታ አፈፃፀም ላይ ደርሰዋልም›› ይላሉ። እስከ ጥር መጨረሻ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ጥርጥር የላቸውም፡፡
ፕሮጀክቱ ሁሉም ክፍለ ከተማና በሁሉም ወረዳዎች ላይ እንዲተገበር ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መስፍን፣ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማም አስራ አምስቱም ወረዳ ላይ ታስቧል፣ይሁንና በጀት፣ ዲዛይንና ጨምሮ በተለያዩ ምክንያት አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ችግር ገጥማቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር ‹‹ቆሻሻ ወደ አካባቢያችን መቅረብና መከማቸት የለበትም እና የማቆያ ፕሮጀክቶቹ በአካባቢያችን ሊገነቡ አይገባም ››የሚሉ ቅሬታና የግንዛቤ ክፍተቶችም የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ህልውና ላይ ተደቅነው ከነበሩ ከባድ ተግዳሮቹ መካከል ያካትታል፡፡በዚህ ምክንያት ብቻ በአንዳንድ ቦታዎች የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ስፍራዎች የቦታ ለውጥ እንደተደረገላቸው ሳይጠቁሙ አያልፉም፡፡
በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ልዩ ትኩረት እንደተሰጣቸው የተናገሩት አቶ መስፍን፣ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅም ቅድሚያ እንደተሰጠውና አፈፃፀሙ ታይቶ የተቀሩትን የማስጀመር ተግባር እየተፋጠነ ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ፡፡
ቀጣይ የሚሰሩ ተግባራትን በሚመለከትም፣ ፕሮጀ ክቶቹ በሁሉም ወረዳዎች ተፈፃሚ ከማድረግ አንፃር ተከታታይ መድረክ በመፍጠር ከሚገነቡበት አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ስለ ፕሮጀክቶቹ ዓላማና ጥቅም ውይይት ማድረግና መግባባት ላይ መድረስ የግድ እንደሚል ይናገራሉ። ይህን ማድረግና የጋራ መግባባት መፍጠር ከተቻለም ፕሮጀክቶቹ የበጀትም ሆነ የባለሙያ እጥረት የሌለባቸው በመሆኑና በአሁን ወቅት ከተሰጣቸው ትኩረት አንፃር ትግበራቸው ቀልጣፋ እንደሚሆን ጥርጥር እንደሌላቸው ነው ያመላከቱት ።
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013