ሰላማዊት ውቤ
በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረን መደዳውን የተሰደሩ የላስቲክ ቤቶችን ቃኝተናል። ገርጂ፣ መገናኛ፣ አቧሬ፣ ካዛንቺስ፣ ፒያሳ፣ አራት፣ ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ ከቃኘ ናቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። በደምሳሳው የላስቲክ ቤቶች የሌሉበት፤ ተወጥረው ያልተዘረጉበት የከተማዋ አካባቢዎች የሉም። አብዛኞቹ የሚገኙት በአውራ እና ገባ ባሉ ቅያስ መንገዶች ውስጥ ነው። ታዲያ እኛም እንደታዘብነው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት አብዛኞቹ ቤቶች በፀሐይ ተበልተዋል። በክረምት ዝናብ ሳስተዋል። በአቧራ ተውጠዋል። እውነት ለመናገር ለዓይንም አይማርኩ። የአንዳንድ ህንፃዎችን ውበትና የአጠቃላይ የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ አጠልሽተውት ይስተዋላሉ። በዓለም ከሚገኙ አሥር የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ለሚነገርላት ለውቢቱ አዲስ አበባም በፍፁም አይመጥኑም። ይሁን እንጂ ዕለት ዕለት ቁጥራቸው በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
አንድ ላስቲክ ቤት መወጠሩን ተከትሎ ሌሎች በርካታ ላስቲክ ቤቶች አካባቢውን በፍጥነት ሲያጥለቀልቁት ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል። ነገር ግን እስከ መቼ? የሚለው የሚመለከተውን አካል ምላሽ ይሻል። ከእነዚህ የላስቲክ ቤቶችና ባለቤቶች መካከል አራት ኪሎ ‹‹ሰብለ አሣ ጀርባ የተለያዩ አልባሳት ነጋዴዎች ማህበር ተብለው የሚጠሩትን ለማሳያ መርጠናል።
ካብቱ ሽኩር በዚህ አካባቢ ካሉ ላስቲክ ቤቶች በጫማ ንግድ ላይ ከተሰማሩት አንዱና የማህበሩም ሰብሳቢ ነው። እንዳጫወተን የማህበሩ አባላት ቁጥር 90 ደርሷል። ከዘጠናዎቹ አባላት መካከል 30ዎቹ ሴቶች ናቸው። ሁሉም ቀደም ሲል ጫማን ጨምሮ አራት ኪሎ አደባባይ አካባቢ በህገወጥ የተለያዩ አልባሳት ንግድ ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል። እናም በቦታው ትሰሩበት በነበረ አካባቢ ተደራጁ ተብሎ ከተደራጁ በኋላ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ላስቲክ ቤት ሰርተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ወደ ሥራ ሲገቡ በየፊናቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም መነሻ የሚሆናቸው አምስት፣ አምስት ሺህ ብር ብድር ተመቻችቶላቸዋል። በእርግጥ ታድያ ለእነሱ የተሰጣቸው ቦታ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘውና ሰብለ አሣ ቤት ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለውና ገባ ብሎ የሚገኘው የኮብል ስቶን ንጣፍ ያለበት ቅያስ ነው። ቦታው የተሰጣቸው ጊዜያዊ በሚል ሲሆን በመጠኑም ቢሆን ሰወር ያለ በመሆኑ ለዕይታ ተጋላጭ አይደለም።
በከተማዋ ዋና ዋና አውራ መንገዶች ዳር ላይ ተሰድረው የሚስተዋሉት የላስቲክ ቤቶች ግን ከዕይታ በተጨማሪ ለአቧራና ለዝናብ ተጋላጭ በመሆናቸው የከተማዋን ውበት እንደሚያጠለሽቱ አይጠረጠርም። የእነሱም ቤቶች ይሄን ያህል ለዕይታ ተጋላጭ ናቸው ባይባልም እንደ አጠቃላይ ሲቃኘው የከተማዋን ውበት መቀነሳቸው አይቀርም።
ግን ደግሞ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርና የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ሥራ ያስፈልጋቸዋልና የግድ ተኮልኩለዋል። መንግስት ይህን ዕድል ባያመቻችላቸው በተለይ በዚህ በኮሮና ዘመን የእሱ አምስት ቤተሰቦች በረሀብ ያልቁ ነበር። ዘንድሮ ልጆቹን ማስተማርም ቢሆን በፍፁም አይችልም። ከዚህ አንፃር ከውበት ይልቅ ዳቦ በልቶ ማደር ይቀድማል። መንግስትም በቦታው ላይ እንዲሰሩ የፈቀደው ይሄንኑ ታሳቢ አድርጎ ነው።
በሴቶችና በህፃናት አልባሳት ሥራ የተሠማራችው ወይዘሮ ጀሚላ አምደላ እንደነገረችን በቦታው ከወንድሟ ጋር ተጠግታ ነው የምትሰራው። ለረጅም ዓመታት ቤሩት ቆይታለች። የአራት ዓመት ከስምንት ወር ደመወዟን በመጠየቋ በአሰሪዋ የሚያደነዝዝ መድሃኒት ተሰጥቷት እራሷን ስታ ነበር በወገን ድጋፍ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው። እራሷን ካወቀችና ከዳነች በኋላ በምግብ ዝግጅትና በሌሎች ሙያዎች ብትሰለጥንም እስከ አሁን ሥራ አላገኘችም። ከአረብ ሀገር ከተመለሰችና ስልጠናውን ከወሰደች ዘንድሮ ስድስተኛ ዓመቷን ጨርሳ ሰባተኛዋን ይዛለች።
ከወንድሟ ጋር በላስቲክ ቤት ውስጥ ተጠግታ በምታገኘው ገቢ አንድ የምታሳድጋትን ልጅና ሁለት ልጆቿን ጨምሮ እራሷን ጨምሮ አራት ቤተሰብ ታስተዳድራለች። ደግነቱ የቤት ኪራይ የለባትም። ቢሆንም ዕድሜ በዚህ የላስቲክ ቤት ላስጠጋት ወንድሟ ለሰጠው መንግስት የእሷንና የቤተሰቧን የዕለት ጉርስ መሸፈን ችላለች። የላስቲክ ቤቱ በከተማዋ ገጽታ ላይ የሚያስከትለውን ችግርም እንደ ዜጋ ከዕለት ጉርሷ ባሻገር ታያዋለች። ውበቷን ማጠልሸቱ ይታወቃታል። እናም እንደ አማራጭ ላስቲክ ቤቶቹን በላሜራ ወይም በሌሎች የከተማዋን ውበት በማያጠለሹ መቀየር ተግባር እንደ አማራጭ ቢወሰድ የሚል ሀሳብ ታቀርባለች።
ከሚመለከተው አካል ጊዚያዊ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ መግባታቸውን በመግለፅ አስተያየቱን የጀመረው አቶ ፈድሉ ሁሴን በሸሚዝ ልብስ ንግድ ተሰማርቷል። ፈድሉ የማህበሩም አመራር ነው። እንደሰጠን አስተያየት አሁን ላይ ቦታውን በፈቀደላቸው አካል ካፒታላችሁ ከፍ ሲል በዚሁ ቦታ ወደ መደበኛነት ትገባላችሁ ተብለዋል። የእነሱ ላስቲክ ቤት ከዕይታ የተሰወረ ቅያስ ቦታ ላይ በመሆኑና ላስቲኩ እንብዛም ያረጀ ባለመሆኑ ይሄን ያህል ለዓይን ያስጠላል ብሎ አይገምትም። ቢሆንም የከተማዋን ውበት የማጠልሸቱ አጀንዳ በቅርቡ ወደ መደበኛነት ሲፈቀድላቸውና ቤቶቹ ወደ ላሜራ ወይም ኮንቴነር ሲለወጡ ይዘጋል የሚል ተስፋ አለው።
እስከዛው ችግሩን አቻችሎ ማለፍ እንደሚገባ አስተያየቱን የለገሰን ደግሞ በዚሁ ቦታ በሴቶች ጫማ ሽያጭ የተሰማራውና በእርግጥም ቤቶቹ በአዲስ አበባ ከተማ ውበትና ፕላን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥቶ የገለፀልን ወጣት አንዱዓለም ተክለሃይማኖት ነው። እንደ ወጣቱ አስተያየት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በ2002 ዓ.ም ነው የጨረሰው። ቀጣይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አግኝቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ውጤት ባለማምጣቱ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ሥራ ፈትቶ ተቀምጧል።
በአንድ ዘመዱ ምክርና ቤተሰብ በሰጠው ጥቂት ገንዘብ ስራ በፈታ 10ኛ ዓመቱን ሊይዝ በተቃረበበት አጋማሽ ላይ አራት ኪሎ አደባባይ አካባቢ ሕገወጥ የጎዳና ንግድ ጀምሮ ይሰራ ነበር። ብዙ ጊዜ በደንብ አስከባሪዎች ንብረቱ ተወርሶበታል። ተይዞ ተደብድቦም ተደጋጋሚ ጉዳት አግኝቶታል። የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ግን ይሄን ታሪኩን የቀየረው አሁን የሚሰራበት የላስቲክ ቤት ስለተሰጠውና ተረጋግቶ መሥራት የሚያስችል ዕድል በማግኘቱ ደስ ብሎታል።
በሥራው በሚያገኘው ገቢ ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቆ፣ ቀለቡንና የቤት ኪራይ ችሎ ራሱን ለማስተዳደር በቅቷል። ቢሆንም እንደማንኛውም ዜጋ በተለይም እንደ አፍላ ወጣት ከተማዋ በላስቲክ ቤቶች መወረሯ ያሳስበዋል። ላስቲክ ቤቶች ቢያንስ እንደነሱ ቅያስ መንገድ ውስጥ እንጂ ለውጭ ዜጎች፣ ቱሪስቶችና እንግዶች ዕይታ ተጋላጭ በሆኑ አውራ መንገዶች ዳር እንዲሰደሩ ባይደረግና በሌሎች ቁሶች ቢተኩ ተመራጭ ነው ሲልም ይመክራል።
በላስቲክ ቤቶቹ ትይዩ ባለው ቅያስ በአበበና ጓደኞቹ ፓርኪንግ ተቀጥሮ የሚሰራው አቶ ፋንታሁን ደምሴ እንደሰጠን አስተያየት፤ ላስቲክ ቤቶቹ መኪና በሚተላለፍበትና መንገድ ላይ ነው ያሉት። በእርግጥ መንገዱ ኮብል ስቶን በመሆኑ ይሄን ያህል የሚያስነሳው አቧራ የለም። ሆኖም በፀሐይና በዝናብ በመበላቱ ቶሎ ስለሚበላሽ በተደጋጋሚ ላስቲኩን ሲቀይሩ አስተውሏል። በተጨማሪም በተለይ እነሱ መጥተው ላስቲክ ከዘረጉ መንገዱ ጠብቧል።
የፓርኪንግ አገልግሎት የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ቁጥር ጨምሯል። በዚህ ምክንያት ቀድሞ 1ሺ200 የነበረው ደመወዙ አሁን ላይ ወደ 1ሺህ 600 ብር ማደጉ ማሳያ ነው። በዚህ ላይ ከአምስት ብር ጀምሮ ጉርሻ የሚሰጠው ተገልጋይ አለ። ሆኖም መንገዱ ለፓርኪንግም ሆነ ለንግድና ለእግር መንገድ እንዳልበቃ አይቷል።
አብዛኞቹ ነዋሪዎቹ በአጠቃላይ በአንድ ወገን የላስቲክ ቤቶቹ ባለቤቶች፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤቶቹ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ላጨናነቃትና ሥራ አጥነት ለተንሰራፋባት፣ ከዚህ የተነሳ አብዛኛው ነዋሪ የዕለት ጉርሱን ፍለጋ ለሚራወጥባት አዲስ አበባ ዓይነተኛ መፍትሄ መሆናቸውን ይናገራሉ። ውበትና ፕላን ሆድ ከሚሞላ ዳቦ መቅደም የለባቸውም ባይም ናቸው። በሌላ ወገን ለመኪናም ሆነ ለእግር እንቅስቃሴ ምቾት አለመስጠታቸው፣መጨናነቅ መፍጠራቸው፣ለትራፊክ ደህንነት ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውም ጉዳይ መታሰብ እንዳለበት ያስጠነቅቃሉ።
እንደ ፋሽን ዕለት በዕለት በየሥፍራው የመስፋፋትና የመዘርጋታቸው ሂደት ቢያንስ ከአሁን ወዲያ እንኳን ያለውን የከተማዋን መፀኢ ሁለንተና ገጽታ ታሳቢ ባደረግ እርምጃ በሚመለከታቸው አካላት መገታት እንዳለበትም ያሳስባሉ። የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በሚል አንዳንዴ የሚከፈሉት ሳይጨመሩ ቀደም ብሎ የማዕከላዊ ስታቲስቲክ ባወጣው መረጃ መሰረት ከተማዋ ተከፋፍላ በ11 ክፍለ ከተሞች እና በ116 ወረዳዎች የተዋቀረችው አዲስ አበባ ቀድመው ላጠሯትና ውበቷን እያጠለሹ ላሉት የላስቲክ ቤቶች አንድ መላ እንዲዘይዱ ይጠይቃሉ።
አቶ ደምሴ ግርማ እንዲህ ዓይነቱን አስተያየት ከሚጋሩት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። እንደ አስተያታቸው የላስቲክ ቤት ባለቤቶቹ በዋንኛነት በእነዚህ መዋቅሮች አማካኝነት የሚተዳደሩ በመሆናቸው መዋቅሮቹ ለመፍትሄው ቀዳሚ መሆን አለባቸው።
እንዲህ ዓይነቶቹ ቤቶች እንዲሰሩና ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውሉ የማድረጉ ሚናም የመዋቅሮቹ ነው። በመሆኑም የፊቱ አንዴ ቢያልፍም ከአሁን በኋላ የከተማዋን ፕላንና ገጽታ እያበላሹ መሆኑን ቆም ብለው ሊያዩ ይገባል። ቢያንስ ከአሁን ወዲህ እንዲህ ዓይነቶቹ ቤቶች እንዳይገነቡ ማድረግ አለባቸው። በእርግጥ ቤቶቹ ባለቤቶቻቸው ወደው ሳይሆን ከችግራቸው አንፃር ኑሯቸውን የሚመሩበት ገቢ ለማግኘት የሚቀይሷቸው መሆናቸው ይታወቃል። መንግስትም ሆነ የከተማዋ አስተዳደር ቤቶቹን ቸል ብሎ እየተመለከታቸው ያለው ይህን ታሳቢ አድርጎ ነው። ቢሆንም ደግሞ መዋቅሮቹ የግድ ለእነዚህ ዜጎች ሌሎች አማራጮችን መፈለግ አለባቸው። ያሉትን በሌሎች የከተማዋን ውበት በማያጠለሹ ቁሶች እንዲገነቡ ማድረግ ይችላሉ። በአሁኑ ሰዓት የእግረኛንም ሆነ የመኪናን እንቅስቃሴ በሚያውክ እንዲሁም የትራፊክን ደህንነት በሚያስተጓጉል አካባቢ ያሉት የላስቲክ ቤቶችን ግን ደግሞ ተለዋጭ ቦታ በመስጠት የግድ ማስነሳት ይገባቸዋል። ወደፊት እየተገነቡ ያሉትን አዳዲስ የላስቲክ ቤቶችም የግድ ማስቆም መቻል አለባቸው። ለምሳሌ፦ በከተማዋ ያሉ ጫካ መሰል ክፍት ቦታዎችን መንጥሮ ደርዝ ባለው ሁኔታ ሸንሽኖ የመስጠት አማራጭ መጠቀም ይችላሉ ሲሉም ምክራቸውን በመለገስ አቶ ደምሴ አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
አቶ ነብዩ አሰፋ በዚሁ በላስቲክ ቤቶቹ ፊት ለፊት የሚገኘው ሪቪያ ባርና ሬስቶራንት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የሪቪያ ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ አሰፋ የላስቲክ ቤቶቹ ድባብ የሆቴሉን ገበያ እንዳበላሸው በምሬት ነግረውናል። እንዳከሉት መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ በመስፈሩ በኮብል ስቶን የታነፀው መኪና መንገድም ላይ ጭንቅንቅ ፈጥሯል።
እሳቸው ፊት ለፊት ያለው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎች እንደታዘቡት እግረኛ መንገዱ በቤቶቹ በመያያዙ አስፋልት መሀል ገብቶ ለመሄድ እየተገደደ ያለበት ሁኔታ ፈጥሯል። አቶ ነብዩ ሳቅም ምሬትም በተቀላቀለበት ድምፀት ሆኖም 50 በመቶ ጉዳት ያላቸው ላስቲክ ቤቶቹ 50 በመቶ ጥቅም እንዳላቸውም አጫውተውናል። ለባለቤቶቻቸው መፍጠር የቻሉትን የሥራ ዕድል ቀዳሚ ጥቅም አድርገውታል።
በዚህ አካባቢ ቀን በተለይም ደንገዝገዝ ሲል ማታ ስለሚነጠቅ ወንድም ሆነ ሴት ቦርሳ ይዞና የእጅ ስልክ ጆሮው ላይ ይዞ ማለፍ አይችልም ነበር። በአካባቢው የቆሙ መኪኖችም ተደጋግመው ይፈቱ ነበር። አጥሩ ላይ ሽንት ስለሚሸና ነዋሪው ለጉንፋን ለበሽታ ይጋለጥና የሆቴሉ ተገልጋዮችም ደስ አይላቸውም ነበር። አሁን ላይ የላስቲክ ቤቶቹ በመሰራታችው አልፈው ተርፈው በማዋጣት አራት የጥበቃ ኃይል ቀጥረው በማሰማራታቸው ችግሮቹ በሙሉ ተቀርፈዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ አሰፋ እንደገለፁት፤ የላስቲክ ቤቶቹ የከተማዋን ፕላን የሚያበላሹ ብሎም ከተማዋን የሚያቆሽሹ ናቸው። ለገጽታዋም ጥሩ አይደሉም። መንግስት አንዳንዴ እንደ አቅጣጫም የዜጎችን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ስለሚውሉ ነው ቸል የሚላቸው። ዜጎች ለጊዜውም ቢሆን አማራጭ እንዲያደርጓቸው እንዳንዴም አቅጣጫ የሚመስሉ አሰራሮችን የሚያወርደው። ሆኖም ከከተማዋ ጋር ስለማይሄዱ ቢያንስ ለተሰሩት ከተማ የማያቆሽሹና ቦታ የማይፈጁ አማራጮችን መጠቀም አለበት። ከእንግዲህ ላስቲክ ቤቶች በከተሞች መዘርጋት የለባቸውም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013