መርድ ክፍሉ
ሰው ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት መሆኑ ነው። ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው።
ሰውን መርዳት እንደ ፅድቅ የሚቆጠር ተግባርም ነው። አብዛኛው ለፈጣሪው ይበልጥ የሚቀርብበት መንገድ አድርጎ ስለሚቆጥረው በተለያዩ አካባቢዎች ድሆችን መርዳት የተለመደ ነገርም ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት አሁን አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ በሌላ ጊዜ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
ዛሬ በሻኪሶ የሚገኘውና በጎዳና የሚገኙ ልጆችንና በልመና የሚተዳሩትን ሰዎች የሚደግፈው እኔን ሻኪሶ በጎ አድራጎት ማህበር እንቃኛለን። እኔን ሻኪሶ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሊቀመንበር ወጣት ዳኛቸው አየለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማህበሩን መስርቷል። ከወጣት ዳኛቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተው አቅርበነዋል።
የማህበሩ አመሰራረት
እኔን ሻኪሶ በጎ አድራጎት ማህበር ሲመሰረት የሚቀራረቡ ጓደኛሞች በመሰባሰብ ጓደኝነትን ለማጠናከር በጎ የሆኑ ስራዎች ለምን አይሰራም የሚል ሀሳብ መጣ። በሌላም በኩል የተቸገሩትን ለመርዳት የሚፈልጉ ሰዎችና ማህበራት መስርተው ያልተሳካላቸው ይኖራሉ በሚል በቅርብ የሚገኙ ሰዎችን ለማናገርም ታሰበ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለ18 ሰዎች ጥሪ ቢደረግም ስምንት ሰዎች ብቻ በተገኙበት ውይይት ተደረገ። በተከታታይ ለሶስት ወር ያክል ውይይቶች ተደርገዋል። በተደረጉ ውይይቶች ማህበሩ ምን ይስራ፣ አባላት እንዴት ይመልመሉ፣ እነማን አባል ይሁኑ፣ ማህበሩ እስከየት ድረስ መስራት አለበትና ፈቃድ እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚለውን ነገር ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ከአንድ ዓመት በፊት ማህበሩ የበጎ ስራ ማከናወን የጀመረው በጎዳና የሚገኙ ልጀችንና በልመና የሚተዳዳሩትን ሰብስቦ በማብላት፣ ልብስ በማልበስና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ነበር። ማህበሩ በትንሽ ሰዎች ተመስርቶ ከመቶ በላይ አባላት ቢኖሩትም በቋሚነት 60 የሚሆኑት አባላት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
በሰባት ከሚቴዎች የተዋቀረ ሲሆን የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል። ማህበሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ሰፊ ስራዎችን አከናውኗል። በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች የቫይረሱ ስርጭት በከተማ እንጂ ወደ ሌሎች ቦታዎች አይዛመትም በሚል ተዘናግተው ነበር። ማህበሩ አባላቱን በማሰማራት በመኪና በመዘዋወር የግንዛቤ ስራዎችን ሲያከናውን ነበር።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ሳሙና፣ ሳይኒታይዘርና ማስክ በመያዝ በየቤቱ በመዞር ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ትምህርቶች ተሰጥተዋል። መኪና በማስቆም ተሳፋሪው እጁን እንዲታጠብ በማድረግ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። በዚህ ስራ ማህበሩ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። አብዛኛው የማህበሩ አባላት የግል ስራዎች ያሉት ቢሆንም ባላቸው ትርፍ ሰዓት ስራዎችን ያከናውናሉ።
የማህበሩ ስም ሲታይ ‹‹እኔን ሻኪሶ›› ነው የሚለው። ‹‹እኔን›› የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ አባባል ሲሆን አንድ ሰው ሲጎዳ ለኔ ያድርገው የሚል ስሜት አለው። ለዛም ነው ማህበሩ ስያሜውን መጠቀም የፈለገው።
በአሁን ወቅት ሻኪሶ ውስጥ የተለያዩ ማህበራት በጎ ስራ ለማከናወን ፈቃድ ሲሞክሩ ሲታይ ጥሩ ስሜት ይሰጣል። አንዳንድ ማህራት ደግሞ እኔን የሚለውን ቃል ወደ ኦሮሞኛ ቀይረው ‹‹እኔ›› በሚል ስራዎች እየሰሩ ናቸው። ሌሎችም ተቀራራቢ የሆነ ስም ሰጥተው በጎ የሆኑ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።
እኔን የሻኪሶ በጎ አድራጎት ማህበር ዝም ብሎ እዚህ የደረሰ አይደለም። የተለያዩ ውጣ ወረዶችን አልፏል። ያጋጠሙት ችግሮች በአንድ ዓመት ውስጥ ከተመሰረተ ማህበር የማይጠበቁ ናቸው። ማህበሩን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ የሚጠቀምባቸውን ሎጎዎች ቀይሩ እስከመባል ተደርሶም ነበር።
የኦሮሞኛ ቋንቋ አይጠቀሙም በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ ወቀሳ ተሰንዝሮበታል። በተቃራኒው ደግሞ በኦሮሞኛ ቋንቋ እየተጠቀሙ ለማህበሩ ጥብቅና የሚቆሙ ሰዎችም ነበሩ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ማህበሩን አፍርሰው በስሙ መጠቀም ይሞክሩ ነበር።
ማህበሩ በየወሩ ከተማ በማፅዳትና ደም በመለገስ ይታወቃል። ይህ ስራ ሲያከናውን እንደ ማህበር ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ፈጣን ሆነው ነገሮችን የሚያከናውኑና እገዛ የሚያደርጉ ሰዎች ነበሩ። ከኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት ለደም ልገሳ የሚሆኑ ድንኳኖችን በመከራየት ትብብር የሚያደርጉ ብዙ ናቸው።
ማህበሩ ትልልቅ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር ከራሱ አካውንት አውጥቶ አያውቅም። የማህበሩ አባላት በየወሩ 50 ብር እንዲያዋጡ ቢወሰንም እስካሁን ከአስር ሰው በላይ መዋጮ የሚያደርግ ሰው የለም። መስራች አባላቱ አብዛኛውን ወጪ ከራሳቸው እያወጡ ይገኛሉ።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ በዋናነት በልመና የሚተዳሩት ላይ ሰፊ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል። በመጀመሪያ ጎዳና ላይ የወጡ ልጆችን የማንሳት ስራ ይሰራል። የኮቪድ-19 በገባት ወቅት ከ80 በላይ በጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆችን በመሰብሰብ ምግብ የማብላት ስራ አከናውኗል። ከዚህም በኋላ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡትን ስም በመመዝገብ ከሚመለከተው ክፍል ጋር በማገናኘት ወደ መጡበት የሚመለሱበት ሁኔታ አመቻችቷል። ለምሳሌ ከኦሮሚያ ክልል ከአንድ ወረዳ የመጡትን ለወረዳው ደብዳቤ በመፃፍ ጎዳና የወጣው ልጅ የሚያስፈልገው እርዳታ በራሳቸው እንዲያደርጉ ወይም በማህበሩ ድጋፍ እንዲደረግ ይነጋገራል። ከነበሩ ችግሮች በመማር ለመስራት የታቀዱ ስራዎች አሉ።
በልመና የሚተዳደሩትን በተመለከተ ደግሞ ሰዎቹ ከሰው በሚሰጣቸው ምፅዋት የሚተዳደሩ እንደመሆናቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ለችግር ተጋልጠው ነበር። እነሱን ለመደገፍ ልብስ በማዘጋጀት ባሉበት ቤት በመሄድ ምግብ የማቅረብም ስራ ተከናውኗል።
ሰዎቹ ከልመና ወጥተው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ከማመቻቸት በዘለለ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ማስክ በመስጠት እንክብካቤ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። በቀጣይ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን ካሉበት ችግር ለማውጣት እቅዶች ተዘጋጅተዋል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ህብረተሰቡ ማህበሩን ተቀብሎ እገዛ እያደረገ ይገኛል። አንዳንድ ሰው ለምን አባል አላደረጋችሁንም ብለው ወቀሳ እስከማቅረብ ይደርሳሉ። አባል ማግኘት ያስቸግራል በሚባልበት ወቅት አባል አድርጉኝ የሚል ካለ መታደል ነው። ምክንያቱም የአባልነት መታውቂያ ወስደው የሚጠፉ ብዙ ስለሆኑ ነው።
የከተማ ፅዳት በሚደረግበት ወቅት ከአባላቱ ይበልጥ የየአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ ወጥቶ እገዛ የሚያደርገው። በጎ አድራጎት ማህበሩ የሚፈልገው ነገር አለ ከተባለ በከተማ አስተዳደሩም በኩል የሚደረገው ድጋፍ አስደሳች ነው።
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ቢሮ የለውም። በግለሰብ የስራ ቦታ ቢሮ ውስጥ ነው። የተወሰነ ጊዜም በኪራይ ቢሮ ውስጥም ስራ ተከናውኗል። ህብረተሰቡ በማህበሩ ስራ በጣም ደስተኛ ሲሆን በተለይ በደም ልገሳና በጎርፍ የፈረሱ ቤቶች ሲጠገኑ ህብረተሰቡ ርብርብ አድርጓል።
በመንገድ ጠረጋና በኮቪድ-19 የእጅ ማስታጠብ ስራም ህብረተሰቡ ማህበሩን አግዘዋል። አንዳንድ ሰዎች ማህበሩ ከመንግስት ጋር ተባብሮ የሚሰራና በጀት ተመድቦለት የሚንቀሳቀስ አድርገው ያዩታል።
ማህበሩን ያጋጠሙት ችግሮች
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት የበጀት ጉዳዮች በጣም እጥረት አለበት። ለምሳሌ ባለፉት አንድ አመታት በግል አንድ ሰው ከአስር ሺህ ብር በላይ አውጥቷል። ሊቀመንበሩ፣ ጸሀፊውና ቁጥር ኮሚቴው አብዛኛው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ዋና የገቢ ምንጭ የነበረው ወርሃዊ ክፍያ ነበር። መዋጮውን ለመሰብሰብ የግድ ቢሮ አስፈላጊ ነው። ቢሮ አለመኖር የማህበሩን ስራ ከባድ አድርጎታል።
በማህበራዊ ሚድያው ማህበሩን በተመለከተ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች ነበሩ። የተወሰኑ ስም ማጥፊያ ገጾች ላይ ያልሆኑ ነገሮች ሲሰራጩ የነበረ ሲሆን አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ይዘዋወር ነበር። በመጨረሻም ማህበሩ የሚወራውን ነገር ለማስተካከል ውይይቶች አድርጓል። በውይይቱም የማህበሩ አርማ ላይ የሚገኘውን ባንዲራ እንዲቀየር አስተያየቶች መጡ። ማስተካከል የሚገቡ ነገሮች ሲስተካከሉ ነገሮች መርገብ ጀመሩ። ማህበሩ ምንም አይነት ችግሮች ቢያጋጥሙትም መስራት ያለበትን እየሰራ ይገኛል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅዶች
በቀጣይ የማህበሩ ፍላጎት አገር አቀፍ መሆን ነው። ምክንያቱም ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በአንድ ወረዳ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚሰራ በመሆኑ ነው። ማህበሩ ለሰራቸው ስራዎች የተለያዩ ሸልማቶችን አግኝቷል። በቅርቡ በፌደራል ደረጃ ከስር ተነስተው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ በጎ አድራጎት ማህበር ተብሎ ለመጠራት እየሰራ ይገኛል። ሌሎችም ማህበራት ከማህበሩ እንዲማሩ ለማድረግም እቅዶች አሉ። አነስተኛ ስራዎችን በመስራት እና እውቅና በማግኘት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፍ የመክፈት እቅድ አለ።
ማህበሩ እንደ ማህበር እንዲቀጥል ለማስቻል ፈታኝ ነገሮች እያጋጠሙ ይገኛሉ። ችግሮቹን ለመፍታት ጥር አንድ ቀን 2013 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በሻኪሶ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል። በዋናነት ከሩጫው የሚገኘው ገቢ ወደ ማህበሩ አካውንት ይገባና ማህበሩ ለሚሰራቸው በጎ ነገሮች ያውለዋል። በተጓዳኝ ፕሮፖዛል በመቅረፅ ለቀጣይ ስራዎች ዝግጅት ተደርጓል። ፕሮፖዛሉ በዋነኝነት በጎዳና ላይ የሚገኙት ይሁን ሌሎች ተረጅዎች ሁልግዜ ተደጋፊ እንዳይሆኑ የሚያስችል ነው።
በቀጣይ ማህበሩ የስራ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰዎች እራሳቸውን የሚደግፉበት ነገር ለመስራት አቅዷል። በጎዳና የሚገኙ ልጆችንና አረጋውያንን እንዲሁም በልመና የሚተዳደሩ አዛውንቶችን ለማገዝ ስራዎች ታስበዋል። በጎዳና የሚገኙ ሰዎችን የስነልቦና ስልጠና በመስጠት አንድ ማእከል ውስጥ ለማስገባት ሀሳብ አለ። በከብት ማደለብና በዶሮ ማርባት ስራ የሚገኙ ትርፎች አዛውንቱን ለማስተዳደር በጣም በቂ ነው። ማህበሩ መስራት የሚፈልገው ጎዳና ላይ የወጡትንና አቅመ ደካሞች ላይ ብቻ አይደለም።
አንዳንዴም ቤት ውስጥ ሆነው ግን ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት ታስቧል። በተለይ የመስራት አቅም ያላቸውን እናቶች ማሰራት ካልተቻለ ልጆቻቸው ጎዳና ይወጣሉ። ይህን ለማስቀረት እናቶች በችግር ልጆቻቸውን ሳይበትኑ በፊት ለመድረስ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በሌላም በኩል ስራ ለመስራት የሚመጡ ሰዎችን ችሎታቸውን በመለየት የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማጥናት ሰዎቹ ወዳዘነበሉበት ስራ እንዲገቡ ይደረጋል።
ማህበሩ በአገሪቱ ብሄር፣ የቆዳ ቀለምና ቋንቋ ሳይለይ ለተቸገረ ሁሉ አለኝታ የመሆን ህልም አለው። ሰው ወገኑን እየገፋና እየገደለ ባለበት ሰዓት ላይ ወገኔ ነው ብሎ የሚሰበስብ ካለ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ያድጋል። የደግነት ስራዎች ማከናወን ሲቻል ነው ወደ ቀደመው ኢትዮጵያዊነት መመለስ የሚቻለው። ኢትዮጵያን ወደ ፊት ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላም የነበረችበትን በማሰብ ለውጥ መፍጠር ይቻላል። ቀጣይ እኔን የሻኪሶ በጎ አድራጊት ማህበር እየሰራቸው ባሉት ብቻ የሚቆም አይደለም።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ ሲሆን ማህበሩ አንድ አባል ብቻ ቢኖረው መክሰም እንዳይችል ተደርጎ የተዋቀረ ነው። በማህበር ውስጥ የሚገኙት አባላት መልካምነት ሰው ኖረም አልኖረም የሚቀጥል ነገር ነው። በጎ አድራጎት ማህበር ከተመሰረተ አይቀር ስራውም እየተሰራ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየር ይሰራል። በጎ ስራ መስራት በእምነትም የሚደገፍና ተቀባይነት ያለው ስራ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013