ለዘላቂ ሠላም ዓለም አቀፍ ትብብር!

በዓለማችን ግጭቶች እና ጦርነቶች ከዕለት ዕለት እየተባባሱ በመምጣታቸው የሠላም ጉዳይ ከመቼውም ይልቅ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል። ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሀገራት መሪዎች፣ ተደማጭነት ያላቸው ግለሰቦች.. ወዘተ ሠላምን ዋነኛ አጀንዳ አድርገው ሲንቀሳቀሱ እና ዓለም ለሠላም ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለባት አበክረው ሲያስገነዝቡ ይስተዋላል ።

በርግጥም ዓለማችን አሁን ላይ በብዙ መልኩ እያጋጠማት ካለው የሠላም እጦት፤ ከችግሩ ጋር በተያያዘ እየከፈለች ካለው ያልተገባ ዋጋ አኳያ፤ የሠላም ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት በብዙ መልኩ የሚበረታታ ብሎም የሁሉንም ድጋፍ እና ቀና ትብብር የሚጠይቅ፤ ፈጥኖ መንቀሳቀስንም የሚሻ ነው።

ሠላም ከግለሰብ የሚጀምር ለማኅበረሰብም ሆነ ለሀገር ሕልውና ወሳኝ አቅም ነው። ነገን በብዙ ተስፋ ለሚጠብቀው የሰው ልጅ የሠላም ጉዳይ የማሰብ አቅሙን በአግባቡ ከመጠቀም ጀምሮ፤ የሚያስበውን ተጨባጭ አድርጎ ነገዎቹን ብሩህ ለማድረግ ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ስኬት የማይተካ ሚና አለው።

ያለ ሠላም ነገን ቀርቶ ዛሬን በአግባቡ ማሰብ አይቻልም፤ ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው። በቀደሙት ዘመናት ከሠላም እጦት ጋር በተያያዘ ዓለም የከፈለው ያልተገባ ዋጋ፤ በሰው ልጆች ጥቁር ታሪክነት ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ አካባቢ ሠላም የቱን ያህል እንደሚያስፈልግ ሕያው ማስተማሪያም ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ዓለማችን በየዘመኑ የተለያዩ ጦርነቶች እና የርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግዳለች። በእነዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት እና ለአካለ ጎዶሎነት ተዳርገዋል፤ ቁጥር ለመገመት የሚያዳግት ሀብት ወድሟል። አንዳንድ ጦርነቶች እና ግጭቶች ፈጥረውት ያለፉት የሥነልቦና ስብራት ዛሬም ጠባሳው በአግባቡ አላገገመም።

ይህም ሆኖ ግን ዛሬም በዓለማችን አራቱም ማዕዘናት ጦርነቶች እና ግጭቶች አሉ። በነዚህም ከቀደሙት ዘመናት በከፋ መንገድ ሚሊዮኖች ለሞት እና ለአካለ ጎዶሎነት እየተዳረጉ ነው። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሠላማዊ ሕይወታቸው ተፈናቅለው አስቸጋሪ ሕይወት እየገፉ ነው። በትሪሊዮን የሚቆጠር ሀብትም እየወደመ ነው።

ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ በድርድር ከመፍታት ይልቅ፤ አሁናዊ አቅምን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እየሰፋ ነው። ብሔራዊ ጥቅሞችን ሰጥቶ በመቀበል በፍትሐዊነት ከማስጠበቅ ይልቅ በሴራ ተጨባጭ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ዓለምን ወደ አልተገባ የሠላም እጦት እየወሰዳት ነው።

በአንድ በኩል የተሻለች ዓለም ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ፤ በዚህም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሕይወትን በብዙ መልኩ እያቀለለ ባለበት አሁንዊ ዓለም፤ አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ በድርድር መፍታት አለመቻል ዓለማችንን ሁለት ገጽታ እንድትላበስ አድርጓታል።

ይህ ተጨባጭ እውነታ ከሁሉም ለአፍሪካ ሀገራት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖባቸዋል፤ እነዚህ ሀገራት እና ሕዝቦቻቸው ለእነዚህ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ መልክ ባላቸው ግጭቶች ሰለባ እየሆኑ ነው። ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመውጣት ለሚያደርጉት ትግልም ተጨማሪ ፈተና እየሆነባቸው ነው።

በብዙ መልኩ በተሳሰረው አሁናዊው ዓለም የሚፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች መላውን ዓለም በአንድም ይሁን በሌላ መንካታቸው የማይቀር ነው። ለዚህም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ በእሥራኤል ሀማስ፣ በእሥራኤል ሂዝቦላ፣ በየመን እና በሱዳን ወዘተ ያሉ ግጭቶችን ማየት በራሱ ተገቢ ነው።

እነዚህ ጦርነቶች እና ግጭቶች አጠቃላይ በሆነው የዓለም የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አሰላለፍ ላይ እየፈጠሩት ያለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዓለማችንን ወደ ከፋ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ሊከታት እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ነው። ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ነፃ ሊሆን የሚችል ሀገር ሆነ ሕዝብ ሊኖር አይችልም ።

ከስጋቱ ለመውጣት ያለው አማራጭ፤ ስለ ሠላም ድምፅን ከፍ አድርጎ ማሰማት፤ ችግሮችን ዘመኑን በሚዋጅ የሠላም ድርድር/ውይይት መፍታት፤ ለዚህ የሚሆን ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ትናንት ያስተባበረችው አሕጉር አቀፍ የሠላም ኮንፈረንስ የሚኖረው ሚና እጅግ ትልቅ ነው፡፡ ከትናንት የጦርነት እና የግጭት ታሪኮች በመማር ስለ ሠላም አብዝቶ ማዜም፤ ለስኬታማነቱም ከሁሉም በላይ ዓለም አቀፍ አጋርነት መፍጠር ነው።

በተለይም አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃነት ማግስት ጀምሮ የሚፈታተናቸውን የሠላም እጦት ለዘለቄታው ለመፍታት የሠላማቸው ባለቤት ሊሆኑ ይገባል። ለሠላማቸው ማንንም ሳይጠብቁ ራሳቸው መፍትሔ መሆንም ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የሚሆን አጋርነት እና ሁለንተናዊ ቁርጠኝነት ለመፍጠርም ከዛሬ የተሻለ ሌላ ቀን አይኖርም!

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You