ወቅቱ የቡና ነው። በርግጥም የቡና ነው፤ በቡና አብቃዩ የገጠሩ አካባቢ ቡና የሚለቀምበት፣ የሚፈለፈልበት፣ ወዘተ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይሟሟቃል። የቡና ባለቤቶች ብቻ አይደሉም በዚህ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ባተሌ የሚሆኑት። የቡና ልማቱ እየሰፋ እንደ መምጣቱ በርካታ ቡና ለቃሚዎች በዚህ ሥራ ይሰማራሉ። እሽት ቡና ተፈልፍሎ ታጥቦ ለውጭ ገበያ ዝግጁ የሚደረግበት ወቅት እንደ መሆኑ በዚህ ታላቅ ሥራ ሰፊ የሰው ኃይል ይሰማራል። እናም ቡና የሚለማባቸው አካባቢዎች እንቅስቃሴ በብዙ መልኩ ይሟሟቃል።
በአንዳንድ ቡና የሚለማባቸው ሰፊ አካባቢዎች ለዚህ ሥራ የአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል ፤ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ሠራተኞች ለቡና ለቀማ የሚፈለጉበት ሁኔታ እንደነበርም አስታውሳለሁ። አሁን ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ የሥራ እድል የሚፈጠርበት ወቅት እንደመሆኑ የሰው ኃይል ከሩቅ መማተር ላይኖር ይችላል።
ወቅቱን የቡና ወቅት የሚያደርጉት ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ቡና ሁለት ዓይነት እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ የቡና ዓይነቶች ኮሜርሻል እና ስፔሻል ቡና ይባላሉ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና ኮሜርሻሉ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዝ ነበር። ይህ ቡና ከስፔሻል ቡና አኳያ ሲታይ የሚሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ ነው፤ ስፔሻሊቲ ቡና ግን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።
ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኘው የቡና ዓይነት ላይ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች። ይህን ተከትሎም ለውጭ ገበያ የሚላከው ስፔሻሊቲ ቡና በመቶኛ እየጨመረ ይገኛል። ይህ መልካም እድል ደግሞ የቡናውን ጥራት ለመጠበቅ በሚከናወኑ ሰፋፊ ሥራዎች በቡና ላይ የሚሰማራውን ሠራተኛ ቁጥር ይጨምረዋል ተብሎ ይገመታል።
ሀገርንም አምራቹንም ላኪውንም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለው ይህ የቡና ዓይነት መሆኑ በእጅጉ ታምኖ ለስፔሻሊቲ ቡና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለበት ሁኔታ ቡና የሚለቀምበትን፣ የሚታጠብበትንና የመሳሰሉት ሥራዎች የሚከናወንበትን ይህን ወቅት ወሳኝ ያደርጉታል።
ቡና አዘጋጆች፣ አቅራቢዎች፣ ላኪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በዚህ ወቅት ሥራ ላይ ያውላሉ። የፋይናንስ ተቋማት በገንዘብ አቅርቦትና ዝውውሩ በንቃት ይሳተፋሉ፤ የመንግሥት አካላትም እንዲሁ ቡናው በወቅቱ ተሰብስቦ በጥራት ተመርቶ ለገበያ እስከሚቀርብ ድረስ ቅድሚያ የሚሰጡት ሥራ አይኖራቸውም። ለእዚህ ሥራ ድጋፍ በማድረግ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ይጠመዳሉ።
ልማቱ በሚካሄድበት አካባቢ ለተሰማራው ማህበረሰብ እንደ ምግብ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የመሳሰሉትን የሚያቀርቡ በጣም በርካታ ናቸው። በቡና ላይ የሚካሄደው ተግባር ከቡና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸውን የሸቀጣ ሸቀጥና የአልባሳት መደብሮች፣ በአጠቃላይ ግብይቱን ጭምር የተሟሟቀ ያደርገዋል። እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ወቅቱ የቡና ወቅት መሆኑን በሚገባ ያመለክታሉ።
ቡና በሚለማባቸው ክልሎች ከቡና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ ከዓለም አቀፍ የቡና ገበያ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸው ቀጥሏል። በየአካባቢዎቹ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚያስተላልፉት መልእክትም ይህንኑ የሚጠቁም መሆኑ እንዳለ ሆኖ የቡና የውጭ ገበያው መረጃዎች ለአልሚውም፣ በንግዱ ሥራ ለተሰማራውም፣ ለሀገርም ወዘተ ትልቅ የምስራች መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ወደ ውጭ የምትልከው የቡና መጠንም የምታገኘው የውጭ ምንዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህን ስኬት ማስመዝገብ የተቻለው በቡናው ዘርፍ የተካሄደውን ሪፎርም ተከትሎ መሆኑ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ተጠቁሟል። ሪፎርሙ ወደ ውጭ የሚላከውን የቡና መጠን እንዲሁም ከቡናው የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ መጠን ማሳደግ አስችሏል። ወደ ውጪ የሚላከው ቡና እየጨመረ መጥቶ ባለፈው በጀት ዓመት ከ300 መቶ ሺ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል፤ በዚህም ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።
ሌላው በቡናው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ በሚችለው ስፔሻሊቲ ቡና ላይ የተመዘገበው ነው። የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ እንዳመለከተው፤ የዛሬ ሶስት ዓመት ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና የኮሜርሻል ቡና መጠን በመቶኛ ሲታይ 70 በመቶውን፣ የስፔሻሊቲ ቡና መጠን ደግሞ 30 በመቶውን ይሸፍኑ ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሁኔታ ተለውጧል፤ የስፔሻሊቲ ቡና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛውን እጅ እንዲያዝ ማድረግ ተችሏል። በዚህም ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና 60 በመቶው ስፔሻሊቲ ቡና እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ የኮሜርሻሉን ወደ 40 በመቶ ማውረድ ተችሏል። በቀጣይም ከዚህ በታች ለማውረድ እንደሚሰራ ይጠበቃል።
በሪፎርሙ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ማሳደግ ተችሏል። ከሪፎርሙ በፊት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና 200 ሺ ቶን ደርሶ እንደማያውቅ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል። በ2016 በጀት ዓመት ይህን አሀዝ ወደ 300 ሺ ማሳደግ ተችሏል።
ይህ ሁሉ ለውጥ በከፍተኛ ርብርብ የተገኘ ነው። ይህን ለውጥ አሁንም ማስቀጠል ወሳኝ ነው፤ መንግሥትም ወደ ውጭ የሚላከውን የቡና መጠንም ሆነ ከዚህ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ አቅዶ እየሠራ ነው። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ሁለት ቢሊየን ብር የሚጠጋ ለማድረስ ታቅዷል። በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ጥሩ አፈጻጸም ይህን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ ተብሏል፤ ባለፈው ጥቅምት ወርም ተመሳሳይ ስኬት መመዝገቡን መረጃዎች እየጠቆሙ ሲሆን፣ በዘርፉ የሚደረገውን ርብርብ ይበልጥ በማጠናከር ለእዚህ ስኬት መሥራት አሁንም በእጅ ያስፈልጋል።
ከፍ ብዬ እንዳመለከትኩት ቡና ላይ በትኩረት መሠራቱን ተከትሎ ነው ይህ ሁሉ ለውጥ የመጣው። አሁንም ከቡና የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚቻል ታምኖበት እየተሠራ ነው። ከቡና ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን በልማቱ እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በግብይቱ ላይ በትኩረት ለመሥራት የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ለማድረግ መላው የቡና ቤተሰብ ተቀናጅቶ መሥራት ባለበት ወቅት ላይ እንደሚገኝ ለማስታወስ እፈልጋለሁ። ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት የቡና ቤተሰቦች በጣም በርካታ ናቸው። እነዚህ ቤተሰቦች ከገጠር አንስቶ በከተሞች፣ በመላው ዓለም ጭምር የሚሠሩ ናቸው። በእዚህ ከቡና ብዙ በሚጠበቅበት ዘመን እነዚህ ተዋንያን በሙሉ በማነቃነቅ በጋራ አብረው መሥራታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ ይገባል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ቡና በሚለቀምባቸው፣ በሚታጠብባቸውና በአጠቃላይ በሚዘጋጅባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በሙሉ ለቡና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ቡናው ገዥዎች እጅ እስከሚገባ ድረስ በእያንዳንዱ መዳረሻ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን የሚጠይቅ ሰብል እንደመሆኑ ሲለቀም፣ ሲታጠብ፣ ሲከማች፣ ሲጓጓዝና ሲላክ በሁሉም ምዕራፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
ሀገር ከዚህ ቡና ብዙ ትጠብቃለች፤ አርሶ አደሮችም ላኪዎችና አቅራቢዎችም ከዚህ ቡና ብዙ ይጠብቃሉ፤ የሚጠብቁት እውን መሆን የሚችለው አንድም ቡና በጥራትና በጥራት ብቻ ተዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ሲላክ ነው። የመጋዘኖች፣ የማጓጓዣዎች፣ የማሸጊያ ጆንያዎች ከኬሚካል ከመሳሰሉት የጸዱ መሆን ወሳኝ ነው። ከጥራት አኳያ በእዚህ ልክ ከተሠራ ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ማስጠበቅ ይቻላል።
የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ የቡናን ጥራት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ገበያው በፈጠረው መልካም እድል ለመጠቀም አተኩሮ መሥራትም ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ቡና ጥሩ ዋጋ ያለው ስለመሆኑ ሀገሪቱ ባለፉት አራት ወራት ከቡና ያገኘችው ገቢ ያመለክታል። ገበያው በደራበት በአሁኑ ወቅት ቡናውን በሙሉ ወደ ገበያ ማውጣት ይገባል።
የተሻለ ዋጋ መጠበቅ ክፋት ባይኖረውም የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚወሰን መሆኑ ይታወቃል። ዋጋው አንዳንዴ ሊወርድ የሚችልበት ሁኔታ ሊያጋጥም የሚችል ስለመሆኑ ያለፉ ተሞክሮዎች ያስገንዝባሉ። የተሻለው አማራጭ ገበያው ጥሩ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ቡናውን ለገበያ በማቅረብ ራስንም ሀገርንም መጥቀም ነው።
ቡና እንዳይባክን ማድረግ ላይ መሥራትም ሌላው ተግባር ነው። ቡናው በወቅቱ ገበያ ካልወጣ ሊባከን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ለዜጎችም ለሀገርም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ የሚችልን ቡና በሀገር ውስጥ ባልተገባ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፤ ሰፋ አርጎ በማሰብ ሀገር በእጅጉ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ሌላው ሀገሪቱ ከቡና የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን ሲያደርጋት የኖረው የኮንትሮባንድ ንግድ ነው። የሀገሪቱን ቡና ጨምሮ የቁም እንስሳት፣ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት፣ የተለያዩ ዓይነት እህሎች ወደ ጎረቤት ሀገሮች በሕገ ወጥ መንገድ እንዲወጡ ይደረጋል።
የኢትዮጵያ ቡና ወደ ጎረቤት ሀገሮች በኮንትሮባንድ እንዲወጣ እየተደረገ አንድም እግር ቡና የሌላት አንድ የጎረቤት ሀገር ከቡና ላኪ ሀገሮች ተርታ የተሰለፈችበት ሁኔታ እንደነበርም ሲጠቀስ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚህም ምን ያህል የሀገሪቱ ቡና በኮንትሮባንድ እንደሚወጣ መረዳት ይቻላል።
ሀገሪቱ በቡና ልማትም ግብይትም ብዙ ርቀት ለመጓዝ እቅዱ እንዳላት ይታወቃል። በቡናው ዘርፍ እንደ ሀገር የሚላከውን ቡና መጠን በመጨመር የሚገኘውንም የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ ላይ የሚከናወነው ተግባር አንድ ነገር ሆኖ ከዓለም ቡና አምራች ሀገሮች ልቆ ለመውጣት ታቅዶ እየተሠራም ነው። በቡና ምርታማነት ኢትዮጵያን ከሚበልጡት ብራዚልና ቬትናም ጋር ለመወዳደር ታስቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ፤ ዘንድሮ ከብራዚልና ከቬትናም በስተቀር በቡና ምርታማነት ኢትዮጵያን በዓለም የሚበልጣት ሀገር አይኖርም ሲሉ ጠቅሰው፣ በርካታ ሀገራትን አልፈን መጥተን አሁን የቀሩን ብራዚልና ቬትናም ናቸው ብለዋል። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የጀመርነውን የቡና ተክል ጉንደላና ችግኝ ተከላ አጠናክረን ከቀጠልን ከብራዚል በስተቀር በቡና ምርት ኢትዮጵያን የሚበልጣት ሀገር እንዳይኖር ታቅዶ እየተሰራ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ዘንድሮ ግን ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሰው፣ ከቬትናም ጋር ያለው ልዩነት እንደሚታወቅ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በሚከናወኑ ሥራዎች ከዚያ ያላነሰ ምርት ማምረት እንደሚቻል፣ ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት መገኘቱን፣ በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊየን ዶላር ገደማ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
የቡና ምርት እያደገ ስለመጣ በሀገር ውስጥ ያለው ተጠቃሚነት ያደገ ቢሆንም ለውጭ ገበያ የምናቀርበውም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘንድሮ ከአራት መቶ ሀምሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ቶን ድረስ ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል። የዛሬ አምስት ዓመት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ቶን አይሞላም ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ ሁሉ በቡና ላይ በትኩረት የመሥራትን አስላፈጊነት ያስገነዝባል። ወቅቱ በርግጥም የቡና ነውና ስለቡና ለቡና እንስራ። በዚህ የቡና ወቅትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት ከመላው የቡና ቤተሰቦች ይጠበቃል። መንግሥት በቡና ላይ ይህን ያህል ተስፋ ሰንቆ እየሠራ ባለበት ወቅት ከቡና ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያለው አካል በሙሉ ቡና በጥራት ተመርቶ ለዓለም ገበያ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ ሁሉ እንደ ሀገርና ሕዝብ ሆኖ መሥራት ይኖርበታል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም