አዲስ አበባ፡– በግብርናው ዘርፍ ያሉትን እምቅ አቅሞች በመለየት ወደ ተግባር በመግባት በአጭር ጊዜ አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡ አገልግሎቱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በመንግሥት ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋሉ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተጨባጭ ተግባራዊ እየሆኑ ነው ብሏል፡፡
በመንግሥት ከሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የጋዘጠኞች ቡድን በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ባሌ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በተጨባጭ ሁኔታ መሬት ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የግብርና ሥራዎችን ምልከታ አድርጓል፡፡
በባሌና አርሲ ዞኖች ምልከታ በተደረገባቸው የተለያዩ ወረዳዎች በሁሉም ዘርፍ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥ በመንግሥት ተቀርፆ ተግባራዊ እየሆነ ካለው አዳዲስ መርሐ ግብሮች (ኢኒሼቲቮች) መካከል የግብርና ልማት ሥራዎች አንዱ ሲሆን፣ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን መመልከት ተችሏል፡፡
በክላስተር የለማው የስንዴ ምርት፣ በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ፣ ዘመናዊ ቀፎን ተጠቅሞ በንብ እርባታ ላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች፣ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ በሌማት ትሩፋት ሥራ ኑሯቸውን እየቀየሩ መሆኑን መመልከተ መቻሉን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በሚዲያ ቅኝቱ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ግብርናን በተመለከተ የመንግሥት ዋናው ትኩረት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና በቂ ምርት አምርተው ለገበያ ማቅረብ ሲሆን እቅዱ በተጨባጭ ተግባራዊ መሆኑን፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅሞች በመለየት ወደ ተግባር በመግባት በአጭር ጊዜ አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የሕይወት ዘይቤ እንዲቀየርና ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብርና ከባሕላዊ ዘዴ ወደ ዘመናዊነት እንዲሸጋገር በማድረግ ላይ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ተግባር ለማሳካትም መንግሥት ለአርሶ አደሩ ከሙያዊ እገዛ ጀምሮ እስከ ሜካናይዜሽንና የግብርና ግብዓት አቅርቦት ትራክተር፤ ኮምባይነርና የሌሎች ግብዓቶች አቅርቦትን በማመቻቸት ዘርፈ ብዙ ድጋፎች መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም መንግሥት በአርሶ አደር ማሳ ላይ የሚመረት ምርት በብዛት፤ ጥራትና ፍጥነት እንዲመረት የመንግሥት ቁልፍ ተግባር በመሆኑ በክላስተር፤ ጥምር ግብርና እና ሌማት ትሩፋት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አመላካች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ እንደ ሀገር መንግሥት የኢኮኖሚው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን አራቱ የኢኮኖሚ ግቦች ብሎ የለያቸው ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፤ ኤክስፖርትን ማሳደግ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በባሌ እና አርሲ ዞን በተጨባጭ ሁኔታ ሁለንተናዊ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ አዲስ ኢኒሼቲቭ የሆነው የግብርና ዘርፍ ስንዴን በክላስተር ማምረት፤ በቢራ ገብስ፤ በሌማት ትሩፋት እና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውና ለሁሉም ልማት ሥራዎች ወሳኝ የሆነ በዞኖቹ ሠላም በመረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም