ሠላም የትምህርት ዘርፍ ልማት እስትንፋስ ነው!

የፀጥታ መደፍረስ ቀጥተኛና ከፍተኛ ጉዳት ከሚያደርስባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ትምህርት ነው። የሠላም እጦት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እና የትምህርት ተቋማት ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግ በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። በሠላም እጦት ሳቢያ ትምህርት ቤት ውስጥ መዋል የነበረባቸው ሕፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ለተለያዩ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች ይጋለጣሉ፤ የአላስፈላጊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ተገዥ ይሆናሉ።

ሀገር ባቀደችው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አምራች ዜጎችን ሳታገኝም ትቀራለች። እነዚህ አስከፊ ጫናዎች ሁሉ ተደምረው የሀገሪቱን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት በእጅጉ ወደኋላ ይጎትቱታል።

የትምህርት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲገመገም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት መከታተል ከነበረባቸው 32.5 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት 24.5 ሚሊዮን እንደሆኑ ተገልጿል። የተቀሩት ግን ከተፈጥሮ አደጋና ከሠላም እጦት ጋር በተያያዘ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ ተጠቁሟል። ከአኅዞቹ መረዳት የሚቻለው ከስምንት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል። ይህ እጅግ አሳሳቢ ነው።

ይህን ያህል ተማሪ ከትምህርት ገበታ ቀርቶ፣ አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆን ሀገር በብዙ መልኮች ለጉዳት ትዳረጋለች። ሀገር ‹‹ተምረው ችግሬን ይፈቱልኛል›› ብላ በተስፋ የምትጠብቃቸው ተማሪ ልጆቿ በሠላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ፣ ችግሯን መፍታት ይቅርና፣ ተጨማሪ ችግር ይሆኑባታል። የተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን በተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን በወላጆችና በኅብረተሰቡ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ያሳድራል። ይህም ቀውሱ ከጥቂት ግለሰቦች ተሻግሮ ማኅበረሰብ አቀፍ ችግርን ያዋልዳል።

ስለሆነም በተለይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚስተዋሉ ግጭቶች አፋጣኝ መፍትሔ በማበጀት ሠላምን ማስፈንና የትምህርት ዘርፉን መታደግ ይገባል። ሠላምን ማስፈን ሲባል ደግሞ ዘለቄታዊነት ያለው ሠላም ማስፈን መሆን አለበት። በተለይ ደግሞ የኃይል አማራጭ ዘላቂ ሠላምን እውን ማድረግ እንደማይችል ማመን ይገባል፤ ሁሉም ወገን ለሐቀኛና መተማመን ለሰፈነበት የሠላም ድርድር ዝግጁና ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል።

ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትም እንዲሁ እንደ ምገባ መርሐ ግብር ያሉትን በስፋት በመተግበር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱና ተረጋግተው እንዲማሩ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የምገባ መርሐ ግብር በሌሎች ሠላም በሰፈነባቸው አካባቢዎችም የሚተገበር እንደመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎችም በልዩ ሁኔታ መተግበር ዜጎችንም የትምህርት ሥርዓቱንም መታደግ ይገባል።

ሠላምን አስፍኖ ከትምህርት ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉትንም በምገባ መርሐ ግብር ማቀፍ ብቻቸውን ሀገራዊ የትምህርት ዘርፍ እቅድን ለማሳካት በቂ እንዳልሆኑም መገንዘብ ይገባል።

የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የዘርፉን እቅድ ለማሳካት ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ብዙ ጥረቶችን ማድረግ ይጠበቃል። በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባውን የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓትና የተሻሻሉ አሠራሮች ትግበራን እስከመገምገም የዘለቀ ተግባር በማከናወን ውጤቱን መተግበር ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የነበረው የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻልና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን እንዳበረከተ ባይካድም፣ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም ነበሩበት። ምክንያቱ ከአቅም ጋር ሊያያዝ ይችላል፤ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ በንድፈ ሀሳብ እንጂ የተግባር ክህሎትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ አይደለም። የምዘና ሥርዓቱም ለተግባራዊ እውቀት ትኩረት የሰጠ አልነበረም።

ሥራ ፈላጊ እንጂ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም። የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራው ጎልብቶ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መጠን ሲያግዝም አይስተዋልም። ከትምህርትና ሥልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና የሥራ ፈጣሪነት አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ ትውልዱ ዲግሪና ዲፕሎማ (ወረቀት) አምላኪ ሆኗል። ይህም የትምህርት ዘርፉን ጉዞ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል።

የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት መበላሸት የሀገሪቱ ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሠላም የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ያለባት፣ ምጣኔ ሀብቷ ያደገና ፖለቲካዋ የሰከነ ሀገር እውን ማድረግ የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት የተገነባ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው። ጥራት በሌለውና በወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ትውልድ ለሀገር ሕልውና ትልቅ አደጋ ይሆናል። ለዚህም ነው ‹‹አንድን ሀገር ለማፍረስ ጦር ማዝመት ሳያስፈልግ፣ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ማበላሸት በቂ ነው›› የሚባለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ የምንሰማው።

በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብዕናቸው የተገነባ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት ነው።

አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው። የሰው ኃይል መገንቢያው ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ ትምህርት ነው። አስተማማኝና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብቸኛው መንገድ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋት ነው። ‹‹ዋናው ሽፋን/ብዛት ነው፤ የጥራቱ ጉዳይ ቀስ ብሎ ይታሰብበታል›› የተባለው አካሄድ ለኢትዮጵያ ምን እንዳቆያት አይተናል። የትምህርት ሥርዓቱ ብልሽት ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፤ እያስከፈላትም ይገኛል፤ የዚያ ሥርዓት ትምህርት መዘዝ ገና ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።

የትምህርት ጥራትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተማሪዎችን ያማከለ ዘመናዊና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደት መከተል፤ የመምህራንን ጥራትና ተነሳሽነት ማጎልበት፤ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል፤ ተማሪዎችን ማነቃቃት፤ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራርን ማብቃት፤ ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፤ የማስተማሪያ ግብዓቶች ማሟላት እንዲሁም የተማሪዎች ሥነ ምግባርን ማሳደግ ይገባል።

የተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ የመከታተል፤ የመምህራን በጥራት የማስተማር፤ የትምህርት አመራር ስትራቴጂካዊ አመራር የመስጠት እንዲሁም የወላጆች ልጆቻቸውን በንቃት የመከታተልና የመደገፍ ተግባራት በቅንጅት ሊከናወኑ ይገባል። በትምህርትና ሥልጠና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ዓመታት የትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት ገምግሞ ጠንካራውን ማስቀጠል፣ ጎታቹን ማራገፍ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በሥነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ፣ የሀገሪቱን ዕድገትና አንድነት የሚያስቀጥል እንዲሁም ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ለሥራ ፈጣሪነትና ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን በሚገባ መፈተሽና ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የተሻለ የፈተና ውጤት የሚመዘገበው፣ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ሲኖር ነው!

የትምህርት ሥርዓቱን/የመማር ማስተማር ሥራ በተግባር ተኮር እውቀት በመደገፍ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት መጣር ያስፈልጋል። አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ይህን ጥረት እውን ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ስለሆነም በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ሥራ ፈጣሪነትን ባሕሉ ያደረገ ትውልድ እንዲፈጠር የትምህርት ሥርዓቱን ትግበራ በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት መምራት ይገባል!

በቅድሚያ ግን ለሠላም በተለይ ለዘላቂ ሰላም ጉዳይ ትኩረት መስጠት ይገባል! ሁሉም ነገር በሠላም ማሕቀፍ ውስጥ የሚፈጸም ነውና።

ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You