በከተሞች ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት ከገጠር ሰባት እጥፍ እንደሚልቅ ተገለፀ

አዲስ አበባ፡-በከተሞች ያለው የኤች አይቪ የስርጭት መጠን ከገጠር አካባቢዎች በሰባት እጥፍ እንደሚልቅ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዘርፍ ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል፡፡

እንደ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ገለፃ የኤች አይቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ በገጠር 0 ነጥብ 4 በመቶ አካባቢ ሲሆን በከተሞች ግን ወደ ሦስት በመቶ ይጠጋል፡፡

ዓለም ላይ 39 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕዝብ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይገመታል የሚለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ በየዓመቱ ደግሞ አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕዝብ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደሆነና 630ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት እንደሚሞቱ ያብራራል፡፡

በኢትዮጵያ ከ600ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩም መረጃው አመልክቶ፤ በዓመት ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደሚሆኑ እና በየዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጿል፡፡

እንደሀገር የስርጭት መጠኑ ከአንድ በመቶ በታች በመሆኑ ከወረርሽኝነቱ ወጥተናል ያለው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ፤ የሀገሪቱን አካባቢዎች የስርጭት መጠን ሲታይ አሁንም ወረርሽኝ ውስጥ ነን የሚያስብል መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከአንድ በመቶ በታች የሆነ ውጤት ሲመዘገብ ውጤታማ ነን ማለት እንደሚቻልም አመላክቷል፡፡

አዲስ ተጋላጮችን እንዲሁም በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ ታቅዶ ሲሠራ እንደቆየ የሚያሳየው መረጃው፤ አዲስ ተጋላጮችን ከመቀነስ አኳያ የዕቅዱን 70 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል፡፡

በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ከመቀነስ አኳያ ግን አርባ ዘጠኝ በመቶ ብቻ ማሳካቱን የገለፀው ሚኒስቴሩ ብዙ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

በተለይ በከተሞች ለሚታየው የስርጭት መጠን እንደ መፍትሔ ሦስት ቁልፍ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተብለው የተለዩ አካላት ላይ መሥራት እንደሆነ ያመላከተው ሚኒስቴሩ፣ እነሱም በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች፣ እስረኞች እና በመርፌ የሚወሰዱ ሱስ አስያዥ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡

የምርመራ አገልግሎቱን ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ማድረግ፣ የአቅም ግንባታና የክትትል ሥራን ማጠናከር፣ ግንዛቤና ቅድመ መከላከል ላይ መሥራትም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተብለው በሚኒስቴሩ ከተጠቀሱት ጥቂቶቹ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You