ጽጌረዳ ጫንያለው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህንና ሰባኪ ወንጌል ናቸው። በዘመናዊው በኩል ደግሞ በሙያቸው የሥነልቦና አማካሪ ሲሆኑ፤ በሙያው ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። ቢሮ ከፍተው የተለያዩ የማማከር ሥራዎችን እየሰሩም ይገኛሉ። በዚህ ሥራቸውም ብዙዎችን ከሥነ-ልቦናቸው በምክራቸው አክመዋል።
አሁንም ይህንን የሥነልቦና ህክምና በተለያየ መልኩ እየሰጡ ይገኛሉ ቀሲስ ይግዛው መኮንን። እናም ይህንን ሙያቸውን መሰረት አድርገን የዘመኑን የትውልድ ቀረጻ ጉዳይ ከወቅታዊው ጋር በማዛመድ በጭውውታችን አውግተናልና። እንዲማሩበት ስንል እንደሚከተለውም አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– በአገራችን ያለውን አሁናዊ የስነ ልቦናና ስነምግባር ሁኔታን እንዴት ያዩታል፤ በተለይ ከሃይማኖትና ከባህል አንጻር ቢተነትኑት?
ቀሲስ ይግዛው፡– ከትርጓሜው ብንነሳ ሥነምግባር ማለት መልካም ሥራ የሚለውን ይይዛል። መልካም ሥራ በአሁኑ ወቅት በጣም እየቀነሰ ሄዷል። ሥነምግባር የትውልዱ ትልቅ እሴትና መገለጫ ባህሉ ነበር። የማንነት ነጸብራቁም ነበር። ሆኖም በተለያዩ መንገዶች አሁን ላይ እየደበዘዘ፣ በሌላ ምግባር እየተተካ መጥቷል። ከሃይማኖት አንጻር ሲታይ ደግሞ ሥነምግባር በጎ መስራትን ፤ መከባበርን ይይዛል። በዚህም በማንኛውም የእምነት አስተምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ይመከራል፤ በትምህርት መልኩ ይሰጣል።
በሃይማኖት ሥነምግባር ለሌሎች በጎ ማድረግን ብቻ ሳይሆን አንዱ ለአንዱ መሰዋዕት መሆንንም ጭምር የሚያስተምር ነው። ሆኖም በአንዳንድ የስም ሃይማኖት በያዙ አካላት አንዱ አንዱን እንዲገፋ እየሆነበት ይታያል።
ይህ የሆነው ደግሞ ከአስተምሮው አንጻር ሳይሆን ከግለሰብ ፍላጎት ተነስቶ ነው። እንዲያውም አንድ መጽሐፍ ሳነብ ያገኘሁት እንዲህ ይላል። ‹‹ሥነምግባር እንዲጠፋ ባይደረግ ኖሮ ሥጋዊ ጥበበኞች የሚያጠፋቸውን ጥበብ ለመፈልሰፍ ባልተገደዱ ነበር›› እናም ሰው የሚያጠፋውን ነገር የሚያደርግበት ዋነኛ ምክንያት የሥነምግባር ማነስ ያመጣው ነው።
ሥነምግባር የነፍስ ድህነትን ብቻ ሳይሆን ለሥጋም ቢሆን ፈውስ ነው። ችግሮችን መፍቻ ቁልፍና ሌሎችን ማሸነፊያ መንገድ ነው። ከባህል አንጻር ሲታይ ደግሞ ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው ብዙ ነገር ቢኖራትም ብዙዎች ለዚህ ሲገዙ አይታይም። ለአብነት በእምነቱ ጽኑ መሆኑን ብቻ ብናነሳ አንድ ሰው በእምነቱ ጸና ማለት እምነቱ የሚያዘውን በሙሉ ያደርጋል።
በተለይ በመከባበርና ለሌላው መኖር ላይ ከተማረውና ከእምነቱ አንጻር ብቻ ቢተገብረው ሥነምግባር ያብብ ነበር። ሆኖም እምነቱ ከውስጥ ባልሆኑ የተነሳ ለሰው ከማሰብ ይልቅ የእኔ ብቻ የሚለውን ያስቀድማል፤ ሰዎች ሲኖራቸው በራሱ ይቀናል።
የሥነምግባር ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ለመምጣቱ ማሳያው የነበረ ባህል እየቀረ መምጣቱ ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያ አንድ ነገር ላንሳ። አንድ እናት ያላቸውን ማካፈል የሚወዱ ናቸው። ከጊዜ በኋላ ችግር እቤታቸው ሲገባ ራሳቸውን እንኳን ለማኖር አቃታቸው። እናም ሁኔታውን ሲያስረዱ ‹‹አሁንስ እንኳን መብላት ማብላትም ቀረ›› ነበር ያሉት።
ይህ ማለት የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ከባህልና ሥነምግባራቸው አንጻር የሚያስቀድሙት ማብላትን እንጂ መብላትን አይደለም። ራስን ሳይሆን ሌሎች ይቅደሙ ነው የሚሉት። ዛሬ ግን ተቃራኒ መሆኑን ቤት ውስጥ ሳይቀር የእኔ ነው ያንተ አይደለም ገብቷል። ውጣልኝ ነግሷል።
አዲስ ዘመን፡– የውጣልኝ አስተሳሰብ ሰው ብቻውን ለመኖር ያቀደው አይመስሎትም፤ ይህስ ይቻላልን?
ቀሲስ ይግዛው፡– እንኳን ሰው እንስሳትና እጽዋትም ብቻቸውን መኖር አይችሉም። ለሰው ልጅ እንኳን ሰው ይቅርና ያለ እንስሳትና እጽዋት ለመኖር ይቸገራል። ምክንያቱም እነርሱን ተመግቦ፤ ከእነርሱ አየር አግኝቶ፤ ተጠቅሞባቸው በሕይወት እንዲቆይ የተፈጠሩለት ናቸው። በአባባል እንኳን ቢመጣ ‹‹ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው›› ይባላል። በመጽሐፍ ቅዱስም ቢመጣ ‹‹ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ አይቻለውም›› ተብሏል። በዚህም ሄዋኖች ለአዳሞች እንዲፈጠሩለት ሆኗል።
የውጣልኝ ምክንያቱ የሀጢያት ብዛት፤ የበደል ውጤት ነው። ይህ ባይሆንማ የጽድቅ ውጤት የሆነው ናልኝ፤ በሞቴ አፈር ስሆን ብላልኝ በአገራችን ላይ በርትቶ እናይ ነበር። ሆኖም የበደላችንና የሰራነው መልካም ያልሆነ ተግባር ውጣልኝን እንድናስተናግድ አድርጎናል።
ሌላው የውጣልኝ መሰረታዊ ምክንያት የሚታዩና የማይታዩ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚታዩና ለጊዜው ምክንያት ናቸው የሚባሉት አይበቃኝም ባይነት፤ እኔ ልብላ፤ እኔን ይድላኝ ነው። የማይታየው ደግሞ እርስ በእርስ ውጣልኝ ስንባባል ከጀርባ እንጀራቸውን የሚጋግሩ አካላት መኖራቸው ነው።
ቀድሞ የተሰሩ መፍትሄ ያልሰጡ ተግባራት ሞልተው ሲገነፍሉ የምናገኘው ውጤት ነው። በተለይ ለአንተ እኔ አውቅልሀለሁ መብዛቱና ለእነርሱ ቦታውን ሰጥቶ ገሸሽ መባሉ አላስፈላጊ ዘሮች እንዲዘሩ እድል ሰጥቷል።
በዚህም አሁንም እኔ አውቅልሀለሁ የሚሉ ሰዎች የፈለጋቸውን በፈለጋቸው ጊዜ እንዲያደርጉ ሆነዋል። በዚህ ደግሞ መጠቀሚያው ሕዝብ ስለሚሆን የእነርሱን አላማ እንዲያስፈጽምለት ውጣልኝ ይላል።
አዲስ ዘመን፡– 98 በመቶ አማኝ ተብላ በምትጠቀስ አገር ውስጥ ይህ መሆኑን እንዴት ያዩታል፤ እውነት አማኝ አለ ማለትስ ያስችለናል?
ቀሲስ ይግዛው፡- አንድ ሰው ማመኑ ብቻ መንግስተሰማያት እንደማያስገባው በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል። ነገር ግን እምነት ከምግባር ጋር አስተባብሮ መያዝ ግዴታ ነው። ‹‹ሃይማኖት አለኝ የሚል ነገር ግን መልካም ሥራ የማይሰራ ሰው እምነቱ የሞተ ነው›› ተብሎ በያቆብ መልዕክት ላይም ተቀምጧል።
እንደውም ከሰይጣን ጋርም ያወዳድረዋል። ሰይጣን አምናለሁ ይላል፤ እግዚአብሔርን ይፈራዋል ይንቀጠቀጥለታልም። ግን ምግባርና መልካም ሥራ የለውም። ስለዚህ አማኝነት ከዚህ አንጻር የሚተነተን ስለሆነ የዛሬ ሰው እንኳን ማመን ወደ እምነቱ የሚጠጋ ነገር አለው ብሎ ማመን ይከብዳል።
አዕምሮና ልቦና ያልተሳተፉበት የአፍ መንፈሳዊነት የትም አያደርስም። ምክንያቱም የማስመሰል ሥራ ይሰራበታልና። ተግባራዊ የምናደርገውም ቢሆን ሥጋዊ ስሜታችንን ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በማህጸን ውስጥ ያለ የተበላሸ ሽልን ይመስላል። በዚህም ራሱን ብቻ ሳይሆን እናቱን ይገድላል።
ሞቶም ሌላውን ይገድላል፤ ህያው የሆነ ሽል ግን ሌላውን ዘላለማዊ ያደርጋልና ሥነምግባር የሌለውና ውጣልኝን መለያው ያደረገ አንድ ሰው ራሱን ገድሎ ሰዎችንም እንደሚገድል ማመንና ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች መራቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት እምነት፤ ህግ፤ መልካምነት ብሔር እስከተጠበቀ ድረስ የሚኖሩ ብቻ ሆነዋል። ይህንን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ቀሲስ ይግዛው፡– ክፉ ተግባር እየበዛ ሲመጣ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደተቀመጠው ሰዎች የክፋታቸው ልኬት መጠን አልባ በመሆኑ ከፈጠረን በላይ እንሁን ብለው እርሱን ለመንካት ትልቅ ግንብ መስራት ጀመሩ። ይህ ክፋታቸውም ትክክል እንዳልሆነ ሊነግራቸው ስለፈለገ ቋንቋቸውን ደበላለቀባቸው።
መግባባት እንዳይችሉም አደረጋቸው። በተመሳሳይ ለመልካም የተነሱ ዓለምን እንደ ጨው ለሚያጣፍጡና ሰዎችን ወደ መልካም ነገር ለሚያመጡ ቋንቋ ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ በማመን ለሐዋርያት 72 ቋንቋን እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።
ስለሆነም ቋንቋ አንድም ለጸጋ፣ ለክብር፣ ሰዎች ከሰዎች ጋር ተግባብተው መልካም ሥራ እንዲሰሩ ማድረጊያ ነው። አንድም ጎራ ለመለያና ክፉ ተግባርን ለመከወኛነት የሚያገለግል ነው። በዚህም ነው ዛሬ ላይ ክፉ ምግባራችንና ሥራችን ልቆ ስለወጣ ቋንቋን አንዱን ከአንዱ ጋር ለማባላት እየተጠቀምንበት ያለነው።
ሰዎች ብሔር ብሔር እያሉ እንዲያቀነቅኑ ያደረጋቸው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት እየላላ መምጣት ነው። ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር በጥብቅ ከተሳሰሩ እንኳን የሰዎችን ሊወስዱ የራሳቸውንም ነገር ነው የሚተዉት።
መልካም ነገር እንጂ ክፉ ነገር አይታሰባቸውም። በተመሳሳይ ይህንን ነገር ያመጣው እሴቶቻችንን ችላ ማለታችንና ለሌሎች ባህሎች ራሳችንን አሳልፈን መስጠታችን ነው። ከዚያ ሻገር ሲልም የሉላዊነት ጉዳይም ተጽዕኖው ላቅ ያለ ነው። የግላዊነት ምንጩም ይኸው ነው።
ዘመናዊነት ሁሉን ነገር አድርግ እንጂ ክልከላ የለበትም። ሃይማኖት ግን በተለይ ክፉ ነገሮችን ይከለክላል። መልካም ነገሮችም ቢሆኑ በልኩ ይሁኑ ነው የሚለው። ስለዚህም ሃይማኖት በመጠን ኑር ሲል ዓለም ደግሞ እኩል ሆነህ ኑር ስለሚል ተቃራኒ ሀሳቦችን እንዲያስተናግዱ ሆነዋል። ሰዎች ሲከለከሉ ይብስባቸዋልና የተከለከለውን ማድረግ ይመርጣሉ። ለዚህም ነው ሁሉን አድርግ በሚለውና ለእኔ ብቻ በሚለው ውስጥ እየባዘኑ የሚገኙት።
አዲስ ዘመን፡– አገራችንን ከዓለም አገራት ምን ይለያታል፤ እውነት እንደምትባለውስ ዛሬ አለች ይላሉ?
ቀሲስ ይግዛው፡– በዓለም ላይ ልዩ የሆነ ባህልና መልካም እሴት ባለቤት ያላት መሆኗ ይለያታል። መከባበሩ፣ አብሮ መብላቱ፣ ችግርን አብሮ ማሳለፉ ወዘተ በማንነትና በብሔር የተገደበ ያለመሆኑ ልዩ ያደርጋታል። በሥነ ሕንፃ ለየት ያሉ ጥበባትን መጠቀም መቻሏም አንዱ መለያዋ ነው። ዓለም ባልሰለጠነበት ወቅት ኢትዮጵያ ብዙ የሥልጣኔ ማሳያዎችን እውን ያደረገች መሆኗ፤ የራሷ የሆነ የዘመን መለወጫ፣ ቋንቋና ፊደል ያላት መሆኗም እንዲሁ ልዩ የሚያደርጋት ነው።
ሙሉ ለሙሉ የትናንትናው እሴት ተጠራርጎ ጠፍቷል ማለት አይቻልም። ነገር ግን ቀንሷል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አንድነትነት፤ መከባበር የሚባሉት ነገሮች እንዲጠፉ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ለማጥፋትም የሚጣርበት ሁኔታ ብዙ ነው። ሆኖም ሕዝቡ በትምህርቱ እንኳን ላቅ ባይልበት ይህ ልዩ የሚያደርገውን እሴት ተፈጥሮ አስተምሮት እንዳይጠፋበት እየታገለ ይገኛል።
ይህንን ደግሞ በተለያየ ነገር መግለጥ ይቻላል። ቢቻልና ወደቀደሙት አባቶች ሄደን አሁን ያለንበትን እሴት ብናሳያቸው ይህንን ነው ወይ አለን የምትሉት ሊሉ ይችላሉ።
ተከታዮቻችንን ብንወስዳቸው ደግሞ በራሳቸው ያፍራሉ። ስለዚህም እሴትና ባህላችንን በምንገለጥበት ደረጃ አስቀጥለነዋል ወይ ቢባል ልኬቱ እንደ ዘመኑ ይለያያል። ሆኖም ከነገ ዛሬ እንደሚሻል ማመን ተገቢ ነው።
አሁን በህይወት ያለነው ዜጎች እንደትናንቱ አይደለንም፤ ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ለመጠበቅ እየሞከርን ነው ጥቂቶችም ብንሆን። ነገ ግን በዚህ ሁኔታችን ካስቀጠልነው የከፋውን ልናወርስ እንችላለን። ገና በአርባዎቹ ላይ ሆነን የዛሬ ይህን ዓመት እንዲህ ነበር ማለት ተጀምሯል።
ይህ ደግሞ ባህልና እሴት መጠበቅ ምን ያህል እየቀነሰ እንደመጣ ያሳየናል። በዚህም ትውልዱ ዛሬ ቢነቃ አልመሸምና የትናንት ተናጋሪ ብቻ እንዳንሆን ዛሬን ለተሻለ ነገ መገንባት ይጠበቅብናል። ዛሬ የሚከለከል ነገር የለም። የሚሰራ ሥራ ሞልቷል። እነዚህን ነገር ግን ትውልዱ በመልካም ነገር እየቀየረ ችግር ማስወገጃ፤ አገርን ማሳደጊያና ለራሱም ከችግር መውጫ ማድረግ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– በትውልዱ ላይ የሚታዩ ያልተገባ ባህሪ ምንጫቸው ምንድነው ይላሉ?
ቀሲስ ይግዛው፡– የመጀመሪያው የሥነምግባር መላላት ነው። ይህንን ደግሞ ያመጡት የውስጥና የውጭ ተጽዕኖዎች ናቸው። የሚታዩና የሚሰሙ ነገሮች፤ ሉላዊነቱ ማለትም ዓለምን ወደ አንድ ሥርዓት ማምጣት የሚለው ጉዳይ ነው።
የሰው ልጅ እንዴትና ለምን የሚሉ ጥያቄዎችን ካልተጠቀመባቸው መረን ይሆናል። የተባለውን፤ ያየውን ዝም ብሎ ማድረግ ነው የሚቀናው። ለዚህም ነው በዓለም ላይ ያለ የጸጉር አቆራረጥ፣ የአለባበስና መሰል ነገሮች በአንድ ጊዜ አገር ውስጥ ገብተው እየተከተላቸው ያለው።
ራስን አለመሆን፤ ከራስ ይልቅ ለሌላው ቅድሚያ ሰጥቶ በእነርሱ ምቾት ራስን ለማመቻቸት መሞከር ይህንን አምጥቷል። በጎውን እያደረጉና እያስደረጉ አለማስቀጠልም ሌላው ችግር ነው።
አብዛኛው ቤተሰብም ልጆቻቸውን ምን ዓይነት ልብስ፣ ምን ዓይነት ትምህርት ቤት ይማሩ እንጂ ምን ዓይነት ሥነምግባር ይኑራቸው፤ ምን ዓይነት ትዳር ሊመሰርቱ ይገባልና ወዘተ አይሉም። በራስህ ተወጣው ብሎም ነው የሚተውላቸው። ይህ ደግሞ በልጆች ላይ ገደብ አልባ ነጻነት ይሰጥና መብት እንጂ ግዴታቸው እንዳይታያቸው ያደርጋል።
ሌላው የሥነምግባር ብልሽት ምንጩ መጥፎ ታሪክን እየነገሩ ማሳደግ ነው። ሰው ልጆቹን እንደ ሙሴ ልጅ ለወገኔ እንዲል አድርጎ ማሳደግ ያስፈልጋል። ስለ አገሩ እንጂ ስለ ብሔሩ ብቻ እንዳያይና ጽንፍ ያለው አመለካከትን እንዳያዳብር ማድረግ ላይም መስራት አለበት። የሚውሉባቸውን ቦታዎችም መምረጥ ይገባል።
በተለይ በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው ወጣቶች እንዲሁም ጎልማሶች ጭምር የስፖርታዊ ቁማር የሆነው እነ ቤቲንግ የሚባሉ ጨዋታ መሰል ተግባራት ቤትና ንብረትን እያሸጡ ነው። ቀን ተዘግተው ውለው ሌሊት አሸሼ ገዳሜ የሚባልባቸው ቦታዎች እውቅና ተሰጥቷቸው ብዙውን ትውልድ እያበላሹት ይገኛሉ። እናም መንግሥት ለእነዚህ አካላት መልካም ነገር የሚተገብሩበትን የሥራ አማራጭ ሰጥቶ ትውልዱ በፈጠራ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ላይ መስራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– አስረካቢና ተረካቢ የሚለውን ከትውልድ አንጻር እንዴት ያዩታል፤ በአገራችን ደረጃ እነዚህ አሉ ለማለት ይቻል ይሆን?
ቀሲስ ይግዛው፡- አስረካቢ ካለ ተረካቢ አለ። ተረካቢ ትውልድ ስለነበረ እነላሊበላን፤ አክሱምንና መሰል የሕንፃ ጥበብ ውጤቶቻችን አግኝተናቸዋል። ስለሆነም ዛሬ ተጠያቂ የሚሆነው ተረካቢው ሳይሆን አስረካቢው ትውልድ ነው። ተረካቢ ማለት ሕፃናት ናቸው።
ወደፈለግንበት ልንነዳቸው የምንችለውና የፈለግነውን እንዳይለቅ አድርገን የምንጽፍባቸው። ስለዚህም ዛሬ ላይ ወጣት የሆኑት ትናንት የተተከለባቸውን እየኖሩ ይገኛሉ። የምንወቅሳቸውም ትናንት መልካም ዘር ሳይዘሩባቸው ለዛሬው ስለሰጧቸው ነው።
እናም አገር አትጠቅምህም፤ እንትና የሚባለው ብሔር አንተን የረገጠህ ነው እየተባለ ያደገን ወጣት ዛሬ ላይ ሆነን እንትናን ውደድ ብንለው መስበር ካልሆነ በቀር ልናቀናው የምንችልበት ሁኔታ ቀላል አይሆንም። ስለዚህ አስረካቢው ትውልድ ብዙ ነገር ይጠበቅበታል። ትክክለኛ ታሪክ መንገር፤ መልካሙን ነገር ማሳየትና አገር ወዳድነትን እንዲያጎለብት ማድረግ ሲችል ተረካቢውን ያፈራል።
አዲስ ዘመን፡– የትውልድ ግንባታ ላይ እነማን ናቸው ድርሻ ያላቸው?
ቀሲስ ይግዛው፡– ቤተሰብ፣ ኅብረተሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ መንግሥት እያልን ዘርዘር አድርገን መጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው ቤተሰብ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተቀመጠው ‹‹ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለ ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም›› ይባላል። በችግኝ ላይ እሳት እያነደዱ ተረከብ፣ አገር ውደድ ማለት ግን የማይመስል ነገር ነው። ተወቃሹም እርሱ ብቻ ነው።
ቤተሰብ ልጆቹን ሲያሳድግ አራት ዓይነት መንገዶችን ተከትሎ እንደሆነ ሳይንሱ ያስረዳል። የመጀመሪያው አምባገነናዊ ወይም ወላጅ መር የሚባለው ዓይነት ሲሆን፤ እኔ በምልህ ብቻ ሂድ የሚል ዓይነት ነው። ከዚያ ውጪ ወጣ ብሎ የራሱን ፈጠራ ካከለና ከተቃወመ ቤተሰቡን እንደማያከብር የሚወሰድበት ዓይነት ነው። ሁለተኛው ልቅ ወይም መረን የሚባለው ዓይነት ሲሆን፤ እንደፈለገው ይሁን አትንኩት ልጄን የሚባልለት ዓይነት ነው።
ሲያጠፋም በርታ የሚባለው ዓይነት። ሦስተኛው ደንታ ቢስ የሚባለው ሲሆን፤ ለልጁ ምንም ግድ የሌለው ዓይነት አስተዳደግ የሚያሳድግ ነው። አራተኛው ደግሞ ዲሞክራት የሚባለው ዓይነት ሲሆን፤ ተመራጭና ሰዎች በዚህ ቢመሩ ትውልዱን በመልካም ሥነምግባር መኮትኮት የሚችሉበት ነው። ይህ ዓይነት አስተዳደግ በማሳየት፣ በማስተማር፣ በተግባር፣ ከስህተቱ በመመለስና መንገድ በማሳየትም የሚያሳድግ ነው።
‹‹ በጎ ነገር ማድረግ እንዳለበት አውቆ የማይሰራ እርሱ ተጠያቂም ሀጢያተኛም ነው›› እንዲል መፅሐፍ ቅዱስ ክፉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሀጢያተኛ የሚያደርገው በጎ አለማድረግም ሀጢያተኛም ተጠያቂም ያደርጋል። ስለሆነም ይህንን የማያደርግ ቤተሰብ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም።
በተለይም ክፉ ዘር ክፉን መልካም ዘር ደግሞ መልካምን ያፈራልና መልካሙን ለማግኘት ከቤተሰብ በተጨማሪ መምህራንና ተቋማትም ቢሆኑ ክፉ ነገርን አለመንገር፤ በጎ ነገሮችን አለማድረጋቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውምና ይህንን እያሰቡ መስራት አለባቸው።
ሰው የሚነበብ ነው። ስለዚህም ቤተሰብም ይነበባል። ይህ ሲሆን ደግሞ መልካሙን አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ሆኖም ክፉ የሚነበብበት ቤተሰብ ከሆነ ተከታዩም ክፉ ይሆናል። አሁን ክፉ የምንላቸውም ከቤተሰባቸው የተበላሸ ማንነትን ወርሰው ስላደጉ እንጂ በሰውነታቸው መጥፎ ሆነው ተፈጥረው አይደለም።
ሁለተኛው ትውልድ የሚቀርጸው የሃይማኖት ተቋማት ሲሆኑ፤ እነዚህ ተቋማት መጀመሪያ ራሳቸው ተስተካክለው ሌላውን ለማስተካከል መሞከር ይኖርባቸዋል። ሌሎችን ተስተካከሉ ብሎ መምከር ግን ማንንም ከፍ ሊያደርግ አይችልም። በቤተ እምነት ውስጥ በምንም መልኩ ክፍፍልና፣ መጣላትን የሚሰብክ አካል አለ ተብሎ አይታሰብም። ሆኖም ችግር ያለባቸው ሰዎች ሊያደርጉት ይችላሉና እነርሱን መታገል ግዴታ ነው። ምክንያቱም እምነቱን ያሰድባሉና።
በተመሳሳይ ከሃይማኖት ተቋማት እኩል ትምህርትቤቶች በጎ ዜጋን የምንፈጥርባቸው ቦታዎች ናቸው። እንደፈለጉት እየነገሩ የሚያበላሹት ወይም በመልካም ሥነምግባር የሚከተኩቱት ለጋ ዜጋንም ስለያዙ ይህንን ተግባራቸውን ለአገር በሚጠቅም መልኩ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይም አንዱን ከአንዱ ጋር የመለያየት ተግባር ላይ እጅጉን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
ሌላው በትውልድ ቀረጻ ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው ኅብረተሰቡ ሲሆን፤ ጥሩ የሆኑ ባህሎችን ሁሉ ማውረስ ይኖርበታል።
በተለይም ጥሩ የአካባቢ ሰላም መፍጠርና ልጆች ነፃነት እንዲሰማቸው ማድረግ ላይ ከመቼውም ይበልጥ ሊሰሩ ያስፈልጋል። ከኅብረተሰቡ ጎን ለጎን መንግሥትም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። ለአብነት መልካም እሴቶች ላይ ጥበቃ ማድረግ ቢችል ክፉ ነገሮችን ነቅሎ ቢጥል። ማለትም ወጣቱን ወደ ክፉ ነገር የሚመሩ መሸታ ቤቶች፣ ዝሙትና ምሽት ቤቶች ላይ እገዳ አድርጎ ያንን በተሻለ አማራጭ ቢቀይረው ትውልዱ ከክፉ ተግባር ሊታቀብ ይችላል።
ነውር የሆኑ ነገሮች ሁልጊዜ አየኝ አላየኝ ተብለው የሚተገበሩ ናቸው። ስለሆነም ከዚህ መሸሸግ ወጣቱን ማውጣት ቢቻል የተሻለና ለአገር የሚጠቅም ትውልድ ማፍራት ይቻል ነበር። ወጣቱ ዛሬ ላይ የሚፈልገው ወደ መልካም ጎዳና የሚመራውን ጥሩ መሪ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ አድርግ የሚባለውን ከውስጥ በመነጨ ስሜት ያደርገዋል።
ለዚህም በአብነት የሚነሳው በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ የሚያደርጉት ርብርብ ነው። ስለሆነም ሁሉ ነገር በጠበበት ዓለም ውስጥ እየዋኘ ያለ ዜጋን መዋያ ሰጥቶ የፈጠራ ባለቤት በማድረግ ማዳን የሁሉም ድርሻ ይሆናል። በተለይ መንግሥት የሥራ ዕድሉን በመልካም እሴቶች ላይ ቢያደርግና የወጣቱ ችግር ምንድነው የሚለውን በጥናት ለይቶ መፍታት ላይ ቢያተኩር የበለጠ ትውልዱን ማስተካከል ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የትውልድ ቀረጻን አሉታዊና አወንታዊ ጎን ከሳይንሱ አንጻርና ከሃይማኖት አንጻር እንዲት ይታያል?
ቀሲስ ይግዛው፡– አወንታዊ ወይም አሉታዊ ሥራዎች ወይም መልካምና ክፉ ተግባራት የማንነት መለኪያ ናቸው። ስለሆነም መልካም ሰሪ ታላቅ እንደሆነ እንረዳበታለን።
ምክንያቱም በሽበት ሳይሆን በአዕምሮ በልጦ ስለሚገኝ ነው። በእርግጥ ሽበት ጸጋ ነው። ግን አዕምሮ ወይም እውቀት ግን ሊታከልበት ይገባል። መልካም ማድረግ የሕይወት ሕንፃ ነው፤ ዘላለም እየተጠቀሰ የሚኖር። መልካምነት እግዚአብሔርን መውደድም ነው። መልካም ሰው ከሞተም በኋላ ሰዎችን ይጠቅማል። ምክንያቱም በስሙ ብዙ መልካም ነገሮች እየተደረጉ ይቀጥላሉ፤ ብዙዎች አርአያነቱን ተከትለው ይድናሉ።
ክፉ ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል። በተለይ ክፉ ሥራ በትል እስከመበላት እንደሚያደርስ በመጽሐፍ ቅዱስ ተቀምጧል። እናም ዛሬ በትል ላለመበላት መልካም ምግባሮቻችን ሊያይሉ ይገባል።
አልበርት አንስታይን እንዳለው፤ እኔን የሚያስፈራኝ የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ ሳይሆን በሰው ልብ ውስጥ ያለው የክፋት ፍንዳታ ወይም ኃይል ነው። ዛሬም አገርን እያስፈራ ያለው ነገር ይህ ነው። የሰው ልጅ የክፋት ፍንዳታ ዛሬ ፈንድቶ የሚያቆም ሳይሆን ነገም የተለየ ቁርሾ ይዞ የሚመጣ ነው። እንዲያውም በየአካባቢው የሚታየው ያልተገባ ተግባርም የተሰራው ክፉ ሥራ ቀስ እያለ እየፈነዳ በመምጣቱ ነው።
ዛሬ ቤተሰብ ቀብሮ ለነገ ማሰብም የመጣው በተለያየ ጊዜ ምን ዓይነት ችግር ይፈጠር ይሆን የሚለውም ስለሚያሳስባቸው ነው።
‹‹ የቱ ጋር ነህ ስትባል የማታፍርበት ላይ አትገኝ›› እንደሚባለው፤ ሰዎች በሚውሉበት ቦታም ሊፈረጁ ይችላሉና ለመልካምነት መገንቢያቸው ይህንን መጠቀም ቢችሉ የተዋጣላቸው ይሆናሉ። በጎ ማድረግ በጎ ነገር ይመልሳል።
አዲስ ዘመን፡– ቤተ እምነቶች አገርን ከማቆም አንጻር ከመንግሥት በላይ ኃይል እንዳላቸው ይታመናል። ሆኖም በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ይህ ሲሆን አይታይም። ምክንያቱ ምን ይሆን?
ቀሲስ ይግዛው፡- የተለያዩ ተጽዕኖዎች ናቸው ይህንን እንዳያደርጉ የገደባቸው። የመጀመሪያው የውጭ ተጽዕኖዎች ሲሆኑ፤ የሉላዊነት፣ የአለማዊነትና የግላዊነት ተጽዕኖ ያረፈባቸው አካላት ቤተ እምነቶችን እንዲመሩ ተደርገዋል።
ይህ የተደረገው ደግሞ በሆነ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎም ሊሆን ይችላል። በብሔር ጭምር እንዲመሩና እንዲመረጡም እየተደረገባቸው ነው። ለእምነቱ ሳይሆን ለፖለቲካውና ሌላ አካል ለመጠቀም የሚመችበትን ሁኔታ እየታየም ይመደባል። ይህ ደግሞ ተልዕኮው ለቤተ እምነቱ ሳይሆን ለአስገባው ብቻ ይሆንና ቤተ እምነቶቹ ተሰሚነታቸው እንዲከስም ይሆናል።
በቤተ እምነት ውስጥ አሁን ካሉት በላይ በእውቀትም በአገር ፍቅርም የተሻሉ በርካቶች ይኖራሉ። ግን እየተገፉ በመሆናቸውና ኃይሉ ተመርጦ የተቀመጠው በመሆኑ አንድ ሊቅ እንዳለው ‹‹እውነት እንዳልናገር ዓለም ይጠላኛል፤ ውሸት እንዳልናገር ደግሞ ፍርድ ይጠብቀኛል። ከዚህ ሁሉ ዝም ማለት ይሻለኛል›› ያሉ ብዙ አባቶች መኖራቸው ቤተ እምነቶች መፍትሄ አመንጪና አገርን ከመንግሥት በላይ ጠባቂና አዳኝ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
የአንዳንዶች ክፉ ተግባር በተለይም አርአያ መሆን ይኖርባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ የቤተ እምነት መሪዎች ተግባር ሕዝቡ ሁሉንም በአንድ ጎራ እንዲመድባቸውና አባት የለም እንዲሉም አድርጓል። ይህ ደግሞ ተሰሚነትን ቀንሶ ኃይል ያለው ቤተእምነት እንዳይፈጠር መንገድ ዘግቷል።
በአገር ደረጃ ያለው ፖለቲካ ትርጓሜ ትክክለኛ ያልሆነ ስያሜ የተሰጠው ነው። የፖለቲካ ምሁር ባልሆንም ካነበብኩት አንጻር ፖለቲካ አገርን መውደድ፣ ማስተዳደር፣ ለአገር መሞት፣ ሕዝብን መጠበቅ ነው። ይህ ደግሞ ግድ ለፖለቲከኛው ብቻ የሚተው አይደለም። የሃይማኖት አባቶች ጭምር ሊሳተፉበት የሚገባው ነው።
ምክንያቱም ሁሉም መልካም ነገሮች ናቸው። መልካም ማድረግ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር በመሆኑ ለቤተ እምነት መሪም ሆነ ለአማኙ ይፈቀዳል። ግን በተጣመመ መልኩ እየተረጎምነው ስለመጣን መተው የሌለብንን እንድንፈራውና እንዳንሳተፍበት ሆነናል።
መድረክ ሲወጣ ከአነጋገር ጀምሮ አርአያ መሆንና አገርን የሚያገለግል ወጣት መቅረጽ ላይ ትኩረታቸውን አለማድረጋቸውም ገነው እንዳይወጡና ሌላውን እንዳያሸንፉ አድርጓቸዋል።
ያለፉና አገርን ያቆሙ የሃይማኖት አባቶችና እናቶችን ታሪክ ከመማርና ከማስተማርና ከመተረክ ባለፈ ሕይወታቸውን በተግባር የሚኖር አባት እየቀነሰ መምጣቱም ሌላው ተጽዕኖ የፈጠረ ጉዳይ ነው። ለመልካም ፍሬ መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ አካል ያለመኖርም ሌላው ችግር ነው። አገር የሃይማኖት ተቋማትን እንድትሰማ በተለይ
ከኢትዮጵያ የሚፈልጉት ነገር ያላቸው የውጭ አካላት አይፈልጉም። ምክንያቱም ሃይማኖት ለአገር ብዙ አበርክቶ እንደሚኖራት፤ ሕዝብን ጨምሮ ለመያዝ ኃይል እንዳለው ያምናሉና ነው።
አዲስ ዘመን፡– አገር አሁን ካለችበት ችግር እንድትወጣ ምን ይደረግ ይላሉ?
ቀሲስ ይግዛው፡– ከሁሉም በላይ ሁሉም ሊረባረብ የሚገባው ትውልድ ቀረጻ ላይ መስራት ነው። የምናልፍ እንደመሆናችን መጠን የማያልፍ ሥራ መስራት ላይ ማተኮር ይገባናል። ዘመኑን ለመዋጀት የዘመኑን ክፋት አውቆ ቀድሞ መፍትሄ የሚሆን ነገር መስራት ያስፈልጋል። በእውቀት ራስን አበልጽጉ ሌሎችንም በመልካም ጎዳና የሚሄዱበትን መስመር መዘርጋት፤ እንዲያውቁም ማድረግ ይገባል። ክፋትን በክፋት ለመመለስ አለመሞከር።
ጥበበኛ ሰው የተወረወረበትን ድንጋይ መልሶ የሚወረውር ሳይሆን በተወረወረበት ድንጋይ ቤት የሚሰራ ነውና ይህንን ሰው ለአገር መፍጠርም ተገቢ ነው። መቼም ቢሆን መች ትዕግስት ያሸንፋል፤ መቼም ቢሆን መች መገፋት ነገ መነሳት አለው። ስለሆነም ያንን እያሰቡ መስራት አገርን ከችግር ማውጣት ነው።
ቀን የሚያመጣው ነገር በቀን ያልፋል። ምክንያቱም ትናንት የነበሩ ቀኖች ዛሬ የሉም። ስለሆነም ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ክፉ ነገር መትከል ተገቢ አይደለም። ይልቁንም ዘላለማዊ የሚሆኑ መልካም ዘሮችን መዝራትና የነገው ሰው እንዲጠቀምባቸው ማድረግ ከምንም በላይ አገርን መገንባት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
መልካም ቀንን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ቀን ለማደግና ለመበልጸግ ጊዜን ይፈልጋል። እናም መኖር ማለት ማዕበሉ ጸጥ እስኪል መጠበቅ ሳይሆን ከማዕበሉ ውስጥ ሆኖ እንዴት መውጣት እንደሚቻል ማሰብ ነውና አገርም ዛሬ በማዕበል ውስጥ ስለሆነች ይህ እስኪያልፍ ዝም እንበል ሳይሆን እንዴት ከችግሩ እንውጣ በማለት መስራት ነውና ሁሉም ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ላይ መረባረብ አለበት። መንግሥትን ብቻ ተወጣው ማለት ተገቢነት የለውም።
ሰው ሊሳሳትና ሊያጠፋ ይችላል። ነገር ግን ከስህተቱ እንዲታረም ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ነው። ስህተት ልምድን ይጨምራል። ልምድ ደግሞ ስህተትን ይቀንሳልና ይህንን እያዩ መራመድም ለአገር መፍትሄ ይሰጣል።
ያልተሰራ አዕምሮ የተሰራ ከተማን ያፈርሳል የተሰራው ግን የበለጠ እንዲያምር ይታትራልና ዛሬ ትውልዱ ሲወድቅ ያልሰራነው ሥራ እንዳለ ከማሰብ ይልቅ እየፈረድንበት ነውና ይህንን ማንሳትና ለአገሩ እንዲጠቅም በማድረግ አገር ገንቢ ልናደርገው ይገባል። የተሰራውን ከተማ የሚያሻሽልና ባለው ላይ የሚጨምርም ማድረግ ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን፡– በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመሪዎች፣ ለመምህራንና ለሕዝቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ቀሲስ ይግዛው፡– ለሀገር መሪዎች የምለው ነገር አንድ ከአነበብኩት ያገኘሁትን ሀሳብ ነው። ይህም ‹‹ ሕዝብ የሚያስበውን አውቆና ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ የማይሰጥ ከሆነ የመጀመሪያ ስኬቱን እንዳጣ ይወቀው›› ይላል።
እናም ሕዝብ ምን ይፈልጋል፣ ሕዝብ ምን እያለ ነው፣ ሕዝብ ምን ጎደለው የሚለውን ማየትና መፍትሄ መስጠት ለአገርም ሆነ ለመሪዎች ህልውና እጅግ ጠቃሚ ነው። ሕዝብን እንጂ ራስን ማስቀደምም በፍጹም ተግባሩ ሊሆን አይገባም።
ለመምህራን የምለው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ታዛዥ፤ ደግና ጀግና ነው። አሁንም እነዚህ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ስለዚህም ዓለምን በሚያጣፍጠው ትምህርታችሁ ይህንን በጎነታቸውን እንዲያጎለብቱ እንጂ እንዲጠሉ አታድርጓቸው።
እያንዳንዱ የእምነት ተቋማት ላይ ያሉ አማኞቻችንን መልካምነትን ብቻ ብንሰብክላቸው ዛሬ ያለው ችግር አይደለም ሊፈጠር ለሌሎችም መከታና ተገን እንሆናለን።
ለሕዝቡ ደግሞ እናትና አባት በመልካም ሠነምግባር የተኮተኮተ ልጅ ካሳደጉ ጥሩ መሪ እንዳዘጋጁ ይቆጠራል። ጎረቤት ጎረቤቱን እየቆነጠጠ ቢያሳድገውም ከቤት ያመለጠውን አጥፊ ልጅ መመለስ ይቻላል።
በተመሳሳይ ትናንት የሰራነው ሥራ ዛሬ ለልጅ ልጆቻችንም ሊተርፍ ይችላልና ዛሬ ላይ ቆመን ለነገ የሚሆን መልካም ስንቅ መሰነቅ ካልቻልን የነገውንም ትውልድ መግደላችን የማይቀር ነውና ይህንን በማድረጉ ዙሪያ ሁሉም ሊሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እጅጉን እናመሰግናለን።
ቀሲስ ይግዛው፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013