ጽጌረዳ ጫንያለው
በአገረሰብና አገር በቀል ፍልስፍናዎች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይታወቃሉ። በግብርና ምህንድስና የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተው በሙያው በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠትም ረጅሙን እድሜያቸውን ያሳለፉ ናቸው።
አሁን ደግሞ በማኅበረ ቅዱሳን የተቋማት ልማት ዘርፍ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ያገለግላሉ። የኃይማኖት መምህርም ናቸው። በዚህም የልደት በዓልና ኃይማኖታዊ አስተምሮውን እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን እያነሳን አጠር ያለች ቆይታን አድርገናል። ስለዚህ ብዙ አስተማሪ ነጥቦችን አንስተናልና በወቅታዊ አምዳችን ተከታተሉን።
አዲስ ዘመን፡- በዓላት በኢትዮጵያ ምን አይነት መልክ አላቸው፤ በተለይ ኃይማኖታዊ በዓላት ?
መምህር ፋንታሁን፡- በዓል ሲባል የተለያየ ትርጉም ይሰጠዋል። በባህል፣ በኃይማኖትና አስቻይ ሁኔታዎችን በማየት የሚከበር በዓል በማለት። ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአብዛኛው በዓላት የሚታዩት የዘመንና የወቅቱን ኡደት መሰረት አድርገው ነው። በዓሉንም የሚያከብሩት ለአምላካቸው ምስጋና ለማቅረብ ሲሆን፤ አሁን በሴኪውላሪዝም እና በሉላዊነት ጊዜ ግን ነገሮች ተቀይረው እግዚአብሔርን ማምለክና ማመስገን እንደ ኋላ ቀርነት ተደርጎ ተወሰደ እንጂ። ይህ ደግሞ የቀደመው የበዓል ትርጉም ከእምነት ጋር ሳይገናኝ ለቢዝነስና ለተዝናኖት እንዲሁም ለፖለቲካ ፍጆታ እንዲውል አድርጎታል።
ኃይማኖት ከበዓል ውስጥ ሲወጣ ቢዝነስና ፖለቲካ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓሉ ትርጉም እንዲያጣ በግዳጅም እንዲከበር ያደርጋል። ለዚህም ማሳያው ባህላችን ነው የሚል ዶግማ ተጨምሮበት ቀጣይነቱን እንዲጠበቅ መደረጉ ነው። ሰው ባህላችን ነው እያለ ያከብረዋል እንጂ ምን ምን ጥቅም እንደሚሰጠው አይረዳም። ስለዚህ አሁን የበዓላት መልክ በኢትዮጵያ ፖለቲካን፣ ቢዝነስን እንጂ ኃይማኖትን አልያዘም። ባህልንም ቢሆን ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል።
በዓል ቀደም ሲል የነበረው ትርጉም በአምልኮ ውስጥ ሆኖ ራስን መግዛትን በሚያስተምርና መተሳሰብን በሚነግር ሁኔታ ነበር የሚስተናገደው። ዛሬ ግን ከዚህ የራቀ ሆኗል። አልራቀም ለማለት ደግሞ ሽፋኑ ባህል ይሆንና በዩኔስኮ ይመዘገብልን፣ ይጠበቅልን፣ አትንኩብን የሚል ጥያቄ እንዲነሳና በዚያው እንዲቀጥል ይደረጋል።
ነገር ግን በዩኔስኮም ቢመዘገብም፣ ባህል ነውም ቢባልም ፖለቲካው ገብቶበታልና የብጥብጥ መነሻ ሆኖ ሲያገለግል በጥምቀት ብቻ መመልከት ይቻላል።
የፖለቲካ አመራሮች በእውቀት፣ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ህዝብን የማስተባበሪያ ችግር ሲገጥማቸው በኃይማኖታዊ በዓላት ሳይቀር ባህልንና ትርክትን ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ በዓላት ለአንድ ቡድን ብቻ ተሰጥተው መልክ እንዲያጡ ይሆናሉ። ለምሳሌ ኦርቶዶክስ የአማራ፤ ገዳ የኦሮሞ ምናምን እየተባለ የሚከናወነው ክብረበዓል አንዱ ነው።
በዓላት ተፈጥሯዊና አገራዊ ቢሆኑም በፖለቲካው እጅ ውስጥ በመግባታቸው ማን በምን ከማን ይለያል የሚለውን ብቻ እንዲያጎሉም ሆነዋል። መንፈሳዊ ምስጢሩን ታሪካዊ መሰረቱንም ለቀዋል። ለዚህም ብዙ የዳኝነት ሥርዓቶች ቢኖሩንም ግጭቶችን በዳኝነታችን እየፈታናቸውና እያረገብናቸው ያልመጣነው ለዚህ ነው።
ታሪኮች ለብሔራችን በሚመች መልኩ ይቀረጹና የመሰባሰቢያ መድረክ እንጂ የመማማሪያ እንዳይሆኑ ተደርገዋል። ትርጉም የለሽ ስብሰባ ደግሞ ታሪክን፣ ባህልንና እምነትን ከማጥፋት ውጭ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ባህላዊ በዓል ከሥራና ከመፈሳዊው ጋር ተሰናስሎ ማህበራዊነት የሚጠናከርበት፤ ሰው የሚታረቅበት፣ የበደለ የሚክስበት ወዘተ እንዳይሆንም የተደረገው በዚህ ምክንያት ነው።
በዓላት በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ሲገቡ ህዝብን ለያውም አንድ ቡድንን ለማስደሰት የሚል መልክ አለው። አንዱን ወደፊት አምጥቶ ሌላውን የሚገፉበትና ባዕድ ነህ የሚልበት ነው። ይህ ደግሞ የሌላውን አለማየትን ፣ አለማክበርን፣ የእኔ ብቻ ማለትን፣ ኃይማኖታዊ ምስጢርን አለመረዳትንና በተግባር አለማዋልን ያመጣል።
ለዚህም ነው ዛሬ በበዓላቶቻችን መተራረቅ ሳይሆን መጨቃጨቅና መደባደብን ልምዳችን እያደረግን የሄድነው። በተለይ ኃይማኖታዊ በዓላት ሲታሰቡ ብዝሃነት መቼም ባይረሳ ይህ እንዳይሆን ማድረጉ አገር ጭምር እንዳትረጋጋ አድርጓል።
መሪዎች ማለትም የፖለቲካ ወይም የኃይማኖት መሪዎች በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነገር አድርገው አልፈዋል። ይህ ደግሞ በህዝቦች መካከል መፍለስ፣ መመለስ፣ መተካካት፣ ቤተሰብ መመስረት ወዘተ ፈጥሯል። ህዝቡ እንደ ህዝብ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙትም በአብሮነት ለመመለስ ጥሯል።
ምክንያቱም ብዝሃነት አለውና መነጣጠልና ብቻውን መሆን አይችልም። የጋራ እሴትን መስርተውም ስለነበር ያንን በማስታወስ እየተገበሩ በጥቂቱም ቢሆን መረጋጋትን አስፍነዋል። ዛሬም ቢሆን ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ እየወጣን ያለነው በእምነቱ ውስጥ ባህሉን እያየ የሚኖር ዜጋ በመኖሩ ነው።
ቻለው የሚባል ነገር ግን ለኢትዮጵያን አይስማማም። ለኢትዮጵያ መቻል ሳይሆን ፍቅር ነው እውነቱን የሚያረጋግጥላት። ስለዚህ የከፋፈሉንን የማንነት ፖለቲካና አክራሪነት ማጥፋት መቻል አለብን።
የሴኩላሪዝም አስተሳሰብም እንዲሁ ከኃይማኖት ተወስዶ የጋራ የሚደረግ፤ ከባህል ተወስዶ የጋራ የሚደረገውን ለአንድ ጎራ ሰጥቶ እኔ የበላይ ነኝ በማለት ሁኔታዎችን አወሳስቦታልና ይህንንም ማጥራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የልደት በዓል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አገራት ጭምር በአዲስ ዓመት መልኩ የሚከበር ነው። ሆኖም በዓሉ በኢትዮጵያ ሲከበር ግን የውጭውን ባህል በአንፀባረቀ መልኩ እንደሆነ ይታያል። ይህንን ጉዳይ እንዴት ይገመግሙታል፤ ምክንያቱስ ምንድነው ይላሉ?
መምህር ፋንታሁን፡– አስተሳሰባችን በዓለማዊነት የተያዘና ሴኩላሪዝምን የሚያስተጋባ በመሆኑ በመደበኛው ትምህርትና በሚዲያ እየተመራን የራሳችን ባህልንና ኃይማኖትን እንዲሁም በዓሎቻችንን እንዳናከብር ሆነናል። ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ድምቀቱና ጫጫታውን እንድንወድም አድርጎናል። ከመደነቅና ትኩረት ከመሳብ ጋርም የሚያያይዘውም አለ።
ከዚያ ከቱሪስት ጋር ሲገናኝ ደግሞ ባህሉን ረስቶ የእነርሱን ባህል ተረክቦ በእነርሱ ባህል ካልተመራን ማለት ይጀምራል። ለአብነት ዋናው ልደት ነገ ሆኖ እያለ ዛሬ ላይ ኢቭ ብሎ ከኃይማኖታዊ ትርጉሙና ከባህሉ በወጣ መልኩ ያከብራል። የጌታ ልደት በጾም በጸሎት ለማክበር እየተዘጋጀን ሳለን በዝሙትና በመዳራት በመደነስና በመጨፈር ገና ያልደረሰውን በዓል ማክበርም ይጀምራል።
ይህ ደግሞ ባህልንም ሆነ ኃይማኖትን የማጥፋት ዘመቻ እንደሆነ ያሳያል። የጌታን ልደት በዝማሬና በቅዳሴ እንዳያሳልፍ አዳሩ በዳንኪራና ከበዓሉ ጋር በማይገናኝ ሥራ እንዲሆንም መፍረጃ ነው። ስለዚህም የበዓል ትርጉም ለእርሱ ፈጣሪ የለምን፤ ህሊናን ማታለልንና ባህል ለእኔ የውጭዎች ነው የሚለውን ሀሳብ አላብሷል።
ባህልን ጠባቂዎቹ የባህል አባቶችና ወላጆች ናቸው። ሆኖም በተለይም ባህል አስቀጣይ አባቶችና ጀግኖች የምንላቸውንና የአገር በቀል እውቀቶች ባለቤትነታችንን በዘመናዊው ትምህርት ሙሉ ለሙሉ መተካታችን የውጭ አምላኪ እንድንሆን አድርጎናል። ጃንሆይ እነዚህን ጀግኖቻችንን ከሙያው እንዲወጡና በካናዳዊያን እንዲተኩ ማድረጋቸውም ሌላው የፈተናው ምንጭ ነው።
በእርግጥ እርሳቸው መልካሙን አስበው፣ የህዝቡና የሠራዊቱ እልቂት ቁጭት ውስጥ ከቷቸው ያደረጉት ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያን የእውቀት ልኬት ከውጭው በላይ ማድረግንም ያለመ ስለነበር ነው። ነገር ግን የእኛ የሆኑ መምህሮቻችን አብረው ባለመቀጠላቸው የአገራችን ነባር እውቀት ማስተላለፊያ ገመድ ተቆረጠ። ባህልን በማያውቁት ትምህርቱ ቀጠለ። በዚህም የውጭዎችን እንጂ የእኛን ባህል የሚያውቅ ትውልድ ጠፋ።
ከ20 ዓመት በኋላም ከፖሊሲ ማርቀቅ እስከ ማስፈፀም ሥራ ላይ የሚመደበውና የሚሰራው በውጭው የተማረው ባህሉን ያልተረዳውም ሆነ። የዚህን ጊዜ በዲግሪ የሚመጣ አዲሱ ድንቁርና ጫካ ገብቶ ጀግናዎቹን የሚገል፤ ዘር ቆጥሮ የራሱን ዜጋ የሚያርድና አገር የማይወድ ትውልድም ተፈጠረ። የውጭ ባህልን የሚያንፀባርቅ የልደት አከባበርም የኖረን በእነርሱ የበላይነት ስለምናምንና ለምደን፣ ተምረን ያደግነው ስለሆነ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዓላት የኃይማኖት ሳይሆን የገበያ ምሪትና የፖለቲካ መድረኮች ሲሆኑ ይታያሉ ምክንያቱ ምን ይሆን?
መምህር ፋንታሁን፡- ኃይማኖታዊ በዓላት ቀጥታ ግንኙነታቸው ከፈጣሪ ጋር ነው። ባህል የሚባልው ብቻውን አይጠራም። ምክንያቱም ባህል ኃይማኖት፣ እሴትን ነጥሎ የሚይዝ አይደለም። መንፈስ ያለበትና ለብርና ለታይታ የሚሆንና የሚደረግ አይደለም። ተረፈ ምርቱ ግን ለቱሪዝም መሳቢያ እንዲሁም ለአገር ገጽታ ግንባታ ይውላል እንጂ።
ነገር ግን ኃይማኖቱና ባህሉ ስለተተወ ቦታውን ገንዘብና ፖለቲካው ተክቶታል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መሰረቱ ለፖለቲካው የሚሰጠው ግምትና የእኔነት ስሜት ልቆ መታየቱ ነው። ምዕራብያን ከእኛ ይበልጣሉ ብሎ ማመንም ሌላው ምክንያት ነው።
የኃይማኖትና የባህል መለያየትም አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ድሮ ለባህል ድምቀትና ለኃይማኖታዊ ክብረበዓላት በነፃ በፍቅርና በአገር ወዳድነት የሚዘፈኑ ዘፈኖች ዛሬ መልካቸውን ቀይረው በትልቅ ክፍያ በሙያተኞች ደረቅ ስሜት በሞላበት መልኩ በኮንሰርት ስም ይነገድባቸዋል።
ለያውም ደጋፊው ተለያይቶ። ይህ ደግሞ ሁሉንም አገራዊ ስሜቶች አድርቆታል። ቀኑን ቆጥሮ የገበያ ማድመቂያ ስለሚሆን እንዳይቀርም የገበያ በዓል እንድናከብር ሆነናል። ስለዚህ ይህ የገበያና የፖለቲካ በዓል በማስተማር መቀየር አለበት። ተግባሩ ሲከወንም ማስተማር ከሚዲያ ጋር፣ ማስተማር የመንግሥት አስተሳሰብን የሚመራውን ህዝብ ባህልና እምነት ከማስተሳሰር ጋር፤ ማስተማር ህዝብ ባህሉንና እምነቱን እንዲጠብቅ ከማድረግ ጋር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በዓላት ሲነሱ ማህበራዊ ትስስሮች መነሳታቸው ግድ ነው። በዓላትና ማህበራዊ ግንኙነቶች ከእምነት አስተምሮ አንፃር እንዴት ይታያሉ?
መምህር ፋንታሁን፡– ይህ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው ሴኩላር ሲኮን ነው። ምክንያቱም ሴኩላር ካልተሆነ ኃይማኖት፣ ባህል ተነጣጥለው አይታዩም። እንደ እምነት አለማዊ መንፈሳዊ የሚባል ነገርም አይኖርም።
ሁሉም በመንፈስ እይታ ስለሚቃኝ በአንድ መንገድ ይጓዛል። የሚደረጉት አምልኮዎች ካልሆኑ በስተቀር በሥራ መልካምን ነገር የሚያመጡ ሁሉ የእምነት ውጤቶች ናቸው። እናም በዓላት በኃይማኖት የሚኖራቸው መልካምነት ከማህበራዊነት ተነጣጥለው አይታዩም። እምነቱ ስለሚያዝ ግዴታ የሚደረጉና የሚሆኑ ናቸው።
ሥራ ውስጥ ክፍያ ብቻ ሳይሆን እምነት አለ። ነገ በሰማይ የሚከፈልን ዋጋን መጨመርንም ይጠይቃል። ስለዚህም በክርስትና ትምህርት ሰው የሚድነው ሌላ ሰው ሲያገለግልና ምሳሌ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር መንገድ ሌሎችን ሲያመጣ ነው። ክርስቶስን መምሰልንም እንደ ዋና ሕግ ይወስዳል። እናም ማህበራዊ ሲባል የጋርዮሽ የሆነ ተግባር መከወን ሲሆን፤ አንዱ ለአንዱ የሚኖርበት ግንኙነት ነው። ለዚህም በአብነት የሚጠቀሰው የጥምቀት በዓል ነው።
መንፈሳዊ በረከት አገኛለሁ ተብሎ መንቀሳቀስ ሲጀመር መተዋወቅ፣ የተጣላ መታረቅ፣ በአንድነትና በእምነት ሥራዎችን ማከናወን፤ ቤተሰብ መመስረት የሚያስችል ተግባር ላይ መድረስ ይመጣል። ድሮ ይጣላ የነበረውም ቢሆን በኃይማኖቱ አስተምሮ ምክንያት ንዴቱን ይተውና ይተራረቃል።
ቤተሰብ ድረስ ሄደውም የማስታረቅ ሥራም የሚከናወነው በእምነት ቦታ በሚገኝ መስተጋብር ነው። ስለሆነም ለእምነት ሲባል የማይተው ቂም አይኖርም። አብሮነት ብቻ ነው የሚታየው። ይህ ደግሞ የተራጋጋ ሰላም በአገርና በህዝብ ላይ ያመጣል። ስለዚህም በዓላት የሚያምንና የማያምን ሰው ሲያደርጋቸው ፍጹም የተለያዩና ውስጣቸውም እንዲሁ አራንባና ቆቦ ነው።
ሰኩላሪዝም አስተሳሰብ ያለው ሰው ከማያምነው ምንም አይለይም። ምክንያቱም በዓሉን የሚያከብረው ከእምነቱ ወጥቶ ሲሆን፤ አንድም ለገጽታ ግንባታ አንድም ለገበያ ሲል ነው። እናም በዓላት ለእነዚህ አካላት ሰጥቶ መቀበል ይሆናሉ። በአማኝ ዘንድ ሲመጣ ደግሞ በእምነት ውስጥ ባህልን ይዞ መጓዝ ስላለበት ፍቅርን ያላብሳል።ኃይማኖትና ዘር ሳይለይም ለመንቀሳቀስ ያስችላል።
መስፈርቱ ሰው እንጂ ነጠላ መለያም አይሆንም። ክፉ እንኳን የሆነ ሰው ቢሆን ክፋቱን ከመቀነሱም በላይ አብሮነቱን ያጎለብታል። በፍቅር የተገነባ ማህበራዊነት ይኖረዋል፤ ለሌሎች ማሰብን፣ ሌሎችን ማክበርን ይለምዳል። እንዳይዘርፉኝ ብሎ የሚያደርገው ነገር አይኖርም። ለእውቅናና ለታይታ ሳይሆን ለፍቅር ሲል ራሱን አገልጋይ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዓለም ስትጠቀስ እንግዳ ተቀባይና መሰል ባህሪያት ተሰጥቷት ነው። አሁን ግን ተቃራኒ መልክ እንድታገኝ ሆናለች። ምክንያቱ ምን ይሆን?
መምህር ፋንታሁን፡- እንግዳ ተቀባይ ነበርን። የተባሉ መለያ ባህሪዎችም ለዘመናት ነበሩ። ለአብነትም በታሪክ ከንጉሥ አርምሃ ብንጀምር ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሀመድ ቤተሰቦችን ተቀብለው ያስተናገዱ ናቸው። ሰዎቹ በብዙ መልኩ የወቅቱን የኢትዮጵያ እምነትም ሆነ ባህል ከዚያ አለፍ ሲል ዜግነት የላቸውም።
ከዚህም ልቆ በአገራቸው ሚዛን ወንጀለኞችና ሊያጠፏቸው የሚፈልጉ ናቸው። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ሰውነት ይቀድማል በሚል ነበር ሲያጎርሷቸውና ሲንከባከቧቸው የቆዩት።
የምታመልኩትን መርጣችሁ አምልኩ በሚልም ነው የሚያመልኩትን ቦታ ጭምር የሰጧቸው። ስለዚህም የቀደምት አባቶችና ነገሥታቶቻችን እምነት በራሳቸው እንዲሆን ፈቅደው፣ ቦታ ሰጥተው፣ ማንም ሰው ሊነካችሁ አይገባም ብለው ፍትህ ሰጥተው የሚኖሩ ናቸው። ይህንን ሁሉ ተሰጥቶ የሚኖርበትም አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነው። ስለሆነም እንግዳ ተቀባይነታችን በተግባር ጭምር የተደገፈ መሆኑ ከዚህ የተነሳ የሚታይ ነው።
አሁን ግን ጥቁሮቹ፣ ነጮቹ ፣ የዚህ ብሔር እያልን ሰው አራጅ ሆነናል። ከዚያ ባስ የሚለው ደግሞ በብሔር አሰልጥነን በአይሱዙ እየጫንን፤ በፖሊስ እያጀብን አገር እንዲያተራምስ እያደረግን እንገኛለን። ስለዚህም እንግዳ መቀበል የሚለው ትርጉሙን እንዲያጣ ሆኗል። ለምን ከተባለ መሰረታዊ መነሻው በእምነት የማይደረጉ ነገሮች መብዛታቸው ነው።
ቀደም ሲል የነበሩ አባቶች ሁሉን ነገር እምነቱ ዋጋ እንደሚያስገኛቸው አምነው የሚያደርጉት ነበር። ከሰው የሚጠብቁት ክፍያም የለም። ንግሥናቸው፣ ማህበራዊ ህይወታቸው፣ የፍትህ አሰጣጣቸውም እምነታዊ ነው። ሰውነት ለእነርሱ ትልቅ ቦታ አለው። ትርጓሜውም በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ፤ ሁላችንም አዳማዊያን ነን ብለው ነው የሚያምኑት።
በእግዚአብሔር ሕግ ስለምገዛም የማባርረው የምነጥቀው ሰው የለምም ባይ ናቸው። እንደ ህዝብ ሲታሰብ አሁንም እምነት አለበት። ክርስቶስ ሲመጣ ሥራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ ስታረዝ አላለበሳችሁኝም እንዳይባሉና አላውቃችሁም እንዳይላቸው ሕጉን ይፈጽማሉ። ስለዚህም ህዝብ እንግዳን መቀበልን እንደ ቱሪዝም፣ እንደ ገበያ አማራጭ ወይም ሰጪ ተቀባይ አይነት መልክ ሳሆን በእምነት የሚደረግ አድርጎ ሲተገብረው ቆይቷል።
ለእምነት ሲባል እንግዳ መቀበልን የመሰሉ ተግባራት ኢትዮጵያን በመልካም ስም እንድትጠቀስ አድርጓታል። ከዚያ በኋላ ግን ዩኒቨርሲቲ ከፍተን የማይሆን ትምህርት ሰጥተን ትውልድ በመሥራት ያንን መንፈስ ስላጠፋነው ዛሬ ስሙ እንዲቀየር ሆኗል። ዋናው ሰበካ ውድድር፣ መሻማት፣ የእኔ ብቻ ማለት ስለሆነም ሰው ስናይ ይሻማናል፤ ተፈጥሮን ይጠቀልለዋል፤ ያጣብብብናል ወዘተ የሚል እይታ ውስጥ እንድንገባና በጥላቻ እንድንመረዝ በር ከፍቷል።
ኢትዮጵያዊ አስተምሮ ሲጠፋም ነው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት አብሮ ያከተመው። በመሆኑም የትምህርት ብልሽት ማህበራዊ፣ ሥነ መንግሥታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ብልሽቶችን ያመጣልና መልካም መለያችንን እንድንነጠቅ ሆነናል።
አዲስ ዘመን፡- 98 በመቶ አማኝ በሆነባት አገር ሰምተን ዓይተን የማናውቀው ተግባር እያየን ነው። የምንሰማውም ብዙ ነው። እውነት አማኝ አለባት ማለት እንችል ይሆን ? ለምን?
መምህር ፋንታሁን፡- አይቻልም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሲባል መሬቱና የአቀማመጥ ሁኔታው ብቻ አይደለም። ሰውን መጀመሪያ ማንሳት ይገባል። ስለዚህም ይህ ሰው ምን ያምናል፤ እንዴት ያምናል የሚለውን ማየት ይገባል። ስለዚህም 98 የሚባለው ከምን እንደመነጨ አይታወቅም።
ምክንያቱም እምነት ማለት አምላክ ፈጣሪ ነው፤ አዳኝ ነው፤ ጠባቂ ነው፤ ፈራጅ ነው ። እንዲህ ኑር ተብያለሁ በዚህ ባልሄድ ደግሞ ፍርድ ይጠብቀኛል ማለት ነው። ከእምነት ሻገር ብሎ ደግሞ በውስጡ ሥራን ይይዛል። ይህም መታመን ነው። ለሕግና ሥርዓቱ መገዛትም ነው። አሁን ያለው ትውልድ አማኝ ነው ለማለት የማያስችለው በርካታ ምክንያቶች አሉት።
አማኝ ቢሆኑ ኖሮ ንጉሥ አይገሉም፤ ጳጳሳትን በአደባባይ አይሰቅሉም፤ በአቢዮት ስም ትልልቅ የአገር ባለውለታዎችን አይፈጅም። ከምንም በላይ ዘር አይቆጠርም ነበር። ጫካ ገብቶ ብሔርን እየነጠለም ነፃ አወጣለሁ ብሎ አይገልም። ሰው ስለተጠመቀም ብቻ አማኝ አይሆንም። ለዚህም ነው በሆነ አካል ግፊት ስለተጠመቀ አምኖ እንዲከተለው በሥራውም እንዲተገብረው አልሆነም።
ምክንያቱም ሰው ለመግደል መሰለፍ፣ በሲኖ ትራክ ሰው መጨፍለቅ፣ በአንድ መቃብር ውስጥ ብዙዎችን አርዶ መቅበርና መሰል ተግባራትን መሥራት 98 በመቶ አማኝ ነን ማለት ተቃራኒ ናቸው። እንደውም እምነታቸው እነ አልቃይዳን መከተል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር ሰውነት የሚለው አስተሳሰብ አለ ያስብለናል። የጥላቻችንስ መንስኤው ምንድነው ይላሉ?
መምህር ፋንታሁን፡- ዘመናዊ ድንቁርና ነው። ይህ ማለት ደግሞ ዘመናዊነትን እናመጣለን ብለን ትምህርትን ለእኛ ከማይተኙ ተዋስን። ጠላቶቻችን ሰማይ ላይ ያወጡትን አውሮፕላን እንድናወጣና እንድንሰራው የሚያደርጉን መስሎን ተቀበልናቸው። ነገር ግን እነርሱ ከዚያ ይልቅ እነርሱን እንድናመልክ አደረጉን እንጂ የፈለግነውን አልሰጡንም።
ስለዚህ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ የሚለውን እንድተው ሠሩብን። ኢትዮጵያዊነትን የሠራውንም ኃይማኖትን አስለቀቁን። ከዚያ ልቀውም ለራሳችን እንጂ ለሰው እንዳናስብ አደረጉን። አንተ ትበልጣለህ፣ ዘርህ መልካምና ከሁሉ የሚልቅ ነው፤ አታካፍል ብለው ሠሩን። የበላይ አድርገን ስለምናስባቸውም ተከተልናቸው። ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ የደረስንበትን የጠለሸ ፍሬ እንድንሰበስብ አደረጉን።
ትምህርቱ ሰውን በተለያየ መንገድ ለመመደብም የሚያስችል ነበር። በዚህም አናሳ ብሄር፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ አድራጊና አግላይ አንገዋላይም በመሆኑ ጥላቻ ነግሶ መዋደድ ቦታ እንዳያገኝ ሆነ።
እናም አስተምሮና ፖለቲካ እንጂ ሰው የማይካድራውን፣ የሻሸመኔውን እንዲሁም የቤኒሻንጉሉንና የትጋራዩን ወዘተ አልፈፀመውም። በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሆነን እንጂ በአዕምሮ ድርቡሻዊዊያን ሆነንም ተሠርተናል። ዝንጀሮ እንጂ ሰው ነን ብለው የማይቀበሉ ፍጡራንንም መስለናል።
በፖለቲካው የደረቀ ሰውነትና ባህል እንዲሁም እምነት ውጤቱ ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። ግን ይህ ሁሉ ቤተክርስቲያንና መስኪድ እያለ ሰው እንዴት ይህንን ያደርጋል ተብሎ ሲወቀስ ይሰማል። ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ሳለ አንዱ በአንዱ ላይ ጣቱን ይቀስራል።
ቤተ እምነትንም ሊከስ ይፈልጋል። እንደ መንግሥት ቤተ እምነት እየተጨቆነ ይገኛል። ጣልቃ አይገባም ለይስሙላ ይዞ የፈለገውን ይሾማል ይሽራልም። ከዚያም አለፍ ሲል በቤተ እምነት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ውሳኔ ያሳልፋል። በዚህም ቤተ እምነቶች የማይታገሉት አይነት ሆኖባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኃይማኖት አገር ይሠራል፤ መንግሥትን አርሞም ትውልድን ይቀርፃል። በዚያው ልክ ካልተሰራበት አገር ይገላል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን ኃይማኖት የቱ ላይ ይቀመጣል ? አገርንስ እያተረፈ ነው ብለው ያምናሉ?
መምህር ፋንታሁን፡- አላምንም። ምክንያቱም ምንም ዕድል አልተሰጠውም። የአመራሮችና የፖለቲካ ኃይል እንጂ የቤተ እምነቶች ወይም የኃይማኖት መሪዎች ድምጽ አይሰማም። በብዙ መንገድ መንገዱ ተዘግቶበት ለምን ይህን አላደረክም ተብሎ ሊወቀስ አይገባውም። የማምለኪያ ቦታ ሳይቀር የሚወሰንለትና የሚቀማው በመንግሥት አመራሮች ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የኖረና የቀደመ ሀብቱ ጭምር ይነጠቃል። በዓላቱንም እንዳታከብር እየተባለ ነው።
በእርግጥ የኃይማኖት አስተምሮዎች የተለያየ ባህሪያት አሉት። እንደ ኦርቶዶክስ ይህ ሁኔታ እንዴት ይታያል የሚለውን ካነሳን ከታሪክ መነሳት ግድ ይለናል። ይህም ቢሆን ተወስኖ የኢትዮጵያን ብቻ ማየት ያስፈልጋል። ምክንያቱም እንደ ግብጽና ሮማን የኦርቶዶክስ አማኞች ዓለም ሁሉ ለክርስትና ጠላት በመሆኑ ተደብቀው ሰውን ሥልጣን ለማሲያዝ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ነው ያስተማሩትም።
በዚህም በርካታ ፈተና አግኝቷቸዋል። ግን የሮማን ግዛት መሙላት ቻሉ። መደበቅ ቀረናም እስከ ንግሥና ድረስም መድረስ ተቻለ። ይህ ደግሞ በኃይማኖት ቀብቶ ማንገሥ እንዲጀመር አደረገ።
ሕገ መንግሥቱም የእግዚአብሔርን ቃል ያከበረ አደረጉት። ስለዚህም ኃይማኖት አገርን ወደማዳንና ህዝብን በሥነ ምግባር ወደማሳደግ ተገባ። ይህ ማለትም ንጉሡ በሰይፍ ዳር ድንበር ሲጠብቅ የኃይማኖት አባቶች ደግሞ ነብስ ይጠብቃሉ። በኢትዮጵያ ግን ከዚህ የተለየ አነሳስ አለው።
ከላይ ወደ ታችም ነው የተነሳው። ነገሥታቱ ይጠመቃሉ ከዚያ ህዝቡን የእኔ ተከታይ ሁን ብለው ያዛሉ። በዚህም ተዋረዳዊ መዋቅርን የመዋጋት ባህል እኛ ውስጥ የለም። ተው እረፍ የሚል ልምድም የለንም። ከዚያ ይልቅ በየጊዜው የሚዘራብንን ተቀብለን መፈፀም ነው ሥራችን።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ቤተ መንግሥትንና ቤተ ክህነትን እናምናለን። በዚህም አድርጉ የተባለውን ማድረግና ሁለቱም ለእኛ በተለያየ መልኩ እረኞቻችን እንደሆኑ እናምናለን። ሆኖም በእስከዛሬው እምነት የመገኘቱ ሁኔታ አክትሟል። አንዱ በአንዱ ጣልቃ አይገባም ተብሎ ተለያየ።
ይህ ባልከፋ ነበር። ጣልቃ መግባቱ ለኃይማኖቱ አይሠራም፤ ለቤተመንግሥቱ ግን ይሠራል። ስለሆነም መንግሥት ለሥልጣኑ በሚመቸው መልኩ እንደፈለገ ኃይማኖቱን ይጫነዋል።
የፖለቲካው ዘር ቆጠራም በኃይማኖቱም ተደግሞ እንዲታይና የእርስ በእርስ መተማመንም እንዳይኖር የሆነው ጣልቃ አይገባም ተብሎ መገባቱ ነው። የማትገባዋ ቤተክርስቲያን መብት እንዳይኖራት ብቻ ሳይሆን ሕግና ፍትህ እንዳትሰጥ ካደረጋት በኋላ እርሱ ግን ይገባል።
ለዚህም ማሳያው ልጆቼ ምኞታቸው፣ አሠራራቸው፣ ባህላቸው፣ አለባበሳቸው፣ አመራራቸው ሁሉ ክርስቲያን እንዲሆኑ ፈልጌ ከቤት አስተምራቸዋለሁ። መንግሥት ግን ትምህርት ቤት ከፍቶ ኃይማኖት እንዳይነገር ከማድረጉም በላይ ባህላቸውን ከልክሎ አዕምሯቸውን አጥቦ ሴኩላር አደረጋቸው። በምዕራብያኑ አስተሳሰብ አድገው በፖለቲካው ተበላሽተው ማንነታቸውን እንዲረሱም ሞረዳቸው።
በሴኩላሩ እውቀት መጥቶ የኃይማኖት አስተምሮው ሳይነካ እንደ ሰው የምንስማማባቸውን ባህሪያት ወስዶ ሲያጎለብት፤ በተሰጠኝ ቦታ ላይ እንዳስተምር ዕድልና ሰዓት ሰጥቶኝ፤ በጀት መድቦ ማስተማር ስችል ነው ጣልቃ አልተገባም የሚባለው።
እናም ባህላችን ወደ ላይ መሥራት ስላልነበረ መንግሥትን መምራትና ማስተካከል ኃይማኖቱ ተስኖታል። ነገር ግን ጫናው በፖለቲካ እያረፈበት መሆኑን ሲረዳና አገርና ህዝብን ማዳን እንዳለበት ሲያውቅ ብዙ የማይተባበራቸው ነገሮች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ በርከት ያሉ ኃይማኖታዊ በዓላት ይከበራሉ። ሆኖም ወቅታዊ ሁኔታው ብዙ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። አንድኛው ጥላቻን ከማጥፋት አንፃር ያለው ሲሆን፤ ሁለተኛው የኮሮና ጉዳይ ነው። ስለዚህ እነዚህ በዓላት እንዴት ሊከበሩ ይገባል ይላሉ?
መምህር ፋንታሁን፡– በዓልን ለጫጫታ፣ በዓልን ለቱሪዝም ብቻ፣ በዓልን ለመዝናኛ ካደረግነው መቼም ቢሆን ለውጥ አይመጣም። በዓሉ እስከ እነትርጉም መከበር ከቻለ ብዙ መንፈስን የሚያረጋጉ ነገሮችን እናገኛለን። መጠላላትም ሆነ ኮሮና የሚባለው ነገር ጠፍቶ ለሰው መኖር ይታሰባል።
የፈጠረን አምላክ ሰው የሆነው ወደቀደመ ክብራችን ሊመለስነው ብለን ካመንንና በዓላትንም በዚህ መንፈስ ካከበርናቸው ፍቅር ፈጥኖ ቦታውን ይይዛል። ምክንያቱም እርሱን ሰው ያደረገው ፍቅር ስለሆነ። የፍቅር በዓል የሚያከብር ሰው ጥላቻን ይፀየፋል፤ ንስሃ ይገባል፤ የበደለውን ብቻ ሳይሆን የበደሉትን ይቅር ይላል። ይህ ደግሞ የቀደመ ክብርን ይመልሳል።
አሁን ባለው ሁኔታ ጎረቤት እየተገለማመጠ ማክበሩ አይቀርም። ሆኖም ዘለቄታዊ የአገር ማዳን ተግባር ግን በፍጹም አይመጣም። ስለዚህ በዓሉን ስናከብር ዋጋ እምናገኘው የሚከበርበትን ምክንያት በሚመጥን ልክ ራሳችንን መርምረን ንስሀ ገብተን ስናከብረው ነው። በሽታውን በተመለከተ ደግሞ በሽታው የሚተላለፍና ሰውን የሚጎዳ ስለሆነ ራስን መጠበቅ፤ በፍቅር ስንኖር ለሌላውም ማሰብ ይገባናልና አድርጉ የተባለውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ያነሳናቸው ጉዳዮች አገርን ፈተና ውስጥ የከተቱና ለኃይማኖቱም ቢሆን ከባድ ችግር የፈጠሩ ናቸው። ዛሬን ተሻግረን ነገን በተሻለ መልኩ እንድንቀላቀለው ምን እናድርግ?
መምህር ፋንታሁን፡– እንደ ክርስትና አገራችን ላይ የመጡት መገዳደሎች የሰዎቹ ክፋት አይደለም። የክፋት ምንጫቸው በማያውቁት ትምህርት አዕምሯቸው ስለታጠበ ነው። ይህንን ያደረገው ደግሞ የተሳሳተው የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ነው።
ለዚህም ስህተት የሰውን ትርጉም ከምዕራባውያን አስተሳሰብና ፍልስፍና ቀድተን ስላደረግነው ነው። ስለዚህ ወደ ኢትዮጵያዊ ኃይማኖታዊና አገር በቀልና ባህላዊ እውቀታችን መመለስ አለበት።
ለመንግሥትም ቢሆን ምክረ ሀሳቦችን መስጠት ይኖርብናል። መንግሥት ሲባል የሰዎች ስብስብ ነው። እናም ያለውን ወቅታዊ ችግር በመመካከርና ችግሮችን በመነጋገር ህዝብንና አገርን መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነውና ሁሉም እዚህ ላይ መረባረብ ይጠበቅበታል።
ወጣቱ የተሳሳተውን እውነት አድርጎ እንዳይቀጥልበትም የኃይማኖት አባቶች፤ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራኑ መምከርና ወደ ትክክለኛው መስመር መውሰድም አለባቸው። ገለልተኛና ሴኩላር ማለት እጅግ የተለያዩ መሆናቸውንም ማስረዳት ተገቢ ነው። ባዕድ ናፋቂነትን መቀነስ፣ አገር በቀል እውቀቶችን ወደ አገልግሎት ማምጣት፣ ጭፍን ገልባጭነትን መዋጋት፣ ሉላዊነትንም አጣርተን መጠቀም፣ ያለንን መመርመርና ጥቅም ላይ ማዋልም ይገባል። የተለያዩ ስምምነቶች ሲደረጉ ከባህል፣ ከትውፊቱና ኃይማኖት ጋር ይጋጫል ወይ የሚለውን የሚያይ ተቋም ቢመሰረት የተሻለ አማራጭ እናገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
መምህር ፋንታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013