ራስወርቅ ሙሉጌታ
ህፃናት በእናት ጉያ በቤተሰብ ፍቅርና እንክብካቤ ስር ሆነው ሲያድጉ በጤንነታቸው፣ በአስተሳሰብና ቅልጥፍናቸው፣ በፈጠራ ክህሎታቸው ብሎም አካላዊና አዕምሮአዊ እድገታቸው ሳይዛባ አምራች ዜጋ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። በተቃራኒው በተለያዩ ምክንያቶች የልጅነት ግዜያቸውን ከወላጆቻቸው ጋር ለማሳለፍ እድሉን ሳያገኙ ሲቀሩ ደሞ ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸው አይቀርም።
እንዲህ አይነቱ ችግር ደግሞ ይህቺን አለም ከተቀላቀሉ ገና ቀናትን ብቻ ባሳለፉ ጨቅላ ህጻናት ላይ ሲከሰት ነገሩን ሁሉ የተወሳሰበና ድርብርብ ችግር ያደርገዋል። ምንም እንኳን ህጻናቱ በወቅቱ የማይረዱት ቢሆንም ውድ ከሆነው የእናት ትንፋሽ እስከህይወታቸው መጨረሻ ጤንነታቸውን የሚጠብቅላቸውን የእናት ጡት ማጣቱ የራሱ ትልቅ ጠባሳ አለው።
ይህም ሆኖ ወላጅ ያጡ ህፃናት እንደማንኛውም ወላጅ ያላቸው ህፃናት ሁሉም ነገር ባይሟላላቸውም በቂ የሆነ ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው መልካም ዕድል እንዲፈጠርላቸው እንዲሁም ራሳቸውን ችለው ውጤታማ የማህበረሰብ አካል እንዲሆኑ ከግለሰብ እስከ ተቋም የሚሰሩ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች አሉ።
ለዛሬም በደብረማርቆስ ከተማ የህክምና ባለሙያዎች የችግሩ ቅድሚያ ተመልካች በመሆናቸው ለበርካታ ህጻናት ቤተሰብ ያስገኙና በተቋም ደረጃ እንደ ቤተሰብ የሚሆን ተቋም በመመስረት ህጻናትን በመንከባከብ ላይ የሚገኙትን ወጣቶች ስራዎች ልናስነብባችሁ ወደድን።
«እናት ደብረ ማርቆስ የተጋላጭ ህፃናት መርጃ ማህበር» ይባላል። ማህበሩ በጥቂት የህጻናት ህመም በሚያማቸው፤ ችግራቸው በሚያስጨንቃቸው፤ የህክምና ባለሙያዎች የተጀመረ ሲሆን ከአመታት ጉዞ በኋላ በአሁኑ ወቅት በህጋዊ ድርጅትነት ተመዝግቦ በርካቶችን እየታደገ ይገኛል።
በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ የሆኑትና የእናት ደብረ ማርቆስ ህፃናት መርጃ ማህበር የፕሮጀክት ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ በትረማርያም ዘለቀን ስለ ማህበሩ አመሰራረትና ጉዞ ጠይቀናቸው እንደሚከተለው አጫውተውናል።
ከዚህ ቀደም በደብረማርቆስ ከተማ ለረጅም ግዜ ህፃናት በተለያዩ ቦታዎች ወድቀው ሲገኙ ፖሊስ አልያም ያገኛቸው ግለሰብ ወደ ደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጨቅላ ህፃናት ክፍል (የህፃናት ሙቀት ክፍል) ያመጣቸውና እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። በአብዛኛው ተጥለው ይገኙ የነበሩት ህጻናት ደግሞ ከተወለዱ ሰአታት የሆናቸውና በጣም ከረዘመ የሳምንት እድሜ ብቻ ያላቸው ነበሩ።
እነዚህ ህጻናት ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የሚገኙት ደግሞ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በጫካ በቦይ ውስጥና መሰል ህብረተሰቡ ቶሎ ሊደርስባቸው በማይችል ቦታዎች ነበር። እናም ወደ ሆስፒታል በሚመጡበት ወቅት አንዱ ተግዳሮት የነበረው ለልጆቹ የወደፊት ህይወት ማሰብ ሳይሆን ከነበሩበት የሞት አፋፍ ጤነኛ አድርጎ በህይወት እንዲሰነብቱ ማድረጉ ነበር ።
አቶ በትረማርያም በአንድ ወቅት በዚህ አይነት የገጠማቸውንና የሚያስደስታቸውን ነገር እንዲህ ያስታውሱታል «አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ አንድ ውሃ ዳር የወደቀ ጨቅላ ህጻን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶች ድምጹን በመስማታቸው ጠቁመው እንዲነሳና ወደ ሆስፒታሉ እንዲመጣ ያደርጋሉ። በወቅቱ ህጻኑ ህይወቱ ልታልፍ ምንም አልቀረውም ነበር።
ሌላው ቀርቶ ሙቀቱ ቴርሞ ሜትሩ ሊለካው ከሚችለው በታች በመሆኑ ጥሩ ነገር ላይከሰት ይችላል ብለን በጣም አዝነን ነበር። ነገር ግን እንደ አንድ የህክምና ባለሙያ ሁላችንም ተስፋ ባለመቁረጥ አስፈላጊውን ትብብር ስናደርግለት ቆይተን ህጻኑ ነፍስ እየዘራ መጣ። ከቀናትም በኋላ በማይታመን ሁኔታ ሙሉ ጤናው ተመልሶለት እንደማንኛውም ህፃን ለመሆን በቃ።
ዛሬ ይህ ህጻን ከአንድ አመት በላይ ሆኖት በሙሉ ጤነኝነት እንደማንኛውም ልጅ ድክ ድክ እያለ መጫወት ጀምሯል። ይህ አጋጣሚ በዛ ሆስፒታል ላለን ሰዎች ብዙ አስተምሮ ብዙ ተስፋ እንድንሰንቅ አስችሎን ያለፈ ነው።» በማለት ይናገራሉ።
ይህም ሆኖ በአካባቢው ሌላ የህጻናት ማቆያ ያልነበረ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ነፍስ እንዲዘሩ የተደረጉት ልጆች አሳዳጊ ተገኝቶ እስኪሄዱ ድረስ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ህፃናቱን የመንከባከብና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን የማሟላት ሰብዓዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለሙያዎቹ ከከተማው ሴቶችና ህፃናት መስሪያ ቤት ጋር በመሆንም አሳዳጊ አፈላልገው ቀሪ ህይወታቸውን በተስተካከለ ሁኔታ በቤተሰብ ውስጥ እንዲያሳልፉ ሲያደርጉም ነበር። ይህም ሆኖ ለህጻናቱ አሳዳጊ የማግኘቱ ነገር እንዲህ ቀላል አልነበረም፣ የሚወስዱና እንደ ቤተሰብ የሚያሳድጉ ቢገኙ እንኳን በአንድ ወገን እድሜያቸው ከፍ እስኪል መጠበቅ የሚፈልጉ ሲሆን በሌላ በኩል የጾታ ምርጫ የሚያቀርቡትም በርካቶች ናቸው።
እነዚህ ሁኔታዎች የጨቅላ ህጻናቱን የሆስፒታል ቆይታ የሚያራዝሙ ጉዳዮች ነበሩ። አንዳንድ ግዜም ከአመት በላይ ቆይተው መራመድ እስኪጀምሩ በሆስፒታሉ የሚቆዩም ነበሩ።
በዚህም ምክንያት ታዲያ አንዳንድ ግዜ የሆስፒታሉ ሠራተኞችም በዚህ ሁኔታ የመጡ ህፃናትን ራሳቸው እቤታቸው እየወሰዱ እስከማሳደግ ይደርሱም ነበር። በ2010 ዓ.ም ግን ሁለት ልጆች በሆስፒታሉ ረዘም ላለ ግዜ ቆይተው የሚቀበላቸው ጠፍቶ ስለነበር ወደ ገዳም ለመላክም የተገደዱበት አጋጣሚ ነበር።
በዚህ አይነት ለዓመታት የቆዩት የዛሬው የማህበሩ መስራች የሆስፒታሉ ሰራተኞች ችግሩ የሚቆም አለመሆኑን በመረዳትና ከፈቃደኝነት በዘለለ በኃላፊነት መሰራት እንዳለበት ሲመክሩ ቆይተው ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ። እናም ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ህፃናቱን የሚረዳ የበጎ አድራጎት ማህበር በሕግ አግባብ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም እናት ደብረ ማርቆስ የተጋላጭ ህፃናት መርጃ ማህበርን ለማቋቋም ይበቃሉ።
ማህበሩ በዚህ አይነት ከተመሰረተ በኋላ የመጀመሪያዎቹ አባላት የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኞችና በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰሩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሐኪሞች ብቻ ነበሩ። የድጋፍ አሰባሰቡንም በመጀመሪያ የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢ በመቅጠር በካሽ መንገድ ለመቀበል ስራዎች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም የመዘግየትና አንዳንዴም የመቋረጥ ነገር ስለነበር በነጻነት ለመንቀሳቀስ ሳያስችላቸው ይቀራል።
በኋላ ግን ህጋዊ ፈቃድ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በቀጥታ በፔሮል ከደሞዝ የሚከፈልበትን መንገድ ሆስፒታሉ በማመቻቸቱ ቀጥታ ከደሞዝ ማስቆረጥ በመቻሉ ወጥነት ያለው ስራ ለመስራት ይበቃሉ። ይህም ገንዘቡ በአንድ በተወሰነ ግዜ እንዲገባ ያስቻለ ነበር።
ከዚህ በኋላ የማህበሩን ዓላማ የተረዱ በርካታ ወገኖች ህፃናትን ለመርዳት ቋሚ አባል በመሆን ከ 15 ብር እስከ 500 ብር ድረስ በየወሩ ከደሞዛቸው በመቁረጥ አስተዋፅኦ ማድረግም ይጀምራሉ። በዚህ አይነት ጉዞውን የጀመረው ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ከደብረ ማርቆስ ሆስፒታል 401 አባላት፣ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከ55 በላይ አባላት፣ ከደጀን ሆስፒታል ከ45 በላይ አባላት፣ ከአዲስ አበባ 1፣ ከቡሬ ከተማ 1፣ ከእንጅባራ ከተማ 1፣ በጠቅላላው ከ504 በላይ ቋሚ አባላትን ባለፉት ሁለት አመታት ለማፍራት በቅቷል። ከእነዚህ ቋሚ አባላት በተጨማሪም ህፃናትን እንደ አስፈላጊነቱ በመርዳት በክብር አባልነት የሚያገለግሉ በርካታ የከተማው ነዋሪዎችና የውጭ ሐገር ዜጎችም አካቶ በመጓዝ ላይ ይገኛል።
በዚህ ሁኔታ ሚያዚያ ሶስት 2011 ዓ.ም ለመጀመሪያ ግዜ ማህበሩ ራሱን ችሎ በቤት ኪራይ አራት ህጻናትን በመያዝና ሞግዚቶችን በመቅጠር ስራውን እንደአዲስ ከሆስፒታሉ ውጪ ለመጀመር ይበቃል። በወቅቱ የሚገኘው ገንዘብ የሚጠበቀውን ያህል የሚያንቀሳቅስ ባለመሆኑ ቤት የተከራዩት ከሆስፒታሉ በርቀት በከተማው ዳርቻ ስለነበር ለመቆጣጠርም ለህጻናቱም ምቹ አልነበረም።
ከሶስት ወር በኋላ ግን የደብረ ማርቆስ ከተማ ሰላም አንድነትና ፍቅር የታክሲ ማህበራት ሶስት ሺህ ብር በየወሩ ለመደጎም ስለተስማሙ ሙሉ ለሙሉ ምቹ ባይሆንም በመሀል ከተማ የተሻለ ማረፊያ ለማግኘት ይበቃሉ። በዚህ ሁሉ ሂደትም የሆስፒታሉ ሰራተኞች ከመዋጮም ባለፈ በየወቅቱ በአካል በመገኘትና አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ከቤቱ አይጠፉም ነበር።
ከዚህ በኋላ ነበር ስራቸውን ያስተዋለውና ከሁሉም በላይ የማህበሩ ቀዳሚ ችግር ለህጻናቱ በቂ ማረፊያ ቤት ማግኘት አለመቻል መሆኑን የተረዳው የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሁለት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጣቸው የፈቀደላቸው። ነገር ግን ቦታው ከከተማው ራቅ ያለ በመሆኑና ከይገባኛል ነጻ ባለመሆኑ ለመረከብ ሳይችሉ ይቀራሉ። በአሁኑ ወቅት ሌላ አዲስ ምትክ የከተማ ቦታ እየተመቻቸላቸው ሲሆን በተጓዳኝ ቦታው ተፈቅዶ ሲሰጣቸው የህንጻውን ዲዛይን በነጻ ለመስራት በከተማዋ ያሉ የምህንድስና ባለሙያዎች ቃል ገብተውላቸዋል።
እናት ደብረ ማርቆስ ህፃናት መርጃ ማህበር የሚረዳቸው በዋናነት እንደተወለዱ በተለያዩ ቦታዎች ወድቀው የሚገኙ በደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው ያሉ ቤተሰብ አልባ ጨቅላ ህፃናትን ነው። ነገር ግን ከዛ በተጨማሪ አንዳንድ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው እናቶች በተለያዩ ቦታዎች የሚተዋቸውንና ጉዳት ሊያደርሱባቸው የሚችሉ ህፃናትንም በመሰብሰብ እንክብካቤ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ እስካሁን ለአሳዳጊ ከተሰጡት ህጻናት በተጨማሪ አስራ አራት አሳዳጊ ያላገኙ ጨቅላ ህፃናትን በሁለት ፈረቃ የሚሰሩ ስድስት ሞግዚቶችን፤ አንድ ጥበቃና አንድ ፅዳት ሰራተኛ በመቅጠር ራሱ በተከራየው ቤት እየተንከባከበና እያሳደገ ይገኛል ።
የትኛውም ህጻን በማቆያ ከሚያድግ በቤተሰብ ውስጥ ቢያድግ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያገኛል። የሚሉት አቶ በትረማርያም የማህበሩ ቀዳሚ ስራ በተቻለ አቅም ህጻናቱን የሚወስድ ቤተሰብ ማገናኘት ነው ይህም ሆኖ ግን የሚወስዳቸው ካላገኙ እንደ ቤተሰብ በሚንከባከቧቸው ሞግዚቶቻቸው ስር ሆነው እንዲቆዩ እያደረገ ይገኛል። በዚህም እስከመቼ እንደሚቆዩ ስለማይታወቅ ማህበሩ የረጅም ግዜ እቅድን ይዞ በጥሩ ስነምግባርና ጤንነት ማህበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ይላሉ።
አቶ በትረማርያም በአንድ ወቅት «በዚህ ሁኔታ ልጅ ወልጄ መውለዴ ቢሰማ አባቴም እኔን ይገድለኛል እናቴም ራሷን ታጠፋለች» ብላ ወደዚህ ችግር ውስጥ የገባች ወጣት እንዳለች በማስታወስና ልጅ ወልዶ መጣል በተለያዩ አካባቢዎች እየተለመደ የመጣ ተግባር መሆኑን በማንሳትም የሚከተለውን ምክረ ሀሳብ ይለግሳሉ። ለችግሩ መፈጠር ምክንያቶች እናቶች ብቻ አይደሉም እንደ ግለሰብም እንደ ማህበረሰብም መለወጥ ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ በማለት እንደሚከተለው ይገልጻሉ።
በአብዛኛው ተጥለው የሚገኙት ህጻናት ራሳቸውን ካልቻሉ ወጣት ልጆች የሚወለዱ ናቸው። በቅድሚያ ጥንዶች በጓደኝነት ሆነው እንዲህ አይነት ነገር ቢፈጠር ከመደባበቅና ከመሸሽ ይልቅ በጋራ ያቺን ቀን ለማለፍ መተባበር አለባቸው። ቤተሰቦችም ነገሮችን ቀድሞ ለመቆጣጠር ማድረግ ያለባቸው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ነገሮች ከተፈጠሩ በኋላ ግን ልጆቻቸውንም ህጻናቱንም የሚጎዳ ነገር እንዳይፈጠር ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።
የሃይማኖት አባቶችም ችግሩ እንዳይፈጠር በስፋት የሚሰብኩትን ያህል ለወጣት ሴቶች የሰው ልጅን ያህል ፍጡር መጣል እንደማይገባ ማስተማር ይኖርባቸዋል። በተለይ ደግሞ ለወላጆች በባህል ተተብትበው ለክብራቸውና ለስማቸው በሚል የሁለት ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ተግባራት መታቀብ እንዳለባቸውና ልጆቻቸው ይህ ነገር ቢገጥማቸው የእነሱ ጥፋት ብቻ አድርጎ ከመውሰድ እንዲታቀቡ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።
አቶ በትረማርያም ጨምረው እንደተናገሩት ወጣት ሴት ልጆችም በየትኛውም አጋጣሚ ዘመኑ ያመጣቸውን መከላከያዎች መጠቀምን መልመድ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ በየአካባቢው ያሉ የትምህርትና የጤና ተቋማት ድርሻ ነው። የትኛዋም እናት ልጇን ማሳደግ የምትችልበት ሁኔታ እያለ አውጥታ እንደማትጥል ይታመናል፤ ነገር ግን ብዙ ግዜ በችኮላ የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዳይኖሩ በመጠንቀቅ በጉዲፈቻ መስጠትን ጨምሮ እያንዳንዷን አማራጭ መፈተሽ ህጻናቱንም ከችግር እናቶችንም ከጸጸት የሚታደግ ይሆናል።
ይህም ሳይቻል ቀርቶ ከህጻኑ ጋር መቆየት የማይቻልበት ሁኔታ እንኳን ቢፈጠር ቢያንስ ሰው ሊደርስበት በሚችልና ጤናውንም በማይጎዳ ህይወቱንም በማያሳጣው ቦታ ለማስቀመጥ ቢችሉ ይመረጣል። በዚህ ረገድ ይህ ችግር ገጥሟቸው አገር ለቀው በልመና ተሰማርተውና በተለያየ በከፋ ችግር ውስጥ እንኳን ሆነው ከልጆቻቸው የማይለዩትን እንደምሳሌ መውሰድና ማስተማር ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013