ዘካርያስ ዶቢ
በአዲስ አበባ ግብይቱ ጦፏል። ዋናው ዋዜማ ዛሬ ሆኖ እንጂ ሰሞኑ ጭምር ዋዜማ ዋዜማ ሲል ቆይቷል። እሁድ የሚዘጉ ሱቆች ሳይቀሩ በዚህ በአል ወቅት ተከፍተዋል። በየመኖሪያ መንደሮች፣ ገበያ አካባቢዎች፣ አብያተ ክርስቲያናት መግቢያና መውጫ አካባቢዎች፣ ወዘተ ሁሉ ገበያ ሆነዋል።
በየህንጻዎች ላይ የሚገኙ ንግድ ቤቶችም በየደጃፋቸውና ወለላቸው ላይ ሞንታርቦ ገጥመው እዚህ አለን እያሉ ናቸው፤ የድምጹ ብክለት አይጣል ነው፤ ለሽያጭ የቀረቡትን ሸቀጥና ምርት በሚቻላቸው ሁሉ እያሳዩ ግዙን ማለታቸውን ተያይዘውታል።
ለክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ። ዛሬ የገና ዋዜማ ነው፤ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሥነሥርዓት የሚከበረው እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት /የገና/ቀን በአል በኢትዮጵያውያን የክርስትና አምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል። የከተማው መድመቅ ምክንያትም ይሄው ነው።
ኢትዮጵያውያን ለገና በዓል የራሳቸው እምነት በሚፈቅደው መልኩ ዝግጀት ያደርጋሉ፤ይህ ብቻም አይደለም በምእራባውያኑ ተጽእኖ ሳቢያ ደግሞ ለሌላ ወጪም ይዳረጋሉ። ይህም የገና በአል ዝግጅታቸውን አስፍቶባቸዋል።
ስለቄጤማ፣ እጣን፣ ዳቦ ጠላ ወዘተ.ማሰቡ አለ፤ በዚህ ላይ ደግም እንደ ፈረንጅም አርጓቸዋልና የገና ዛፍ፣ መብራቶች፣ ከረሜላው፣ ኬኩ፣ ወዘተ ተጭኖባቸዋል። ስጦታ መለዋወጥ፤ አልባሳት መግዛት በስፋት የሚስተዋልበት በዓል እንደመሆኑ ገና ከየትኛውም በአል ይልቅ ይደምቅ ይመስለኛል።
የእምነቱ ተከታዮች ክፉ አለ ደግ አለ ብለው ካስቀመጡት ላይ በማውጣት በአሉን በደስታ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት እና ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ጭምር በመሆን ያከብራሉ። አርሶ አደሩም ከተሜውም በዚህ በዓል ወቅት ልዩ ዝግጅት ስለሚያደርጉ አስቀድመው ግብይት ቢሆንም፣ የዛሬዋ ዕለት ግን ለብዙዎች ወሳኝ ናት። አስቀድመው የገዙትም ቢሆኑ ያጎደሉትን የሚሞሉበት ቀን ነው።በዚህ ቀን አርፎ የሚቀመጥም አካልም ቀልብም የለም።
ይህን የህብረተሰቡን ፍላጎት በሚል አዳዲስ ገበያዎች በራሳቸው ተቋቁመዋል። ዋና ዋና ገበያዎች ይህን ፍላጎት ሊያሟሉት አይችሉም፤ ይህም አንዱ ምከንያት እየሆነ ጭምር ነው አዳዲስ ገበያዎች የሚቋቋሙት። ከዋና ዋና የገበያ መዳረሻዎች በቅርብ ርቀት ላይ ሸማች የሚመላለስባቸው መንገዶች ሁሉ ዋና የገበያ ስፍራ ይሆናሉ። በዚህም በጉ፣ ዶሮው፣ ቄጤማው፣ አልባሳቱ፣ ወዘተ በየጎዳናው ዳርቻ ይሞላል።
ህብረተሰቡ ለመገብየት የሚፈልግበት ቦታ ይለያያል። አንዳንዶች ለግብይት ርቀው ላለመሄድ ብለው ወይም ገበያው ልዩነት የለውም ብለው በአሉ ካፈራቸው የአካባቢው ገበያዎች ፈጽመው ይመለሳሉ። ብዙዎች በዚህ ገበያ በዋጋም በጥራትም ይጎዳሉ ይባላል። እውነት ነው ገዥዎች የዋጋ ጥናት ሳያደርጉ ግብይት ውስጥ ገብተው ከሆነ ሊጎዱ ይችላሉ።
አንዳንድ ሸማቾች ይሉኝታም ያጠቃቸዋል። የገበያ ላይ ይሉኝታ ምን ይሉታል።ዋጋ ሰብረው አይጠይቁም፤ጥሩ ተብለው ተለምነውም አሳምረው አይጠሩም፤ ትንሽ ቅናሽ አርገው ይጠራሉ። ነጋዴው ተግደርድሮ ሊሄዱ ሲሉ ወሰዱት ይላቸዋል። የሱፐር ማርኬት ገበያ ይመስል በባህላዊው ግብይት ላይ ዋጋ ቢቆርጡ አንዳች ክፉ ነገር ያደረጉ ነው የሚመስላቸው።
ነጋዴው ለእናቴ አልሸጠው ውሰዱት ብሎ ሲወረውርባቸው እውነት እየመሰላቸው ይገዛሉ። ጎበዝ ከመቶ በመቶ በላይ ዋጋ ይጠየቃል። በቅርቡ 120 ብር የተባልኩትን አንድ ልብስ በ50 ብር ገዝቻለሁ። ይህን ምን ይሉታል ታዲያ።
ሌሎች ደግሞ ከዋናው ገበያ ውጪ ንክች አያረጉትም፤ ቢያርም ቢመርም እዚያው ነው የሚገበዩት። ትልቁ ገበያ እስከሚደርሱ ግን እያጠያየቁ የመሄድ ልምድ አላቸው።
ስለገበያው አስቀድመውም በግ ስንት ተጠራ፣ስንት ተሸጠ፤ በሬ ስንት ተጠራ፣ ስንት ተሸጠ. ወዘተ እያሉ ይጠያይቃሉ። ያለፈውን በዓል ገበያ ዋጋ ጭምር ለዚህ በዓል ግብይታቸው እንደ ግብአት ይጠቀሙበታል።
ለግብይት ይህ አይነቱ የተለምዶ ጥናት ወሳኝ ነው።የመግዛት አቅማቸውን ያዩበታል፤ በዚህ ላይ ተመስርተው ግዥውን ይፈጽማሉ። ሌሎች ግዥ ሲፈጽሙ በቆረጣ ይመለከታሉ። ዋጋ ሲጠሩ በመቶ ፐርሰንት ጭምር ቀንሰው ነው።
ከእንደነዚህ አይነቶቹ ገዥዎች ጋር ለግብይት መውጣት በጣም ያደክማል፤ መረጃ ጠይቀው አያበቁም። ሄደው አይደክማቸውም፤ በይሉኝታ አይሸነፉም። ዋጋ ሲሰጡ አይፈሩም። ከሆነ ይሆናል ካልሆነ አይሆንም ብለው ነው ዋጋ የሚሰጡት። ጽናቱን ከሰጣችሁ ከእነዚህ ጋር ሆናችሁ ብትሸምቱ ታተርፋላችሁ።
ከግዥ ከፈጸሙ ዋጋ መጠየቅም ሊጠቀም ይችላል። አንዳንዴ ግን ገዥዎች ጥሩ መረጃ ላይሰጡ ይችላሉ። እንደነዚህ አይነቶቹ ገዥዎች በግዥ ተሞኝተሃል እንዳይባሉ ይሰጋሉ። ስንት ገዛኸው ሲባሉ ከገዙበት ዋጋ አሳንሰው ይነገራሉ፤በጥሩ ዋጋ አግኝተሃል እንዲባሉ። ሌሎች ደግሞ ከፍ አርገው ይናገራሉ፤የገዙትን ግን አያሳዩም። እነዚህም ጥሩ ግዥ ፈጽመዋል እንዲባሉ ነው። በተለይ በከብት ወይ ዶሮ ግዥዎች ዘንድ ይህ ይንጸባረቃል።
ነጋዴውም ዘንድ የተለያዩ ስሜቶች ይታያሉ። ተገቢው ጥራት ያለው ምርት አቅርቦ ተገቢውን ዋጋ የሚያቀርብ ሊኖር እንደሚችል ሁሉ ጥራት የሌለው ምርት የሚያቀርብ አለ፤እንዲያውም እየተበራከተ የመጣው እንዲህ አይነቱ ነጋዴ ነው።
ጥራት የጎደለውን ጥራት አለው ብሎ በአይንዎ ያዩትን እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ጥቂት አይደሉም፤ ግብይቱ በምላስ ብዛት የሚሆንበት ጊዜም አለ።አንዳንድ ነጋዴዎች አይለቅዎትም። ችክ ይላሉ። የሚያውቃቸው ትቷቸው ይሄዳል፤ ያላወቀ በይሉኝታም ይሁን በሌላ ይገዛቸዋል። እነዚህ ነጋዴዎች ለመሸጥ ሲሉ ሲምሉ አያፍሩም፤ አይፈሩም። ይህን ያህል ምሎ ተገዝቶ ብለው ግዥ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ የዋሆችን ያገኛሉና ።
ያለውን የተትረፈረፈውን ከሀገር ጠፍቷል፤ በመከራ ነው ያገኘነው የሚሉም ሞልተዋል። አንድ አባባል አለ፤ ቅቤ ነጋዴ ሁሌም ስለ ድርቅ ያወራል የሚባል። እንዲህ አይነቶቹ በዚህ አይነት መንገድ ካልሰሩ በቀር ያተረፉ የማይመስላቸው ናቸው። ምርቱ በየገበያው ሞልቶ እያለ ዘንድሮ ምርት የለም፤ ድርቅ ነው፤ ገበሬው ይዞታል ሊለቀው አልፈለገም እያለ በውድ ዋጋ እንዲገዙ ሊያግባባዎት የማይሞክሩት መንገድ የለም።
እዚያ ጋ ያለው ዋጋ እና የእናንተ ሰማይና ምድር ለምን ሆነ በሚል ሲጠይቁ የአካባቢ ልዩነትን እንደምክንያት ሊያነሱ ይችላሉ። የዚህ አካባቢ ምርት ነው የዚያ አካባቢ ምርት ነው ይልዎታል። በእርግጥ ምርቱ የሚመረትበት አካባቢ በዋጋ ላይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። የእነሱ ግን ይህን እንደ ከለላ መጠቀም ነው እንጂ እንደተባለው ሆኖ ላይሆን ይችላል።
እናም የገበያ ሁኔታ ብዙ ማጤንን ይጠይቃል። በዛሬው ግብይትዎም የበዓል የመጨረሻ ሰአት ግዥዎን በጥንቃቄ ያርጉ። ባለፉት ቀናት ከተደረጉ ግዥዎች ይነሱ፣ በእለቱ ያለውን ዋጋ እየተዘዋወሩ ይመልከቱ፤ቢችሉ ገበያ አዋቂ ይዘው ይወጡ።
ወጪ ላይም ይጠንቀቁ። በሀገራችን የኑሮ ውድነት እየናረ ነው። ብዙ ብር ተይዞ ተወጥቶ የሚሸመተው እንዳለፉት ዘመናት አይደለም። በአንድ ወቅት የአዘቦት ግብይት ላይ ጆሮዬ ጥልቅ ስላለው ላንሳላችሁ። ሰውየው የሆነ የሆነ ነገር ይገዛል፤ ለእዚህም አንድ መቶ ብር ለባለሱቁ ይሰጥና መልስ ይጠብቃል።
ባለሱቁ መልስ ይሰጠዋል። በሸማቹ አእምሮ ውስጥ ያ ብር ብዙ ነገር ይገዛል የሚል ነበር፤ የተሰጠው መልስ አነሰበት። ‹‹መቶ ብር በቃ ዝርዝር ሆነ ማለት ነው ››ሲል ለራሱ ተናገረ፤ ጮክ ብሎ አሰበ። ይሄ የሆነው የሁለት መቶ ብር ኖት ከመምጣቱ በፊት ነው። አሁን ግን መቶ ብር ዝርዝር ሆኗል።
ተረጋግተው ካልሸመቱ ጮክ ብሎ ማሰብ ይመጣል፤ ጮክ ብሎ ማሰቡ የኑሮ ውድነቱ ባስከተለው የዋጋ ውድነት ብቻ የሚመጣ አይደለም፤ ለበዓል በሚደረገው ከፍተኛ ወጪ እንዲሁም በተገዛው ቁስ እና ምርት ጥራት ጉድለትም ሊሆን ይችላል፤ የግብይቱ ሰአት እየረፈደ ቢሆንም፣ ተረጋግቶ መገብየት እና ከጮክ ብሎ ማሰብ መዳን ይገባል። መልካም በአል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013