አስቴር ኤልያስ
በሕንጻ ኮንስትራክሽን ተገቢውን ትምህርት በመቅሰም የሚሰራው ስራ ውጤታማ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን በዘርፉ የሚሰማራ ባለሙያ አግባብነት ያለውን ትምህርት ካላገኘ የጎንዮሽ ወደሆነውና ወደመሰል የትምህርት አይነት ዞር ማለት የግድ ይላል። ይህ ሲሆን ደግሞ ተገቢውን እና እንከን የማይኖረውን ውጤት ለማግኘት እንደሚያስቸግር የአደባባይ ምስጢር ነው።
ስለሆነም በአገር አቀፍ ደረጃ በሕንጻ ኮንስትራክሽን ዙሪያ በዲግሪም ሆነ በሁለተኛ ዲግሪ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት የታሰበ ነገር ስለመኖሩና የከተማ እድገት፣ ሽግግር፣ ደረጃ እንዲሁም ወደከተማ ስለሚደረገው ፍልሰት ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ህንጻ ግንባታ እና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ከሆኑት ዶክተር ህያው ተረፈ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ከተሞች ዘላቂ ልማትና ለመኖሪያ ምቹ ሆነው እንዲጓዙ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን መገንባት ያስፈልጋልና በዚህ ጉዳይ መንግስት ድርሻውን እንዴት እየተወጣ ነው?
ዶክተር ህያው፡– ጥሩ የመኖሪያ አካባቢ እንዲፈጠር ትልቁ ነገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ብቻ ሳይሆን ከጀርባም ያሉ ወሳኝ ነገሮች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። እቅዱ ራሱ ሲታቀድ ጥሩ የማቀድ አቅም ሊኖር ያስፈልጋል። እቅዱን ወደተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ የዲዛይን ስራዎችም አሉ። በመሆኑም የተሻለ የሚባል የዲዛይን ስራ ወሳኝ ነው።
ለምሳሌ ከከተማ ፕላን ወደከተማ ዲዛይን ወርዶ፤ ከከተማ ዲዛይን ወደህንጻ ዲዛይን እንዲሁም ወደሰፈር ዲዛይን ወርዶ ነው ቀጥሎ ወደኮንስትራክሽን ዲዛይን የሚሄደው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአግባቡ ከተስተካከሉ ወደኮንስትራክሽን ሲሄድ ማቴሪያል ከየት እናመጣለን? ቴክኖሎጂ አለን ወይ? የሰው ኃይላችን እንዴት ነው? ለኮንስትራክሽን የሚሆን ፋይናንስ አለን ወይ? ማስተዳደርስ እንችላለን? የሚሉ ነገሮችን ወደሚጠይቅ ነገር ይወርዳል።
እነዚህ ነገሮች ሁሉ ቢስተካከሉና የኮንስትራክሽኑ ደረጃ ላይ ብንደርስ ችግሩ ውስን ይሆናል። አሁን ችግራችን በፕላኑም፣ በዲዛይኑም፣ በአርክቴክቸሩም፣ በህንጻ ዲዛይኑም ክፍተት መኖሩ ነው። እንዲሁም በኮንስትራክሽኑም በኩል ችግር አለ። ችግሩ ያለው ሁሉም ቦታ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች አንድ ላይ አስተሳስሮ እንዴት መስተካከል እንዳለበት እየተጠና ቀደም ሲል የጠቀስኩልሽ ችግር ደግሞ ጎን ለጎን እየተጠና ሲሄድ በየጊዜው ችግሩ እየቀለለ ይመጣል።
የዛሬ ሃያ እና ሰላሳ ዓመት የነበረው ሁኔታና አሁን ያለው ሁኔታ አንድ አይደለም። ፕላን እንዲሁም ዲዛይን የመስራት አቅም ጨምሯል። በጎን ደግሞ ኢኮኖሚውም እየተሻሻለ ነው። እንዲሁም ደግሞ ኮንስትራክሽንም እየተሻሻለ ነው፤ ግን የሚጎድለው ነገር ቢኖር ኮንትራክተሮች ራሳቸውን ማብቃት የሚያስችላቸው የትምህርት መስክ አለመኖሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ራሳቸውን ብቁ ሊያደርጉ የሚችሉበት የትምህርት መስክ እንዴት አይኖርም? ላለመኖሩ ችግር የሆነው ምንድን ነው?
ዶክተር ህያው፡– ቀደም ሲል ይማሩ የነበሩት በዚህ በእኛ ኮሌጅ ነበር። በመሃል ግን የትምህርት መስኩ ተዘጋ። እንዲህም ስል በተለይ የህንጻ ኮንትራክተሮችን የሚመለከት ነው። እነዚህ ኮንትራክተሮች የትምህርት መስክ የላቸውም። በፊት ይማሩ የነበረው በቀድሞው አጠራሩ ህንጻ ኮሌጅ ነበር።
አሁን አሁን ያሉ ኮንትራክተሮች ያጠናችሁት ትምህርት ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ ሲቪል አሊያ አርክቴክት ነን ሲሉ ይመልሳሉ። የራሳቸው የሆነ የትምህርት መስክ የላቸውም።
ቀደም ሲል በዚሁ ኮሌጅ ተምረው በርካታ ስመጥር የሆኑ ኮንትራክተሮች ነበሩ። የትምህርት መስኩ በዲግሪ ደረጃ ይሰጥ ከነበረበት ወደ ዲፕሎማ ወረደ፤ ቀጥሎም ዲፕሎማ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ አይሰጥም የሚል ነገር ሲመጣ ከነጭርሱ እንዲቋረጥ ተደረገ፤ አልተተካም። በዚህ ምክንያት ኮንትራክተር የምንሆነው የዲዛይን ሰዎች ነን።
የዲዛይን ሰው ደግሞ እንደአጠቃላይ እውቀት ነው ኮንስትራክሽኑን የሚሰራው እንጂ መደበኛ ሙያው ግን ዲዛይን ነው። ሲቪል ኢንጂነሮች አሉ፤ እነሱም ቢሆኑ የዲዛይን ሰዎች ናቸው። የተማሩት ዲዛይን ነው፤ ነገር ግን ኮንስትራክሽንን እንደ ተጨማሪ ትምህርት የተማሩ በመሆናቸው ሊሰሩት ይችላሉ። ይሁንና ኮንትራክተርነት እንደዋና ትምህርት ስለማይሰጥ መልሶ ማምጣት ያስፈልጋል።
ይህ የትምህርት መስክ የኮንስትራክሽን ግንባታን የሚያካትት ሲሆን፣ በጠቅላላ ኮንስትራክሽንን የሚመለከት እና ለዚህ ብቻ ተብሎ የሚያሰለጥን የትምህርት መስክ ነው እንጂ ዲዛይን ተምሮ ኮንስትራክሽን መስራት ማለት አልነበረም። እያንዳንዱ ሙያ መሰራት ያለበት በራሱ በባለሙያው ነውና ይህንን የትምህርት መስክ መልሶ ማስጀመር የግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- የእነዚህ ሙያተኞች አለመኖር በኮንስትራክሽኑ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ህያው፡– ለምሳሌ እኔ የተማርኩት ዲዛይን ነው፤ የኮንስትራክሽን ሰው ሆኜ ዲዛይን ብሰራ የምሰራው ዲዛይን የአማተር ዲዛይን ነው የሚሆነው። ከዚህም የተነሳ የተዋጣለት ስራ መስራት አያስችልም። ኮንስትራክሽኑን ኮንትራክተሩ በተማረውና በሰለጠነበት መስክ ሊሰራ ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንድ ሰው ብቻ ሁሉንም ይስራ የሚባል ከሆነ ጉዳዩ እንከን ያጋጥመዋል።
ለዲዛይን የሰለጠነ ሰው ትምህርቱ በዲዛይን ላይ ብቁ ስለሚያደርገው ዲዛይን ላይ የሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ አግባብነት ያላቸው ይሆናሉ። ልክ ዲዛይን የሰለጠነ ሰው የራሱን ዘርፍ ብቁ አድርጎ እንደሚሰራ ሁሉ የሕንጻ ኮንስትራክሽንም እንዲሁ የራሱን ዘርፍ በአግባቡ ይሰራ ዘንድ በዘርፉ በቂ የሆነ ትምህርት ሊያገኝ ይገባል ነው። በዚህም ስራው የተሻለ ይሆናል።
የሕንጻ ኮንስትራክሽንን በተመለከተ የሚሰጥ ትምህርት ከሌለ ስራው በሌላ ሙያተኛ ተተክቶ ሊሰራ የግድ ስለሚል እሱ ደግሞ ውጤታማ ሊያስደርግም ስለማይችል ራሱን ችሎ ትምህርቱ መሰጠት ይጠበቅበታል። ልክ ከተማ ፕላን እንደሚያደርገው፣ ለህንጻው ዲዛይን እንደሚያወጣ፣ በሰፊው የተጠናውን የከተማ ፕላን በየሰፈሩ ወደከተማ ዲዛይን እንደሚለውጠው ሁሉ የህንጻ ኮንስትራክሽን ላይ ለኮንትራክተሮች ትምህርቱ ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ።
ኮንትራክተሮቹ የህንጻ ኮንስትራክሽንን ከተማረ ዲዛይን ወይም ፕላን እና ሌላ ሌላ ውስጥ ሳይገቡ እሱን ብቻ ይሰራሉ። ምክንያቱም በዘርፉ የጠለቀ እውቀት የሚኖራቸው እነርሱ ናቸውና ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህንጻ ኮንስትራክሽን ትምህርት ለማስቀጠል ምን የታሰበ ነገር አለ?
ዶክተር ህያው፡– እኛ አሁን የህንጻ ኮንስትራክሽን ትምህርትን ልናስጀምር መርሐግብር ነድፈናል። ማጥናት የሚገባንን አጥንተናል። የጥናቱን ግኝት ለዘርፉ ባለሙያዎች የሰጠናቸው ሲሆን፣ ካሪኩለም እያዘጋጁለት ነው። በዚህ መልኩ መርሐግብሩን መልሶ ለማምጣት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።
ህንጻ መገንባት ማለት እና ህንጻ ዲዛይን ማድረግ ይለያያል። የኮንስትራክሽኑ ሰው ሳይት ላይ ሰራተኛውን ተቆጣጥሮ እንዲሁም መሳሪያዎቹን አስገብቶ፣ ቴክኖሎጂውን አምጥቶ በመቀጠልም ቤቱን ቀይሶ፣ ሲሰራ ደግሞ ሱፐርቫይዝ አድርጎ በተባለው ጊዜ፣ በሚፈለገው ጥራትና ይሰራል በተባለው ዋጋ ለማውጣት የሚሰለጥን ሰው ነው።
ህንጻ ዲዛይንንም የሚሰለጥን ሰው ደግሞ እንዲሁ በዘርፉ ትምህርት ላይ በሚገባ ይሰለጥናል። እርግጥ ነው ህንጻ እንዴት ተደርጎ እንደሚሰራም መማሩ አይቀርም። ይሁንና ዋና ትኩረቱ ግን ዲዛይኑ ላይ ነው። ወደኮንስትራክሽኑ ሲኬድ ግን እንደዋናው ባለሙያ መሆን አይቻልም። ስለዚህ በዲግሪም በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃም መሰጠት ይኖርበታል።
እኔ እስካሁን በማውቀው ሁኔታ ለኮንትራክተርነት ሙያ ውጭ አገር ሰልጥኖ የመጣ አካል ያለ አይመስለኝም። ዩኒቨርስቲያችን ለትምህርት በሚልክበት ወቅት ኮንስት- ራክሽን ማኔጅመንት የሚባል አለ፤ የማኔጅመንቱን ዘርፍ ብቻ ተምረው የሚመጡ አሉ። ኮንስትራክሽንን መስራት በሚመለከት ዲግሪ ይዞ የመጣ ሰው አላጋጠመኝም። በጥቅሉ ማለት የምፈልገው እያንዳንዱ ሰው በሚሰራው ስራ ባለሙያ መሆን ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ኢንስቲትዩት በከተማ ልማት ላይ ትምህርት እንደመስጠቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የአከታተም ሂደት ደረጃውን የጠበቀ ነው ማለት ያችላል?
ዶክተር ህያው፡– ደረጃ በሚባልበት ጊዜ ብዙ ጊዜ ከሚታዩ ነገሮች ውስጥ አንዱ የከተማ ሽግግር ደረጃው (ልኬቱ) ነው። የእኛ አገር የከተማ ደረጃ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነው። 20 በመቶው የተጠጋው ራሱ በቅርቡ ነው። እንዲህም ሲባል 80 በመቶ ያህል የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የሚኖረው በገጠር ነው። ስለዚህም የከተሜነት ደረጃችን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ነገር ግን ወደ ከተሜነት የሚደረገው ሽግግር በጣም ፈጣን ነው።
የሕዝቡ ወደከተማ የመፍለስ አካሄድ ፈጣን ነው። እስካሁን በዓለምአቀፍ ደረጃ ሽግግሩ በመቶኛ ታየ ከሚባለው ጋር ሲተያይ ከፍ ያለ ነው። ከ3 ነጥብ 84 እስከ 5 ነጥብ 3 በመቶ አካባቢ በየዓመቱ እየጨመረ ነው የሚሄደው።
ከዚህ ቀጥሎ የከተማ ደረጃ የሚባለው ደረጃውን የሚወስነው በአንድ በኩል ኢኮኖሚውም ጭምር ነው። እንደሚታወቀው የእኛ ኢኮኖሚ ደግሞ በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው። በብዛት የሚሸጠው የግብርና ምርት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት ነው። የኢንዱስትሪ ውጤት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በከተሞች የሚታየው እድገት የነዋሪውን ፍላጎት ያገናዘበ ነውን?
ዶክተር ህያው፡– በከተማ ደረጃ ያለውን እድገት ስናነሳ በእኛ አገር ደረጃ የሕዝብ ቁጥርን ነው ከግምት ውስጥ የምናስገባው። የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ነው ከተማ አደገ የሚባለው። እንዲያውም የእኛ አገር የከተማነት መስፈርት የሚንጠለጠለው በሕዝብ ቁጥር ላይ ነው። ከሁለት ሺህ በላይ ሕዝብ ያለው ማንኛውም መንደር ወይም ሰፈራ የሚወሰደው እንደከተማ ነው።
ከዚህ ውጭ ከተማው ያለው የመሰረተ ልማት ምን ይመስላል የሚለው ነገር እምብዛም ከግምት ውስጥ አይገባም። የሕንጻው ግንባታ እንዴት ነው የሚለውም እንዲሁ ነው። ዋናው ነገር ይህን ያህል የሕዝብ ቁጥር ተብሎ የተቀመጠውን ነገር መስፈርት በማድረግ የከተማነት ማዕረግ ይሰጠዋል ማለት ነው። ይህ አይነቱ መስፈርት ደግሞ ጥራት ላይ እንዳልተመሰረተ ስለሚታወቅ ነዋሪው የሚፈልገውን ነገር ያገኛል ማለት አያስደፍርም።
የነዋሪው ፍላጎት ሊሟላ የሚችለው በያዘው ገንዘብ ገበያ ውስጥ የሚፈልገውን ነገር ማግኘትና መግዛት የሚያስችል አቅም ሲኖረው ነው። ነገር ግን ያለው ነዋሪ የመክፈል አቅሙ ዝቅተኛ ከሆነ ከገበያ መግዛት አይችልም። ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ጉዳዩ የሚዞረው ወደመንግስት ይሆናል።
መንግስት ደግሞ አቅሙ ውስን ስለሆነ የተወሰነውን ፍላጎት ብቻ ነው ማሟላት የሚችለው። እንዲህ የተሳሰረ ነገር ስለሆነ በድምሩ በከተማ ያለው ነዋሪ ፍላጎት ሊሟላ የሚችለው ነዋሪውም የመስራት ፍላጎት ሲጨምር ነው። ይሄን ለማምጣት ደግሞ የስራ ፍላጎታችን ሊያድግ የግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- የደረጃ ሽግግር የሚፈቀድላቸው ከተሞች በአግባቡ መስፈርቱን አሟልተው የተሰጣቸው ናቸው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ህያው፡– እንደ አገር አቀፍ ወደ ስድስት የከተማ ደረጃዎች አሉ። በኢትዮጵያ ደረጃ ከአንድ መንደር ወደከተማ የሚያድገው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ነው። ከሁለት ሺህ በላይ ከሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ከተማ የሚባለውን ስያሜ ያገኛል። ሃያ እና ሃምሳ ሺህ ሲሆን ደግሞ እንዲሁ ደረጃው ከፍ እያለ ይሄዳል። ደረጃው ከፍ እያለ የመሄዱም ምስጢር በሕዝብ ቁጥሩም ልክ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብም ጭምር ነው።
በኢትዮጵያ ደረጃ ያለው የከተማ ደረጃ ከሌላው አገር የተለያየ ነው። አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አገሮች መስፈርታቸው አነስተኛ ነው። የሕዝብ ቁጥሩ ከፍ ያለ አገር ከሆነ መስፈርቱ ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥርን የሚጠይቅ ሲሆን፣ አነስ ካለ ደግሞ ዝቅ ያለ የሕዝብ ቁጥርን የሚጠይቅ ይሆናል። ደረጃውም እንደዛ እያደገ ይመጣል። ለምሳሌ በእኛ አገር አዲስ አበባ የከተማ ደረጃዋ ደረጃ አምስት የሚባለው ነው። ይህ ልኬት የአገር ውስጥ ሲሆን፣ የውጭ አገር ከተሞች መለኪያ ከኢትዮጵያ የሚለይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዜጎች ወደከተሞች የመፍለሳቸው ምስጢር በገጠር ያለው ገፊ ምክንያት እንዲሁም በከተማ ያለው ሳቢ ምክንያት እንደሆነ ይነገራልና በዚህ ጉዳይ የመንግስት ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር ህያው፡– መፍለስ በራሱ ችግር አይደለም። ምክንያቱም ለዘላቂ ህይወት የከተማ አይነት አኗኗር መኖር አለበት። ሕዝቡ ተበታትኖ የሚኖር ከሆነ አገልግሎት ለማድረስ በጣም ከባድ ነው። ሀብትንም በአግባቡ መጠቀምም አይቻልም። ስለዚህም ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የከተማ ኑሮ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን።
ከተማ ለእድገትም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለኢኮኖሚ እድገትም የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማበርከቱ በተጨማሪ ነዋሪውም ቀለል ያለ ህይወት እንዲኖር የሚያደርገው ነው። ዜጋው በከተማው ውስጥ በሚፈጠረው ስበት ከገጠር የሚመጣ ከሆነ እሱ ተፈላጊ ስበት ነውና ችግር የለውም። ምክንያቱም ከተማ አካባቢ የተፈጠረው ስራ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገው ከገጠር ወደ ከተማ የመምጣቱ ጉዳይ ችግር አይሆንም።
ነገር ግን መጥፎ ስበት የሚሆን ከሆነ እዛው በገጠር ያለውን ችግር ወደማቃለሉ መግባት ያስፈልጋል። መንግስት ደግሞ ሁለቱም አገር ስለሆነ እዚህም ሆነ እዛ ገጠር ውስጥ ለዜጋው ምቹ የሆነ ነገር ይሰራል። በሂደትም ዜጋው በከተማ ይኖር ዘንድ የሚያስችለውን ስራ በመስራት ወደከተሜነት እያሸጋገረው ይሄዳል።
በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚሰራ ግብርናን በማካሄድ በገጠር የሚኖር ዜጋ የሚኖር ሲሆን፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሳተፍ የስራ እድልንም በመፍጠር ደግሞ በከተማም እንዲኖር ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል።
ነገር ግን የአገሪቱ ትልቁ ችግር በከተማው ያለው ኢኮኖሚ ደካማ መሆን ነው። ምንም እንኳ በገጠር ያለውን የሕብረተሰብ ክፍልን ወደከተማ ቢስብም የተሻለ ኑሮን መምራት የሚያስችል ጥሩ ስራ ግን የሚሰጥ አይደለም። ጥሩ ስራ የማይኖር ከሆነ ደግሞ ሰዎች በተገባቸው የኑሮ ደረጃ መኖር አይችሉም። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀደም ሲል ከነበረበት ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪው መር ካልተሸጋገረ ኑሮን በአግባቡ መምራት አስቸጋሪ ይሆናል።
ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ አድጎ ቢሆን ግን ዜጋው በተለያየ መስክ እንደየችሎታው ስራውን መስራት ስለሚችል ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ማሟላትና የሚያስፈልገውን ክፍያ ሁሉ መክፈል ስለሚችል መንግስት ላይ ተጨማሪ ሸክም አይሆንበትም።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ከተሞች እየተካሄደ ያለው ኢንቨስትመንት ለየከተሞቹ መስፋፋት ትክክለኛ ሂደት ነው ብለው ያስባሉ? በአገሪቱ ብዙ ባለሀብቶች ከኢንዱስትሪው ይልቅ ህንጻዎችን ሰርተው በማከራየት የተጠመዱ ይመስላሉና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ህያው፡– ባለፈው ጊዜ ኢንቨስትመንት በራሱ ተጠንቶ ለሁለት ተከፍሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። አንደኛው ድሮ ልማታዊ ይባል ነበር። ለኢንዱስትሪው መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርግ ነበር። ሌላው ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ የሚል ስያሜ ይሰጠው ነበር። ይህ ደግሞ ትርፍ የሚያስገኝ ማንኛውም ነገር የመስራት አይነት ነገር ላይ የተንጠለጠለ ነው። ዝም ብሎ ለትርፍ ብቻ የሚሰራ እና የኢኮኖሚ ችግር ያልሆነው ላይ ብዙ አስተዋጽኦ የማያደርግ አይነት አከፋፈል ተከፍሎ ነበር ውይይት ሲደረግ የነበረው።
ስለዚህ ከተማ ውስጥ ጥሩ ኢንቨስትመንት ማለት ትልቁን ክፍተት መዝጋት የሚችለው ነው፤ እሱም ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ አገሪቱ ወደዚህ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ልትሸጋገር የግድ ይላል። ይህ ግን እስካሁን አዝጋሚ የሆነ ነው። ይህን ክፍተት የሚዘጋ አሰራር የሚመጣ ከሆነ ሁልጊዜም ጥሩ ኢንቨስትመንት ነው ሊባል የሚችል ነው።
ይኸኛው አይነት ኢንቨስትመንት ሲመጣ ኢኮኖሚው በአግባቡ ይንቀሳቀሳል፤ የቴክኖሎጂም ሽግግር ይኖራል። ለምሳሌ አንድ ኢንዱስትሪ ቢከፈት ሰራተኞችን ይቀጥራል፤ ሰራተኞቹ ደግሞ በኢንዱስትሪው መከፈት የስራ እድል ያገኛሉ፤ ኑሯቸውን ይመራሉ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለሚኖር እውቀት ይቀስማሉ።
እጣ ፈንታቸው በዛ ኢንዱስትሪ ስለማይወሰን ከዛ ይወጡና ምናልባትም ለዛ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሆነ ነገር ለማቅረብ የተወሰነ እሴትን በመጨመር በራሳቸው ስራ ይሰማራሉ። ሌላውም እንዲሁ በተለየው ዘርፍ የራሱን በመክፈትና በመቅጠር አገሩ ሁሉ ወደተፈለገው ወደኢንዱስትሪ ሽግግር መሄድ ስለሚችል የተሻለ ኑሮን መምራት ያስችላል።
ይህ ህንጻ ተሰርቶ ለተለያየ ዓላማ ይሆን ዘንድ ለኪራይ ማቅረቡ አይነት ስራም ቢሆን በወቅት በመጥፎ ሁኔታ የሚታይ አልነበረም። ለምሳሌ ሪልእስቴትን ብንወስድ በሌሎችም አገሮች የሪልስቴት ገበያ ከፍ የሚለው ኢንዱስትሪው ደካማ ሲሆን ነው። ምክንያቱም ኢንቨስተሮቹ አዋጭ ከሆነው ነገር ነው በመጀመሪያ መጀመር የሚፈልጉት።
ኢንዱስትሪው ብዙም ተስፋ የሚያሳይ አይነት ከሆነ ካፒታሉ ቁጭ ካለ ስለሚያልቅና ስለሚበላ የሆነ ቦታ ብሩን ማስቀመጥ ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ የትኛው ዘርፍ ነው ብለው ሲያስቡ ወደቤት መገንባቱ ይመጣሉ። ቤት ሰርተው በመሸጥ ሂደት ውስጥ ብሩ እየተሸከረከረ ስለሚሄድ ኢንዱስትሪውም ደካማ እየሆነ ይመጣል።
በዚህ ጊዜ የመንግስት ትልቁ ራስምታት የሚሆነው ቁልፍ ወደሆነው ወደኢንዱስትሪ ሽግግር ባለመገባቱ ላይ ይሆናል። ይህ የኢንዱስትሪ ሽግግር በተወሰነ መልኩም ቢሆን መንቀሳቀስ ቢጀምር ብዙ የስራ እድል ስለሚፈጠር ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በጣም ብዙ ሕዝብ ተነቅሎ መምጣት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማው እድገትም ሆነ መስፋፋት ዙሪያ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ድርሻ የተጠበቀውን ያህል ነው ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር ህያው፡– መንግስት ዋና ስራው ልማትን መምራት አይደለም። ልማትን የሚመሩት አሁን ባለው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ገበያው ሲሆን፣ እሱም የግል ዘርፉ ነው ተብሎ ተቀምጧል። በገበያ ውስጥ ክፍተት ከተፈጠረ ግን መንግስት ክፍተቱን ይሞላል። መንግስት ክፍተቱን ለመሙላት ደግሞ አንዱ በልማት ድርጅት በኩል ሊሆን ይችላል። የሚገባበትን ክፍተት ሊደፍን ሲገባ ግን የገበያውን ቦታ ለመውሰድ አይደለም።
ገበያውን ለመምራት መግባት አይኖርበትም። አሁን ባለው ሁኔታ አመራሩ የግል ዘርፉ በመሆኑ ቢዳከምም እሱን ማጠናከር ነው ከመንግስት የሚጠበቀው። የግል ዘርፉ ክፍተት በፈጠረበት ቦታ ግን አገልግሎቱ ለሕዝብ መቅረብ ስላለበት ክፍተቱን መንግስት ለመሙላት ይገደዳል።
የልማት ድርጅቶቹ በዚህ አይነት አካሄድ በመሄድ የገበያ ክፍተቱን ለመዝጋት ነው መሄድ ያለባቸው፤ ነገር ግን አካሄዳቸው ገበያ ለመተካት ከሆነ ደግሞ አግባብነት አይኖረውም። ውስጥ ተገብቶ ሲታይ ደግሞ እነሱ የሚያቀርቡት አገልግሎት ከሌላው ይልቅ ውድ የሚሆን ከሆነ ይህም ትክክል ያልሆነ አካሄድ ነው።
ለምሳሌ በቅርቡ ከማውቀውና ከእኛም ኮሌጅ ጋር በጋራ ለመስራት በስምምነት ሂደት ውስጥ ያለው የቤቶች ኮርፖሬሽንን ተሞክሮ ብጠቅስልሽ በቅርቡ በስራ ላይ እንድናማክራቸው የመጡበት ጉዳት ለመንግስት ባለስልጣናት መኖሪያ ቤት ማቅረብን የተመለከተ ነው። ድርጅቱ ደግሞ ወደፊት ፕራይቬታይዝድ የመሆን እቅድም ያለው ይመስለኛል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ራሳቸውን የሚችሉ ከሆነ ያው ገበያ ሆኑ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዋና ዋና ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው ኮንስትራክሽን ደረጃውን የጠበቀ ነው ይላሉ? ካልሆነስ ለምን?
ዶክተር ህያው፡– አሁን በራሳችን የምንጠብቀውን ደረጃ ካየነው ዲዛይኑም ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። የከተማ ዲዛይኑም እንዲሁ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። ኮንስትራክሽኑም ደረጃውን የጠበቀ አይደለም።
ስለሆነም በሁሉም ረገድ ያለውን ደረጃ ማሻሻል ይጠበቅብናል። ደረጃው ዝቅተኛ ነው ማለት ክፍተት አለ ማለት ነው። ክፍተት በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ ክፍተቱን የሚሞላው መንግስት ነው።
በአሁኑ ወቅት ዲዛይን የሚሰራው ገበያው ነው እንጂ መንግስት አይደለም። ፕላኑን መንግስት ያሰራል፤ በፕላን በኩል ክፍተት ካለ የራሱ ክፍተት ተደርጎ ይቆጠራል። የህንጻ ዲዛይን ቢቀንስ የቀነሰው ገበያ ነው ይባላል። ምክንያቱም የግል ድርጅቶች ናቸው እንጂ መንግስት ዲዛይን አይሰራም።
ኮንስትራክሽኑ ዘንድ ስንሄድ ደግሞ ኮንስትራክሽኑን የሚሰራው የግል ድርጅት ነው። መንግስት የሚሰራው የተወሰነው ያህል ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚሰራው በግሉ ዘርፍ ነው። በዚህ አካባቢ ሲሰራ የሚፈጠር ችግር ካለ ክፍተት እንለዋለን። እሱን ክፍተት ማነው መዝጋት ያለበት ወደሚለው ሲመጣ ደግሞ ያው መንግስት ነው የሚሆነው።
እንዴት ነው የሚሞላው ከተባለ ደግሞ ግማሹን በፖሊሲ ገሚሱን ደግሞ በስልጠና ሌላውን ደግሞ ፈቃድ በመስጠት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ሙያውን እንዲያሻሽል የትምህርት መስኩን በመለወጥም ሊሆን ይችላል። እንዲያ ከሆነ እያንዳንዱ ኮንትራክተር የራሱ የሆነ ሙያ በዲግሪ ደረጃ ብቻም ሳይሆን በሁለተኛ ዲግሪም ጭምር ስለሚሆን እነዚህን መሰል አስተዳደራዊ ስራ እየሰራ ነው ክፍተቱን መሞላት የሚቻለው ማለት ነው።
መንግስት ሁሉንም ነገር ማኔጅ ለማድረግ በከተማና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚያስፈልጉት ምን ምን ነገሮች ናቸው የሚለውን እኛ ሞዴሉን እየሰራን ነው። እዛ ሞዴል ውስጥ በመግባት በእያንዳንዱ ጥናት ይሰራል። ጥናት ሲጠና ደግሞ ክፍተቶቹ ይመጣሉ። ክፍተቶቹን በማስገባት ሙሉ ቤቱን መስራት እንችላለን።
ከዛ በኋላ የጥናቱ ምክረ ሐሳብ ይወጣና ለሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር ግንኙነት በመፍጠር ወደፕሮጀክት ተቀይሮ ፕሮጀክቶች ይሰራሉ። በዚህ መልኩ ክፍተቶቹ እየተዘጉ ይሄዳሉ። ስለዚህ የትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ጉዳይ በግል ማንም ሊሰራ አይችልም።
እኛ ግን በዩኒቨርስቲ ደረጃ ስለሆንን ሁሉንም ሙያ ያካተተ ሞዴል ነው የምንሰራው። በዚህ አይነት መልኩ ትስስሩን መፍጠር ይቻላል ማለት ነው። ይህም አካሄድ ውጤታማ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ ፕላን ዝግጅትን የሚመለከቱ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ ነው?
ዶክተር ህያው፡– እሱ ነው አንዱ ጥያቄ። ቅድም እየሰራናቸው ነው ያልኩሽ ሞዴሎች ውስጥ አንዱ ራሱ ስለግቡ ነው። ለምሳሌ በከተማ ልማት የሚቀመጠው ግብ ሲጀመር መሆን ያለበት ምንድን ነው የሚለው መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።
ሌላው ደግሞ ከላይ እስከታች አንድ ነው ወይ የሚለውም መታየት ያለበት ነው። ከላይ እስከ ታች ያለው ግብ የተቀናጀና የሚጣጣም መሆን ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነ ሊተገበር አይችል ማለት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ተቋም ያስፈልገዋል። ተቋሙ ደግሞ የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። በመሆኑም በቂ የሆነና ባለሙያ የሆነ ነው የሚያፈልገው። ባለሙያ ካልተገኘ ስራውን በአጥጋቢ ሁኔታ መስራት አይቻልም። ባለሙያው ባለሙያ መሆን የሚችለው ደግሞ ትክክለኛ ትምህርት ማግኘት ሲችል ነው። ለዚህም ነው ወደትምህርት ስርዓቱ የሚወስደን።
ሶስተኛው ደግሞ ፖሊሲው ነው፤ ፖሊሲዎች በትክክል ይተገበራሉ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ናቸው የሚባሉት ሁሉም አሉ ወይ የሚለው በራሱ አነጋጋሪ ነው። እንዲህም ሆኖ ፖሊሲዎች ሲወጡ የሚንደረደሩት ወደዋናው ግብ ነው ወይ የሚለውም ሌላው ጉዳይ ነው። የወጡ ፖሊሲዎች ለሁሉም እርከን ከፌዴራል እስከ ክልል እና ከዛም በታች ባለው መዋቅር ነው የሚለውም አንድ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው።
ይህ ሁሉ በአግባቡ የተቀመጠ ነው ከተባለ በኋላ ደግሞ አፈጻጸሙ እንዴት ነው ወደሚለው ይመጣል። ለመፈጸምስ የሚያችል የሰው ኃይል አለ የሚለውም ጉዳይ ተጠቃሽ ነው። ቴክኖሎጂና ሌሎች ግብዓቶችም እንዲሁ መኖራቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ውጤት መጠበቅ የሚቻለው። በእነዚህ ውስጥ ጉድለት የሚኖር ከሆነ ውጤቱ ላይም ጉድለት እንደሚኖር መጠበቅ የግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ህያው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013