ግርማ መንግሥቴ
ኢትዮጵያ ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርት መምራት ከጀመረች 1ሺህ 700 ዓመታትን ዘላለች። ይህም ከማንም በፊት፤ ቅድሚያ ብቻ ሳይሆን የቅድሚያ ቅድሚያ ላይ ያስቀምጣታል ማለት ነው። በሥርዓተ ትምህርት ላይ ስትወዛገብ የኖረች መሆኗም እንዲሁ እድሜ ፈጅ ነው።
በጉዳዩ ላይ ውዝግቡ ሁሌም ሲሆን እንደ አሁኑ ግን አብዝቶ ያከራከረ የለም። የሚያሳዝነው ትውልድን ሰለባ ካደረገ በኋላ አሁን በራሱ፣ በመንግስት “የማይረባ” መሆኑ በአደባባይ እየተነገረ መሆኑ ነው። ይህን ሃሳብ በተለይ አዲስ የተቋቋመውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥናቶችን በማገላበጥ መረዳት የሚቻል ሲሆን፤ ፖሊሲው ምን ያህል የወረደ እንደ ነበር ሁሉ እዛው ሰነዶቹ ላይ ተመልክቶ ይገኛል። በዚሁ ምክንያትም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደገና በ”ልየታ” (Differentiation) አማካኝነት የማዋቀር ስራ እየተሰራ መሆኑንም በእግረ መንገድ መገንዘብ ይቻላል።
ከላይ በጠቀስናቸው ረዥም አመታት (ክፍለ ዘመናት) ውስጥ ጉልሁን ስፍራና ትልቁን አገራዊ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ከነበሩት ትምህርት ቤቶች ቀዳሚው “የአብነት ትምህርት ቤት” ሲሆን ከተማሪዎቹ ደግሞ “የቆሎ ተማሪ” ነው።
ይህ በቀድሞው ጊዜ እራስን ከፍ አድርጎ ካለማየት፣ ከትህትናና ከአጠቃላይ ማህበራዊ ህይወትና ኑሮ አንፃር በወቅቱ “የቆሎ ተማሪ” ይባል እንጂ ዛሬ ላይ በአንዳንዶች ዝቅ ተደርጎ እንደሚታየውና የኋላ ቀር ሥርዓተ ትምህርት (ማንም እየተነሳ “ትራዲሽናል” እንደሚለው) ውጤት ተደርጎ እንደሚቆጠረው አይደለም።
እርግጥ ነው፤ የቆሎ ተማሪ ከፍተኛ የትምህርት ጥማትና ጥልቅ የሆነ የማወቅ ፍላጎት አለው እንጂ የካበተ ሀብትም ሆነ የተንደላቀቀ ህይወት የለውም። ሁሉ ነገሩ ከእጅ ወደ አፍ ሲሆን በከፍተኛ ጥረትና ልፋት ህይወቱን የሚመራ ነው። እሱ ብቻ አይደለም፤ ከእራሱም አልፎ ቤተሰቡን ባለው ነገር ሁሉ የሚያግዝና አንዳንዴም ሁሉ ነገር በእሱ ትከሻ ላይ የሚወድቅበት ወቅት አለ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ነው እንግዲህ ትምህርቱን የሚከታተለው፤ በመንፈሰ ጠንካራነቱ፣ ትምህርትና እውቀት ፈላጊነቱም እንዲታወቅ ያደረገው ይሄው ከባድ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባርና ከባዱን የአብነት ትምህርት የመከታተልና ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ስለ ቆሎ ተማሪና ትምህርት ቤቱ ያለን አረዳድ እንደ እውነታውና ታሪካዊነቱ አይደለም። አተያያችንም ቀና ሳይሆን ትንሽም ቢሆን ሸውረር ይላል። ፈቃዳችንም ቢሆን እዚህ ግባ የሚሉት አይነት አይደለም፤ ንቀት ቢጤ አያጣውም። ተማሪውም ሆነ ትምህርቱ እንደ ኋላ ቀርነት፣ ያለመሰልጠን የሚመስለን ሁሉ ብዙ ነን። ባጭሩ “የቆሎ ተማሪ” ልብ ውስጥ እኛ አለን፤ እኛ ልብ ውስጥ ግን የቆሎ ተማሪ የለም።
አለ ከተባለም “አለ” ለማለት ያህል እንጂ ሙሉ ሆኖ አናገኘውም። ቢኖር ኖሮ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ፤ በተለይም በቋንቋ ትምህርቶች (ቢያንስ በአንድ ምንባብ ደረጃ እንኳ) ውስጥ ስለ ቆሎ ተማሪና አጠቃላይ ማንነቱ ትንሽ እንኳን፤ እንደው አለ አይደል፣ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያህል እንኳን በተጠቀሰ ነበር። ግን ይህ ሲሆን አልታየም።
ስለ ቆሎ ተማሪ በግለሰቦች ደረጃ (እንደዚህ አይነት ጽሑፎች) አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ ስለ ማንነቱና አጠቃላይ ሁኔታው ከሚነግሩን ባለፈ ምንም የለም። ጉዳዩ ትልቅና ልዩ ቦታን ሊያገኝ የሚገባው ሆኖ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንኳን በጉዳዩ ላይ ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ የሚያጠና ሰው እንኳን የለም።
የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ሲነሳ ሊረሱ ከማይገባቸው፣ ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ሊፈተሽ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል የአብነት ትምህርት ቤት፣ የቆሎ ተማሪ እና የትምህርት ሥርዓቱ ሆኖ እያለ አንድም ጊዜ የድሮውን በጅምላ ኮንኖ ከማለፍ ውጪ እንደ አንድ የታሪካችን አካል፣ የሥልጣኔያችን መነሻና መሰረት ወዘተ ተደርጎ እንኳን ሲጠቀስ አይታይም። ሲጠቀስ አይደለም በአለፍ ገደም እንኳን ስሙን መስማት ብርቅ እየሆነ ነው።
የቆሎ ተማሪም ይሁን የአብነት ትምህርት ቤት ጉዳይ ለአብዛኛው ሰው ተረት፤ በተለይም ለወጣቱ ምናባዊ ወግ እስኪመስለው ድረስ ቀልሎ ነው የሚነገረው። በተለይ በተለይ እራሱን የውጪው ዓለም ምርኮኛ ያደረገው አካልማ “የቆሎ ተማሪ” ሲባል እልም ያለኋላ ቀርነቱና ከፈረንጆቹ ጋር በንፅፅር ሲታይ የሚያሳፍር ሁሉ እየመሰለው ልክ ልጥ እንዳየ በሬ ይበረግጋል፤ ስለ ጉዳዩ ማውራትም ሆነ መስማት ከቶም አይፈልግም። ይህ ደግሞ የእሱ ጥፋት አይደለም። ጥፋቱ የማን እንደ ሆነ ይታወቃል። ከየት ያምጣውና ይመፃደቅበት፣ ምንስ ብሎ በማንነቱ ይኩራ?
የቆሎ ተማሪ ለራሱ የትምህርት ፍቅርና ለራሱ የእውቀት ጥማት ሲል እስከ መለመን ድረስ በዘለቀ ህይወት ውስጥ ያልፍና ትምህርቱን አጠናቅቆ ለወግ ማእረግ ይብቃ እንጂ አበርክቶቱ ለአገርና ህዝብ ነው።
በብዙዎች እንደተገለፀውና በብሩህ ዓለምነህ (2010፣ 217) ሰፋ ተደርጎ እንደተብራራው እስከ 20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ድረስ የአብነት ትምህርት ቤቶች በዚህ ሥርዓተ ትምህርት አማካኝነት ለቤተክህነትና ለመንግስት ስራ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ሲያመርቱ ቆይተዋል። መሳፍንቱና መኳንንቱም ይሄንን የሰው ኃይል በየቤታቸው በመምህርነት በመቅጠር ትምህርት እንዲስፋፋ ትልቅ አበርክቶት አድርገዋል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ሁላችንም እንደምናውቀው ከአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች አገርና ህዝብ የተጠቀሙት ብዙ ነገር አለ።
የየኔታ መቋሚያ የቆሎው ተማሪ
የሞተን ቀባሪ ለአምለኩ ዘማሪ፤
ከተማርከው ትምህርት ካጠናኸው ቅኔ
በኮፈዳህ ዋሻ ላክልኝ ለጎኔ።
የተባለለት የቆሎ ተማሪ ከሁሉም ግን ስነ ቃላዊ ትውፊትን የተመለከተው አበርክቶቱ ከሁሉም ይገዝፋል። ቅኔው፣ ቃል ግጥሙ፣ ምስጥራዊ ፍቺው ወዘተ ሁሉ በአብዛኛው የእነሱው ውጤት ሲሆኑ፤ አሁን አሁን ይህ እሴት እየነጠፈ መምጣቱ ሌላው የአብነት ትምህርት ቤቶቹ እየተዳከሙ ስለመምጣታቸው አመላካች ነው።
ብሩህ በዚሁ ገፅ የግርጌ ማስታወሻው ላይ “ተማሪዎች እንደ ምግብ ያሉ የኑሮ ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ከትምህርት ጊዜአቸው በመቀነስ በልመናና ተባራሪ የጉልበት ስራዎችን በመስራት” መሆኑን የሚናገር ሲሆን፤ ዲያቆን ታደለ ሲሳይ (ሐመር፣ ጥር 2006)ም ይህንኑ የብሩህ አስተያየት ካረጋገጡ በኋላ ዛሬ ምንም ቢለምኑም ሆነ ምንም ቢያደርጉ የሚረዳቸው ሰው ሊያገኙ እንዳልቻሉ፤ ይህ በመሆኑም የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱንና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይገልፃሉ።
ለዚህም በደብረ መድኃኒት ዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ወመርቆሬዎስ ቤተክርስቲያንን በማስረጃነት የሚያቀርቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያኑ የሚሰጠው የአብነት ትምህርት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የተማሪዎች ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው ሊቆም ሁሉ እንደሚችል አሳስበዋል።
በቤተ ክርስቲያኑ ከመጽሐፈ ጉባኤ ውጪ በርካታ የአብነት ተማሪዎችን ያቀፈ የአቋቋም ጉባኤ እንደሚገኝ፤ በውስጡም ከስልሳ በላይ አዳራሾችን የያዙ (እያንዳንዱ አዳራሽ በውስጡ አንድ ወይም ሁለት ጀማሪ ተማሪዎችን ይይዛሉ) መኖራቸውን የሚናገሩት ዲያቆን ታደለ ሲሳይ በአሁኑ ሰአት ቀደምት ሊቀ መዛሙርትን ሊተኩ የሚችሉ ደቀ መዛሙርት እየተመናመኑ መምጣታቸውንም ይናገራሉ።
“ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የደቀ መዛሙርቱ ችግረኛ መሆንና የህብረተሰቡ ቸልተኝነት” መሆኑንም ያሰምሩበታል። ለመፍትሄውንም “የቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት በዘላቂነት ለማስቀጠልና የአገልጋዮቹን ችግር ለመቅረፍ ዘላቂ መፍትሄ” እንደሚያሻው ተደርሶበት የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
ለመሆኑ በአብነት ትምህርት ቤት በጥናት መስክነት የሚሰጡ፤ የቆሎ ተማሪው የሚከታተላቸው የትምህርት አይነቶች ምን ምን ናቸው? ደረጃዎችስ አሏቸው? የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱና ሊመለሱ የግድ ይሆናል። ይህ ካልሆነ የተቋሙንም ሆነ የተማሪዎቹን አስፈላጊነቱን ማሳየት ስለማይቻል ነው።
የቆሎ ተማሪ ወይም የአብነት ትምህርት ቤት ትምህርት ከ”ሀ ሁ . . .” በመጀመር ነው ወደ እላይኛው ትልቁና ከፍታው ደረጃ የሚገሰግሰው። በዚህ ግስጋሴ ውስጥ በጣም በርካታ የጥናት መስኮች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ መስኮችም በፕሮግራም የተከፋፈሉና በየደረጃው እያደጉ የሚሄዱ ናቸው። በማዕረግም እስከ “አራት አይና” (በዘመናዊው አጠራር “ፕሮፌሰር”) ድረስ የሚዘልቁ ሲሆን ተቋሙ ካፈራቸው አራት አይናዎች መካከልም ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
የቆሎ ተማሪ ከሀሁ … ፊደል መቁጠር ጀምሮ የሚወስዳቸው ኮርሶች በርካታ ሲሆኑ አቡጊዳ ይማራል፣ መልዕክተ ዮሐንስን ይቆጥራል። መልዕክተ ዮሐንስን ቁጥር እንደ ጨረሰ ውርድ ንባብን ያጠናል፤ ከዛም ቁም ንባብን ያውቃል።
በዚህ አያበቃም፣ ቀጥሎ የቃል ትምህርትን “አአትብ ገጽየ” በማለት ይጀምራል፣ መልዕክተ ዮሐንስን ማንበብ ይጀምራል። (የቃል ትምህርት ማለት ቀን ቀን ከሚሰጠው የቆሎ ትምህርት በተጨማሪ ማታ ማታ (ያለ መጽሐፍ) የሚሰጥ ነው።)
በቀኑ መርሀ ግብር ወንጌልን፣ ግእዝ ንባብን፣ ውርድ ንባብና ቁም ንባብን ይማራል። በማታው መርሀ ግብር ደግሞ የዘወትር ፀሎትን ያጠናል።
ዲያቆን ታደለ ሲሳይ እንዳሰፈሩት ብዙ ጊዜ የቃል ትምህርቱ የሚሰጠው ማታ ማታና ሌሊት ሲሆን ከማታው ወንበር እስከ ሌሊቱ ያለው ሰዓት ለቅጸላና ለእረፍት የሚያገለግል ግዜ ነው። “ቅጸላ ማለት በዘመናዊ ቋንቋ ጥናት ማለት ሲሆን ወንበር ማለት ደግሞ ትምህርት ነው።” ሲሉም የጽንሰ ሀሳቦቹን ብያኔ ያስቀምጡልናል።
በቀኑ ወንበር ወንጌሉን ዘልቆ ዳዊት ሲጀምር፣ በቃል ትምህርቱ ደግሞ ውዳሴ ማሪያምን ዘልቆ አንቀፀ ብርሀን፣ ይዌድስዋ መላእክት፣ መልክአ ማሪያምና መልክአ እየሱስን ያጠናል። (እዚህ ላይ ፀሐፊው በቅርብ የሚያውቀውን ሃይማኖት ጠቀሰ እንጂ በእስልምናውም “መድረሳ”ን እና “ሀሪማ”ን የመሳሰሉትን በዚሁ መልክ ማብራራት ስለሚቻል ቀረብ ያሉ ወይም ግንዛቤው ያላቸው ጸሐፍት ይሄዱበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።)
የቆሎ ተማሪዎቹ በተማሩት ትምህርት መሰረት ይፈላሰፋሉ፣ ግጥም ይገጥማሉ፣ ይቀኛሉ የሚሉት ዲያቆኑ ተማሪው አጥፍቶ ወይም ስራውን ሳይሰራ መጥቶ ወይም አቅቶት የኔታ ሲቀጣ የተቀጣበትን ምክንያትና የቅጣቱን ክብደት፤ እንዲሁም የራሱን ጥፋት ወዲያውኑ በሚያስገርም ግጥም ቅኔውን እንደሚያዥጎደጉደው የተለያዩ ምሳሌዎችን በማቅረብ ያስረዳሉ። “ገና [ከ]ህፃንነቱ ጀምሮ በሚደርስበት ጥቃቅንና ከባድ ፈተናዎች [ላይ] ተመስርቶ ቃላት መርጦ፣ ሀረግ ለውጦ፣ ስንኝ ቋጥሮ፣ ቤት መትቶና ዜማ መጥኖ ወደ ፊት የሚጠብቀውን የቅኔ ፍልስፍና በፈጠራና በምርምር ይለማመዳል።” ሲሉም ሂደቱን ይነግሩናል። (እዚህ ላይ የየኔታ ጉዳይ እራሱ ችሎ ብዙ የሚባልለት መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው።)
ዛሬ ዘመኑ ከ”ዘመናዊነት” (Modernism)ም አልፎ ድህረ ዘመናዊነት (Postmodernism) ሆነና ይህ ሁሉ የተረት ያህል፣ የቅዥት ያህል፣ የልጆች ጨዋታ ያህል ይቆጠር ጀመረ እንጂ ድሮ ድሮ ዲያቆን ታደለ ካሉት በላይ ሁሉ እንደነበረ በጉዳዩ ላይ አብዝተው የለፉት ይናገራሉ። በተለይም ትምህርት ቤቱና የጥናት መስኮቹ በርካታ “የቀለም ቀንድ” የሚባሉ ምሁራንን ለአገርና ሕዝብ ያፈሩ መሆናቸውን የሚናገሩት እንደሚሉት የተቋሙ መቀጨጭ፤ ወይም በመጥፋት ላይ መሆን ይቆጫል ብቻ ሳይሆን አገራዊ ኪሳራና ውድቀት ነው።
እነ ሀዲስ አለማየሁን የመሰለ ድንቅ ሰው ያፈራ ጥንታዊ ተቋም ዛሬ ላይ ባለው ትውልድ ቸልተኝነትና የርዕዮተ አለም ግራ መጋባት ምክንያት ለዚህ ሲዳረግ ያሳዝናልም ባይ ናቸው። በተለይ ድምፅን ወደ ጽሑፍ (ድርሰት) የቀየረውና በአለማችን የመጀመሪያ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ሲታሰብ ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤት በዚህ ደረጃ መቀጨጭና ለመጥፋት አንድ ሀሙስ የቀረው መሆን በእጅጉ ያሳዝናልና አሁንም ከታሰበበት ጊዜ አለ።
ማንነትን መጠበቅ፣ ማስጠበቅና ማቆየት፤ አቆይቶም ለትውልድ ማስተላለፍ የትም ያለ ነው። የተረገሙቱ ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ ይህንን አድርገውት ዛሬ ድረስ ከፍሬው እየገመጡና እያጣጣሙ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ አገራት የታወቁ ጥንታዊ የልህቀት ማዕከላት መኖራቸው (ብሩህ፣ ገፅ 217) በቂ ማሳያ ሲሆን፤ ፓሪስ በስነ መለኮት ትምህርት፣ ቦሎኝ በህግ፣ ቻርትረስ በስነፅሁፍ ይታወቁ ዘንድ አብቅቷቸዋል።
ይህ እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ የዘለቀው የአገራችን የአብነት ትምህርት ቤት አብዮቱ በአብዮት ከገረሰሳቸው እሴቶች አንዱ ሲሆን፤ አብዮቱና አብዮተኞቹም ዛሬ ለሚታየው የእውቀት ድርቀትም ሆነ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን አስቀድመን ለጠቀስነው “ልየታ” መዳረግ ቁልፍ ምክንያት መሆናቸውን ልብ ማለት ተገቢ ነው።
የጥናት መስኮቹን በፕሮግራም ስናስቀምጣቸው ንባብ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ ሰዋሰውና ቅኔ ቤት፣ ትርጓሜ (የመፃህፍት) ቤት (በ”አራቱ ጉባዔያት”ም ይታወቃል) ድረስ የሚዘልቁና በድምሩ ከ30 አመታት በላይን የሚወስዱ መሆናቸው ይታወቃል። ለምሳሌ ያህልም “ትርጓሜን” እንኳን ብንወስድ ብሉይ ኪዳን፣ ሀዲስ ኪዳን፣ መጽሐፈ ሊቃውንት፣ እና መጽሐፈ መነኮሳትን የሚሸፍን ሆኖ እናገኘዋለን። በመሆኑም ነው በርካታ አራት አይናዎች እና የቀለም ቀንዶች ምንጭ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሆነው በርካታ ለአገርና ለወገን የተረፉ ሰዎችን ማፍራት የተቻለው።
ይህ ነባሩን ሥርዓተ ትምህርት የመጎንተል፣ የመቃወም ቀስ በቀስም ወደ ማስወገድ የመሸጋገር ሁኔታ የመጣው አገራት፣ እኛን ጨምሮ፣ ዘመናዊነትን (የምዕራቡን ስልጣኔ) ወደ አገራቸው ለማምጣት የነበራቸውን ፈጣን ፍላጎታቸውን ተከትሎ መሆኑ በብዛት የተጠናና በሁሉም በሚባል ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ ጉዳይ ሲሆን ንጉሥ ኃይለ ሥላሴም በእንደዚህ አይነቱ ግራ መጋባት ውስጥ ገብተው እንደ ነበር ተገልጿል።
የእሳቸው ግራ መጋባት ባለበት ሁኔታ ነው አብዮቱ ነባሩን “አሮጌ” ብሎ ነቅሎ ጣለውና ገላገለው፤ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ “የትምህርት ፖሊሲ ስር ነቀል ማሻሻያ / The radical reformulation of the educational policy” በማለት የደርጉን ተግባር ይገልፁታል።
ባጠቃላይ አሁን ያለንበት ዘመን ግራገብነታችን ጎልቶ የማይታይበት ዘመን ነው። አይደለም ለሥርዓተ ትምህርት ለውጥ በህይወት ስለመኖራችን እንኳን በእርግጠኝነት ለመናገር ፍርሀት ፍርሀት የሚልበት የከፋ ወቅት ነው። ባልተገባ “እኛ” እና “እናንተ” ክፍፍልና በሰከረ ፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ ነው። ይሁን እንጂ አበሻ ግን እጁን ወደ ላይ ዘርግቶ “ወደ ፊት የተሻለ ቀን ይመጣል”፣ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እና የመሳሰሉትን የተስፋ ቃላትን እያሰማ ነው ያለው።
በመሆኑም እነዚህ አገር በቀል እውቀቶቻችን ላይ የጋራ ትኩረት በማድረግ፣ የተሳሳተውን በማረም፤ ተገቢውን በማስቀጠል ተገቢውን ስራ እንሰራለን ተብሎ ይታሰባል። ድሮ ተጀምሮ የነበረውን፣ የሚራገፈውን አራግፎ፣ የሚጠናከረውን አጠናክሮ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የትምህርት ሥርዓት አፍሪካዊ የማድረጉ ስራ እንደገና ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ወቅት ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013