አዲስ አበባ፡-ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ወጭን ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ስድስተኛው አገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት የኤግዚቢሽን፥ ባዛርና ሲምፖዚየም ከጥር 30 እስከ የካቲት 6 እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡስማን ሱሩር ትናንት በሰጡት መግለጫ ፤የኅብረት ሥራ ማህበራት በተለይ በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት በማረጋጋት ሚና ሲወጡ መቆየታቸውን፣መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባቸውን እንደ ምግብ ዘይት ያሉ መሰረታዊ ፍጆታዎችን በማምረት የገበያውን ክፍተት ለመሙላት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ 15 የሚደርሱ የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀን 10ሺ ሊትር የምግብ ዘይት በማምረት ላይ እንደሚገኙና የኑሮ ጫናን ለመቀነስ እንዲሁም ገበያ ለማረጋጋት ተጨማሪ አምራቾች ለማፍራት የልምድ ልውውጥ በመድረክ እየተመቻቸ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የካበተ ልምድ ያላቸው የህብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውንና የግብርና ምርቶችን የማቅረብ አቅማቸውም ማደጉን ጠቁመው፣ ለኅብረተሰቡ የሚያደርጉት ድጋፍም ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ ማህበራቱ የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት ማጎልበት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ለአገር ግንባታና ለማኅበረሰብ ልማት በሚያደርጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦም የእድገትና የለውጥ አሳላጭ ሃይሎች ሆነው በተምሳሌትነት ተጠቃሽ ለመሆን መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከጥር 30 እስከ የካቲት 6 በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል የሚካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር፤በማህበራቱ መካከል ጠንካራ የግብይት ትስስር ለለመፍጠርና በመተባበር ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ዘላቂነት ላለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ግንባታ አካታችና አሳታፊ በሆነ አግባብ የሚያከናወኑትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ለማሳየት እንዲሁም የግብይት ተግዳሮቶቻቸውን ለመፍታትና ተደራሽነታቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኤግዚቪሽንና ባዛሩ ላይ 225 የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን እና አገልግሎታቸው፣ እንዲሁም የግብርና ውጤቶች፣ የግብርና ግብዓቶችና የሜካናይዜሽን ማሽኖች ለጎብኝዎች በግዢ እና ለእይታ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡ኤግዚቪሽንና ባዛሩን 45ሺ የከተማዋና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች ነዋሪዎች እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡
ከኤግዚቢሽኑና ባዛሩ መክፈቻ በፊት የመኪና ትርዒትና ቅስቀሳ ፣ጥር 30 ደግሞ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአገር ውስጥና የውጭ የተሳተፉበት ሲምፖዚየም እንደሚካሄድና የልምድ ተሞክሮም የሚገኝበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን አባላት፥ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያፈሩ ፥ ከ85ሺ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት፥ 388የኅብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኖችና ሦስት የህብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ መሆናቸውን የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጥር 24/2011
ማህሌት አብዱል