* የመረጃ አሰባሰቡ ስርዓት በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ይከናወናል
* መጠይቆች በአምስት ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ
አዲስ አበባ፡- አራተኛው የኢትዮጵያ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንደሚከናወንና የመረጃ መጠይቆቹም በአምስት የክልል የሥራ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጁ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ትናንት እንዳስታወቁት፤ አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከባለፉት ቆጠራዎች በተለየ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በዚህም የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንደሚታገዝና የባለፉትን የቆጠራ ሥርዓት ቅሬታዎች ለመፍታት ለመረጃ አሰባሰብ የተዘጋጁ መጠይቆች በአምስት የክልል የሥራ ቋንቋዎች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡
እንደ አቶ ቢራቱ ገለጻ፤ ከዚህ በፊት በወረቀት ይሰራ የነበረው የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሰራ የተደረገ ሲሆን፤ ይህ የአሰራር ለውጥ በሌሎች አገሮችም ውጤት ያስገኘና የአገሪቱንም የቆጠራ ሂደት የሚለውጥ ብሎም አገራዊ መረጃ የመሰብሰብ ሥርዓት በማዘመን አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ለቆጠራ ሥራው 152ሺ የቆጠራ ቦታ ካርታዎችና 37ሺ መቆጣጠሪያ ቦታ ካርታዎች በዲጂታል ተዘጋጅተዋል፡፡
የዋናው ቆጠራ መረጃ የመሰብሰብ ተግባርም በ‹‹ታብሌት›› በተባለው ቴክኖሎጂ የሚካሄድ መሆኑን አስገንዝበው፤ ለህዝብና ቤት ቆጠራው የተዘጋጁ መመሪያዎች፣ መጠይቆችና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የአሰራር ሥርዓት በሦስት የሙከራ ቆጠራዎች እንዲፈተሸም መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የመረጃ ጥራት መከታተያ ሥርዓት በመስክና በማዕከል ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንደሚተገበርም ጠቅሰው፤ ቆጠራው በተጠናቀቀ አጭር ጊዜ ውስጥ ውጤቱን ገምግሞ ለመግለጽ የሚያስችል ሁኔታዎች መፈጠራቸው ጠቁመዋል፡፡ የመረጃ ደህንነት ለመጠበቅና የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችም መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ከመንግሥት በተመደበ ከፍተኛ በጀት 180ሺ ታብሌቶችና የኃይል ማከማቻ፣ 126ሺ ‹‹ፓዎር ባንክ›› ግዥ ተፈጽሟል፡፡ በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተገኘ ድጋፍ ለቆጠራ ቦታ ካርታና ዋናው ቆጠራ ሁለት ሺ ‹‹ፒዲኤና ታብሌቶች›› 35ሺ ‹‹ሶላር ፓዎር›› እንዲሁም ‹‹ዳታ ሴንተር›› እቃዎች ግዥ ተፈጽሟል፡፡
ቀደም ሲል ለህዝብና ቤት ቆጠራው የዋሉ መጠይቆችና መመሪያዎች በአንድ ቋንቋ ብቻ ይዘጋጅ እንደነበር አቶ ቢራቱ አስታውሰው፤ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታን በመፍጠሩ በአሁኑ ቆጠራ በአምስት የክልል መንግሥታት የሥራ ቋንቋዎች ማለትም፤ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛና ሱማልኛ እንዲዘጋጅ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ «ይህም ለመረጃ ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል›› ብለዋል፡፡ አክለውም በቆጠራው ላይ የሚሰማሩ ቆጣሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ የቴክኖሎጂ አስተባባሪዎች በድምሩ 182ሺ ባለሙያዎች በክልል መንግሥታትና በከተማ አስተዳደሮች በኩል ምልመላ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ቆጠራውን በሚጠበቀው ጊዜ በአስረኛው ዓመት በሁሉም ቦታዎች ህዳር ወር 2010ዓ.ም ለማካሄድ አቅዶ የነበረ ሲሆን፤ በውቅቱ በነበረው አለመረጋጋትና የጸጥታ ችግር ማካሄድ እንዳልተቻለ አስገንዝበው፤ አጠቃላይ ሁኔታውን በመገምገም ለ2011ዓ.ም እንዲተላለፍ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ደረጃውን የጠበቀና ተዓማኒነት ያለው ህዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የህዝብ ቆጠራው በኢትዮጵያ ጂኦግራፊ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያከተተ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በቀደምት የህዝብ ቆጠራዎች በአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜ ይካሄድ የነበረው ቀርቶ በሁሉም አካባቢዎች በአንድ ጊዜ አንድ የቆጠራ ቀንን መሰረት በማድረግ ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መጋቢት 29 ቀን 2011ዓ.ም ይጀመራል፡፡
ጥር 24/2011
አዲሱ ገረመው