ሰላማዊት ውቤ
የአዲስ አበባ ከተማን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ እየተገነቡ ካሉ መኖሪያ ቤቶች አሥር ዘጠና፣ ሃያ ሰማንያ፣ አርባ ስድሳ ተጠቃሽ ናቸው። ይህም የቤት ፈላጊውን ችግር ያቃልላሉ ተብሎም ይታመናል። የመኖሪያ ቤቶቹ አፈፃፀም ያማረና የሰመረ እንዲሆን ይፈለጋል። ይሁን እንጂ የቦሌ አያት ሁለት 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች ለዚህ አልታደሉም።
እነዚህ ቤቶች በ2008 ዓ.ም ተጀመሩ ከተባሉት የአርባ ስድሳ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች ሁሉ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ዘግይተው ነው የተጀመሩት። ይህ ሳያንስ ከዕጣ አወጣጡ በኋላ የነበረው የአሰጣጥ ሂደታቸውም ግራ የሚያጋባ ነበር። በእርግጥ ዕጣው ይፋ የሆነበት የዕድለኞች ስም ዝርዝርና አጠቃላይ መረጃ ቤቶቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ስር እንደሚገኙ ይጠቀሳል።
ነገር ግን ቤቶቹ የሚገኙት ወረዳ 15 ሆኖ ሳለ ዕድለኞቹ ውል እንዲፈፅሙ የተደረገው ወረዳ 10 ስር እንዳሉ ተደርጎ ነው። በውሉ ሂደት ካርታ የተሰራውና ሙሉን ለከፈሉ የተሰጠውም ይሄንኑ የተጣረሰ መረጃ መሰረት በማድረግ ነው። አሁንም ቢሆን እነዚህ ቤቶች በወረዳ 15 ስር ስለመሆናቸው የተገኘ ማስረጃ የለም።
ዕድለኞቹ ከምዝገባ ሂደት ጀምሮ እስከ ውል ማሰር ያለውን ሂደት ያከናወኑት በዋናነት በቦሌ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ 10 መሆኑ ሲታሰብ ዕውን መረጃው የተጣረሰው ወረዳው ለሁለት በመከፈሉና ቤቶቹ በወረዳ 15 ስር በመገኘታቸው ብቻ መሆኑን ያጠራጥራል። ባለ ዕድለኞቹ እንደሚሉት ከበስተጀርባው ሌላ ሸፍጥ ያለም ያስመስለዋል።
‹ሳይት ቦሌ አያት ሁለት› የሚለውና በምዝገባ ሂደት ወቅት ችግር ሲፈጥር የነበረው ስያሜ በራሱ አሻሚና ‹ቦሌ አያት ሳይት ሁለት› ከሚለው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ሸፍጥ የመኖሩን ጉዳይ ያጎላዋል። ይሄው ቤት ወረዳ 10 ሥር መገኘቱ ደግሞ ምን አልባት አሻሚውን የሳይት ስያሜ ተጠቅሞ ቤቶቹን የመለወጥ ተግባር ሊከወን መቻሉን ያስጠረጥራል።
የቤቶች ልማት ኤጄንሲ አመራሮች በዚህ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጭምር ቤቶቹ ዕጣ የወጣባቸው የሳይት፣ የህንፃና የቤት ቁጥር ተለጥፎባቸውና ተለይተው መሆኑን ደጋግመው መናገራቸው ጥርጣሬውን ይደግፈዋል። ሳይት ቦሌ አያት ሁለቶቹ ገና ከጅምር ዕጣ ሲወጣ በመዋቀር ላይ የነበሩና ለዚህ ማዕረግ የበቁ ካለመሆናቸው ጋር ሲደመርም ጥርጣሬውን ዕውነት ያስመስለዋል።
በአጠቃላይ ባለ ዕድሎቹ እንደሚሉት ቤቶቹ አሁንም አድራሻቸው የት እንደሆነ አጥርቶ ማወቅ አለመቻሉ፤ ግንባታቸው እስከ አሁን አለመጠናቀቁ፤ በተደጋጋሚ ቁልፍ ርክክብ በዚህ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ ቢለጠፍም በተባለው ወቅት ርክክቡ አለመደረጉ እያሳዘናቸው ይገኛል። ቤቱ እጃቸው ባልገባበት በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጫና ካለው ወለድ ጋር የባንክ ዕዳ እየከፈሉ ለመቆየት ተገድደዋል። ይሄ ለግለሰብ ከሚከፍሉት ኪራይ ጋር ተዳምሮ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፈጥሮባቸዋል።
‹‹እኛ በአንድ በኩል ለግለሰብ ቤት የቤት ኪራይ እየከፈለን በሌላ በኩል ደግሞ ለእነሱ እንከፍላለን›› ሲሉ ቤቱ እጃቸው ባለመግባቱ ምክንያት ለሁለት ወጪ መዳረጋቸውን በመጥቀስ አስተያየታቸውን የጀመሩልን የቤቱ ዕድለኛ ወይዘሮ አዳነች ገዛኽኝ ናቸው። ወይዘሮ አዳነች ወደደረሳቸው ቤት ለመግባት ስለጓጉና ተከራይተው ስለሚኖሩም ቤቱን ሰርክ ይጎበኙታል።
የግንባታ ሂደቱ ለውጥ ሳያሳይ አሁንም ከሦስት ወር በፊት እንዳዩት ነው። ያኔ ያዩት የደረጃ እምነበረድ አሁንም አልተሰራም። የተሰራው የመስኮት ፍሬምና ጠርዝ ነው። መስኮት እንኳን አልገባለትም። ከላይ ወደ ታች ነው መሥራት የጀመሩት። ከ11ኛው ወለል በላይ ያለው ብሎኬት ነው የተደረደረው ቢበዛ ልስን ነው ማለት ይቻላል። ቀለም እንኳን በሙሉ አልተቀባም።
በእርግጥ የእነዚህ ህንፃዎች ማብሰያና መታጠቢያ ቤቱ፣ ሴራሚክ አገጣጠሙና ጥራቱም፤ የእንጨት በሩም ይሻላል። ደረጃው እምነ በረድ፣ መውረጃው በሁለት ወገን መሆኑ፣ የጋራ መጠቀሚያው መስፋቱና ተጨማሪ አሳንሰር መኖሩ ጥሩ ነው። ሆኖም ግንባታው ቃላት ሊገልፀው በማይችል ሁኔታ እጅግ የተጓተተ ነው። ‹‹በዚህ ይዘቱ መቼ ቤቱን ታገኝዋለሽ ብትሉኝ ከ2014 በፊት እንደማላገኘው እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ›› ይላሉ። የዚህ ቤት ዕጣ የወጣው ቢያንስ ብሎኬት
ተደርድሮ ካለበት አንፃር ቢበዛ መሰረት ተጥሎ ቢሆን እንኳን ግንባታው ይጠናቀቅ እንደነበርም ይናገራሉ። ምዝገባው የተካሄደው 2005፤ ዕጣው የወጣው የካቲት 27 ቀን 2011፤ አሁን ያለንበት 2013 መሆኑን በመጥቀስ የፈጀውን ጊዜም ወይዘሮዋ ያስታውሱታል። ከምዝገባው ጀምሮ የነበረው የባንክ፣ የቤቶች ልማት በመገናኛ ብዙሃን ምዝገባ በዚህ ቀን ይካሄዳል፣ በዚህ ቀን ደግሞ ቁልፍ ይሰጣል የማይባልበትና ውጣ ውረድ የበዛበት ግልጽነት የጎደለው አሠራር ግን እሳቸውን ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑን ምነው ባልደረሰኝ ያሰኘ ሂደት እንደነበረም በመንገፍገፍ አውግተውናል።
አዛውንት፣ ነፍሰ ጡር፣ አካል ጉዳተኛና በሽተኛ ሳይለይ በፀጥታ አስከባሪ ይገፈተርበትና ይሰቃይበት የነበረ ነው። ቤቶች ልማት የሆነ ነገር ሲል ባንክ ሲኬድ የነበረው ችግር ቤት ደርሷችኋል ሲባሉ ከውጪ የመጡትን የመመለሻ ቀን ትኬት ከማራዘም አልፎ አማሮ ያስለቀሰና የብዙዎቹን ሕይወት ያናጋ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
ወይዘሮዋ እንደሚሉት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ደግሞ ቁልፍ መስጠት ተጀመረ፤ በመካከል ተቋረጠ። ሆኖም እንደታዘቡት ቁልፍ የተሰጣቸው ዜጎች እስከ አሁን ቤታቸውን ማፅዳትም ሆነ መኖር አልጀመሩም። እንዳስተዋሉት ቁልፍ መሰጠት የተጀመረው ለታይታ ተብሎ ይሁን ሌላ ግልፅ ባይሆንላቸውም የአብዛኞቹ ቤቶች ግንባታ ሳያልቅ ነው። ቤቶቹ እስከ አሁን ውሃና መብራትም አልገባላቸው። ቢቸግራቸው በሌሎች ሳይቶች ቤት የደረሳቸው ኮሚቴ አቋቁመው ለማስገባት ጥረት አድርገው አልተሳካላቸውም።
በመሆኑም ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ቤቶች ልማት ኤጄንሲ ከነዚህ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት አለበት ሲሉም ይመክራሉ። አብክረው ‹‹ዋናው የችግር ምንጭ የቤቶች ልማት ነው›› ይላሉ። ዕድለኛዋ አሰራሩ ግልፅነት የሌለው፣ ግልጽ መረጃ የማይሰጥ፣ ስህተቱ ሲነገረው ፈጥኖ የማያርም መሆኑንም አስረግጠው ይናገራሉ።
በዚህ ሳይት እሳቸው የደረሳቸው ህንፃ የሚገኘው በወሬ ደረጃ እንደሚባለውም በወረዳ 15 ሆኖ ሳለ በወረዳ 10 ሥር እንዳለ አድርጎ ውል እንዲፈፅሙ ብሎም ካርታ እንዲሰራላቸው ማድረጉ የስህተቱ ማሳያ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ይሄን ተቋም ጨምሮ ዋንኞቹ የነዚህ ቤቶች ተዋናዮች ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 10ና 15 ሲነገራቸው የዝሆን ጆሮ ይሰጠኝ ማለታቸው፣ በባለ ዕድለኛው ላይ የሚያመጡት ምንም ጉዳት እንደሌለው መጥቀሳቸው፣ የወረዳ መከፈልን ምክንያት ማድረጋቸው የሚያዋጣ እንዳልሆነም ይጠቅሳሉ።
‹‹ቤቱ ወረዳ 15 ሆኖ ወረዳ 10 ነው ብሎ ካርታ መስጠት ግራ የሚያጋባ ነው›› ያሉን እሳቸውም ሰነድ የተሰራላቸው በዚህ መልክ መሆኑን የጠቀሱልን ቤቱ ዕድለኛ ከሆኑት መካከል አቶ ውቤ ሰላሙ ናቸው። ቤቱ በወረዳ 15 ሥር ነው መባሉን ባለፈው ዓመት ክረምት ቁልፍ እርክብክብ ሲጀመር ነው የሰሙት።
ሆኖም ዕጣው እንደወጣ ሳይት ላይ በነበሩ የቤቶች ልማት የሥራ ኃላፊዎች ጥቆማ የእኔ ቤቴ ብለው ያዩት ቦሌ አያት ሳይት ሁለት የተሰኘውን ነበር። ይሄ ቤት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ከመሆኑ ባሻገር ውሃና መብራት የተሟላለት ሲሆን ከአሳንሰር በቀር መንገድም ተሟልቶለት ነበር።
ይህ ቤት ከቤት ቁጥሩ ጀምሮ ህንፃ ቁጥሩ፣ ካሬው ዕጣው በወጣበት ወቅት የዕድለኞች ዝርዝር ላይ ከሰፈረው መረጃ ጋር ይመሳሰላል። የእሳቸው ሳይቱ የሚጠራው ሳይት ቦሌ አያት ሁለት በመባል ከላይና ከፊት ቦሌ አያት ሳይት ሁለት ከሚለው ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል።
ስያሜው አሻሚም ነው። ደግሞ አንዳንዴ ሳይት የሌለው ቤት በማለት ይጠሩታል። በዚህ የተነሳ በምዝገባ ሂደት ወቅት እሳቸውን ጨምሮ ሳይት በሚለው ቦታ ምን እንሙላ የሚል ጥያቄ ተነስቶም እንደነበር ያስታውሳሉ። በባለ ዕድለኞቹ ዝርዝር ላይ የሰፈረውን እንዳለ ጽፈው በመዝጋቢዎችና በአስተባባሪዎች ቦሌ አያት ሳይት ሁለት ብለው ሙሉ መባላቸውንም እንዳልዘነጉት ይጠቅሳሉ። በተሰጠው ርዕስ በዚህ ላይ ይሄ ወረዳ 15 ሥር የሰፈረውና በቁልፍ ርክክብ ወቅት የእናንተ ነው መባሉን የሰሙት ቤት ዕጣ በወጣበት ወቅት ገና ጅምር ላይ ነበር።
የቤቶች ልማት የሥራ ኃላፊዎች በሳይት ባገኝዋቸው ጊዜና በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ቤቶቹ ዕጣ የወጣባቸው የሳይት፣ የቤት ቁጥር፣ የህንፃና የወለል ቁጥራቸው ተለጥፎባቸውና ተለይተው መሆኑ ሲናገሩ ከማድመጣቸው ጋር በትክክልም የእኔ ቤት ቦሌ አያት ሳይት ሁለት ነው ብለው ደምድመው ነበር።
ይሄ ድምዳሚያቸው ስህተት መሆኑን ያወቁት አሁን ድረስ ሳይት ቦሌ አያት መሆኑ በግልጽ ምልክት ያልተደረገበት ወረዳ 15 ውስጥ የሚገኘው ቤት በቁልፍ እርክብክብ ወቅት የእናንተ ነው ሲባል በወሬ ደረጃ በመስማታቸው ነው። አሁንም ለእሳቸው የደረሳቸው ዕጣ ወረዳ 10 ውስጥ ያለው ነው የሚመስላቸው።
በዚህ አድራሻ ቅፅ እንዲሞሉ መደረጋቸውና በምዝገባ ወቅት በኋላ እንዳጣሩት የቦሌ ክፍለ ከተማ ባንክ የፃፈላቸውን በተመዘገቡበት ወቅት የነበረ መረጃ ቀይረው ካላመጡ እንደማይመዘገቡ ስላስገደዳቸው ቀይረው በማምጣት መመዝገባቸው ቤታቸው በወረዳ 10 የሚገኘው መሆኑን አረጋግጦላቸዋል።
ሆኖም ይሄን የትክክለኛነት ጥርጣሬያቸውን በወቅቱ በቃል ከዛም በኋላ በማመልከቻ ለቤቶች ልማትና እዛው አካባቢ ላሉት ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸውን ይገልፃሉ።
በዚሁ ሳይት ኪብኮ የተባለ ሥራ ተቋራጭ በመወክል ሲሰሩ ያገኘናቸው አቶ ገብረሕይወት መብራህቶም እንደገለፁልን ቀደም ሲል በግብዓት አቅርቦትና ክፍያ በመፈፀም መጠነኛ የሥራ መስተጓጎሎች ነበሩ። ሆኖም አሁን ቤቶቹ በመጠናቀቅ ላይ ናቸው። በዚህ ላይ የእሳቸው ተቋም ከዚህ ሳይት ሦስት፤ ከሳይት አራት ደግሞ አንድ ህንፃ ይዟል። ይሄን መያዝ የቻለው ህንፃ 11ና 12ን በፍጥነትና በጥራት ሠርቶ በማስረከቡ ነው።
በዚሁ ሳይት አካባቢ ጊዚያዊ ቢሮ ውስጥ ያገኘናቸው የግንባታ ክትትል ባለሙያ እንደገለፁልን በሳይት ቦሌ አያት ሁለት ያሉት 50 ቤቶች ናቸው። እነዚህ ቤቶች የተጀመሩት ዕጣ ከወጣባቸው ቤቶች ውስጥ መጨረሻ ላይ ነው። ከዓመት ከስድስት ወር በኋላ ነው የተዋቀሩት። አሁን ያሉበት ዕጣ ሲወጣ ግንባታቸው ተጠናቀቀ ከሚባለው በሚቀራረብ ደረጃ ነው።
በመሆኑም አሁን ላይ አፈፃፀማቸው የተሻለ ነው ለማለት ይቻላል። ተቋራጩ ግብዓት እንዲያቀርብ የተደረገው ዕጣው ከወጣ በኋላ ነው። በኮንትራክተሩ መቅረብ የነበረባቸውን ግብዓቶችን የሦስትዮሽ ውለታ በማሰር ቤቶች ልማት ለአቅራቢ እየከፈለ እያስገቡ ነው የሚገኙት። ክፍያው ይዘገያል በማለት የሚያነሱት ቅሬታም አሁን ተፈትቷል።
በለሚ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ትርፌ እንደገለፁልን ወረዳ 10 እጅግ ሰፊና ከኮንዶሚኒየም ግንባታም ሆነ ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ የሕዝብ ፍልሰት እየመጣ ያለበት ነው። በመሆኑም አገልግሎት ለመስጠት እንዲያመች የዛሬ አራት ዓመት ለሁለት ተከፍሎ ወረዳ 15 ለመመስረቱ መረጃ አላቸው።
ቀድሞ ሁሉም በወረዳ አሥር ስር የነበረው የዚህ አካባቢ አደረጃጀት ሁለት ጊዜ ነው የተሠራው። የድሮው ቦሌ ወረዳ 15 የነበረው ለአገልግሎት አሰጣጥ እንዲያመች በከፊል ከወረዳ 10 ወስዶም ከአንድ ወር በፊት በፓርላማ ፀድቆ ወረዳ ሦስት፣ ወረዳ አራትና ወረዳ አምስት ተብሎ ለሦስት ተከፍሏል። ያም ሆነ ይህ መፍትሄው በዚህ ምክንያትም ሆነ በአፈፃፀም የተጣረሰ መረጃ ካለ ለሚመለከተው አቅርቦ ቀስ በቀስ እንዲስተካከል ማድረግ ነው።
‹‹የፀጥታ ሥራ ላይ ቆይተን አሁን ወደ መደበኛ ሥራችን ገብተናል። የተረከብነው መረጃ እንዲስተካከል ይሄንኑ የተጣረሰ መረጃ የማጥራት ሥራ እየሰራን ነው›› ያሉን ደግሞ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አመራር ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር የተለያየ ጥረት ብናደርግም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013