ማህሌት አብዱል
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካበቢ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በነፃነት ጮራና በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1982 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣው የአቃቢ ህግ ሥልጠና ላይ ለመሳተፍ ተወዳድረው አለፉ።
እናም ለዛሬው ማንነታቸው መሰረት የጣለላቸውን ትምህርት ቀሰሙ። በተለይም በስራ ዘመናቸው ሁልጊዜም እውነትን ፍለጋ እንዲተጉ ጉልበት እንደሰጣቸው ነው የሚያነሱት። በስልጠናው መሰረትም በአቃቢ ህግነት ማገልገል እንደጀመሩም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ዲፕሎማቸውን ያዙ።
በመቀጠልም በዛው የትምህርት ተቋም ዲፕሎማቸውን ወደ የመጀመሪያ ዲግሪ አሳደጉ። በዚህም አልተወሰኑም፤ በማኔጅመንት ተጨማሪ ዲግሪ ሰሩ። እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በከፍተኛ አቃቢነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም የአስተዳርና ፋይናንስ ሃላፊ ሆነው ለሶስት አመታት ሰርተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ ተቋማቱን በአዲስ መልክ ሲያደራጁ ፍትህ ቢሮ ሲቋቋምም በቢሮው የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ በመሆን ተመድበው ማገልገል ጀመሩ። ከ1998 ዓ.ም ወዲህም በግላቸው በጥብቅና ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።
በግላቸው መስራት ከጀመሩ ወዲህም በተለይም አገር አቀፍና ጠንካራ የሆኑ የወንጀል ጉዳዮችን በመያዝ የሚታወቁት እኚሁ የህግ ሰው ከእነዚህም መካከል በእነ አቡበከር መዝገብ በቀረበው ክስ ላይ በጥብቅና መቆማቸው ይታወሳል። በአሁኑ ወቅትም ከያዟቸው የወንጀል ክሶች መካከል የቀድሞው የደህንት አባላትና የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች በተከሰሱባው የወንጀል ጉዳዮች ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
አንጋፋው የህግ ሰው አቶ ሞላልኝ መለሰ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ በሀገሪቱ የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥና የሕግ ማስከበር ሂደት በእርሶ እይታ ምን እንደሚመስል ይንገሩንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሞላልኝ፡– በመጀመሪያ ደረጃ ለውጡ ለምንድነው የመጣው የሚለውን ነገር በደንብ ማየት አለብን ብዬ አምናለሁ። ይህንን የምልሽ በአገሪቱ ሁለት የተቀላቀሉ ነገሮች እንዳሉ ሥለሚሰማኝ ነው። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ስለብሔርና ስለልዩነት ይሰጥ የነበረው ፅንፍ የረገጠ ስብከት እንዲሁም የፈጠረው የተዛባ አመለካከት ዛሬም ድረስ ለብዙ ችግሮቻችን መንስኤ ነው ብዬ አስባለሁ።
ከብሔር ጋር ተያይዘው የተሰበኩት ስብከቶች አገራችንን ከቀን ወደ ቀን ወደ ጉድጓድና መቀመቅ ይዟት ሲሄድ ነው የነበረው። ለምሳሌ ለብዙዎች እኔ ሞላልኝ መሆኔ ሳይሆን የሚያሳስባቸው ከጀርባ ያለው የዘር ግንዴ ነው። ብሔራዊ ማንነቴ ቀድሞ እየታየ የእኔ ሃሳብ ወይም አስተሳሰብ ቦታ ያጣበትና ፅንፍ በረገጠው ዘውጋዊ አስተሳሰብ ምክንያት ብዙ ችግሮች ውስጥ ገብተን ቆይተናል።
ይህንን ጉዳይ የፍትህ መድረኩ ላይ አምጥተን ብናየው ብዙ ሰዎች በብሔራቸው፤ በእምነታቸው፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው ነው የነበሩት። እኔ ለምሳሌ እነ አቡበከር መሃመድ ተከሰው በነበረበት መዝገብ ላይ ጠበቃ ሆኜ እሰራ ነበር። እዚያ ጋር እነ አቡበከር አንስተውት የነበረው ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ነበሩ። ጥያቄዎቹ በቀላሉ ምላሽ ሊሰጥባቸው የሚችሉ ነበሩ። እነዚያን ጥያቄዎች በመመለስ አገር ላይ የሚመጣ ምንም ችግር አልነበረም።
ይልቁንም የሙስሊሙ ማህበረሰብ የተሻለ አገሬ ብሎ እንዲያስብ የሚያግዙ እንጂ። እነዚን ጥያቄዎች በመመለስ የሚመጣ ምንም ነገር የለም። እነ አቡበከር ግን ያንን ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ታስረው ሲንገላቱ ነበር። መታሰር ብቻ አይደለም ጥፋተኛም ተብለው እስከ 25 አመት የሚደርስ ቅጣት ተፈርዶባቸው ነበር። ያ የሆነው ለምንድን ነው ብለሽ ብትጠይቂ ምንም አጥጋቢ ምላሽ አታገኚም። በወቅቱ የነበረው የመንግስት አመራር ጥያቄዎቹን መመለስ ከብዶት አይደለም።
ጥያቄውን ያነሱት ሙስሊሞች በመሆናቸው ምክንያት በወቅቱ ከነበረው አለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በማያያዝ በአሸባሪነት በመፈረጅ እንዲከሰሱ ተደረገ። እነዚህ ሰዎች ጥያቄውን ያነሱት ከአሸባሪነት አንፃር ነው ተብሎ እስከመጨረሻው ድረስ ተገፉ። አሳሪዎቹ ከአቡበከርም ሆነ ከሌሎቹ ሰዎች ጋር አልነበረም ችግራቸው። ይህ ተግባራቸው ጠቅላላ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ያስቆጣና ሌላ ችግር ውስጥ የከተተ ነበር።
በአገሪቱ ሰፊ ቁጥር ያለውን አማኝ ማህበረሰብ የሚያስከፋ ነገር እንዲፈጠር ተደረገ። ምክንያቱም ሰውን በአስተሳሰቡ፣ በእምነቱና በብሔሩ፣ በአንድ ኮታ ውስጥ ለይተሽ በምትመድቢበት ጊዜ ቀላል የማይባል ችግር አገር ላይ መፍጠሩ አይቀርምና ነው። የሰውየው አስተሳሰብ ቀላል መሆኑ ሓሰቡ ሃሳብ ብቻ መሆኑ መረዳት ትተሽ ከጀርባው ብሄሩንና እምነቱን መሰረት አድርገሽ የምትመዝኚ ከሆነ ሌላ ችግር ውስጥ እንድትገቢ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- ያለፉት ዓመታት ቁርሾ ለለውጡ ስኬት እንቅፋት ይሆናል እያሉ ነው?
አቶ ሞላልኝ፡– ምን መሰለሽ በአገራችን ላለፉት 27 ዓመታት የመጣንበት መንገድ ብልሹ ሥርዓት በመሆኑ አንድ ሰው ኦሮሞ ከሆነ ‹‹ኦነግ ነው›› የሚባልበት አማራ
ከሆነ ደግሞ ‹‹ግንቦት ሰባት ነው›› በሚል ተፈርጆ በቀጥታ እሱ በማያውቀው ቅርጫት ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ይህን ስታደርጊ ግን ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን የመጣበትን ማህበረሰብ ነው የምታስቆጪው። አንድ ማህበረሰብ ብሔሬ ወይም እምነቴ ተጠቅቷል ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል። በዚህ መልክ የመጣንበት መንገድ አገራችንን መቀመቅ ውስጥ ከቶት ቆይታል። ዶክተር አብይ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ሁለትና ሶስት
አመታት በህይወትም ጭምር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ከእነዚያ ችግሮች መውጣትና ሰው በመሆኑ ብቻ ተከብሮ የሚኖርበት አገር መፍጠር ያስፈልጋል። ሰው በሚኖረው አስተሳሰብ የማይጠቃበትና ጉዳት የማይደርስበት ፍረጃ ውስጥ የማያገባበትን ስርዓት መፍጠር እንደሚገባውም ነው ለውጡ የሚያምነው።
ይሄ ጉዳይ ትርጉሙ በጣም ብዙ ነው። ወደ እኔ ሙያ ቀረብ አድርገን ብናየው ሰዎች በዚህ ምክንያት ታስረው የነበሩበት ነገር መጨረሻ ላይ የፍትህ ጥያቄ ያስነሳል። ያ የፍትህ ጥያቄ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ በአግባቡ ምላሽ አያገኝም ነበር። እኔ ሁልጊዜ የማምንበት አንድ ነገር አለ።
ሰው በተለያዩ የመንግስት አካላት ላይ፣ ተቋማት ላይ ቅሬታ ሲኖረው የመጨረሻ አማራጩ ፍርድ ቤት መሄድ ነው። ፍርድ ቤት የሚሄደውም ፍትህ አገኛለሁ ብሎ ነው። ያንን ፍትህ የሚያገኝ ከሆነ ሁልጊዜም በሰላም ነው የሚኖረው። ነገር ግን ሰው ፍርድ
ቤት ሄዶ ፍትህ የማግኘት መብቱን ቢያጣ የሚኖረው አማራጭ በሃይል መብቱን ለማስከበር መጣር ነው። በሃይል መብት ለማስከበር መሞከር ደግሞ አመፅ ነው የሚሆነው። ፍትህ ላይ የሚፈጠሩት በደሎች ውጤታቸው ከባድ ነው የሚሆነው። እኛ አገር በርካታ በደሎችና ጥቃቶች ተፈፅመዋል። በፍርድቤት ወይም በፍትህ መድረክ እልባት ያገላገኙት ነገሮች ለቀጣይ ረብሻና አመፅ ምክንያት ሲሆኑ ነው የሚዩት።
ከሁሉም አመፆች ጀርባ ሲገለጥ የፍትህ ጥያቄ ነው የሚገኘው። የፍትህ ጥያቄ በጣም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ነው። ስለዚህ ለውጥ መጥቷል ስንል አንዱና በዋናነት ሊያምነን የሚችለው የፍትህ መድረኩ ላይ ነው። ማንኛውም ሰው በአስተሳሰቡ ነፃነት አግኝቷል ስንል፣ በማንነቱ ነፃነቱን አግኝቷል ስንል‹፣ በፍትህ መድረክ ላይ እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚረጋገጡበት ሥርዓት ፈጥረናል ማለት ነው የሚሆነው።
እንግዲህ እነዚህን የተለያየ እይታዎችን ያነሳሁበት ምክንያት ለውጥ አለ ሥንል ለውጡን የምንመዝንባቸው መመዘኛዎች ከዚሁ ጋር የሚካተቱ በመሆናቸው ነው። ከዚህ አንፃር እንግዲህ የዶክተር አብይ መንግስት ከመጣ በኋላ ማንኛውም ሰዉ ቢያንስ የትኛውንም አስተሳሰቡን ይዞ በሚያራምደው ነገር ተፈርጆ ሲጠቃ አናይም። ቢያንስ ይሄ ጉዳይ ዋስትና ያገኘ ይመስላል።
በእርግጥ ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜ ትናንሽ ጉድለቶች ይታያሉ። እነዚያ ጉድለቶች አስቀድሜ እንዳልኩት ወደ ፍትህ መድረክ ሲቀርቡ እልባት የሚያገኙ ከሆነ የአመፅና የረብሻ ምክንያት አይሆኑም። ያ ማለት ለውጥ መጥቷል ማለት ነው። አሁን ላይ በአመለካከት፣ በብሔር፣ በእምነት ጉዳይ ላይ ነፃነት አለ ያልነውን ያህል ፍትህ መድረኮች ላይ ስንመጣ ዋስትና የሚሰጥ ነገር ፅድት ባለ መልኩ በደንብ አናይም። ጉድለቶቹ ይበዛሉ። ፍርድ ቤቶች አካባቢ አሁንም ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ጥቃት ሲፈፀምባቸው እናያለን።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ሪፎርሙ በተጨባጭ የፍትህ መድረኩን አልዳሰሰውም እያሉ ነው?
አቶ ሞላልኝ፡– ልክ ነው። ግን ይህንን የምልሽ ፍርድ ቤት ላይ ብቻ አይደለም። በሁሉም የፍትህ ተቋማት ጭምር እንጂ። እነዚህ መድረኮች ጋር ሙሉ ለሙሉ ለውጥ መጥቷል ፣ ነገሮች ተሻሽለዋል ። ለምሳሌ ጠንካራ በሚባሉ ዳኞች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና ይከፍሉት የነበረው ዋጋ ቀርቷል። ዳኞቹ ከዚያ አኳያ ነፃነታቸው የተከበረበት ሁኔታ ነው ያለው። በተሻለ ነፃነት፣ በተሻለ ሙያዊ ብቃት ስራቸውን ይሰራሉ።
ግን የፍትህ መድረኩ ላይ በፊት የነበሩት ጉድለቶች ባሉበት ሁኔታ ቀጥለዋል። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ በፊት የነበረውን ስርዓት ማስፈፀሚያ ስለነበር በፍትህ መድረኩ ያንን ብልሹ ሥርዓት የሚያስፈፅሙ ዳኞች ሆነ ፖሊሶች አሁንም አሉ።
መኖራቸው ብቻ አይደለም የሚገርመው፤ በተመሳሳይ ተግባር መቀጠላቸው እንጂ። በአዛኞቹ ተቋማት የሚገለገለው ሰው ማንነት ነው የተለወጠው እንጂ የሚያገለግሉት ሰዎች አልተለወጡም። ይህ መሆኑ ደግሞ ነገሮችን የበለጠ ከባድ ያደርጋቸዋል።
ሁሉንም የፍትህ ተቋማት ስታይ በጣም ሰፊ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎች በቅንነት እያገለገሉ ቢሆንም ያለፈው ስርዓት አስቀጣይ የሆኑ ጥቂት ሰዎች የእነዚህን ባለሙዎች ድካም ስራ ሁሉ የሚያቆሽሽ ነገር ሲሰሩ ይስተዋላል። በነገራችን ላይ የቀድሞ ሥርዓት የሚያስፈፅሙት ሰዎች መቀጠላቸው ችግር ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
የተሟላ ለውጥ ማምጣት ያልተቻለውም ለዚህ ነው ብዬ ነው የማምነው። እነዚህን ሰዎች ለማስወገድ ያን ያህል የተወሳሰበ ችግር ሆኖ አይደለም። ሰዎቹንም ማግኘትም ሆነ ሥርዓቱን መለወጥ ያን ያህል ከባድ ነገርም አይደለም። ግን እየታወቀ ለምንድነው እንዲቀጥል የተፈለገው? ብለሽ ከጠየቅሽኝ በፍትህ መድረኮቹ ላይ ትክክለኛ ለውጥ ለማምጣት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ መኖሩ አጠያያቂ በመሆኑ ነው የሚሆነው ምላሼ።
አዲስ ዘመን፡- ለዚህ ማሳያ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
አቶ ሞላልኝ፡- እኔ በፊት እሰራባቸው የነበሩ ጉዳዮችን ለአብነት ብናነሳ እንኳን በሆነ ምክንያት አንድ ሰው ማጥቃት ሊፈለግ ይችላል። ያም መነሻው የፖለቲካ ችግር ሊሆን ይችላል። የግለሰቦችም ጥቅም ሊሆን ይችላል። የፖለቲካውንም ጉዳይ ቢሆን ያንን ለማስፈፀም የተወሰኑ ባለስልጣኖች ናቸው በዚያ ላይ ፍላጎት አሳድረው የሚመጡት። እነዚያ ባለስለጣኖች ፍላጎት አሳድረው ሲመጡ ያንን ተቋም ይጠቀሙና የፈለጉትን ያደርጋሉ።
ለምሳሌ አቃቢ ህግን ወይም ፖሊስን ተጠቅመው የፈለጉትን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ይህ አስተሳሰብ አሁንም ይታያል። ስለዚህ በእኔ እምነት እነዚህን ነገሮች ማጥፋት ስንችል ብቻ ነው በእርግጥ ወደ ተሟላ ለውጥ መምጣት የምንችለው። ማጥፋት ሲባል አንዳንድ ጊዜ ሰዎቹ ይህንን አድርጉ ተብለው ታዘው ሊሆን ይችላል፡፤ ላይሆንም ይችላል። ግን አንድ ጊዜ አስተሳሰቡ በዚያ መልክ የተቀረፀ ባለሙያ ካለ ባለሥልጣን አዘዘውም አላዘዘውም ይህ ነገር የባለሥልጣኖች ፍላጎት አለው ብሎ ሲያምን ባለስለጣኖችን ሊያስደስት የሚችለውን ነገር እያሰበ ሊሰራ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ባለስልጣኖቹ ጋር ሳይሆን ሰውየው ጋር ነው ችግር ያለው ማለት ነው።
በአስተሳሰቡ ነፃ አልወጣም ማለት ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የፍትህ ተቋሙን ተጠቅመን የፈለገውን እናደርጋለን ብለው የሚያምኑ አሉ። ይህ አስተሳሰብ ካልተለወጠ አሁንም እጃቸው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መክተታቸው አይቀርም። ይህም ደግሞ ችግሩ እንዲቀጥል ያደርገዋል። በአጠቃላይ አሁን ባለዉ ሁኔታ የፍትህ መድረኩ እነዚህን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ማፅዳት የቻለ አይደለም።
በመሆኑም ለውጡን በድምሩ ስንመዝነው የተሻሻሉ በርካታ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል አሁንም ያልፀዳ ችግር አለ። እነዚህ ካለፈው ስርዓት የተሻገሩ ችግሮች በአገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ለውጥ መጥቷል ለማለት የማያስደፍሩ ይሆናሉ። አሁንም መታረም ያለባቸው በርካታ ችግሮች አሉ። ይህ ችግር ደግሞ በፖለቲካ አስተዳሩም ሆነ በፍትህ መድረኩ ላይ የሚታይ ነው።
በተለይም አሁን ወዳለው ወቅታዊ ሁኔታ ስንመጣ ከዚህ ቀደም ሰው በብሄር ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት ጥቃት የሚደርስበት ወይም የሚጣላው ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ነው። በዚህ ምክንያት ይታሰራል፤ ሊገደልም ይችላል፤ ከአገር ሊሰደደም ይችላል። ከሌላ ብሔር አባል ግን በቀጥታ ጥቃት ሲደርስበት አይታይም ነበር።
አሁን ግን የአንዱ ብሄር ተወላጅ በሌላው ላይ ሆን ብሎ ጥቃት የሚያደርስበትን ሁኔታ በየአካባቢው እያየን ነው ያለነው። ለምሳሌ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ በየአካቢው ያለውን ማህበረሰብ አሳትፎ ቄሮም ሆነ ፋኖ ወይም ዘርማ የሚል ሥያሜ ቢሰጠውም አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥቃትን እየፈፀመ አልነበረም የመጣው። ልክ በለውጡ ማግስት አንዱ ብሄር በሌላኛው ላይ የሚፈፅመው ጥቃት እየጨመረ መጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- ለዚህ ዋነኛ የሚሉት ምክንያት አለ?
አቶ ሞላልኝ፡- በነገራችን ላይ እኔ ገና እነዚህ ችግሮች ምልክታቸው ገና ማቆጥቆጥ እንደጀመረ ባገኘሁት መድረክ ሁሉ አቆጥቁጠው ከፍ ሳይሉ፤ ጉልበታቸው ሳይጨምር፤ ጥርስ ሳያወጡ እርምጃ መወሰድ አለበት በማለት እናገር ነበር። ያ ካልሆነና እየቆየ በሄደ ቁጥር ልንመልሰው ወደማንችለው ነገር ይዞን ይገባል የሚል ስጋቴንም እገልፅ ነበር። ይህም የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነበር የነበረው።
እነዚህ እንቅስቃዎች ሆነ ተብለው የሚፈፀሙ እንደነበረ ነው የሚሰማኝ። ለምሳሌ ሃዋሳ ላይ በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረው ችግር እናንሳ። ጥቃቱ የተፈፀመው አንዱ ብሔር በሌላው ላይ ቢሆንም መልዕክቱ ለሌሎቻችንም ጭምር ነው። እንደምታስታውሽው የደረሰው በጣም አሰቃቂ ጥቃት አንድ ሰው በብሔሩ ምክንያት ምንአይነት ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ግልፅ አድርጎ ያሳያል። ስለዚህ ሁላችንም ቆም ብለን ወደ ብሄራችን ጠበን እንድናስብ የሚያደርግ ነበር።
በተመሳሳይ ሻሸመኔ ላይ ሰው ዘቅዝቀው ሲገድሉ መልዕክቱ ለሁላችንም ነው የተላለፈው። እኔ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚያ ሰው ዘቅዝቆ ሰቅሎ የተገደለበት ስርዓት ነበር ብዬ አላስብም። ግን ያም ድርጊት ሲፈፀም መልእክቱ ለሁላችንም ነው የነበረው።‹‹መንግስት ህግና ስርዓት የማስከበር አቅም የለውም፤ ስለዚህ በየትኛውም ቦታ ላይ እኛ ይህንን ነገር ማድረግ እንችላለን›› የሚል መልዕክት ነው የነበረው።
ለምሳሌ ጀዋር አንድ ሌሊት ላይ ተከበብኩኝ የሚል መልዕክት ባስተላለፈ ጊዜ የተከሰተውን እልቂት መጥቀስ እንችላለን። ብዙ ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ታርደዋል፤ ተገለዋል። እነዚያን ሁኔታዎችን ስናይ አንዱ ሌላው ላይ በቀጥታ ጥቃት ፈፅሞ ያለምንም መሳቀቅ ራሱን በማህበራዊ ሚዲያው ይገልፅ ነበር። ይሄ ሲሆን መልዕክቱ ሁላችንም በብሄራችን ምክንያት ጥቃት ሊደርስብን የሚችል ሥለመሆኑ እንዲሁም መንግስት ከዚህ አይነት ጥቃት እኛን ለመከላከል የሚያስችል አቅም የለውም የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር የተሞከረው።
ሥለዚህ የመጣውን ለውጥ እንዲቀጥል የማይፈልጉ ቡድኖች በትክክል መልዕክቱን እያስተላለፉ ነበር ለማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ሲመጣ ሰው ለመንግስት ያለው ታዛዥነትና ስርዓትን አክብሮ የመሄድ ፍላጎቱ እየቀነሰና እየጠፋ እንዲሄድ አደረገው። ህዝብም በመንግስት ላይ ያለው እምነት እየጠፋ እንዲሄድ አደረገው።
የዚያኑ ያህል ደግሞ ሕግን የሚጥሱት ሰዎች ህግን ጥሰው የመጨረሻውን አስቀያሚውን ጥቃት እየፈፀሙ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ሥላልነበረ ጉልበታቸው እየጨመረ መጣ። በየትኛውም አካባቢ አንድ ሰው ሊጠቃም ሆነ ሊፈናቀል ወይም ሊገደል ይችላል። ነገር ግን ወዲያውኑ ይህንን የፈፀመውን ሰው በህግ ተጠያቂ አድርጎ ርምጃ የሚወሰድበት ቢሆን፤ የሚቀጣ ቢኖር ሰው በመንግስት ስርዓት ላይ እምነት ይኖረው ነበር። ለምሳሌ ሃዋሳ ላይ ለተፈፀመው ድርጊት የሆኑ ወጣቶች ተከሰዋል።
ለእኔ ለእነዚያ ወጣቶች መከሰስ ለውጥ አያመጣም። እነሱን አደራጅቶ የላካቸው አካል አልተጠየቀም። ሻሸመኔ ላይ አለም ገናም ላይ ያ ሁሉ ሰው ያለቀበት ድርጊት ጀርባ የነበሩ ሰዎች አልተጠየቁም። ጥቃቱን አደራጅቶ ልኮ የፈፀመው አካል ሁሌም አይጠየቅም። ከታች ላይ ያሉ ትንንሽ ሰዎች ሁልጊዜ ተጠያቂ ይደረጋሉ።
የእነዚህ ሰዎች ተጠያቂ መደረግም ሆነ አለመደረግ ለአብዛኛው ማህበረሰብ ትርጉም የለውም። አደራጅቶ የላካቸውን ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ የፍትህ ሥርዓት አልነበረም። ሁሉም የፍትህ ተቋሞቻችን ጋር የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ አልነበርም።
ፖሊስም ጋር፣ አቃቤ ህግም ጋር ሆነ ፍርቤ ቤትም ጋር ቁርጠኝነቱ አልነበረም። ያ የሆነበት ሁኔታ ምንድን ነው ከተባለ እኔ እስከሚገባኝ ያንን ድርጊት የሚፈጽሙት ሰዎች አሁን ባለው የመንግስት መዋቅር ውስጥ ስልጣን ውስጥ የነበሩ ነበሩ።
በተለያዩ ምክንያት ወይንም ከእነርሱ ጋር ተባብረው የሚሰሩ ነበሩ። ስለዚህ የፖለቲካ አመራሩም ርምጃ መውሰድ ያቃተው ችግሩ ውስጥ ስለሆነ ነው። ከውጭ ቢሆን ኖሮ አያስቸግርም ነበር።
አሁን ትግራይ ክልል
የተፈጠረውን ስናስበው ነገሩ
እያደገ እያደገ መጥቶ
በኋላ ላይ ፌዴራል
መንግስትም ላይ መንግስት
የለም የሚል አንድ
ጠንካራ ቡድን እስኪፈጠር
ድረስ ምክንያት ሆነ።
ለምሳሌ ልዩ ሃይል
የሚባለውን አደረጃጀት መመልከት
እንችላለን። ለእኔ እንደ
ህግ ባለሙያ ልዩ
ሃይል የሚል አደረጃጀት
የሚፈቅድ የህግ
ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ክልሎች ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ስልጣን ነው ያላቸው። ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ደግሞ የፖሊስ ሃይል ነው የሚያስፈልገው። ስለዚህ ክልሎች ሊኖራቸው የሚችለው የታጠቀ ሃይል የፖሊስ ሃይል ብቻ ነው መሆን ያለበት።
ፖሊስ ከወታደር የሚለይበት ዋናው ባህሪው የተደራጀ ትላልቅ መሳሪያ የማይታጠቅ ሃይል መሆኑ ነው። ፖሊስ ባህሪው ሲቪል ነው። ከሌላው ማህበረሰብ የሚለየው አነስተኛ የሆኑ መሳሪያዎችን መታጠቁ ነው። ወታደራዊ ስልጠናም አለው። ስራው ግን በዋናነት የሲቪል ስራ ነው። ስለዚህ ክልሎች ሊኖራቸው የሚገባው ይሄ ወይንም ከፖሊስ አቅም በታች የሆነ ሃይል ነው።
በትግራይ ግን የተደረገው ልዩ ሃይል የሚባል ነበረ። ይሄ ልዩ ሀይል የሚታጠቀው መሳሪያ በጣም ልዩ በመሆኑ ሲታይ የወታደር ባህሪ ነው ያለው። ስልጠናቸውንም ስናይ ወታደራዊ ስልጠና ነው የሚወስዱት። ስለዚህ ወታደር የሆኑ ግን ወታደር የሚል ስያሜ ያልተሰጣቸው አካላት ነው የነበሩት።
ይሄ ህገ መንግስቱ ላይ ለክልሎች ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ ሆኖ እናገኘዋለን። መከላከያ ሃይል ነው ማደራጀትም፣ መከላከያን መምራትም፣ መከላከያን ማስተዳደርም ስልጣኑ የፌዴራል መንግስት ነው። ስለዚህ ከፖሊስ በላይ የሆነ ሃይል በሙሉ መደራጀት የሚችለው በፌዴራል መንግስት ብቻ ነው።
በተግባር ግን የሆነው ከፖሊስ ሃይል በላይ የሆነ አሁን በተግባር ስናየው ጭራሽ ከመከላከያ ሰራዊቱ በላይ የሆነ ሃይል ነው ልዩ ሀይል በሚል ሽፋን የተደራጀው። ይሄ ሁሉም ክልሎች ጋር ሲኬድ ትልልቅ አቅም ተፈጥሮለት የተደራጀ ሃይል ስለነበረ ፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጋር የነበረው ግንኙነትና እዛ ላይ የነበረው ህግን የማስከበር ስብስብ እንዲበጠስ ወይንም እንዲቋረጥ ያደረገ ነው። ይሄ ነገር ለዘመናት ተፈቅዶ ሲሰራበት ነበር። ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ ነው ይሄ ሃይል ሲደራጅ የኖረው።
ከእዛ በኋላ ግን በመጠንና በፍጥነት ጨምሮ ነው ሲደራጅ የኖረው። ይሄ ለምንድን ነው የሆነው የፌዴራል መንግስት አቅም የለውም የሚለው አካል በሙሉ ራሱን በእዚህ ደረጃ እያደራጀ መጥቶ ትላልቅ ሃይል እንዲሆን አደረገው ማለት ነው። ስለዚህ ልዩ ሀይል የሚለው አደረጃጀት ትግራይ ላይ ከፌዴራል የመከላከያ ሰራዊት ጋር መዋጋት የሚችል ጠንካራ ሃይል መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
ልዩ ሃይል የሚለው አደረጃጀት በሁሉም ክልሎች ጋር ስንሄድ ዛሬም አለ። የታጠቁት መሳሪያ ዛሬም ከመከላከያ እኩል ወይም በላይ ነው። ይሄን አደረጃጀት አድጎ አድጎ እዛ ጋር ከመድረሱ በፊት ማፍረስ፣ ማስቆም አልተቻለም። አሁን በትግራይ ክልል ችግሩን አይተናል።
በእርግጥ ቀደም ሲልም ያላነሳናቸው ችግሮች መታየት ጀምረው ነበር። በተለያየ መንገድ የፌዴራል መንግስቱን እውቅና የማይሰጥ አስተሳሰብ እያደገ የመጣበት፤ የፌዴራል መንግስቱ በተለይ ህግና ስርዓት በማስከበር አቅም የለውም፤ ስለዚህ ህግና ስርዓትን ለማስከበር የምንችለው እራሳችን ነን ወደሚል አስተሳሰብም በልዩ ሃይል ውስጥ በደንብ እያደገ መጥቶ ክልሎች ፌዴራል መንግስት የለም እስከሚሉበት ደረጃ ደረሱ።
አሁን ትግራይ ላይ የመጀመሪያውን ፈተና አይተናል። ይሄንን ፈተና ተረድተን አሁን ከእዚህ በኋላ ይሄ ልዩ ሃይል እንዴት መሆን አለበት ካልን በሁሉም ክልሎች ላይ በፍጥነት መፍረስ አለበት። ወደ መከላከያ መጠቃለል አለበት።
ክልሎች ከፖሊስ ሃይል በላይ ሊኖራቸው አይገባም የሚል ግልጽ የሆነ አቋም መያዝ ይገባል። ግን ዛሬም ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አቋም ከፌዴራል መንግስቱ ያንሰናል። በተቃራኒው ክልሎች ይበልጥ አሁንም ልዩ ሃይላቸውን እያደራጁ ነው ያሉት።
ስለዚህ ለውጡን ከቀን ወደ ቀን ፈተና ውስጥ እየከተቱት የመጡት ከውጭ የመጡ አይደሉም። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚፈጠሩ ፈተናዎች ናቸው። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተፈጥረው እያደጉ የመጡት ፈተናዎች ከመንግስት ውጭ ያለው አካል ከሚያመጣው ፈተና በላይ ከባድ ናቸው። ምክንያቱም የራሱን የመንግስት መዋቅርን የሚጠቀሙ በመሆናቸው የማስፈጸም አቅማቸው ትልቅ ነው።
የፖለቲካ አቅማቸውም ሆነ የፖለቲካ ትስስሩ ትልቅ ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለውጡ ላይ ስናስብ አንዳንድ ሰው መረር ብሎ ለውጥ የለም የሚል ደረጃ ላይ የሚያደርሰው እነዚህ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ያሉ ስለሆኑ አሁን እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ነገር ከፌዴራል መንግስቱ መምጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ወንጀለኞች ቶሎ በህግ ተጠያቂ ያለመሆናቸውም ሆነ የፍርድ ሂደቱ መራዘም ለወንጀሉ መስፋፋት ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሞላልኝ፡- ይህንን ጉዳይ ውሳኔ ማግኘት ወይም አለማግኘት ከሚባለው ነገር አለፍ አድርገን ማየት አለብን ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ የሰኔ 16 የጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተሞከረው ግድያ እንውሰድ። ፍርድ ቤት ቀርበው የተጠየቁ አራት ሰዎች አሉ። በርግጥ ይሄ ጉዳይ የእዛን ያክል ትንሽ ነበር ወይ? ጥቃቱ እነዚህ አራት ሰዎች ብቻ ጉዳይ ነበር ወይ? ብሎ ማየት ያስፈልጋል። አንድ ነገር ተፈጽሟል ስንል ከድርጊቱ መፈጸም ጀርባ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ትላልቅ ሰዎች አሉ። የፍትህ መድረኩ ትላልቅ ሰዎች ወደ ተጠያቂነት የማያመጣ ከሆነ ለውጥ አለ ማለት አያስችልም። አሁን ትላልቅ የምንላቸው ከውጭ የምንሰማቸው ጉዳዩች አሉ።
በዜና ላይ ሰዎች ተጠያቂ ተደረጉ፣ ተከሰሱ ሲባል ሰዎች የሚያስቡት መንገድና በተግባር ፍርድ ቤት ላይ እየታየ ያለ ጉዳይ በጣም የተለያየ ነው። አሁን ጉዳዩች እየታዩ ስለሆነ ማንሳት ከባድ ይሆናል። ግን ድርጊቶቹ አሁን ሀዋሳና ሻሸመኔ የተፈጸሙትን ማሳያ አድርገን ከወሰድን ውጭ ሰዎች ለተፈፀመው ድርጊት ተይዘው ተጠያቂ የተደረጉና ፍርድ ቤት የቀረቡ ሰዎች አሉ የሚለውን ስንሰማ ሁላችንም የሚገባን ያንን ድርጊት አደራጅተው፣ አቀናብረው፣ በተግባር ፈጽመውና አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች በሙሉ ተጠያቂ መሆናቸውን ነው። በእዚያ ድርጊት ልክ፣ በተፈጸመው ድርጊት ልክ ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እየተደረጉ ነው ብለን እናስባለን።
ጥፋተኛ ሲባሉም በጥፋታቸው ጥፋተኛ ተብለው ተቀጡ ብለን እናስባለን። ውስጥ ገብተሸ ግን የተከሰሱበትን ስትመለከቺ እውነታው ከእዚህ ጋር አይገናኝም። ምናልባት የሆነ ሰው ቤት ሰበሩ፣ አቃጠሉ፣ ገደሉ የሚል ተራ ጉዳይ ሆኖ ነው የምታገኚው። በጉዳዮቹ ተጠያቂነት መጣ ተብሎ ሲነገረን እኛ ያሰብንበት መንገድና በተግባር ሰዎቹ ፍርድ ቤት እየታየ ያለበት የክስ ማመልከቻው ሲታይ አይገናኝም።
አሁንም በፍትህ መድረኮች ላይ የጸዳ ነገር የለም የምልበት ምክንያት ይሄ ነው። ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ሰዎች ተጠያቂ መሆን ባለባቸው ልክ አይደለም ጉዳያቸው እየታየ ያለው። ጉዳያቸው በእዛ ልክ እየታየ አለመሆኑ ነው ለእኔ ትልቁ ችግር የሚሆነው። ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ ለምን ውሳኔ አላገኘም ወደሚለው ነገር ስንመጣ እኔ አሁን የጃዋርን ጉዳይ አላውቀውም፤ እንደማንኛውም ሰው ከውጭ ነው የምሰማው።
ግን ብዙዎቻቸን እነጃዋር ተከሰሱ ሲባል የሚገባንና የምንጠብቀው ነገር አለ። በርግጥ ግን የክስ ማመልከቻውን ብናየው እኛ የምንጠብቀውና ጃዋር ፈጸመ ተብሎ የተጠረጠረበት ነገር በርግጠኝነት አንድ አይነት አይደለም። ምክንያቱም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለ እውነታ ይሄ ስለሆነ ነው።
አሁን ስለሜቴክና ሌሎች ጉዳያቸው እየታየ ያለ ሰዎች ይነሳል። ሰው እነዚህ ሰዎች ተጠያቂ ተደረጉ ሲባል የሚያስብበት ነገርና ፍርድ ቤት ቀርቦ እየታየ ያለበት ክስ አንድ አይነት አይደለም። ይሄ ነው ይበልጥ የእነዚህ ሰዎች ጉዳይ ተፋጥኖ ታይቶ ውሳኔ እንዳያገኝ ወይም እንዲጓተት የሚያደርገው።
ከውጭ ያለው ደስታና በተግባር እየታየ ያለው ነገር አንድ አይነት ስላልሆነ በዛ መካከል ላይ የሚፈጠረው ልዩነት ነው ችግሩን የሚፈጥረው። የጉዳዩቹ መጓተት ብቻ ሳይሆን የጉዳዩቹ ምንነት በእራሱ ችግር ያለበት ነው። ብዙዎቻችን በፍትህ ስርዓቱ ያለንን እምነት ፈተና ውስጥ የሚከት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመዋቅሮች ውስጥ ባሉ አካላት የተፈጸሙ የተለያዩ ግድያዎችና ወንጀሎች እንዳሉነው የሚገለጸውና ከላይ ያለው አመራር ይህንን ለማስፈጸም ለምን አልቻለም ?
አቶ ሞላልኝ፡– ቅድም ስንናገረው ነበር ፈተናውን። ለውጥ መጥቷል። ለውጡ እንዴት ነው የመጣው በርግጥ ለውጥ አለ ወይ የሚለው ፈተናም የሚመጣም ከእዚህ ጋር ነው። ሁላችንም ለውጥ መጥቷል ስንል በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ነው። ኢህአዴግ በሚባለው የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ነው።
ሰው አገራዊ ለውጥ ነው ሲል መታየት ያለበት አንድ አገራዊ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረ መሆኑ ነው። በርግጥ ያ አገራዊ ፓርቲ አገርን እየመራና እያስተዳደረ ከመሆኑ አንጻር እዛ ውስጥ ያለው ለውጥ የሚናቅ አይደለም። አገራዊ ውጤት አለው። ግን እዛ ፓርቲ ውስጥ ለውጥ ሲመጣ ያ ፓርቲ ምን ያህል ራሱን ለውጧል የሚለው መታየት አለበት።
አገራችን ውስጥ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ምክንያት የሆኑትን ፖለቲከኞች ሁሉ ከውስጡ አውጥቶ ስለአገራዊ አጀንዳ ብቻ ያላቸውንና አገራዊ አጀንዳ ላይ ብቻ ለአገር የሚሆን አስተሳሰባቸውን ይዘው መጥተው በፖለቲካ መድረኩ ተወዳድረው አሸንፈው አገር ላይ ለውጥ ስለማምጣት ብቻ የሚሰሩ ንጹህ ፖለቲከኛ ምን ያህል በውስጡ አካትቷል ብለን እንድንመዝን ያደርጋል።
አሁን እዚህ ላይ ፓርቲው ገና በመሆኑ ብዙ ነገር ይቀረዋል። የስያሜ፣ የአደረጃጀት ለውጥ አድርጓል፣ የተወሰኑ ፖለቲከኞችን ከውስጡ ለማውጣት እየሞከረ ነው፤ ይሄ ትልቅ ነገር ነው። ግን አሁንም ብዙ ያልተሰሩ ነገሮች አሉ። የፖለቲካ ፓርቲውን ከግል ስልጣናቸው ብቻ የሚያዩ፣ በፖለቲካ መድረኩ ላይ የፖለቲካ ሃሳባቸውን ይዘው የመጡና በተወዳዳሪነት ለመስራት ፍቃደኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችን አሁንም ይዟል።
እነዛ ሰዎች ደግሞ ተራ ወይንም ትናንሽ ካድሬዎች አይደሉም። እስከ ትላልቆቹ አመራሮች ድረስ ያሉ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች ይዞ ያለ በመሆኑ ፓርቲው አሁንም ገና ነው። ሁላችንም ፓርቲው ውስጥ ለውጥ አለ ብለን በድፍረት የምንናገረውን ያክል ለውጥ አለ እንድንል የማያደርጉን ጉድለቶች ፓርቲው ውስጥ አሉ።
ስለዚህ ፓርቲው ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን ማጽዳት አለበት ብዬ አምናለሁ። ብልጽግና ፓርቲ በሚደራጅበት ጊዜ ህወሓት የእዛ አካል የመሆን እድሉ ነበረው። ግን ራሱን ለምን ከእዛ ውስጥ አወጣ ስንል የአስተሳሰብ አንድነት ችግር ነበር ማለት ነው። የህወሓት አልስማማም ብሎ ራሱን ለይቶ መውጣት አንድ ጥሩ ነገር ነው። ምክንያቱም ግልጽ አቋም መያዙ ለሁሉም ጠቃሚ በመሆኑ ነው።
እንደዚህ ራሳቸውን ለይተው ያላወጡ ነገር ግን ከህወሓት አስተሳሰብ ያልተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ግን አሁንም እዛ ውስጥ አሉ። ህወሓት ራሱን ለይቶ በመውጣቱ ትክክል ነው። በፖለቲካ አመለካከቱ ልንስማማ ላንስማማ እንችላለን። ግን አቋሙን ግልጽ አድርጎ ወጥቷል።
ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ወዘተ ክልሎች ጋር ብንሄድ እዛ ውስጥ ያሉ የፓርቲ አመራሮች እንደ ህወሃት ራሳቸውን ግልጽ አድርገው አልወጡም እንጂ ከእዛ አቋም ያልተናነሰ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ይኖራቸዋል።
በተጨባጭ የተሟላ ለውጥ እንዳይመጣ ያደረጉት በፓርቲው ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው። የፈለጉትን ይሰራሉ፤ የፖለቲካም የህግም ተጠያቂነት የለባቸውም። ምክንያቱም በፓርቲው ሲጠየቁ አናይም፣ በህግም ተጠያቂ ሲደረጉ አናይም። ሁለቱንም ይዘው የሚዘውሩትና ጉልበቱ ያለው በእጃቸው በመሆኑ ነው። አሁን ቤኒሻንጉል ላይ እየተፈጸመ ላለው ድርጊት ለእኔ ከክልሉ አመራሮች የበለጠ ተጠያቂ መሆን ያለበት ሌላ አካል አለ ብዬ አላስብም። ይህንን በሁለት ነገር ማየት ይቻላል።
አንደኛ ነገር የእነርሱ ፍቃድ ሳይኖርበት በእዛ ልክ የታጠቀ ሃይል በእዚያ ልክ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ያንን ሁሉ ጥቃት ሊያደርስ አይችልም። የእዚያኑ ያህል ደግሞ እነርሱ ፍቃዳችን የለበትም ቢሉን እንኳ ይህንን ሃይል ለማስቆም የሚያስችል የመንግስት ስልጣንና አቅም አላቸው። ይሄንን የመንግስት ስልጣንና አቅማቸውን ተጠቅመው ያንን ለማስቆም ምንም ያደረጉት ነገር የለም።
ስለዚህ በሁለቱም ያደረጉት የለም። እኔ ከፖለቲካ አመራሮቹ በሙሉ መምረጥ ያለብን አይመስለኝም። ሁሉም ተጠያቂ መሆን ነው ያለባቸው። ይሄንን አይነት ተጠያቂነት ማምጣት ስንችል ነው ለውጥ አለ ማለት የምንችለው። አሁን ሁሉም ቦታ ላይ መከላከያ እየገባ መፍትሄ እንዲያመጣ ነው እየተደረገ ያለው።
መከላከያን ችግር ውስጥ እየከተትነው ነው ያለነው። የፖለቲካ አመራሮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸውና እነርሱን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባለመኖሩ የበለጠ መስዋዕትነት እያስከፈለን ነው የሚሄደው።
አዲስ ዘመን፡- የህወሃት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሰራዊትም ሆነ በማይካድራ ንፁሃን ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ በአለም አቀፍ ህግ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ ምን መሰራት ይገባል ይላሉ?
አቶ ሞላልኝ፡- ይህ ሃይል በመከላከያ ሰራዊት የፈጸመው ጥቃት ምንም እንኳን የታሪክ አጥኚ ባልሆንም ባለኝ እውቀት ሳየው አንድ የአገር ውስጥ የሆነ ሃይል የፌዴራል መንግስትን የመከላከያ ሃይል ያጠቃበት የመጀመሪያ ታሪክ ነው የሚመስለኝ። ከጥንትም የኢትዮጵያን ታሪክ ስናይ በየቦታው፣ በየክልሉ ያሉ ንጉሶች ግጭት ሲፈጥሩ ይታወቃል። ይሄ ግን ከእዛ ይለያል።
በሰላም ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎ አብሯቸው የተቀመጠን፣ የእነርሱን ጥቅም ለማስከበር ብሎ እነርሱን እየጠበቀ ያለን ሃይል ምንም ባልተፈጠረ ሁኔታ የአንድ ክልል ሃይል መጥቶ ጥቃት ፈጽሟል። ይህም ምናልባት በኢትዮጵያ ታሪክ እንዲህ አይነት ሁኔታ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ ነው ብዬ አምናለሁ።
እንደ አጠቃላይ የተፈጸመው ድርጊት በጣም አሳዛኝ አሳፋሪም ድርጊት ነው። ከህግ አኳያም ስናስበው በጣም ትልቅና ከባድ ወንጀል ነው። ተጠያቂነት ማምጣት ያለማምጣት የሚለው ነገር ክርክር ውስጥ የሚገባም አይደለም። ይሄ ነገር የህግ ተጠያቂነት የማምጣቱ ጉዳይ በጣም ግልጽ ነው። በአገራችን የወንጀል ድንጋጌዎችንም
ቢሆን ይሄንን የሚሸፍኑ ግልጽ ድንጋጌዎች አሉ። አለም አቀፍ ህጎችንም ብንወስድ ተጠያቂነትን ያመጣሉ። ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎች አሉ። እዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች አመራሮች በወታደራዊም ውስጥ እንደየተሳትፏቸው ተለይቶ በማስረጃ አጣርቶ ለሚመለከታቸው ይዞ መቅረብ ይጠይቃል። አሁን እየተሰራ ያለው እርሱ ነው። ቀላል ነገር አይደለም፤ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። ጉዳዩ በጣም ከባድና የተወሳሰበ ስለሆነ ጊዜ ይወስዳል።
ይሁንና የኔ ስጋት የምርመራ ስራው በርግጥ ነጻ ነው ወይ ብለን ማየት እንችላለን። ቀደም ሲልም ትልልቅ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። እነዚያን ወንጀሎች ተጠያቂ የሚያደርግ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ስላልነበረ የምርመራው፣ የክስ አቀራረቡና የፍርድ ሂደቱ በሙሉ ሰንካላ እንዲሆን የተደረገበት ነገር ነበር።
ይህ ምርመራስ ነጻ ነው?። በርግጥ ሁላችንም ስሜታችንን በሚነካ ልክ ያንን ምርመራ አድርጎ እነዚን ሰዎች ወደ ፍትህ መድረክ ይዞ የሚያቀርብ ስራ ነው ወይ እየተሰራ ያለው ቢባል እኔ ያልጠራ ነው ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ምርመራዎችን እንሰማለን፣ ባልኖርበትም ባጋጣሚ ጉዳዮቹም ችሎት ላይ ቀርበው ክርክር ሲደረግባቸው እሰማለሁ። ነጻ ነው ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ ነገር አላየሁም።
በምርመራ ሂደቱ ላይ አሁንም ችግሮች አሉበት፣ ሙሉ ለሙሉ ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ አቅም በእዚህ በኩል የለም የሚል ነገር እንዳስብ የሚያደርጉኝ ነገሮች አሉኝ። ግን ተጠያቂነት መምጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች የተፈጸመው ትልቅ ወንጀል በመሆኑ በተለየ የፍትህ መድረክ ማየት ያስፈልጋል ይላሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ሞላልኝ፡- ሁለት ነገሮች ማየት አለብን። ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ሊደረጉ ይችላሉ። እንደውም ወታደራዊ ፍርድ ቤት በተሻለ አቅምና አደረጃጀት አቋቁሞ አዋጅ ቁጥር 1100/2011 ላይ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሰፊ ስልጣን ነው የሰጠው። አብዛኛው ጉዳይ ወደ እዛ ውስጥ ገብቶ ሊሸፈን ይችላል። የዚያኑ ያህል ደግሞ በመደበኛ ፍርድ ቤትም ታይቶ ጉዳያቸው የሚሸፈንባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ግን ዋናው ነገር በሁለተኛው ቢሆን ማለትም በመደበኛውም ሆነ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተጠያቂነት ሲመጣ በትክክል ፍትህንም በሚያሰፍን መልኩ ተጠያቂነቱ መቅረብ አለበት። የተለየ ፍርድ ቤት ወይንም ችሎት ማቋቋም የሚለው ነገር ብዙም የሚያስኬድ ሃሳብ አይደለም። በህግም ክልክል ነው።
ለአንድ ጉዳይ ተብሎ የተለየ ፍርድ ቤት ማቋቋም በህግ ክልክል ነው። የተለየ ችሎት ማቋቋም ግን ይቻላል። ይሄንን ስራ ብቻ ዋና ስራው አድርጎ የሚሰራ ከሌሎች ስራዎች ነጻ የሆነ በእዛ ምክንያትም የፍትህ ሂደቱን እንዳያጓትተው ችሎቱን በተለየ መንገድ ማደራጀት ይቻላል። አሁንም አልተሰራም የሚባልበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ገና ነው። ከጉዳዩ ስፋትና ክብደት አንጻር አልተሰራም የሚባልበት አይደለም። ጅማሮ፣ ሂደቱ ግን ያንን የሚያሳይ መሆን አለበት። ሂደቱ ወደእዛ ደረጃ የሚያደርሰን መሆኑን ርግጠኛ መሆን አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በማይካድራ በንጹሀን ዜጎች አሰቃቂ ጭፍጨፋ የደረሰበት አጋጣሚ ደርሷል። በአለም አቀፍ ደረጃም በሰብአዊ መብት ተቋማት የተወገዘ የወንጀል ድርጊት ነው። ይህንን ድርጊት ለአለም ህብረተሰብ በማሳወቅ ረገድ በበቂ ሁኔታ ተሰርቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሞላልኝ፡-በማይካድራው ድርጊት የምንሰማቸው ድርጊቶች አሉ። ከምንሰማቸው ድርጊቶች ተነስተን በርግጥ ማወቅ የሚገባንን ያህል አለም አቀፉን ማህበረሰብ እንተወው እኛ በዝርዝር እናውቃለን ወይ ብንል ማወቅ የሚገባንን ያህል አውቀናል ብዬ አላስብም። ያልተነገሩን ብዙ ነገሮች እንዳሉ አምናለሁ።
ምክንያቱም ከቀን ወደ ቀን ትንሽ ትንሽ ነገሮች ይመጣሉ። እነዚያን አጋጣጥመን ስንመለከት የችግሩን ስፋት መረዳት ከባድ አይደለም። በእዛ ደረጃ ግን በዝርዝር ዛሬም ድረስ የተነገረ ነገር የለም። ይሄ ለምን ሆነ ስንል መንግስት የተለያዩ ነገሮችን አስቦ ይሆናል።
ምናልባትም ችግሮቹን በእዛ ደረጃ አግዝፎ በእዚህ ሰዓት መግለጽ ጠቅላላ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከት ሊሆን ይችላል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ስስ የሆነ ጊዜ ስለሆነ በየቦታው ብዙ ውጥረቶች ስላሉ እነዛን ነገሮች በምንገምተው ልክ በዝርዝር ባይባልም ምናልባትም ጠቅላላ አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ ሊከት የሚችል ስለሚሆን ያንን ታሳቢ በማድረግ ነገሮች ተቆጥበው ያሉ ይመስለኛል።
ሌላው መድረክ ላይ የተፈጸሙት ነገሮች ጸድተው እስኪታዩ ስልታዊ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። እርሱ ብቻ ነው ወይ ያልተገለጸው ምርመራው በጥልቀት ተሰርቶ መዝገብ ተደራጅቷል ወይ ሲባልም የሚታይ ነው።
የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተጽእኖ ዋጋ ሰጥተን ማየት አለብን ብዬ አላስብም። አለም አቀፍ ተቋማት ሁልጊዜ ሲመጡ የራሳቸው የሚያስፈጽሙት ሊያሳኩ የሚፈልጉት ዓላማ አላቸው። ያንን ዓላማቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው ዘገባዎችን ሲሰሩም ሪፖርቶችን ሲያቀርቡ የምናየው። መንግስት የሚያስብበት የራሱ መንገድ አለ ይሆናል ብዬም የማስብበት ነው።
እነርሱ ደግሞ ይዘው የሚመጡትና የሚሰጡት መግለጫ ከእዚህ ተቃራኒ ሲሆን የተቃርኖ ምክንያት የመንግስት ድክመት ነው ወይስ የዓላማ ነገር ነው የሚለውን ነገር በደንብ ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። ለእኔ እነርሱ የትኛውንም አቋም ይያዙ የትኛውንም መልዕክት ይኑራቸው ማመን ያለብን ይሄ የመንግስት አቋም ስለሆነ እርሱን መከተል ነው ትክክል ነው ብዬ የማስበው። ይሄንን ብዥታ የሚያጠራ ተከታታይ የሆነ መግለጫና መረጃ ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ አለበት። ይሄ የመንግስት ሃላፊነት ነው። ይሄንን አይነት ግርታ እንዳይፈጠር ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሞላልኝ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013