ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውጥኖቻቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና በተለያዩ መድረኮች መናገራቸው ይታወሳል ፡፡
በዚሁ ጊዜም ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲና ነጻነት እንደሚያስፈልጓቸው፣የሀብት ብክነትንና የተደራጀ ሙስናን መላውን ህዝብ በማሳተፍ ለመዋጋት፣የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር የተለያየ እርምጃ ለመውሰድ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣የሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በቁርጠኝነት መንግሥት እንደሚሰራ ከተናገሯቸው መካከል ይጠቀሳል፡፡እነዚህን ጨምሮ በተናገሯቸውና በሦሰት መቶ የስራ ቀናት ቆይታቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት አመራር ዘርፍ የሁለተኛ ዓመት የድህረ ምረቃ ተማሪ ፍራኦል አብዶ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሦስት መቶ ቀናት ይሠራሉ ተብለው የማይጠበቁ ድንቅ ስኬት አስመዝግበዋል፡፡የተናገሩትንም ፈጽመዋል፡፡ሥራቸው በዓለም ጭምር አድናቆት አስገኝቶላቸዋል፡፡ ከፈጸሟቸው መካከልም የህግ የበላይነትና የፍትህ መረጋገጥ፣ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረጋቸው ፣ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ማከናወናቸው ፣የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደጋቸው፣ ተጠያቂነትን ማስፈናቸው ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ማድረጋቸው፣ የዴሞክራሲ ነጻነት ማስፈናቸው፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፣ በተቋማት አደረጃጀት ላይ ለውጥ ማድረጋቸው ይጠቀሳሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃዎች ከኢትዮጵያም ተሻግረው የአጎራባች ሀገሮችን ችግርም ጭምር ለመፍታት ያስቻሉ የመልካም መሪ ቱርፋቶች መሆናቸውን የጠቆመው ተማሪ ፍራኦል ‹‹በዚህ ዘመን ያለን ወጣቶች በዶክተር ዐብይ መመራታችንን እንደ ትልቅ ዕድል መመልከት ይኖርብናል››ብሏል፡፡ወጣቶች ከጎናቸው በመሆንም ለውጡን ለመቀልበስ የሚፍጨረጨሩ አካላትን በሕግ አግባብ መታገል እንዳለባቸው ገልጿል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች አንጻራዊ ሰላም እየተስተዋለ ነው ያለው ወጣቱ ለውጡ ያልተመቻቸው አንዳንዶች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ቢያደርጉም እንደማይሳካላቸውና እስካሁንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ችግር አለመኖሩን ተነግሯል፡፡
በየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቤተልሄም ደሳለኝ በበኩሏ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ጊዜ በውጤት የታጀበና የተናገሩትንም የፈጸሙ ናቸው ስትል አድናቆትዋን ገልጻለች፡፡በሰሯቸው ስራዎችም በሰላምና በትምህርት ለውጦች እንዲመጡ ያደረጓቸውን ጥረቶች ለአብነት ጠቅሳለች፡፡ ወጣቷ ለሴቶች የሰጡትን ትኩረትም አድንቃለች፡፡‹‹እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ሰዎች የነጻነት ስሜት ተሰምቷቸዋል፡፡መብትና ግዴታችንን ማወቅ ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል›› በማለትም ተናግራለች፡፡
በግል ፋብሪካ ተቀጥሮ የሚሰራው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰለሞን ታደለ ዶክተር ዐብይ በርካታ ሥራዎች እንደሠሩ እና ቃላቸውንም እየፈጸሙ መሆናቸውን በመጠቆም፤ሁሉም በአንድ ላይ እንዲዘምር ማድረግ መቻላቸውን ገልጿል፡፡በስኬቶቻቸው ውስጥ ግን አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ተናግሯል፡፡‹‹በቀጥታ እርሳቸውን የሚመለከት ነው ባይባልም በአዲስ አበባ ከተማ አሁን እየተደራጁ ያሉ ወጣቶችና የመታወቂያ አወሳሰዳቸው ግልጽነት የሌለው ነው፡፡ድርጊቶቹ ስኬቶችን ያጎድፋሉ››በማለት አስተያቱን ሰጥቷል፡፡ ወጣቱ መንግሥት የሙሁራንን ሀሰብ እንዲያዳምጥም፣ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ትኩረት እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በግል ሥራ የምትተዳደረው ወይዘሪት ዘሀራ አጃኢብ ዶክተር ዐብይ አህመድ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሊታመኑ የማይችሉ ሥራዎችን እንደሰሩ ተናግራለች ፡፡እርሷ እንደምትለው በሰላም ጉዳይ አሁን ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ነው ፤ ቀደምሲል የህዝብን ሀብት ያባከኑ፣ ሰዎችን በግፍ ሲያስሩና ሲያሰቃዩ የነበሩ ደግሞ በህግ ፊት መቅረባቸው አስደስቷታል፡፡በአጠቃላይ ዶክተር ዐብይ አገሪቱን መምራት ከጀመሩ ወዲህ የታዩት ለውጦች ተስፋ የሚሰጡና የተናገሩትንም የሚፈጽሙ ሆነው እንዳገኘቻቸው ተናግራለች፡፡
ጥር 24/2011
ኢያሱ መሰለ